Please follow and like us:
0

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አመ ፲ ለወርኃ መጋቢት ፳፻፱ ዓ.ም በዛቲ ዕለት አዕረፈ አባ ገብረ ሥላሴ ወልዱ ለሳሙኤል ዘዋልድባ

በዚችም ዕለት የዋልድባው ታላቁ አባት መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ (አባነጮ) በእረፍተ ሥጋ ከዚህ ዓለም ተለዩ፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ ከአባታቸው ከአቶ ገብረ ሕይወት ዐባይ ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተ ዮሐንስ በ1915 ዓ.ም በዋግ ሕምራ ልዩ ስሙ ሰላምዬማርያም በተባለ ቦታ ተወለዱ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ጊዜ በተወለዱበት ደብር ከመ/ም መ/ጌታ ኃ/ማርያም ከፊደል እስከ ንባብ ከተማሩ በኋላ ለትምህርት ፍለጋ በተለያዩ ጉባኤ ቤቶች ተዘዋውረው አቋቋም፣ ቅዳሴ፣ መጽሐፈ ሐዲሳት ትርጓሜን  ተምረዋል፡፡

ክህነትን በተመለከተ ዲቁና ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ማጨው ቅስና  ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ጐንደር ተቀብለዋል፡፡

እኒህ አባት ከትምህርት ቤት በኋላ በምናኔ ወደ ታላቁ ዋልድባ ገዳም በ1930 ዓ.ም ገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ  በገዳሙ ማኅበር ምርጫ በረድእነት እንዲያገለግሉ ተመድበው የገዳሙን ሕይወት ምናኔ ሀ ብለው ጀመሩት፡፡ አንድ ሰው ኅሊናውን ለምናኔ አነሣሥቶ ወደ ገዳም በሚገባበት ወቅት የሚያጋጥሙት ፈተናዎች እጅግ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓለማችን እንደ ገዳም ያለ ፈተና የሚበዛበት ቦታ የትም የለም፡፡ ሰብአዊ፤ዓለማዊና ሰይጣናዊ ፈተናዎች በሙሉ ተሰባስበው የሚገኙት በገዳም ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙኅ ሕማሞሙ ለጻድቃን ማለት የጻድቃን መከራቸውና ፈተናቸው ብዙ ነው በተባለው መሠረት፣ በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በምናኔ ወደ ገዳም በገቡ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፈተና የበለጠ ክብደት አለውና፡፡

ገዳማውያን አበው መነኰሳት እና እማት መነኮሳይያት በገዳማዊ ሕይወታቸው የሚዋጉት ከዚህ ዓለም ካለው ከሚታየው፣ ከሚጨበጠው፤ ከሚዳሰሰውና ከሚሰማው ፈተና ብቻ ሳይሆን ከማይታዩ፤ ከማይዳሰሱ፤ ከማይጨበጡ ረቂቃን አጋንንት  ጋርም ከመዋጋት አቋርጠው አያውቁም፡፡ ውጊያውም እስከ ዕለተ እረፍተ ሥጋ ድረስ የሚያቆም ውጊያ አይደለም፡፡ ስለዚህ በገዳም በመናንያን ላይ የሚደርሰው ፈተና ስፍር ቁጥር መጠን የለውም፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በገዳማዊ ሕይወት የሥራን ክቡርነት መረዳት፤ የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙ መታገስን፣ ሲታዘዙ ያለማጉረምረምና ያለመታከት የታዘዙትን መፈጸም፣ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ስግደትን፣ ሕርመትን (ጾምን) መለማመድና ገንዘብ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ገዳም የትጉሃን መናኸሪያ እንጂ የሰነፎች መኖሪያ፣ መጦሪያ ወይም መደበቂያ አይደለምና፡፡

ገዳማዊው መነኩሴ መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ በገዳማቸው ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሲመደቡ ማለትም አትክልትን መትከል፣ መኮትኮትና ውኃ ማጠጣትን፣ እርሻ ማረስን ሌሎችንም አስፈላጊና ተገቢ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን፣ በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መሰሎቻቸው ገዳማውያን መነኮሳት ጋር  በመስማማትና ማንኛውንም ዓለማዊና ሥጋዊ ፈቃድን በማስወገድ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጸንቶ በማገልገል መንፈሳዊና ገዳማዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ይህም ተግባራቸውና አገልግሎታቸው ደግሞ የአንድ ገዳማዊ መናኝ ጠባይ፣ ችሎታ፣ ፍቅረ ቢጽነት የሚመዘንበት የምናኔ መስፈርት ነው፡፡ ልክ እንደ አባ ዮሐንስ ሐፂር ትዕግስትን መላበስ ይጠበቅባቸዋልና፡፡

አባ አሞይ የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማ እስክታፈራ ድረስ ውኃ እንዲያጠጣት ለአባ ዮሐንስ አዘዘው አባ ዮሐንስም ያለማጉረምረም በትሕትና በመቲረ ፈቃድ ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ ተሸክሞ እያመላለሰ ያጠጣ ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመት ያች እንጨት ለምልማ አብባ ያማረ ፍሬ አፈራች፡፡

አባ አሞይም በዮሐንስ ታዛዥነት እጅግ ተደሰተ፡፡ ፍሬውን ለቅሞ ለገዳሙ ማኅበር እንካችሁ ይህ የታዛዥነት ፍሬ ነው እያለ ሰጣቸው፡፡ ዮሐንስም በልቡናው ዘወትር እግዚአብሔርን ያስብ ነበር፡፡ ለአንድ ደቂቃ እንኳን ፈጣሪን ከማሰብ አቋርጦ አያውቅም መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባ ነጮ)

በረድእነት ለረጅም ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በገዳሙ ሕግና ሥርዓት በ1947 ዓ.ም ሥርዓተ ምንኩስናን ከመ/ም አባ ተክለገሪማ ተቀብለዋል፡፡ በመቀጠል ማኅበሩ በመደባቸው ማንኛውም የአገልግሎት ሥራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቀዳማዊ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋ፡፡ በተለይ በመምህርነት ገዳሙን ለማስተዳደር የገዳሙ ማኅበር መርጧቸው የገዳሙ አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ገብረ ማርያም (አባነጮ) የዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ አቡነ ጣዕመ ክርስቶስ ገዳም መምህር በመሆን ለረጅም ዘመናት አገልግለዋል፡፡ መምህርነቱን ከለቀቁ በኋላ ለ35 ዓመታት በአብረንታንት ገዳም ተወስነው (በሕርመት) እህል ሳይበሉ ቋርፍ ብቻ በቀን አንድ ጊዜ በመመገብ በጸሎትና በስግደት በተባሕትዎ ነበሩ፡፡ በጠቅላላ በዋልድባ ገዳም ለ71 ዓመታት ኑረዋል፡፡

ሀ. መምህር ወባሕታዊ አባ ገብረ ሥላሴ (አባ ነጮ) ሁሉንም የመነኑ (የናቁ) መንፈሳዊ አባት!!

የዋልድባ ገዳም ገጸ ምድር በሰሜን በኩል የተከዜን ወንዝ በምሥራቅ በኩል የእንስያን ወንዝ በደቡብ በኩል የወይባ ወንዝ በምዕራብ በኩል የዛሬማን ወንዝ የሚያካልሉት ታላቁ የዋልድባ ገዳም በአራት ወንዞቹም በሚገናኙበት የተከበበ ቦታ ተሻግሮ በግርማ ሞገስ የታጀበው በደን ጥቅጥቅ ያለ ቦታ በብዛት የተለያዩ የበረሃ አራዊትና የተለያዩ አዕዋፍ የሚኖሩበት በተለይ የነብሩ ድምፅ ወደ ማታ አካባቢ ለወጣኒ መናኝ እንቅልፍም አያስተኛ፡፡ ከዚህ ጋር የዝንጀሮ አብሮ እየተቀባበሉ በጉሩፕ መጮሕ ምንድነው በዚህ በረሃ (ገዳም) የተፈጠረው ያስብላል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ርጭና ጸጥ ይልና ትንሽ ቆይቶ በአንጻሩ የአባቶች የባሕታውያን ጸሎትና ስግደት የመቁጠርያ ድምፅ ልክ እንደሚጓዝም ንብ ይሰማል፡፡ ያለህበት ቦታ ምንኛ ቅዱስ መሆኑን ሕሊናህ በሙሉ ይሠበራል እኔ ማነኝ የት ነው ያለሁት ከምድር ወይስ ሀገረ ብፁዓን፣ሀገረ መላእክት ያስብላል፡፡ በተለይ በታላቁ አብረንታንት ገዳም ሥራቸውን ምስጋና ብቻ ያደረጉ የምድራችን መላእክት ከአለባበሳቸው እስከ አነጋገራቸው በተባሕትዎ እስከፍጹምነት የደረሱ የዚህን ዓለም ጣጣ ውጣ ውረድ የማያውቁ ከምድራዊ ምኞት ነፃ የሆኑ የዓለም ኅብረተሰብ በተለያየ ምኞት እርስ በራሱ በሚናቆርበትና በሚጠፋፋበት በተለይ በአሁኑ ጊዜ ግማሹ በሃሣብ ግማሹ በተግባር ታላላቅ ምድሪዊ ተስፋዎች አሉን በሚል ምኞት እነኝህ ሐሳቦች ፍላጐቶች ሁሉ ለማግኘት በውኑም በሕልሙም በሚለይበት በአሁኑ ዘመን፡፡

ነገር ግን እንዲህ ያለ ከንቱ ምኞት ዓለም በአንተ እንጂ አንተ በዓለም እየኖርክ አይደለህም እነዚህ ሥጋዊ ተስፋዎችና ፍላጎቶች ስኬታማ ስለማይሆኑ ግራ ትጋባለህ በስሜት ህዋሳትህ ለብዙ ጊዜ ትመራለህ መንፈስህ እነዚህን ስሜቶችህን በተቃወመች ጊዜ እጅግ ትቃወማለህ ከዚህ አይነቱ ተጽእኖ መቸ ትላቀቅ ይሆን? በዓይንህ ያየኸውን በጆሮህ የሰማኸውንና በእጅህ የዳሰስከውን ብቻ ታምናለህ በዓይን ካላየህ በጆሮ ካልሰማህ ሁሉንም ነገር ትጠራጠራለህ ለጥርጣሬህ ምክንያት ምን ይሆን? ለዚህ መንሥኤው በሥጋዊ ፍላጐት መኖርና በስሜትህ መመራትህ ነው ማንም እንዳያይህና እንዳይናገርብህ ስምህ እንዳይነሣ አጸያፊ ነገሮችን በድብቅ ትፈጽማለህ፡፡ ነገር ግን ሰው ሆይ ማንም እንዳላየህ ታስብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሐናንያንና የሰጲራን ሸፍጥና ክህደት ማየት በቂ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መዋሸት አይገባምና፡፡ የሐ. ሥራ 5÷1፡፡

አበው  እንደ መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ አባ (አባነጮ) የመሰሉ እግዚአብሔርን የሚያፈቅሩ ሁሉንም የመነኑ ሕጉንና ትእዛዙን አክብረው በንጽሕና ተጠብቀው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር የማትታይ፤ የማትለወጥ፤ የማትሞት፤ የማትሻር፤የማታልፍ ዘለዓለማዊ ኃይል አምላክ እያሉ ያለማቋረጥ እድሜ ዘመናቸውን በሙሉ ሲያመሰግኑት ኑረዋል፡፡ ለወደፊቱም እንዲሁ እያመሰገኑትና እያመለኩት ይኖራሉ፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምሥጢርን የሚያውቁ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙ ባሕታዊ ፈቃደ ሥጋን በፍጹም ልቡና በቁርጥ ሕሊና ቆርጦ በመጣል የታወቁ አበው ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ጻድቃንሰ ዔሉ ገዳማተ ወበዘብድወ ጠሊ ወበሐሜለት ጻድቃን ሁሉን እያጡ የበግና የፍየል ለምድ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በከርሰ ምድር ተቅበዘበዙ ዕብ. 11÷31-38

እኒህ ባሕታዊና ገዳማዊ አባት ሕይወታቸውን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጡ የሕይወት ዘመናቸውን ሁሉ ከእግዚአብሔርን በማገልገል አሳልፈዋል፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባነጮ) አገልግሎት ከሁሉም በላይ የሚወዱ የሚመክሩ ትዕግስትን ገንዘብ ያደረጉ አባት ነበሩ፡፡ አንድ መነኩሴ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዳሴ ጊዜ በጸአድወ አልባስ ከወትሮ ለየት ያለ መልክ ያላቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያስተናብሩ በተመስጦ አያቸው፡፡እጅግ በመገረምና በዝምታ በመመልከት ከቅዳሴ በኋላ ዛሬ ምንድነው ምክንያቱ ሕገ አበው ፈረሰ እንዴ! እንዴት ነጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ ብለው ጠየቁ፡፡ በገዳሙ ሕግ (ብጫ) ወይም ወይባ ብቻ ነው መልበስ የሚፈቀደው መ/ር አባ ገ/ሥላሴ ለመነኩሴው ሲሏቸው አባ ዝም ይበሉ ብለው ለብቻ ወስደው እርስዎ እግዚአብሔር ያደለዎት ምሥጢሩን የገለጸልዎት ትልቅ አባት ነዎት፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ያዩአቸው ሰዎች አይደሉም መላእክት ናቸው፡፡ ስለዚህ ለማንም እንዳይናገሩ ብለው መክረዋቸዋል፡፡ አባቶች በሰው ልቡና ገብተው ምን እንዳሰብክ ምን እንደሠራህና እንዳጋጠመህ ያውቃሉ፡፡ ልክ ዳዊት በኢዮብ፣ ኢዮብ በዳዊት ልብ፣ ሳኦል በአበኔር፣ አበኔር በሳኦል ልቡና ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያና ሲጲራ ምን እንዳደረጉ እንዳወቁ አበውም በሰው ልቡና ያለውን ሁሉ ያውቃሉ፡፡

ከዚህ በኋላ እኚህ አባት በጸሎት በአታቸው ሆነው አምላካቸውን በማመስገን እንዲወሰኑና ለዚህ እጅግ ጥልቅ ስለሆነው ስለ መንፈሳዊ ማዕረግ ልገልጽልዎት እፈልጋለሁ አሏቸው እና አባም እሺ አሏቸው፡፡ እየውልዎት የባሕታውየን የመጀመሪያው ማዕረግ በአራቱም አቅጣጫ መርሳት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአካባቢህ ስላሉ ሁሉም ነገሮች ምንም ሳትጨነቅ በበአትህ በጸሎትም ሆነኸ በተመስጦ መሆን አለብህ፡፡ ከዚያ ከተፈጥሮ ሕግ በላይ በሚሆን በሌላ ዓለም ትኖራለህ ከዚያ የት እንዳለህ እንኳን በቤት ውስጥ ይሁን በውጭ መሆንህ የምታውቀው ነገር አይኖርም፡፡ ያየኸውንም ተአምር ሁሉ ከእግዚአብሔር የሆነውን ለማንም አትናገር፡፡ ወደ ሀገረ ብፁዓን ብትነጠቅ ወይም ወደ ሰማይ ብትወሰድ እንኳ ምንም የምትለው ነገር የለም፡፡ “እንዲህ አይነቱን ጸጋ ለማግኘት ማንም ራሱን አያታልል፡፡ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን”፡፡ 1ኛ ቆሮ. 3÷18

ሦስቱ አሥራው ካሥሩ አሥራው ጋር የሚሠወሩበት የተክል ቦታ አለ፡፡ ልክ እንደኗ ዋልድባ ገዳም (ሐተታ) በምሥራቅ በኩል ያለ የተክል ቦታ ሌሊት ካደረበት ውርጭ የጧት ሙቀት ያገኛል ቀን ከዋለበት ሐሩር የማታ ጠል ያበርደዋል እንዲህ ሁኖ ሰባት ነገር ያስገኛል፡፡ ቅጠል፣ ልምላሜ፣ ጽጌ፣ ፍሬ፣ ጣዕም፣ መዓዛ፣ ነፍስ ያስገኛል፡፡ እንደ ሙቀት፣ እንደጠል ረድኤት እንደ ውርጭ፣ እንደ ሐሩር መከራ እንደ ተክል የባሕታዊ ሰውነት፣ እንደ ምድሩ ልቡና ነው፡፡ እንደዚህም ሁሉ ባሕታዊ በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቆ የኖረ እንደሆነ ሰባት ሀብታትን ከእግዚአብሔር ያገኛል፡፡ እንደ ቅጠል ሃይማኖት እንደ ልምላሜ አእምሮ እንደጽጌ ትሩፋት፣ እንደ ፍሬ ፍሬ ክብር እንደ ጣዕም ጣዕመ ጸጋ፣ እንደ መዓዛ መዓዛ ጸጋ እንደ ሥጋ ብርሃን ያስገኛልና “ወይስቅዮም”፣ ዐራቱን ባሕርያተ ሥጋ ካምስቱ ሕዋሳተ ነፍስ ጋራ ያከብራቸዋል፡፡ ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ካሥሩ ማዕርጋት ጋራ ይሰጣታሉ፡፡ በፍቅረ ቢጽ በፍቅረ መላእክት በፍቅረ እግዚአብሔር ልብ ከክብር ወደ ሚበልጥ ክብር ይመራል፡፡ ፍቅረ ቢጽ መከራ ይቀበላል፡፡ በፍቅረ መላእክት ወደ ጸጋ ይመራል፡፡ በፍቅረ እግዚአብሔር ለሚያድርበት የአምላክ የክብሩ መገለጫ ለመሆን በፍጹም ክብር ይከብራል፡፡ አንድም ግዙፋንን ረቂቃንን በማየት ልቡና ከክብር ወደሚበልጥ ክብር ይመራል፡፡ ግዙፋኑን በሚያይበት ጊዜ መከራ ይቀበላል ረቂቃኑን የእግዚአብሔር ክብር በሚያይበት ጊዜ ወደ ክብር ይመራል በፍጹም ክብር ይከብራል መ/ም አባ ገ/ሥላሴ ለወጣንያን መነኮሳትና አርድእት ሲመክሩ ፍጹም መሆን ትፈልጋለህ ነፍስህ ከእስር ተፈትታ ነጻነት ወዳለበት ቦታ እንድትሄድ ትፈልጋለህ? ከሁሉ በፊት ከዓለማዊ ምኞት፣ ከዓለማዊ ፍትወት ራቅ፣ ከፍቅረ ንዋይ ራቅ፣ ከስሜትህ ተጽእኖና ዓለም በውስጧ ከሳለችብህ ነገር ሁሉ ራቅ፡፡ በመጀመሪያ  በእግዚአብሔር ፊት ራስህን እንደ ትንሽ ሰው አድርገህ አቅርብ ብለው ይመክራሉ፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ በዋልድባ ገዳም ማንኛውም በገዳሙ የአርድዕትነት ሥራ ያልሠሩት ነገር የለም፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ በትህትና፤ በመቲረ ፈቃድ፤ በፍቅር፤ በመታዘዝ በተመደቡበት ኃላፊነት ሁሉ አሉ የሚባሉ ሥራዎችን በሙሉ ሠርተዋል፡፡ ማኅበሩ ለታላቅ መዓርግ ሲመርጣቸው እኔ ለዚሁ ታላቅ ገዳም ማኅበር በአበ ምኔትነት መምራት አይገባኝም፡፡ በሁሉም ነገር ከኔ የተሻሉ እነ እገሌ እያሉ አይሆንም ብለው በሌሊት ተነሥተው ወደ በረሃማው የገዳሙ ሌላው ገጽታ ገብተው በዋሻ ውስጥ ለመፍለስ ወሰኑ፡፡ ከወሰኑም በኋላ ወደ ዋሻው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን ጥሪው የእግዚአብሔር ስለሆነ የተወሰነ ደቂቃ ከተጓዙ በኋላ ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ በጣም የሚያስፈራ ከውፍረቱም ከርዝመቱም በጣም ትልቅ ዘንዶ መንገዱን ዘግቶ አላሳልፍ አላቸው፡፡ በወዲህ ቢሉ በወድያ እያሉ ለማለፍ ቢጥሩም እያለፈ መንገዱን በመዝጋት ከለከላቸው፡፡ አይ ይህ ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ስላልሆነ ነው ብለው ወደ ማኅበር ተመለሱ፡፡  ዘንዶም ሸኝቷቸው ተሰወረ፡፡ አበው በሁሉም ነገር በትሕትና እኔ አንሳለሁ፤ ከኔ እነ እገሌ ይሻላሉ፤  ለሥራው የበለጠ ውጤት ያስገኛሉ፤እነሱን ለምናችሁ ሹሙ በማለት  ከልብ በመነጨ ቀና አስተሳሰብ ምነናዊ ሕይወት ልሾም፣ ልታይ ልታይ የሚያሰኝ ፆር ጠፍቶላቸው የእግዚአብሔርን ሕግ በመጠበቅ ወደ ፍጹምነት መዓርጋት ይደርሳሉ፡፡ መንፈሳዊውና ባሕታዊ አርበኛ አባ ገብረ ሥላሴ(አባ ነጮ) ምርጫው የገዳሙ ማኅበርም የእግዚአብሔርም ስለሆነ በጸጋ የተቀበሉት በ1970 ዓ.ም ነበር፡፡

ለ. የስም ባሕታዊነት አያጸድቅም!!

በዋልድባ ገዳም በአንድ ወቅት አንድ የስም ባሕታዊ ፀጉሩን አስረዝሞ (ቀራንዮ) የብረት መስቀል ተሸክሞ ከከተማ ወደ ዋልድባ ገዳም የመጋቢት መድኃኔዓለም የዓመቱን ክብረ በዓል ለማክበር ይመጣል፡፡ ዋናው ቦታ ላይ አብረንታንት ከመድረሱ በፊት አውቆ ሠራ የምትባል የአትክልት ቦታ ደረሰ እና በገዳሙ ሕግ እግሩን አጥበው ቋርፍ ሰጥተው በእንግዳ ማረፍያ ቤት እደር አሉት፡፡ እንግዳው የተኛበት ቤት ከታች የአንድ ባሕታዊ መኝታ ቤት ሆኖ ከላይ ፎቅ ነገር ነው፡፡ እንግዳው ከተኛበት በእንቅልፍ ሰዓት ማለትም ሌሊት ሰውየው ይሰግዳል እንዲባል ተንጋልሎ ተኝቶ በእግሩ ቤቱን ይመታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግራ የገባቸው ከታች ያሉት ባሕታዊ ተነሥተው ቀስ ብለው ሲያዩት ሰውየው ተኝቶ እግሩን ብቻ እያወራጨ የተኛበትን መሬት ሲደበድብ ባሕታዊ አዩት፡፡ እኒህ አባት አባ ገ/ማርያም አውቆ ሠራ ይባላሉ፡፡ የአትክልት ቦታ ኃላፊው ናቸው፡፡ ዱላቸውን ይዘው ተነሱ፡፡ የሰውየውን ትክክለኛ ማንነቱን ስለ ደረሱበት አንተ አስመሳይ ሂድ ውጣ እንደ አንተ አይነቱ በአባ እንጦንስና መቃርስ ቆብ የሚቀልድ ወስላታና ውሸታም እዚህ አያድርም ብለው በሌሊት አስወጥተው አባረሩት፡፡

ለምን ቢባል በሰዎች ዘንድ ትልቅ መስሎ መታየት እውነተኛ ሳይሆኑ በሰው ዘንድ እውነተኛ ባሕታዊ መስሎ መታየት በእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ነው (ደካማና ኃጢአተኛ ከሰው ሁሉ የበታች እንደሆንክ ብታስብ ለአንተ መልካም ነው) ዋጋህን ታገኛለህና ዋጋህን የሚከፍልህ ሰው ሳይሆን ራሱ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማንኛውም መልካም ስጦታ ማንኛውም ፍጹም በረከት ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ያዕ. 1÷17፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም አንድ ባሕታዊ የጠለቀ ትምህርት የሌለው ሂዶ ብቻውን ከበረሃ በገዳሙ በአንዱ ክፍል በዋሻ ዘግቶ እየጸለየ እየሰገደ ተቀመጠ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ሰይጣን መጥቶ ምነው ከዚህ እልም ካለ በረሃ ብቻህን አለው? ባሕታዊው ሲመልስም እጸድቅ ብዬ ነው አለው፡፡ ሰይጣኑ ዝም ብሎት ሄደ እንደገና በሌላ ጊዜ መጥቶ ምነው አባ ብቻህን ከዚህ በረሃ አለው? ባሕታዊው ክርስቶስን ባገኘው ብዬ ነው አለው ያው ሰይጣኑ ያሁኑ ይባስ ብሎት ትቶት ሄደ፡፡ በሌላ ጊዜ አባ መቃርስ የሚባል አባት ወደባሕታዊው ሄደና የተደረገው ሁሉ ስለተገለጸለት ካንተ ዘንድ ሰው አልመጣም ብሎ ጠየቀው፡፡ አልመጣም አለው፡፡ አባ መቃርስም የእውነቱን ንገረኝ አለው፡፡ አወ መጥቶ ነበር አለው፡፡ ምን አለህ? አለው፡፡ ብቻህን ከዚህ በረሃ ለምን ተቀምጠሃል አለኝ፡፡ እጸድቅ ብዬ አልኩት፡፡ ዝም ብሎኝ ሄደ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ መጣ፡፡ ምነው ብቻህን አለኝ፡፡ ክርስቶስን ባገኝ ብዬ አልኩት፡፡ ያሁኑ ይባስ ብሎኝ ትቶኝ ሄደ አለው፡፡ አዬ ምነው እንዲህ ማለትህ የምትጸድቅና ክርስቶስን የምታገኝ አንተ ብቻ ነህ በዓለም ያሉ ሁሉ ክርስቶስን የሚያገኙት መሰለህ ተሳስተሃል ለሦሰተኛ ጊዜ የመጣ እንደሆነ የእኔስ ግብሬ የከፋ ስለሆነ ውሻን አሥረው ለብቻው እንደሚያኖሩት እኔም ባሕርዬ ቢከፋ ግብሬ ከሰው ባይስማማ ከዚህ መጥቼ ከሰው ተለይቼ፣ ከበዓት፣ ተከትቸ፣ ውኃ ተጎንጭቸ፣ ድንጋይ ተተርሼ፣ ተቀምጨአለሁ ብለህ በለው እንጂ እንደዛ እንዳትለው አለው፡፡ ሰይጣኑም በሌላ ጊዜ እንደ ልማዱ መጣ ጠየቀውም መነኩሴውም አባ መቃሪ እንደነገረው አድርጎ ነገረው (አኮ አንተ ዘገበርከ ዘንተ አባ መቃሪ ውእቱ) ይህን ያደረገ መቃሪ ነው አንተ አይደለህም ብሎት ትቶት ሄደ፡፡

በጓደኞችህ መካከል በተቀመጥህ ጊዜ እንዳታፍር ጥረው ግረው በላባቸው ያገኙትን ሀብት ተሰብስበው የሚበሉትን፤ የሚጠጡትን አዘጋጅተው ሲበሉ ሲጠጡ እገሌ ተስፋ የለውም ብለው ይጠሩታል፡፡ ያን ጊዜ እኔ ይህን ያህል አገባሁ አገኘሁ እያሉ ሲጫወቱ ያልሠራ ያፍራልና እንደዚህም ሁሉ በመንፈሣዊ ሥራ (አለል ዘለል) ቀልድ፤ አሉባልታ፤ ሐኬት የተቋራኙት ሰው አትሁን፡፡ በጻድቃን መካከል በተቀመጥህ ጊዜ እንዳታፍር በአባ ብሾይ ገዳም የቆስጠንጢኖስን ስም በጸሎተ ቅዳሴ በጸሎተ ማኅበር ይጠሩታል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቆስጠንጢኖስ መነኮሳት በክንፈ እሳት እየበረሩ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሲገቡ አይቶ በአካለ ነፍስ መጥቶ አባ ብሾይን “ሰላም ለክሙ ብፁዓን መነኮሳት” አላቸው አንተም ብፁዕ ነህ በዘመንህ ቀርነ ሃይማኖት ቁሞልሀልና አለው፡፡ ይህንስ አውቄ ቢሆን መንግሥቴን ለቅቄ ከበረሃ ወድቄ ጤዛ ልሼ ደንጊያ ተንተርሼ በኖርሁ ነበር አለ፡፡

የሁሉም አብነቱ አባቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ የትሩፋት አበጋዞች በሰውነት ያለ አእምሮ ጠባይዕ ሥራ ሠርቶ ሊገለጽ ነው እንጂ ተሰውሮ ሊቀር አይደለም፡፡ ሰውነታቸው በወዲህም በወድያም ከበረች (ወጻድቃንሰ ውስተ ሕይወት ዘለዓለም) ሥራውን ሠርተው ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ጻድቃንስ ሁልጊዜ በዘለዓለም ሕይወት ውስጥ ናቸው፡፡ በመሠረቱ ባሕታዊ ማለት ተባሕተወ ብቸኛ ሆነ፤ ከሰው ተለይቶ ሰው ወደማይደርስበት ቦታ ሔዶ ሥጋውን ክዶ ለነፍሱ ብቻ ያደረ ማለት ነው እንጂ በየከተማው እየዞረ የተባሕትዎ ልብስ ለብሶ የማስመሰያ ልብስ ለብሶ በቅዱሳን ባሕታውያን ስምና ልብስ ከተለያዩ ሥጋዊ ችግሮች ለመውጣት የሚደረግ ውዥንብር ፍጹም ሰይጣናዊ ሥራ ነው፡፡ ማታለልን ማስመሰልን እንዲያውም በአባቶች ስምና ልብስ ሳይበቁ በቅቻለሁ፤ ሳያውቁ አውቄአለሁ የሚሉ ምእመናንን ግራ የሚያጋቡ ከቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት ውጭ በፍጹም ከአንድ መንፈሳዊ ነኝ ከሚል እንዲያውም ባሕታዊ ገዳማዊ የማይጠበቅ ተግባራት ሲፈጽሙ ማየት በጣም ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዲህ አይነቱን ተግባር የሚፈጽሙ ግማሾቹ በጭራሽ ምንም አይነት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንኳ የላቸውም፡፡ የተወሰኑት ደግሞ “ዘጎየ እም ዐጸባ” ናቸው እግዚአብሔር ይቅር በላቸው፡፡

በነገራችን ላይ እነዚህን አበው ገዳማውያን መነኮሳትና መናንያን (ግሑሳን) ብለን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ባሕታዊ የሚለው እንዳለ ሆኖ ግሑስ ማለት ትርጉሙ ከዚህ ያልተለየ ሆኖ ፍሉስ፣ ፈላሲ፣ ምንም ምን የሌለው፣ ምንም ምን የማይፈልግ፣ ከምንም ከምን ጋር ግንኙነትና ፍላጐት ሁሉ የተለየ፤ ምሳውንም፣ ራቱንም ጸሎት ስግደት የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ያደረገ ማለት ነው፡፡ ልብሱንም ሳይለውጥ እላዩ ላይ የሚያልቅ የልብስ ዓይነቱም በጣም የተለየ ነው፡፡ ይህውም ሰሌን ወይም አጽፍ ነው፡፡ አጽፍ ማለት ከቆዳ የተሠራ ማለት ነው፡፡ የጽሞና ጊዜያቸው እግር በማታዘረጋ ዋሻ ወይም ጐጆ ሆነው ጌታዬ አምላኬ ሆይ ከራሴ ጋር ብቻዬን በምሆንበት ጊዜ አንተ ከእኔ ጋር ስለሆንክ እኔም ከአንተ ጋር ነኝ እባክህ አምላኬ ሆይ ሰዎችን እንድተውና እራሴን ከአንተ ጋር እንዳደርግ፡፡ እራሴን እንድረሳና ሐሳቤን በአንተ ላይ እንዳደርግ እርዳኝ፡፡ ይህ ለእኔ መልካም ነውና በማለት አምላካቸውን ይማጸኑታል፡፡

 • ራሳቸውን የማይላጩ፣ የሚያሰክር መጠጥ የማይጠጡ፣ ከሁሉም የማይገባ መጥፎ ነገር የተከለከሉ፣ ናዝራውያን ናቸው፡፡ ናዝራዊ ማለት ከክፉ ነገር ሁሉ የተከለከለ ማለት ነው፡፡ ቋንቋው የዕብራይስጥ ነው፣ ናዚር ወይም ናዛር ማለት ከክፉ ነገር ሁሉ የተከለከለ፣ ስእለት ወይም ብፅዓት ያደረገ፣ ሕይወቱን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠ፣ በሰውነቱም የተቀደሰና የተለየ ሰው ማለት ነው፡፡
 • እንደነ ሶምሶን፣ እንደነ ሳሙኤል መሳ. 13 ሳሙ. 11 ዮሐንስ መጥምቅ ሉቃ. 1-15 ናዝራውያን ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በተወለደበትና ባደገበት ናዝሬት ኢየሱስ ናዝራዊ ተብሏል ወይም ተብሎ ይጠራል፡፡
 • አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ከኩነኔና ከዘለዓለማዊ ሞት እንዲያድነው ጽኑ ተስፋና ብፅዐት ሰጥቶ የነበረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ናዝራዊ ተባለ፡፡ “ወቦአ ናዝሬተ ኀበ ተሐፅነ ከመ ይሰመይ ናዝራዊ፡፡” ናዝራዊ ይባል ዘንድ ናዝሬት ገብቶ አደረ፡፡ ማቴ. 2÷23 ለእኛም ተባሕትዎውንም ሆነ በገዳም መወሰንን፣ መጾም መጸለይን፣ መስገድን፣ በገዳም መኖርን የአስተማረን እርሱ ራሱ ሊቀ ካህናት መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስትናንም የመሠረተ እርሱ ነውና “ወእምዝ ወሰዶ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚእ ኢየሱስ ገዳመ ከመ ይትመከር እምኀበ ዲያብሎስ” ማቴ. 4÷1
 • “ወጾመ አርብዐ መዓልተ ወአርብዐ ሌሊተ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ፡፡” ሠራዔ ሕግ ነውና:: ሥራውን በገዳም መሠረተ፡፡ በገዳም ምን መደረግ እንዳለበት አስተምሮና ሠርቶ ካሳየ በኋላ ዓለሙን ለማስተማር “በዓለም በሚገኙት ሁሉ አስተማሪ እንዲሆኑ ሐዋርያትን መረጠ፡፡” መጀመሪያ ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ እንድርያስን ቀጥሎም ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሐንስን ጠራቸው፡፡ “ዓለሙን ተውት እኔን ተከተሉኝ” ማቴ. 4÷1-2፣ ማቴ. 4÷18-22፡፡
 • አባቱንና እናቱን፣ እኅትና ወንድሙን፣ ዘመድ አዝማዱን ትቶ ያልተከተለኝ የእኔ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም አላቸው፡፡ እነሱም ሁሉንም ትተው ተከተሉት፡፡ ማቴ. 4÷22፣ ማቴ. 19÷27፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም የጠየቀው ስለዚህ ነበር፤ እንዲህ ሲል እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፡፡ “ናሁኬ ንሕነ ኀደግነ ኩሎ ወተሎናከ ምንተ እንከ ንረክብ” ሁሉን ትተን ተከተልንህ የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው? አለው ጌታም እንዲህ ሲል መለሰለት፡፡ “አማን እብለክሙ አንትሙ ተለውክሙኒ አመ ዳግም ልደት አመ ይነብር ወልደ እጓለ እመሕያው ዲበ መንብረ ስብሐቲሁ አንትሙኒ ትነብሩ ዲበ ዐሠርቱ ወክልኤቱ መናብርት ወት£ንኑ ዐሠርተ ወክልኤተ ሕዝበ እስራኤል” እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ልትፈርዱ በዐሥራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፡፡ ማቴ. 19÷28

በዘመነ ነቢያት የተገኘ ሥርዓተ ተባሕትዎ በዘመነ አበው በነሄኖክና በእነመልከ ጼዴቅ ተያይዞ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተግባራዊ ሆኖ ከሐዋርያትና ከሰብዓ አርድዕት ደረሰ፡፡ ከዚያም እንደ አባ እንጦዮስ፣ የዋህ ጳውሊ፣ በዘመናችን ደግሞ እንደ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ አባ (ነጮ) ቅዱሳን ተገኝተውበታል፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ አባ (ነጮ) የተባሉበት ምክንያት ከቅላታቸው የተነሳ ነው እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ በጣም ቀይና ርቅቅ ያሉ ከአንደበታቸው ቃለ እግዚአብሔር ብቻ የሚወጣ አባት ናቸው፡፡ ከሠላሳ ሰባት ዓመታት በላይ እህል ሳይበሉ በገደሙ ሕግና ደንብ መሠረት (ቋርፍ) ማለትም ሥራ ሥርና ቅጠላ ቅጠል በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በመመገብ ለቁመተ ሥጋ ያኸል ነበር የሚኖሩት፡፡ ለዚህም ነው ሰውነታቸው (በቋርፍ) ተጐሳቁሎ ይታያል፡፡

9-2

ከአብረንታንት ገዳም ውጭ ወጥተው ሌላ ቦታ አይንቀሳቀሱም፡፡ ከቅጠላ ቅጠል በቀር ሌላ ቀምሰው አያውቁም ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖራለን እንጂ ከማንም እንጀራን አልበላንም እንዲያውም አልበላንም፡፡ ይህም እኛን ልትመልሱ በሥራ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁአለን፡፡ 2 ተሰ. 3÷8

“ብፁዓን እለ ይርኅቡ ወይጸምዑ በእንተ ጽድቅ” አባቶች አብዝተንማ ከተመገብን ሰውነታችን ገቶ ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለው ከሚበሉት ከሚጠጡት ከፍለው የሚራቡ ንዑዳን ክቡራን ናቸው ፡፡ ማቴ. 5÷6

መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ /አባ ነጮ/ ገዳሙን በአበ ምኔትነት በሚያስተዳድሩበት ወቅት የማኅበረ መነኮሳቱ ብዛትና የገዳሙ ዕድገት ልዩ ነበር፡፡ በሌላ መልኩ ፈተናዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ ምንም እንኳን መነኮሳቱ ለፈተና ዝግጁ ቢሆኑም የራሱ የሆነ ታሪክ ትቶ አልፏል፡፡ ለምሳሌ የገዳሙን በርሃ (የኢህአፓ) እንቅስቃሴ ለመደበቅም ሆነ ለመተላለፍ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በከተማው (ደርግ) የሚያስተዳድርበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ማኅበረ መነኮሳቱ የሚለብሱት (አቡጀዴ) መግዛት የተከለከሉበት ቅጠል ለብሰው ጊዜውን በጸሎትና በእንባ ያሳለፉበት ክፉ ወቅት ነበር፡፡ ገዳማውያን መነኮሳት ወደ ከተማ ለማኅበሩ የሚያስፈልግ ፍጆታ ሁሉ ለመግዛት በሚሄዱበት ጊዜ ለሽፍታ ለወንበዴ ነው የምትወስዱት፤ ወንበዴ ነው የላካችሁ፤ በማለት መብታቸውን ያጡበት እንደሰው ያልታዩበት ወቅት ነበር፡፡ በገዳሙ ከ1000 (ከአንድ ሺህ) በላይ መነኮሳት ይኖራሉ፡፡ ለእነዚህ ማኅበረ መነኮሳት ሊቃነ አርድዕት ናቸው የራቀውን የሚያቀርቡ፡፡ ከነዚህ ውጭ የገዳሙ መነኮሳት ያለ ሥራ ወደ ከተማም ሆነ ወደ ገጠር መውጣት አይፈቀድላቸውም፡፡ ገዳሙ በወባ በሽታ የታወቀ ነው፡፡ ምንም እንኳን መነኮሳቱ የወባ (ክኒን) ባይጠቀሙም ነገር ግን በሽታው አቅም ስለሚያሳጣ ስኳር ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው ወታደራዊ ሥርዓት ለመነኮሳቱ ወታደሩ በየኬላው መነኮሳቱን ይፈትሽና ይዘውት የተገኘ ስኳርና ባትሪ ድንጋይ ምንድነው የያዝከው ስኳር ከሆነ ከአንድ ኪሎ በላይ አይፈቀድም ባትሪም እንደዚሁ ነው የተፈቀደው ሌላው ለወንበዴ ነው የምትወስደው መልስ በማለት የተገዛው የመነኮሳት ስኳርና ባትሪ ተወርሶ መነኮሳቱ ስኳር በመግዛታቸው ብቻ ከወር በላይ የታሰሩበት የተገረፉበት ጊዜ ነበር፡፡ በአንጻሩ የገዳሙን በረሃ የተቆጣጠረው (ኢሀአፓ) ደግሞ ለአረጋውያንና ለበሽተኞች የተቀመጠ (አቅምሐት) ማለትም ማር አምጡ በማለት በጉልበት ሲዘርፍ በተለይ በየአትክልት ቦታዎች የተመደቡ አርድዕት የመታሰር የመደብደብ ግፍና በደል ደርሶባቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት ከህወሓት በመዘጋ ወልቃይት አካባቢ ያደረጉት ጦርነት (የኢሀአፓ) ሠሪዊት አፈግፍጎና ተሸንፎ ወደ ዋልድባ ገዳም ሸሽቶ ገባ በዚሁ ምክንያት መነኮሳቱን በማስገደድ ያላቸውን ቋርፍና ቅጠላ ቅጠል በመቀማት የአረጋውያንና የገዳሙን ምግብ አራቆቱት፡፡ በዚህም አልበቃ ብሎ በውጊያ የቆሰሉትን በግዴታ በማሸከም መነኮሳቱን ያሰቃያሉ፡፡ ወደላይ ብንሄድ ወንበዴ በገዳም ቢኖሩ ቀማኛ  ገዳሙ በእንዲሁ የሥቃይ ዘመናትን አሳለፈ፡፡ ገዳሙ በበረሀ እንስሳ የታደለ ነው፡፡ የሌለ እንስሳ አይነት የለም፡፡ ከቀጭኔና ዝሆን በቀር ስለዚህ ከአካባቢ የገጠር ነዋሪዎች ለአደን ወደ ገዳሙ ይመጣሉ፡፡ በአንድ ወቅት በዋሻ የሚኖር ባሕታዊ አዳኙን አየውና ምን አለ መሰላችሁ “አዳኝም ለከርሱ መናኝም ለነፍሱ ማልደው ተነሥተው ሁሉም ገሰገሱ አሉ በዋሻ ያሉ ባሕታዊ ሲናገሩ፡፡ አዳኙ ሰማቸውና ወድያውኑ መሳሪያውን ጥሎ እኔም ለከርሴ ሳይሆን ለነፍሴ ብሎ መነነ”፡፡

 

9-4እንዲሁም አንድ የንጉሥ ልጅ ነበረ ከአባቱ ቤት መነኮሳት መጥተው አደሩ፡፡ ሌሊት መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ ለልጁ እነዚህን መነኮሳት ተከትለህ ሂድ አለው፡፡ ተከትሎም ሄደ፡፡ ከገዳሙ ሲደርስ ወድያውኑ በሽታ አደረበት፡፡ ታመመ (ከሃያ አምስት) ዓመታት በላይ በጽኑ ደዌ ወደቀ መነኮሳቱ ዐሥሩን ዓመታት ረድተውታል፣ ጠይቀውታል፣ አስታመውታል ዐሥራ አምስቱን ዓመታት ግን ሳይጠይቁት ወድቆ በስቃይ ኑሯል፡፡ ከዚህ በኋላ አባ ኪሮስ ጌታችን አምላካችንን  በጸሎት በመጠየቅ የአበው ባሕታውያን እረፍተ ሥጋ ወነፍስ እየዞሩ ለማየት ሲሄዱ ከዚያ ገዳም ደረሱ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ቢገቡ የእመቤታችንን ሥዕል አገኙ (ሰላም ለኪ) ቢሏት ሥዕሏ “ለከኒ” ለአንተም ሰላም ብላቸዋለች፡፡ ማኅበረ መነኮሳቱ የአባ ኪሮስ ፊታቸው እንደ ፀሐይ ሲያበራ መልካቸው ሲያጽደለድል አይተው እዚያው ይደር መነኮሳቱ ይህስ ዓለማዊ ነው ከዚያ ከእንግዳ ቤት በሽተኛው ድውዩ ካለበት ይግባ ብለው ወስዱዋቸው ሲገቡ ከድውዩ ጋር ቅዱስ ሚካኤል በራስጌ ቅዱስ ገብርኤል በግርጌ ሁነው ታማሚው ከመሐከል ወድቆ (ተኝቶ) አገኙት፡፡ አባ ኪሮስ ለመላእክቶች ከዚህ የተቀመጣችሁ ምን ሁናችሁ ነው? አሏቸው የመላእክት መልስ የዚህን ሰው ነፍሱን ከሥጋው ለይታችሁ አምጡ ተብለን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዘን ነበር ነገር ግን ነፍሱን ከሥጋው የማትለይልን ሁና እንጠብቃለን አሉ፡፡ አባ ኪሮስ ታማሚውን ደግሞ መልሰው አንተስ የወዴት አገር ሰው ነህ ብለው ጠየቁት፡፡ ታማሚውም የንጉሥ ልጅ ነበርኩ ከአባቴ ቤት መነኮሳት መጥተው አደሩ፡፡ ሌሊት መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ ተከትለሃቸው ሒድ አለኝ፡፡ እኔም በታዘዝኩት መሠረት ተከትያቸው መጣሁ፡፡ ከገዳሙ እንደ ደረስኩኝ በደዌ ተያዝኩኝ ይኸውና ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ሆነኝ ዐሥሩን ዓመት መነኮሳቱ ጠይቀውኝ ነበር ከዚያ ወድያ ግን አልጠየቁኝም እንዲህ ወድቄ እኖራለሁ አላቸው፡፡ አባ ኪሮስም አዝነው አልቅሰው ሲያበቁ አይዞህ እንዲህ እንደ አንተ ሁሉ የሮም ንጉሥ ልጅ ነበረ መንኖ ወጥቶ ዛሬ ይሙት ይዳን የሆነውን የሚያውቅ ማንም የለም አሉት ራሳቸውን ነው፡፡ አባ ኪሮስ ከዚህ በኋላ ወደ ጌታችን አመለከቱ፡፡ እረፍተ ነፍስ እንዲያገኝ፡፡ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡ ከዚያ ማኅበረ መነኮሳቱ አርፏል እንሂድ ጸሎተ ፍትሐት እናድርስ ብለው መጡ፡፡ አባ ኪሮስ ለመነኮሳቱ “አሰስሉ ማዕጠንተክሙ ሀለው መላእክት የዐጥንዎ” ብለው ገሠጿቸው ምክንያቱ ስልቹዎች በመሆናቸውና የገቡበትን ዓላማ በትዕግስት ያለመወጣት መንፈሣዊ ሕይወታቸውን ስለረሱ ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በገዳሙ ወድቆ በበሽታ ሲሰቃይ ረሱት ዘነጉት ዓለማዊነት አጠቃቸው፡፡ (ፊልክስዩስ) 162 – ገጽ 203

እግዚአብሔር የሚመርጠው እንደ ሰው አይደለም፡፡ ሰው መልክና ቁመት አይቶ ሀብትና እውቀትን ጉልበትን ጤንነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ ለወገን ለዘመድ አድልቶ ይመርጣል፡፡ እግዚአብሔር ግን ፊትን ሳይሆን ልብን አይቶ ይመርጣል ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ለልዩ ልዩ አገልግሎት የመረጣቸው ቅዱሳን በሰው ዘንድ የተናቁትንና ከምንም የማይቆጠሩትን ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከፀሐይ የበሩ ከወርቅና ከእንÌ የከበሩ ናቸው፡፡ በዋልድባ ገዳም አንድ መናኝ ከገዳሙ ከገባበት ዕለት ጀምሮ በጤንነት ይሁን በበሽታ እስከ ዕለተ ሞት ድረስ በሊቀ አበው ይረዳል፡፡ በሥራም ከሆነ እስከተፈቀደለት ያገለግላል፤ ይረዳል ለተባሕትዎ ከተፈቀደለትም በኋላ ብዙ ምግባረ ትሩፋትን ያለሐኬት ሐሳብን ያለመከፋፈል ልቡናን ለዓለማዊ ምኞት ከሚጋብዙ ንግግርና ከሌሎችም ለተባሕትዎ የማይመቹ ጋር ጊዜን በከንቱ ያለማባከን ክፉ ሕዋሳት ከራሳቸው አርቀው እንደ ወጣኒ ሳይሆን በፍፁማን አምሳል ረሀቡን ጥሙን ዋዕየ ፀሐዩንና በሽታውን እየታገሱ በጾም በጸሎት በስግደት ጸንተው ከእግዚአብሔር አምላክ ኀላፍያትና መጻእያት የተገለጸላቸው አባቶች ያለፉም በሕይወተ ሥጋ ያሉም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ የምናኔ ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ ማዐርግ የበቁ አባቶች እግዚአብሔርን በመዘከር የጸኑ ናቸውና (ወይነጽሕ ልቦሙ) ልቡናቸውም ንጹሕ ይሆናልና (እስመ እለኒ ደለዎሙ በዝየ ነጽሮተ ዝንቱ እሙንቱሰ እለተናዘዙ በአንብቦተ እግዚአብሔር) በዚህ ማዕረግ ጊዜ ለነጽሮተ እግዚአብሔር የበቁ ሰዎች እግዚአብሔርን በመዘከር የጸኑ ናቸው፡፡ (ወቦቱ ይቀትልዎ ለሕማመ ሁከቶሙ) የኀልዮ ኃጢአትን ድል ነስተውታል፡፡ ልቡናቸውም ንጹሕ ይሆናል፡፡ ለነጽሮት የበቁ ሰዎች እግዚአብሔርን በመዘከር የጸኑ ናቸው ብቃታቸውም በታናሹ ብርሃን መሸፈን ሳይቀር በታላቁ ብርሃን መሸፈን ሳይኖር እግዚአብሔርን ማየት ይቻላቸዋልና፡፡

ታሪክ እንደ አባ ጳጉሚስ ባንዲት ሴት አጋንንት ሠፍረውባት አየ ጥንቱንም ሰው ደካማ ነው በዝያውም ላይ በሴት ባሕርይ ይህ ተጨምሮ እንደምን ይቻላል ጌታዬ ወደኔ መልሰው ብሎ ጸለየ፡፡ በሴትየዋ የነበሩ ርኩሳን መናፍስት ወድያውኑ ያንድ ቀፎ ንብ ወዳንዱ ቀፎ ያንድ ማድጋ ውኃ ወደ አንዱ ማድጋ እንደሚገለበጥ በሷ ላይ ሠፍረው የነበሩ ርኩሳን መናፍስት ወደሱ መጡ፡፡ አባ ጳኩሚስም ማቅ ምንጣፍ ለብሶ ከመሬትም ካመድም ላይ ተኝቶ ርኩሳን መናፍስቱን ያማስናቸው ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ ከዚህ ሰው እንሒድ እንሒድ ሲሉ ሰማቸው፡፡ ሰው ከወዳጁ ቤት ውሎ አድሮ አይሔድምን? እናንተስ ለምን አትቆዩም አላቸው፡፡ ርኩሳን መናፍስቱ ግን ከገነት ካስወጣነው ከአዳም ልጆች እንዲህ ያለ ጸሎተኛና አርበኛ አይተን አናውቅም ብለው ብን ብለው ሔዱ፡፡ አበው  እንደ አልባሌ ሰው በገዳም ልብሳቸውን ሳይለውጡ የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ጣጣው ሁሉ ጠፍቶላቸው እንደነ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባ ነጮ) ለወጣንያን ሲመክሩ እንዲህ ይላሉ፡፡ በልቡናህ የእግዚአብሔር ፍቅር በተሳለ ጊዜ ጣዕሙን አግኝተህ ደስ ይልህ ዘንድ ሕይወትህን በሙሉ ባለመሰልቸት እግዚአብሔርን በጸሎት በአምልኮት ጠይቀው፡፡ ይህን ምሥጢር በዓይነ ነፍስ ታየው ዘንድ እግዚአብሔር የሚሰጥህ ጸጋና ክብር ይህ ነው ማለት አይቻልም በሰው ልቡና ያልታሰበ ነው፡፡ በርታ የገዳሙን ሕግና ሥርዓት ጠብቀህ አባቶች ከደረሱባት ክብር መድረስ ትችላለህ ብለው ይመክራሉ፡፡

አበው ግሑሣን መነኮሳት

ከብዙ መናንያን (ግሑሣን) መካከል የአባ አስከናፍር ታሪክን መናገር እንችላለን፡፡ አባ አስከናፍር መልካም ሥነ ምግባር ካላቸው ቤተሰብ የተወለደ ነበር፡፡ ስለነፍሱ ብዙ ያስባል፡፡ ብዙም ይጨነቃል ቅዱሳት መጻሕፍትንም በእጅጉ ይከታተላል ያነባል፡፡

ከዕለታት ባንዱ ቀን በተወለደበት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ተሰብስበው ስለመነኮሳት ማኅበራዊ ኑሮ እያነሱ ሲወያዩ ይሰማል፡፡ በሰማውም ታሪክም ልቡ በጣም ይመሰጣል፤ ከዚህ በኋላም ፈጽሞ ሕሊናው ዕረፍት ያጣል፡፡

በአንዱ ገዳም መግባት አለብኝ ብሎ ያስባል፣ አስቦም አልቀረም ተነሥቶ በምናኔ ወደአንድ ገዳም ይገባል በገዳሙም ሆኖ የብዙ አባቶችን ፈቃድ እየፈጸመ እየተጋደለ፣ ሥርዓተ ገዳማትንና ሥርዓተ ምንኩስናን እያጠና አያሌ ዘመናት በዚሁ ገዳም ተቀምጧል፡፡

አንድ ቀን መነኮሳቱ ስለግሑሳን አባቶች ታሪክ ስለ ብቃታቸውና ጸሎታቸው ሲነጋገሩ ይሰማል፡፡ በነገራችን ላይ አባ አስከናፍር የዓለማዊ ወሬ ዋዛ ፈዛዛ ቀልድ ሓሜት ሲናገሩ ሲሰማ ጆሮውን ደፍኖ ይሸሻል ይሮጣል፡፡ ስለእግዚአብሔር መንግሥትና መንፈሳዊ ሕይወት ሲነገር ከሰማ ግን ሁሉንም ትቶ ሥራውንም ጥሎ ጆሮውን ከፍቶ ዐይነ ልቡናውን አቅንቶ በተመስጦ ይሰማል እንጂ አይነቃነቅም፣ ጥሎም አይሸሽም፡፡

አባ አስከናፍር ከፍ ብለን እንደጠቀስነው መነኮሳቱ ስለግሑሳን ኑሮ ሲናገሩ የሰማውን ወድያውኑ በጥያቄ አባቶች ከናንተ የበለጡ ግሑሳን፣ መናነያን አባቶች አሉን? ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነርሱም እንዴታ! እኛማ ከዓለም ትንሽ ነው የራቅነውና የተለየነው፡፡ አዎ ስንታመም አስታማሚ፤ ሐዘን፣ ችግር፣ ፈተና ሲደርስብን ምእመናን እየመጡ ያጽናኑናል፡፡ እነርሱ ግን ከአራዊትና ከጸብአ አጋንንት ጋር ዘወትር እየታገሉና እየተጋደሉ ነው የሚኖሩት፣ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ መላእክቱን ይልክላቸዋል ይሉታል፡፡

አባ አስከናፍር ግሑስ ለመሆን ተመኘ፣ አንድ ቀን ትንሽ ኅብስት ይዞ ከገዳሙ ይወጣል፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ ተጓዘ ያችን ቁራሽ ኅብስት እንኳ ሳይቀምሳት እልም ካለ በረሀና የአሸዋ ሙቀት ከበዛበት ቦታ ይደርሳል፡፡ ደክሞታልና በዚያው በሞቀ መሬት ይተኛል፡፡

ጠዋት ሲነሣ በራስጌው አንድ ቴምር በቅሎ ዐሥራ ሁለት ዘለላ አፍርቶ፣ ከአጠገቡም የውኃ ምንጭ ፈልቆ ሲፈለፍል እና ሲፈስ አይቶ ይደሰታል፡፡ ይህ ቴምር ትናንትና አልነበረም የውኃ ምንጩም እንደዚሁ ፈጽሞ አልነበረም አልታየኝም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እዚህ እንድኖር ፈቃዱ ቢሆን ነው ብሎ ወሰነ፡፡ አንድ የቴምር ዘለላ ለአንድ ወር እየተመገበ፣ ከምንጩም ውኃ እየጠጣ፣ ከእኩያን አጋንንት ከርኩሳን መናፍስት ከኃያላን አናብስትና አናብርት ጋር እየታገለ 67 ዓመት ሙሉ በዚሁ በረሃና ዋዕየ ፀሐይ በሚቃጠልበት ቦታ ኖረ፡፡

(አባ ነጮም) እና አባ አስከናፍር የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር የዓለማዊ ሥራ ሐሜትም ይሁን አሉቧልታ አይወዱም፡፡ እየተቆጡ ርቀው ይሄዱ ነበር፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴም በዋልድባ ገዳም 70 ዓመታት በተባሕትዎ ቋርፍ እየበሉ ማዬ ዮርዳኖስ እየጠጡ ኑረዋል፡፡

አባ አስከናፍር መላ ሰውነቱ የተሸፈነው በጠጉር ነበር፤ ከራሱ  እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ የተሸፈነው በመላ ሰውነቱ በበቀለው ጠጉሩ ብቻ ነበር፡፡ አባ አስከናፍር አናብስት፣ አናብርት፣ ሌሎችም አራዊት ዘገዳም የተገዙለት፣ የሚያገለግሉት፣ የሚያረጋጉትና የሚያጽናኑት መላእክት ታዘውለት ከሰማይ እየወረዱ ነበር የሚላላኩት ከብቃቱ የተነሣ፡፡ “መላእክቱን ስለ አንተ ይልካቸዋል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡልሃል” ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡፡ መዝ. 90/91 ቁ. 12

ከላይ በጠቀስነው ቦታ አባ አስከናፍር 67 ዓመት በሕርትምና እና በትሕርምትና በምነና ከቆየ በኋላ አባ ስንትዮስ የሚባል መነኩሴ ከነበረበት ገዳም በበረሀ በተባሕትዎ ያሉትን አባቶች መጎብኘት አለብኝ ብሎ ታጥቆ ተነሣ፡፡ ሐሳቡንም ለመፈጸም ጉዞውን ወደበረሀ ቀጠለ፡፡ በረሀውን ሲያስስም አባ አስከናፍርን አገኘው፤ አባ አስከናፍር መላ ሰውነቱ በጸጉር የተሸፈነ ስለነበረ አባ ስንትዮስ ባየው ጊዜ በጣም ደነገጠ፡፡ ምትሃት ነው ወይስ ሰው አለና ራሱን ስቶ በድንጋጤ ዝልፍልፍ ብሎ ወደቀ፡፡

አባ አስከናፍርም የአባ ስንትዮስን መፍራትና መርበትበት አይቶ አይዞህ ብሎ ቀኝ እጁን ያዘው እንዲህ አለው “ተንሥእ ኦ አባ ስንትዮስ ሠናይኑ ምጽዐትከ” አባ ስንትዮስ ወደዚህ በረሀ የመጣህበት ምክንያት በደህና ነውን? ብሎ አስነሣው፡፡ አባ ስንትዮስም አባ አስከናፍር በስሙ ስለጠራው ከድንጋጤው ተረጋጋ፣ ተጽናናም ተነሥቶም ቆመ ሁለቱም በሕብረት ጸሎተ ማርያም ጸልየው እንደጨረሱ ነገራተ እግዚአብሔርን እየተነጋገሩ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዓ በረከት ይዞ መጣ፡፡ ሁለቱንም አÌርቧቸው ሔደ፡፡

አባ አስከናፍር መልአኩ ከሔደ በኋላ ፊቱ የእሳት ፍም መሰለ ጥቂት ቆይቶም አረፈ፡፡ አባ ስንትዮስ በሁኔታው እጅግ አደነቀ፡፡ አባ አስከናፍርንም አጥቦ፣ ገንዞ ቀበረው፡፡ አባ ስንትዮስ አባ አስከናፍርን ከቀበረ በኋላ በዚያች ልዩ ቦታ ለመኖር ወሰነ፡፡

አባ ስንትዮስ በዚያች ሌሊት እዚያው ተኝቶ አደረ፤ ጠዋት ነቅቶ ወደቴምሩ ዛፍ ቢመለከት ደርቆ ከሥሩ ተመንግሎ አገኘው፤ ወደውኃው ቢመለከትም ከደረቅ አሸዋ በስተቀር የውኃ ምልክት እንኳ የነበረበት ቦታ አይመስልም ነበር፡፡

አባ ስንትዮስም እግዚአብሔር እዚህ እንድኖር አልፈቀደም ብሎ ወደገዳሙ ተመለሰ፤ የቅዱሳንን ገድል እየጻፈ ኖረ፡፡ የአባ አስከናፍርና የሌሎች ግሑሳን መናንያን አበውን ገድልና ተአምር እየዘገበ እስከ ዕለተ እረፍቱ ኖረ፡፡

ስለዚህ በከፋ ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፤ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌል በመዘጋጀት እግሮቻችሁን ተጫምታችሁ ቁሙ የክፉን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበት የእምነት ጋሻ አንሡ የመዳን ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ዘኢፆረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይጸመደኒ” መስቀሉንም የማይዝ በኋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ባለው ቃል መሠረት እነሆ እነዚህ አበው መነኰሳት ቃሉን ትእዛዙን እንደፈጸሙ ያሳስበናል፡፡ ማር. 8÷34፣ ሉቃ. 9÷23

ነገር ግን ውጫዊ ማንነታችን እንኳን ቢጠፋ ውስጣዊ ሕይወታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፡፡ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘለዓለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘለዓለም ነው፡፡ (2ኛ ቆሮ. 4÷16)

“ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ወይጽልኣ ነፍሶ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ” አበው መነኰሳት በገዳም ሲኖሩ ዋዕየ ፀሐይን ችለው፤ ብርዱንና ረሀቡን ታግሰው፤ ለዚች ለምታልፈው ጊዜያዊት ዓለም ምንም ሳያስቡና ከምንም ሳይቆጥሩ በሰው ዘንድ የተናቁ ከምንም የማይቆጠሩት ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከወርቅና ከዕንÌ ይልቅ የጠሩና የከበሩ ከብርሃናት ይልቅ ሰባት እጅ የሚያበሩ ናቸው፡፡

አበው መነኰሳት እንደ አባት ቅድስት ሥላሴ፤ እንደ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ወንድምና እንደ እኅት ቅዱሳን መላእክት እንደ ርስት እንደ ጉልት የማታልፍ ርስተ መንግሥተ ሰማያት አለቻቸውና ደስተኞች ናቸው፡፡ በገዳማዊ ሕይወት የሚገባ ሐዘን አለ፤ ይኸውም የራስን ኃጢአት አይቶ፤ ግፍዐ ሰማዕታትን ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን አስቦ፤ አምላክ ዓለሙን በሙሉ በምሕረት ዐይኑ እንዲጐበኘው መጸለይና በኃጢአት ምክንያት ለሚጠፋው ፍጥረት ማዘን የምንኩስና ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ በገዳም ውስጥ የሚኖሩ ገዳማውያን የተባሕትዎና የሱባኤያቸው ትርጉም ይህ ነው፡፡

ከኀልዮ ኃጢአት የሚያነጻ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የባሕታዊ ንጽሐ ጠባይዑ ተጠብቆበት የሚኖር በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ባሕታዊን በልሳነ ነፍስ እንዲናገር የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ  ነው፡፡  ረቂቅ ምስጋናን ከመላእክት ጋራ እንደ መላእክት ያመሰግናል፡፡  ምሥጢር የሚገልጥ እግዚአብሔር ያደረበት ባሕታዊ ንዑዱ ክቡር ነው፡፡ አምላክ ልቡናውን   እንዲህ አድርጐ ውስጥ ለውስጥ መንፈሳዊ ምግብን ይመግበዋል፡፡ ሕዋሳተ ሥጋ ሥጋዊውን ምግብ ከሆድ አግኝተው እንዲመገቡ አበው በዚያ ከቅጠልና ስራስር በቀር እህል የማይቀመስበት ገዳም በምስጋና ብቻ ሆዳቸው ሞልቶ ያገኙታል፡፡ እንግዲህ ማነው ከእኛ መካከል ከእህል ተለይቶ ለ40 ወይም 70 ዘመናት መቆየት ይቅርና ለሳምንት የሚሰነብት ማንም የለም፡፡ አባቶች ግን የእግዚአብሔር ጸጋ በዝቶላቸው እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እህል ሳይቀምሱ (በሕርመት) ከእህልም ከሰውም በመለየት ይኖራሉ፡፡ ልቡናን ውስጥ ለውስጥ የሚመግበው መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡

ለዚህ ቅድስና ብፅዕና የሚያበቃ ገድልና ትሩፋት የሠሩ በዚህ መሠረት በጾም በጸሎት ተወስነው ርእሰ ባሕታውያን ለመባል የበቁ ለቁመተ ሥጋ ያህል (ቋርፍ) ተመግበው (ማየ ዮርዳኖስን) ጠጥተው ቅዱስ ውዱስ ስቡሕ እኩት ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ እያሉ በየ ሰዓታቱና በየደቂቃው አባቶች ያመሰግኑታል፡፡ ምስጋናውም ምግብና ፈውስ የሕይወት መድኃኒት ሆኗቸው ይኖራል፡፡

የገዳሙን ዓፀባ ችለውና ታግሰው ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙ ታላላቅ ባሕታውያን ናቸው፡፡ አባቶች የዚህን ዓለም ትዝታ የሚያደርስባቸው ከዚያው ከገዳሙ የሚቀበሉት ፈተና በትዕግሥት ችለው ስለሚኖሩ፣ እርሱም ስለሚበዛባቸው ነው፡፡ ከረቂቃን አጋንንትም ጋር ጭምር ከመዋጋት አቋርጠው አያውቁም፡፡ በተጋድሎ ድል ነሥተው በመጨረሻ ጊዜ የማያልፈውን ዓለም መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ የድል አክሊል ይቀዳጃሉ፡፡

በጸሎትና በትምህርት እንዲሁም በትሩፋት ለሀገርና ለወገን ብሎም ለመላው ዓለም ሰላምና ደኅንነት ደብሩን ገዳሙን፣ አገራችን ኢትዮጵያን ሕዝቧን መንበረ ማርቆስን ቅ/ቤተ ክርስቲያናችንን አጽናልን ጠብቅልን እያሉ ዘወትር እግራቸው ሳይታጠፍ ዓይናቸው እንቅልፍና ሳይሻ የላመ የጣመ ሳይቀምሱ፣ የሞቀ የደመቀ ሳይለብሱ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ወደፍጹምነት ምልአት ደረጃ ላይ ደርሰው እግዚአብሔርን ከማሰብ ለአፍታ ያህል እንኳ ሳያቋርጡ ይጸልያሉ፡፡

አባቶች በፍጹም ተጋድሎ ለወጣት መነኮሳት አርአያ በመሆን ትዕግሥትን ገንዘብ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ አንድ መነኩሴ ራእይ በማየቱ የበቃሁ ሆኛለሁ ብሎ ያስብ ነበር ከገዳሙ አበምኔት ጋርም ስለመንፈሳዊ ሕይወታቸው እያነሱ ሲወያዩ አባቴ እኔ ዛሬ በራእይ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ግፍና በደል አየሁ፡፡ ስለዚህ የበቃሁ ሆኛለሁ ብሎ አጫወታቸው፡፡ አበምኔቱም አባ እስቲ በርትተህ ጸልይ ገና ነህ ብለው መለሱለት፡፡

እንደሁም በሌላ ጊዜ ወደ አበምኔቱ ቀርቦ አባቴ አሁንስ በቅቻለሁ ቅዱሳን መላእክት ከሰማይ ሲወጡና ሲወርዱ፣ የሕዝቡንም ኃጢአት ሲያስተሰርዩ አይቻለሁ አላቸው፡፡ እሳቸውም አባ ገና ነህ አሁንም በርታና ጸልይ ብለው ሸኙት፡፡ ይህም መነኩሴ ወደ ዋሻው ገብቶ አብዝቶ ይጾምና ይጸልይ ጀመር፡፡ ለሦስት ጊዜ ስላየው ራእይ ለአበምኔቱ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው፡፡ አባቴ ሆይ ዛሬስ በዓለም ሳለሁ የሠራሁትን ኃጢአት ሁሉ አንድ በአንድ አሳየኝ፤ የኃጢአቴ ብዛትም ስፍር ቁጥር የለውም ሳለቅስም አደርኩ ኃጢአቴም እጅግ ብዙ ነውና ይቅር ይለኝ ዘንድ ይጸልዩልኝ አላቸው፡፡ እርሳቸውም ልጄ ሆይ የበቃኸው አሁን ነው ብለው አሰናበቱት፡፡

እግዚአብሔር የሚመርጠው እንደ ሰው አይደለም ሰው መልክና ቁመት አይቶ ሀብትና እውቀትን ጉልበትን ከግምት አስገብቶ ለወገን ለዘመድ አድልቶ ይመርጣል፡፡

እግዚአብሔር ግን ፊትን ሳይሆን ልብን አይቶ የመርጣል፤ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ለልዩ ልዩ አገልግሎት የመረጣቸው ቅዱሳን አበው በሰው ዘንድ የተናቁና ከምንም የማይቆጠሩ ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከፀሐይ የበሩ ከወርቅና ከእንÌ የከበሩ ናቸው፡፡

አባቶች የነፍሳቸውን ቅድስና ለሥጋቸው የሥጋቸውን ቅድስና ለአለባበሳቸውና ለአረማመዳቸው የተረፈ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የቅዱሳን ትምህርታቸውና ሕይወታቸው ብቻ ሳይሆን ልብሳቸውም ጭምር የሰውን ሕይወት ይለውጣል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኤልሳዕ ሕይወቱ የተለወጠው ሁሉን ትቶ ለመከተል የቆረጠው የነቢዩ የኤልያስ መጐናፀፊያ ከትከሻው በወደቀበት ጊዜ ነው፡፡ 1ኛ ነገ. 19፣19፡፡

በጸሎት በተዘክሮ ጊዜ ክርስቶስን በልቡ አድሮ የሚያየው ብርሃኑንም አይቶ ደስ የሚለው መነኩሴ ድንቅ ነው፡፡ በልብሰ ብርሃን ተሸፍኖ የሚያየው ብፁዕ ነው ደስ የሚያሰኝ የመላእክትን ምስጋና በልቡ ተሥሎ ሲያመሰግኑ የሚሰማቸው በልሳነ ነፍስ ከመላእክት ጋር የሚያመሰግን ባሕታዊ ንዑድ ክቡር ነው፡፡ ሥጋዊ አንደበት ሊናገራቸው የማይችል ነገራትን ይናገራል፡፡ ማለት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ቸር አምላክ የፍጥረቱ ሁሉ ጠባቂና መጋቢ ምስጋና ክብር ይገባሃል እያለ ከመላእክት ጋር ያመሰግናል፡፡ ለእኔ ንጽሕና ያለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰባት የንጽሐ ልቡና ማዕረግ ይህችን ትመስላለች (ብፁዕ መነኮስ ዘተጠብለለ ልቡ በርእየተ ሥሉስ ቅዱስ) “ዘተጠብለለ፣ ዘጠለለ፣ ዘጠለ” ይላል አብነት ምሥጢራትን በማየት የከበረ መነኩሴ ጌታችን ለማገልገል ከሕፃንነት እስከ እርጅና ከወጣኒነት እስከ ፍጹምነት በትሩፋት የደከመ መነኩሴ ንዑድ ክቡር ነው ከጽማዌ እስከ ከዊነ እሳት ያሉ ማዕርጋትን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ገንዘብ ያደረጋቸው ባሕታዊ ንዑድ ክቡር ነው፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባ ነጮ) ከሕፃንነት ጀምረው እስከተባሕትዎ ደረጃ የደረሱ ገዳሙን በተለያየ መልኩ በመቲረ ፈቃድ በማገልገል ነው፡፡ እኒህ አባት የዘመናችን ጻድቅ ባሕታዊ ናቸው፡፡ በታላቁ ዋልድባ አብረንታንት ገዳም በተባሕትዎ ከኖሩ በኋላ መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም የደብረ ዘይት ቀን በዕለተ ሰንበት በእረፍተ ሥጋ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም ዘለዓለማዊ መንግሥት ፈልሰዋል፡፡ ነፍሳቸውን በአብርሃምና በይስሐቅ አጠገብ ያኑርልን፡፡ በሕይወት ያሉትን አባቶቻችንም ጸጋውን አብዝቶላቸው ለገዳማችን ብሎም ለሀገራችን ለሃይማኖታችን መመኪያ አለኝታ ናቸውና እድሜና ጤና ሰጥቶ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቅልን፡፡

በአጠቃላይ እንደ አላዋቂና ማንኛውም ዕውቀት እንደ ጎደለው ሰው ለማወቅ በእግዚአብሔር ፊት ቅረብ፡፡ ከዚያም ፍጹም ከሰው ልጅ ዕውቀት በሚለይና መንፈሳዊ በሆነው ዕውቀት ትሞላለህ፡፡ ይህም ዕውቀት ያልያዘው የለም፤ መንፈስም ጥልቅ ነገር እንኳን ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና (1ኛ ቆሮ. 2÷10) ድንኳን የሚሆነው ጊዜያዊ መኖርያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን፡፡ (2ኛ ቆሮ. 5÷1) መ/ር አባ ገብረ ሥላሴ በዋልድባ ገዳም 70 ዓመታት ከኖሩ በኋላ በጠቅላላ ከአባትና እናታቸው ቤት ተለይተው በምናኔ እንደወጡ ሳይመለሱ ለፍጹምነት መዓርግ ደርሰው በተወለዱ በ94 ዓመታቸው አረፉ፡፡ ነፍሳቸውን ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር ይደምርልን፡፡ አሜን

 

የጽሑፉ ምንጭ

ባሕታውያን በዋልድባ ገዳም ቁጥር ፩ እና ቁጥር ፪ መጻሕፍት ከአባ ተከስተ ብርሃን ወ/ሳሙኤል በ1995 እና በ1997 ዓ.ም ከታተመው  

 

በአሁኑ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ

መጋቢት 2009 ዓ.ም

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

ሰውና እውነት የሰው ፈቃደኝነት ለእውነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዲያውቁት ብቻ ሳይሆን እንዲወዱት ይሻል፡፡ ከልብ ሲወዱት ያን ጊዜ ያውቁታል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ማወቅና እንዲወዱትም ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን ለመውደድ ደግሞ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው፣ ልቡን ያልሰጠ ሰው  እግዚአብሔርን አያገኘውም፡፡  እግዚአብሔር እንደተሰወረበት ይቀራል፡፡ የእግዚአብሔር የመጀመሪያው ጥሪ ልብህን ስጠኝ የሚል ነው፡፡ ልቡን ለ እግዚአብሔር ያልሰጠ ሰው  እግዚአብሔር ሊያድርበት አይችልም፡፡

የሃይማኖት ትምህርት በሰው ዘንድ የከበደ ትምህርት ነው፡፡ ሃይማኖት ከሥጋ ፍላጐት ጋር ስለማይደራደር በጣም ከባድ ነው፡፡ ሃይማኖት የሰውን ሁለንተናዊ ተግባሩን ህሊናውንም ይቆጣጠራል ይህ ደግሞ በሥጋውያን ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ አያደርገውም ሰው ማንም በዚህ ግባ፣ በዚያ ውጣ ብሎ እንዲያስገድደውና እንዲያዘው አይፈልግም ምክንያቱም ይህን እንደ ግል ጉዳዩ አድርጎ ያስባልና ነው፡፡

ስለዚህም ሥጋዊው ሰው ራሱን ለመከላከል ሲል የሃይማኖት ትምህርት ኋላ ቀር የሆነ ጊዜው ያለፈበት ትምህርት አድርጎ ለማቅረብና በመተቸት በዚህም ራሱን ለማሳመን ጥረት ያደርጋል፡፡ የሃይማኖት ትምህርት ለትእዛዛቱ ሁሉ መነሻ የሚያደርገው ራሱን  እግዚአብሔርን ስለሆነ የፀያፍ ሥራ ዐመል ያለበት ሰው መጀመሪያ ቁጣውን በራሱ በእግዚአብሔር ላይ ይገልፀዋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር የለም፣ ቢኖር ኑሮ ይታይ ነበር ይላል፡፡

እንዲሁም በሰዎች ላይ የሚታዩ የተለያዩ አሰቃቂ ነገሮችና ችግሮች እግዚአብሔር ቢኖር ኑሮ አይኖሩም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያን ሁሉ ዝም ብሎ አይመለከትም ነበር በማለት መቶ ሃምሳውን ምክንያት ይደረድራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሳይንስ ስም እዚህም እዚያም የሚናፈሱትን የመናፍቃንን ሐሳብ በመጠቃቀስ የሃይማኖትን ትምህርት ውድቅ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ሃይማኖትን ይህን ያህል ከሰው ጥርስ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ከሰው የሥጋ ደካማ ፍላጎት ጋር አብሮ የማይሄድ ሕግና ሥርዓት ትምህርት ስላለው ነው፡፡ ትምህርቱ ከሰው ደካማ ፍላጎት ጋር ስለማይሄድ ሃይማኖት በሰው ዘንድ ተወዳጅነት የለውም፡፡

ወንጭፍ ባልኖረ የማሽላ እሸት ደግ ነበር እንዳለችው ወፍ ሰውም የሚቆጣጠረው ሃይማኖት ባይኖር ኑሮ ይወድ ነበር፡፡ ልጓም የሌለው ፈረስ ሃይማኖት የሌለው ሰው አንድ ናቸው ተብሏል፡፡ ፈረስ ልጓምን የማይፈልገው እንደ ልቡ ለመሆን ነው ሰውም የልቡን ለመፈጸም ሃይማኖትን አይፈልገውም ፈረስ ልጓም ከሌለው ሩጦ ገደል ሊገባ እንደሚችል ሁሉ ሰውም የሚቆጣጠረው ሃይማኖት ከሌለ ያው ነው እንደ ልብ ከመፈንጨትና ከመጨፈር ከመዝለል ከመብላት ከመጠጣት ከመዳራት ተሰናክሎ እንዳይቀር የሚገታው ሃይማኖት ስለሆነ ሃይማኖት ለሰው ልጅ ያስፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ያለ አግባብ መበልፀግን ብዙ ሰው እንደሚፈልገው ይታወቃል፡፡ ይሁንና ያለ አግባብ መበልፀግን ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አይሄድም ብሎ ስለሚያስተምር ያለ አግባብ መበልፀግን የሚሻን ሰው የሃይማኖት ትምህርት ያስጠላዋል፣ ያስኮርፈዋልም፡፡ ከሃይማኖት ትምህርት ጋር የማይሄድና በዚህም ሰውን የሚያስኮርፈው ሌላው ዐመል ሴሰኝነት ነው፡፡ የሴሰኝነት ዐመል ያለበት ሰው ራሱን ለዚህ ፀያፍ ሥራ ተገዥ ያደረገ ሰው በመሆኑ ምክንያት ከሃይማኖት ትምህርት ጋር ስምምነት የለውም፡፡ ሃይማኖት ለእንዲህ አይነቱ ዐመል ከኃጢአት ሥር ስለሚመድበውና ጧት ማታ ስለሚያወግዘው ትምህርቱ ያስጠላዋል፡፡ በመሆኑም ሃይማሃትን በተለያዬ መንገድ ለመዋጋት ቆርጦ በተለያየ መንገድ ይነሳል፡፡ ሃይማኖት የሰውን ድካም ፍላጐት የማይቃወም ቢሆን ኑሮ ግን ሰውም ሃይማኖትን ለመቃወም ምክንያት አይኖረውም ነበር፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ የሰው ገንዘብ አትመኝ፣ ሙስና ኃጢአት ነው፡፡ እምነት በተግባረ ሲገለጽ ነው መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት፣ ሃይማኖት በሥራ ካልተገለጸ የሞተ ነው፡፡ ከሃይማኖት የሚርቅ ሰው እንዳሻው በፈለገው መንገድ በማናቸውም ፀያፍ ነገር ላይ እንዳይገኝ ከሚከላከለውና በዚህም ነጻነቱን ከሚገድብበት አንድ ትልቅ ከሆነ ቀንበር ነጻ እንደወጣ ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ ሰው እንደ ሰው ለመሆን ሲፈልገ ቁጥጥር በሚያደርግበት ሃይማኖት ከሚባለው ነገር ራሱን ያገላል፡፡ ራሱን ከሃይማኖት ካገለለና ሃይማኖት በእሱ ላይ ቁጥጥር ማድረግን ከተወ እንደፈለገው ሆነ ማለት ነው፡፡ ከፍ ሲል ሃይማኖት ሰውን ስለሚቆጣጠረው ሰው ሃይማኖትን ለመቀበል አይወድም ሃይማኖትን ለመቀበል ስለማይወድም ልቡን ይዘጋበታል፡፡ ስለሚዘጋበትም ትምህርቱን ለማስተዋልና ለመቀበል አይችልም፡፡

ፈረንሳዊው ፈላስፋና የሒሳብ ሊቅ ፓስካልም ሲናገር እንዲህ ብሏል ልብ አእምሮ ሊያስተውላቸው የማይችሉት የራሷ ምክንያቶች አሉዋት ማለት ነው፡፡ አባባሉ ሲብራራ የአእምሮና የልብ መንገድ የተለያዩ ነው ጥሩ ማስረጃ ያለው፣ ለአእምሮ አሳማኘ የሆነ ሐሳብ ያዛችሁ አንድን ሰው ልታሳምኑት ካልቻላችሁ ችግሩ ያለው ከሐሳባችሁ ላይ ሳይሆን ሰውየው ሐሳቡን ለመቀበል ካለው አለመፈለግ ላይ መፈለግ አለበት የሚል ነው፡፡

ለምሳሌ ሌብነትን ስርቆትን በቀጥታ ሌብነት፣ ስርቆት አይለየውም ለመዋሸትም እንዲሁ ነው እገሌ ቀጣፊ ነው፣ አታላይ ነው፣ አጭበርባሪ ነው ለማለት ተፈልጎ ነገሩን አድበስብሶ ሲያልፍ ብልጥ ነው፣ ጮሌ ነው ብሎ ያልፈዋል፡፡ በአንጻሩ እገሊት ቀጥተኛ ሰው ናት፣ ሐሳቧን ሳትደብቅ እውነቱን፣ ሐቁን ትናገራለች ለማለት እርሷ ሞኝ ናት ጅል ናት፣ ገጠሬ ናት፣ ጥሬ ናት ትባላለች ይሁንና እውነት መናገር ሞኝነት ጅልነት አይደለም፣ ገጠሬነትም አይደለም፣ ጥሬ ነው የሚያሰኝም አይደለም እንደዚሁ ሁሉ ማታለልም፣ ማጭበርበርም ብልጥነት አይደለም፣ ጮሌነትም አይደለም፡፡

ሰው ልቡን ካደነደነ አንድን ሐሳብ ላለመቀበል ከወሰነ ምንም ነገር እንደማይመልሰው በአየሁድ ታይቷል፡፡ የአይሁድ አለቆችንና መምህራን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት አላሳመናቸውም የተአምር ሥራዎች አላስደነቃቸውም በትምህርቱና በሥራዎቹ አልተመለሱም ክርስቶስን ይጠሉት ስለነበርና ሥራውን ላለመቀበል ወስነው ስለነበር የክርስቶስ ትምህርትና ሥራ በእነርሱ ዘንድ ሽንፈት ደርሶባቸዋል እንግዲያውስ ትምህርቱ ግሩም ነበር፡፡ እፁብ ድንቅ ነበር፣ ምንም እንከን የማይዋጥላቸው ቢሆንም የተደረጉትና የተፈፀሙት ተአምራትንም በደቅ ግባብ ላይ አይንን ማብራት ህሙማንም መፈወስ ሙታንን ማንሳት ይፈጽም ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ አልተቀበሉት አላመኑትም ለምን ቢሉ ይዘልፋቸው ስለነበር አስመሳዮች ናችሁ ውሸታሞች ናችሁ እያለ በአደባባይ ይናገራቸው ስለነበር በእረሱ ላይ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ተቋውሞና ጥላቻ ነበራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚያደርገውና የሚናገረው ነገር ሁሉ ከልባቸው ጠብ አይልም ዛሬም ቢሆን ጥሩ ማስረጃ ያለው አሳማኝ የሆነ ሐሳብ ይዛችሁ አንድን ሰው ልታሳምኑት ካልቻላችሁ ችግሩ ያለው ከሐሳባችሁ ላይ ሳይሆን ሰውየው ሐሳቡን ለመቀበል ካለመፈለጉ ላይ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ሐሳባችሁ በቂ ማስረጃ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት ሊሆን ይችላል እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና ሐሳባችሁ ከልብ አይደርስም ከልቡ ስለማይደርስም ሳይቀበላችሁ ይቀራል፡፡

ሰው የሚያስብ ብቻ ፍጡር አይደለም ያሰበው ሐሳብ ጉዳት የሚያመጣበት ከሆነ ወይም እንደዚያ መስሎ ከታየው ሐሳቡን ይጠላዋል፡፡ ስለሚጠላውም አይቀበለውም ስለዚህም አንድን ሐሳብ መቀበልና አለመቀበል ማስረጃ የማግኘትና ያለማግኘት ጥያቄ ብቻ አይደለም ሐሳቡን ለመቀበል ፈቃደኛ የመሆንና ያለመሆን ጥያቄም ጭምር ነው የፈረንሳዩ ሊቅ የፓስካል ንግግርም አእምሮ የሚያውቃቸው የራስ ምክንያቶች አሉዋት ሲል የተናገረው ቃል በዚህ መንፈስ የሚታይ ሐሳብ ነው ክርስቶስ ሲያስተምረው የነበረው ትምህርትና ሲፈጽመው የነበረው ተአምራት በአይሁድ ዘንድ አሳማኝነት ያጣው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ካላሰብን ሌላ ምክንያት አይገኝለትም አይሁድ ክርስቶስን በጣም ይጠሉት ስለነበር የእርሱም ወገኖች ይመለከቱዋቸው የነበሩት እርሱን የማዩባት ዓይን ነበር፡፡ ስለ ራሱ ስለ ክርስቶስና ስለ መንገድ ጠራጊው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የተናገሩትን አስደናቂና ተአምራት መጥቀስ ይበቃል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስን ለማውገዝ ያሰቡበት ትልቅ ምክንያት ይህን ለማለት ያበቃቸውም ዮሐንስ የሚመገበው አጋጣሚ የበረሀ ባሕታዊ ልብስ የማይለብስ እህል የማይበላ (ማቴ. 3÷4) ገና ሳይወለድ ለአባቱ ለዘካርያስ የተገለጠለት መልአከ እግዚአብሔር የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ የማይጠጣ መሆኑን ተናግሮለት ነበር፡፡

ሌላው ሰው የሚበላውንና የሚጠጣውን ስላልበላና ስላልጠጣ አለመብላቱንና አለመጠጣቱን እንደ ኃጢአት ቆጥረውበት ጋኔን አለበት አሉት፡፡ ክርስቶስ ሰው የሚበላውን የሚጠጣውን ሲበላና ሲጠጣ ሲያዩት ደግሞ በላተኛና ጠጪ ነው ብለው አወገዙት እንግዲህ መመልከት ነው አንደኛ መብላትም ሆነ አለመብላት፣ መጠጣትም ሆነ አለመጠጣት ኃጢአት አልነበረም ኃጢአት ነው ቢባል እንኳ ከሁለቱ አንደኛቸው እንጂ ሁለቱም ኃጢአት ሊሆኑ እንደማይችሉ መፍረድ ይቻላል፡፡ ይሁንና የአይሁድ አለቆችና መምህራን በክርስቶስና በወገኖቹ ላይ ምንም ይሁን ምን ኃጢአት ይፈልጉ ስለነበር መብላትንም ይሁን መጠጣትን እንዲሁም አለመብላትንም አለመጠጣትንም ሁለቱንም እኩል ኃጢአት አድርገው ተመልክተውታል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስን ባለመብላቱና ባለመጠጣቱ ምክንያት ጋኔን አለበት ሲሉት ክርስቶስን ደግሞ ሲበላና ሲጠጣ ሲያዩት በዚሁ በመብላቱና በመጠጣቱ ምክንያት በላተኛና ጠጪ ነው አሉት፡፡ ከኃጢአተኞች ጋር ስላዩትም የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ነው አሉት፡፡ ከኃጢአተኞችና ከቀራጮች ጋር ባያዩት ኑሮም ነቀፋቸው አይቀርለትም ነበር፡፡ ከኃጢአተኞች ጋር የማይውለው እኮ፣ ተፀይፎአቸው ነው፣ ትዕቢተኛ ነው፡፡ ሰው ይለያል ያዳላል ይሉት ነበር እነሆ ክርስቶስ በዚህ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡

ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፡፡ እነርሱም ጋኔን አለበት አሉት፡፡ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፡፡ እነርሱም እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ነው ይሉት ነበር፡፡ ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች (ማቴ. 11÷18-19)

በክርስቶስም ሆነ በመጥምቁ ዮሐንስ ላይ የአይሁድ አለቆችና መምህራን ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው የጌታ ቃል መመልከት እንደሚቻለው ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበራቸው የተናገሩት ቃል በጣም የተምታታና ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ሊያስተውሉት አልቻሉም አለመብላትንና አለመጠጣትን እንደ ኃጢአት መቁጠር በአንፃሩም መብላትንና መጠጣትን እንደዚሁ በቁጥር መጃጃል መሆኑን ማንም ሰው ሊያስተውለው ይችላል፡፡ አይሁድ ብቻ አላስተዋሉትም ምክንያቱም ጥላቻቸው የማስተዋል ልባቸውን አጨልሞት ነበርና ነው አንድን የተወሰነ ድርጊት ኃጢአት ነው፣ ጸያፍ ነው ብሎ መልስ መመለስ የእሱንም ተቃራኒ እንደዚያው መንቀፍ አያስኬድም አይሁድ ግን አስኪዷቸው ተናግረውታል፡፡ ይህም በጣም አስገራሚ ነው በትክክል የሚያስቡና ለእውነት የቆሙ ቢሆኑ ኑሮ ከሁለቱ አንደኛውን ወደ ክርስቶስ ወይ ዮሐንስን መምረጥ ነበረባቸው አለመብላትን አለመጠጣትን ከጠገቡ መብላትን መጠጣትን ካወገዙ ደግሞ ላለመብላትና ላለመጠጣት ድጋፋቸውን መስጠት ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ማንኛቸውንም ላለመምረጥ ሲሉ በውስጡ አንዳች የሎጂክ (የእውነት) አካሄድ የሌለበትን ሐሳብ ገልጸዋል እንግዲያውስ ከመብላትና ከመጠጣት ወይም ካለመብላትና ካለመጠጣት የወጣ ነገር አልነበረም የአይሁድ አለቆችና መምህራን እንዲህ ዓይነቱን ለዛቢስ ሐሳብ ቢገልጹም እንዲያውም ለጊዜው ያላስተዋሉት አንድ ነገር አለ ክርስቶስን ስለበላና ስለጠጣ በላተኛና ጠጪ ነው ብለው ሲሰድቡት ራሳቸውንም ጭምር እንደሰደቡ አላስተዋሉም፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ራሳቸው ይበሉና ይጠጡ ነበርና ነው፡፡ አባባላቸው ወደ እነርሱ ወደ ራሳቸውም ሊዞር እንደሚችል ሐሳቡ አልመጣላቸውም፡፡

ይህንን የመሰለ የተምታታ ሐሳብ ከሌላም ቦታ በክርስቶስ ላይ የአይሁድ አለቆችንና መምህራን አንጸባርቀውታል በአንድ በኩል ክርስቶስ ተአምራት ሠርቶ እንዲያሳያቸው ይሹ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ሊያውቁ እንዲችሉ ተአምራት ሠርቶ ያሳየን ይሉ ነበር፡፡

በመሠረቱ በአይሁድ ኅብረተሰብ ዘንድ ተአምር መፈጸም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር እንደተላከ፣ የእግዚአብሔር ኃይል እንዳደረበት ሆኖ ይታመንበታል፡፡ አይሁድ ከእግዚአብሔር የተላከውን፣ የእግዚአብሔር ኃይል ያደረበትን ሰው የሚያውቀት አንደኛው ዋንኛው መንገድ የተአምር ሥራ መፈፀምን ነበር ይህም እምነት ኒቆዲሞስ ከሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው ክርስቶስን አስመልክቶ ተንፀባርቋል፡፡

ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፣ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውና የምታጸናቸው እነዚህን ተአምራቶች ሊያደርግ የሚችል ማንም የለምና መምህር ሆይ ከእግዚአብሔር እንደመጣህ እናውቃለን አለው (ዮሐ. 3÷1-2) ቅዱስ ጳውሎስም ተአምራት ማሳየት በአይሁድ ኅብረተሰብ ዘንድ ታላቅ ቦታ እንዳለው እንዲያው አይሁድ ከሌሎች ሕዝቦች ግሪኮችም ጭምር የሚለዩበት ነገር ቢኖር በተአምር ሥራ የሚያምኑና ተአምር ይፈፀምልን የሚሉ መሆናቸው እንደነበር አስተምሮናል፡፡

መቼም አይሁድ ፍፁም ይለምናሉ የግሪክ ሳዎችም ጥበብን ይሻሉ (ቆሮ. 1÷22) ሲል ተናግሯል፡፡

የአይሁድ አለቆችና መምህራን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመፈታተን ሲፈልጉ ተአምር ሠርቶ በእነርሱ ቋንቋ ምልክት እንደሚያሳያቸው ይጠይቁት ነበር፡፡ የጠየቃትን ሊፈጽምላቸው ዘግይተዋል እንደው ባይሆንለት ነው፣ ቢችል ኑሮ ያደርገው ነበር ሲሉ ይሳለቁበት ነበር፡፡ ተአምር ሲፈጽም ሲያዩ ደግሞ ይህንማ የሚያደርገው በሰይጣንም ኃይል ነው ይሉት ነበር ከዚህም ላይ የተምታታ ሐሳብ ይታይባቸው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተአምራት መፈጸም በእግዚአብሔር ኃይል ከእግዚአብሔር ድጋፍ የሚፈጸም ነው ማለታቸውና በሌላ በኩል ደግሞ በሰይጣን ኃይል በሰይጣን ድጋፍ የሚፈጸም ነው ሲሉ ፍፁም ሊታረቁ የማይችሉ የተምታቱ ሐሳቦች መሆናቸውን ማንም ትንሽ የሎጂክ የእውነት ትምህርት የወሰደ ሰው እንኳ ሊያስተውለው ይችላል ይህንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት፡፡

ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ዕውሩም ዱዳውም እስኪያይና እስከሚናገር ድረስ ፈወሰው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን አሉ ፈሪሳውያን ግን ሰምተው ይህ በብኤል ዜቡል የአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ፡፡ (12÷22-25)

የልብ መጥመም ትልቅ እርግማን ነው ልቡን ላጠመመ ሰው መድኃኒት የለውም ስለዚህ ከዚህ እርግማን ይሰውረን አሜን፡፡

አባ ሳሙኤል፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስአበባ

 

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

የእግዚአብሔር ዕቅድና ፈቃድ ከፍጥረታቱ የተለየ ወይም የራቀ አይደለም፡፡ ዓለምን የፈጠረው ከሰዎች ጋር ዘለዓለማዊ መቀራረብ ወይም ግንኙነት እንዲኖረው ፈልጐ ነው፡፡ ይህ የሚያልፈው ዓለም (ምድር) እንኳን በጊዜው ቢያልፍ በማያልፈው ዘለዓለማዊ ዓለም ከሰዎች ጋር ዐብሮ ለመኖር የማያልፈውን ሰማያዊ ዓለም ፈጥሮአል፡፡ ይህ የሚታየው ዓለም (physical world) የተፈጠረው ለሰዎች መገልገያ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም፡፡” ዘፍ. 1÷28፡፡ “ሰማየ ሰማያት ለእግዚአብሔር ወምድርሰ ወሀበ ለእጓለእመሕያው ሰማይ ለእግዚአብሔር መንበሩ ነው ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” እንዲል፡፡ መዝ. 113÷16፡፡

የብሉይ ኪዳን ጸሐፍት ስለ ሰው የሚገልጽ ብዙ ቃላት ቢጠቀሙም ትልቁን ቁጥር ይዞ የሚገኘውና በብሉይ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል 562 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው አዳም የሚለው ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል የሰው ልጆችን ሁሉ ይወክላል፡፡ አዳም ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ የፍጥረታት ሁሉ ዘውድ የፍጥረታት ሁሉ የመጨረሻና ከፍተኛ ደረጃ ፍጡር ማለት ነው፡፡ ዘፍ. 1÷26-28፣ 2÷7፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው “እግዚአብሔር አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን እንስሳትንና ምድርን ሁሉ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ ዘፍ. 1÷26፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስረዳው እግዚአብሔር ለሰው ምን ያህል ክብር እንደሰጠው የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ምድርን እንዲገዛ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ አዳም የሚለው ስም የመጀመሪያው ሰው መጠሪያ ስም እንደሆነ ገልጾአል፡፡ በብሉይ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ 42 ጊዜ ተጽፎ የሚገኘውና ስለ ሰው የሚገልጸው ቃል በዕብራይስጡ “ኤኖሽ” የሚለው ሲሆን በአማርኛው ሰው የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ኢዮብ 28÷13፣ መዝ. 89÷3፣ ኢሳ. 13÷12፡፡ በመጀመሪያ ሰው የሚለው ቃል በመጀመሪያ ለተፈጠረው (አዳም) መጠሪያ ስም የሚያገለግል ነበር፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም አለ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፡፡ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት፡፡” ዘፍ. 2÷18፡፡ ሰው የሚለው መጠሪያ ኋላ ሁሉን የሚመለከት የአዳም ልጆች የወል መጠሪያ ሆነ፡፡ “ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንም የሚይዝ የሰው ልጅ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፡፡” ኢሳ. 56÷2፡፡ ሌላው በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ 2160 ጊዜ ተጽፎ የሚገኘውና በጾታ ወንድን የሚመለከት ስለ ሰው የሚናገረው የዕብራይስጡ ቃል ኤሽ (ish) የሚለው ነው፡፡ ይህ ቃል ኋላ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚመለከትና መጠሪያ ሆነ፡፡ ወደ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ስንመጣ የምናገኘው አንትሮፖስ (Anthropos) የሚለውን የግሪክ ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል አዳም ሰው “ኤሽ”፣ “ኤኖሽ የሚለውን ቃል ሁሉ ጠቅልሎ ስለ ሰው ተፈጥሮና ጠባይ የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህ ቃል ሰዎች በተፈጥሮአቸው በጠባያቸው ከእንስሳ፣ ከመላእክት፣ ወዘተ እንደሚለዩ የሚያሳይ ብዙ ትርጉም የያዘ ቃል ነው፡፡

 • ሰዎች ከእንስሳ እንደሚለዩ፡- “እንግዲህ ሰው (Anthropos) ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም፡፡” ማቴ. 12÷12፡፡
 • ሰው ከመላእክት እንደሚለይ፡- ዕብ. 2÷5፣ 1ቆሮ. 4÷9፡፡ ምንም እንኳን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው በነሣው ሥጋ ፍጹም ሰው ቢሆንም ፍጹም አምላክም በመሆኑ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው (Anthropos) አልተቀበልኩትም አልተማርሁትምም፡፡” እንዲል ገላ. 1÷12፡፡
 • ሰው ከእግዚአብሔር እንደሚለይ “ከሰው (Anthropoids) እንደሆነ ይጠፋሉና ከእግዚአብሔር እንደሆኑ ግን ታጠፏቸው ዘንድ አይቻላችሁም፡፡” የሐ.ሥ 5÷38-40፡፡

የሰው ጥንተ ተፈጥሮ

እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከዐፈር (ጭቃ) እንደፈጠረውም ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያዋ ሴት (ሔዋን) ከአዳም ጐን እንደተገኘች ተጽፏል፡፡ ማር. 10÷6፣ ዘፍ. 2÷22፡፡ ሰው የተፈጠረው ከዐፈር ቢሆንም ከሌሎች ፍጥረታት የሚለይበት የሰውነት ይዘት (body components) አለው፡፡ ከሰውነት ክፍሎቹም ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙትና ሰውን ከመንፈሳውያን ጋር በመንፈሳዊ ዓለም እንዲኖር ካስቻሉት መካከል (የሚያስብ አእምሮ)፣ ነፍስና አእምሮ ሲሆኑ ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ልብ፣ አእምሮ፣ ኩላሊት፣ ወገብ ጉበት የውስጥ ዕቃ፣ ሥጋ ወዘተ ሰውን ሙሉ የሚያደርጉት የአካል ክፍሎች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ልብ የሚለውን የሚታየውን አካል ዕብራይስጡ ሌቭ ወይም ሌቫቭ ይለዋል፡፡ ግሪኩ ደግሞ ካርዲያ (Kardia) ይለዋል፡፡ ዕብራይስጡም ሆነ ግሪኩ ልብ የሚለው በአብዛኛው ከአስተሳሰብ ጋር የሚገናኘውን አካል ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ጸሐፍያን ደግሞ ኩላሊት (kidneys) የሚለውን በዕብራይስጡ ኪልያህ (kilyah) የሚገልጹበት ሐሳብም ውስጣዊ ነገርን ነው፡፡ “በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ ከልባቸው (ኩላሊት ግን ሩቅ ነህ)፡፡ ኤር. 12÷2፡፡ በአዲስ ኪዳን ስለ ኩላሊት የተነገረበት አንድ ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፡፡” ራእ. 2÷23 የሚለው ነው፡፡ ምንም እንኳን በሚዳበስ አካል ባይገለጽም ፈቃድ (will) ሌላው ከፍተኛው መንፈሳዊ የአካል ክፍል ነው፡፡ ማር. 12÷30፡፡

በአጠቃላይ ሰው ምንም እንኳ አራት ባሕርያተ ሥጋ ቢኖሩትም ከሁለት ዋና ዋና አካሎች የተፈጠረና የተሠራ ነው፡፡ የኸውም ከሥጋ (body) እና ከነፍስ (soul)፡፡ ትራይኮቶሚስቶች (Trichotomists) መንፈስን (spirit) በመጨመር ሰው ሦስት ነገሮችን ይዞአል ይላሉ፡፡ ሥጋ የሚለውን ዕብራይስጡ ከሌሎች ሥጋ የሰውን ሥጋ በተለየ ቃል ባሳር (Basar) ሲለው ነፍስን ደግሞ ነፌሽ (nephesh) ይላል፡፡ ይህም ከግእዙ ጋር ይቀራረባል፡፡ ነፍስ የሚለው ቃል በተለያየ አጠቃቀም 755 ጊዜ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሰፊው ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ ነፍስ ሕይወት ወይም ሰውነት የሚል ትርጉም አለው፡፡ ኢያሱ. 2÷14፣ 1ኛ ነገ. 19÷3፣ ኤር. 52÷28፡፡ ነፍስ ሙሉ ሰውነትን ይገልጻል፡፡ “ዮሴፍ አባቱ ያዕቆብና ሰባ ዐምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ፡፡” የሐዋ. 7÷14፡፡ ነፍስ ሥጋን ይገልጻል፡፡ ማር. 8÷35፡፡ ነፍስ ኀይል የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ማቴ. 22÷37፡፡ ሌላው ከነፍስ ጋር ተያይዞ የሚነገረው መንፈስ (spirit) ነው፡፡ በዕብራይስጥ ሩአህ (Ruah) ይባላል፡፡ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ 387 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ መንፈስ በቀጥተኛ ትርጉሙ ደግሞ የሚንቀሳቀስ አየር ወይም ነፋስ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም መንፈስ የማይዳሰስ ውስጣዊ እንቅስቃሴ ወይም መነቃቃት የሚፈጥር ታላቅ የሰው የአካል ክፍል እንደሆነ ይናገራል፡፡ ምሳ. 16÷32፣ ኢሳ. 26÷9፡፡ መንፈስ በሥጋ ውስጥ እንደሚያድር ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ በማለት ይናገራል፡፡ “በእኔ በዳንኤል በሥጋዬ ውስጥ መንፈሴ ደነገጠችብኝ፡፡” የሚለውን መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ዳን. 7÷15፡፡

ሰው መባል የሚችለው አራቱ ባሕርያት ያሉት ሥጋንና ነፍስን የያዘ አካል ነው፡፡ ሥጋ ብቻውን ሰው አይባልም ነፍስም ብቸዋን ሰው መባል አትችልም፡፡ የበደለ ሰው ነው እንጂ ሥጋ ብቻ አይደለም፡፡ በክርስቶስ ድኅነት ያገኘ ሰው እንጂ ነፍስ ብቻ አይደለችም፤ የበደለ ሰው በመሆኑ ኋላም የሚፈረድበት ወይም የሚፈረድለት ሰው ነው፡፡ ለዚህም ነው የሥጋ ትንሣኤ ያስፈለገው፡፡ ሰው የሁለቱ የነፍስና የሥጋ ውሑድ ነው፡፡ “ትራይከቶሚስቶች” ሰው ሦስት ነገሮችን የያዘ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀጥለን የሚከተሉትን አመለካከቶች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

ሀ. ትራይኮቶሚዝም (Trichotomism)፡- ትራይኮቶሚስቶች አስተሳሰብ ሰው ሥጋ ነፍስና መንፈስ እነዚህን ሦስት ነገሮች የያዘ ነው የሚል አስተምህሮ ያላቸው ሲሆኑ የሰው ልጅ በሥጋው ከሥጋውያን ጋር በሥጋው ዓለም ሲኖር በነፍሱና በመንፈሱ ደግሞ ከመንፈሳውያን ጋር በመንፈሳዊው ዓለም ይኖራል፡፡ ነፍስ ሥጋን የምታንቀሳቅስ የሥጋ ሕይወት ናት፡፡ ይኸውም ደመ ነፍስ የሚባለው ነው፡፡ እንደ እነርሱ አስተሳሰብ ደመ ነፍስ እንደማንኛውም እንስሳ ነፍስ ነው ይላሉ፡፡ ይህቺን ነፍስም የሕይወት እስትንፋስ ወይም የሥጋ ሕይወት ናት ብለው መንፈስ ደግሞ የማይሞት የሰው ከፍተኛው አካል ነው ይላሉ፡፡ ሰው እግዚአብሔርን የሚያውቅበት ዕውቀት ከመንፈሳውያን ጋር የሚኖርበት አካል ነው፡፡ ነፍስ ኀይል የምታገኘውም በመንፈስ ነው፡፡ ነፍስ በሥጋ ውስጥ ስታድር መንፈስ ደግሞ በነፍስ ውስጥ ታድራለች፡፡ መንፈስ በሥጋ ውስጥ ቢያድር ኖሮ ሥጋ መዋቲ ባልሆነም ነበር፡፡ እንስሳት በነፍሳቸው ውስጥ የምታድር መንፈስ ስለሌላቸው ሕያዋን አይደሉም፡፡ ነፍስና መንፈስ በማይለያይ ውሕደት የተጣመሩ ናቸው፡፡ የሰው ነፍስ ሕይወቷ መንፈስ ነው፡፡ እርሱም ከሦስት ነገሮች የተገነባ ነው የሚሉት፡፡

ለ. ዳይኮቶሚዝም (Dictomism)፡- ይህ ቲዎሪ ሰው የሁለት ነገሮች ውሑድ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮችም በዚህ ዓለም ያሉትን ፍጡራን የሚዛመድበት ሥጋ (ቁስ አካል) (material body) እና ከመንፈሳውያን ጋር አንድ የሚያደርገው ነፍስ ወይም መንፈስ (Soul or spirit) ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስና መንፈስን አንዱን በአንዱ በመተካት መንፈሳዊውን ሁኔታ ይገልጽበታል፡፡ ሁለቱም ቃላት ሕያው የሆነውን የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ነገር (element) ይገልጻሉ፡፡ ሁለቱም ቃላት የሚወክሉት አንድ ነገርን ነው፡፡ ይኸውም የማይሞተውን የሰውን ነፍስ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት ምስጋና መረዳት ይቻላል፡፡ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሤት ታደርጋለች” መንፈሴ ኅሊናዬ ሁለንተናየ ማለት ነው፡፡ ሉቃ. 1÷46-47፡፡ የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይቀድሳችሁ ነፍሳችሁን መንፈሳችሁንና ሥጋችሁንም 1 ተሰሎ. 5÷23 የኢዮብም ንግግር “እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ…” እንዲል፡፡ ኢዮብ 27÷3፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስና ነፍስን ጐን ለጐን አንድ ዐይነት መልእክት ለማስተላለፍ በአንድ ጊዜ ይጠቅሳቸዋል፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ስለ መዋቲ ሥጋ ሲናገር “ስለዚህ እላችኋለሁ ስለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” ብሏል፡፡ ማቴ. 6÷25፡፡ እዚህ ላይ ስለነፍሳችሁ ያለው ረቂቁን ወይም የማይሞተውን ነፍስ ለማለት ሳይሆን ሥጋን የሚመለከት ነው፡፡ ስለ ሥጋ ለመናገር ነፍስ የሚልበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በብዙ ቦታ ተገልጿል፡፡ ነፍስ በሥጋ ስለምታድርና ሥጋን ስለምታንቀሳቅስ ስለ ሥጋ ለመናገር ሲፈልግ ነፍስ ይላል፡፡ በዚሁ ወንጌል ላይ ደግሞ ነፍስንና ሥጋን ለይቶ የእያንዳንዱን ባሕርያቸውን ጭምር ተናግሮአል፡፡ “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፡፡” እንዳለ፡፡  ማቴ. 10÷28፡፡ አቤቱ ነቢያትህን ገደሉ መሠዊያችንም አፈረሱ እኔም ብቻዬን ቀረሁ ነፍሴንም ይሻEታል፡፡ ሮሜ 11÷3፡፡ አንዳንዴም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ሰውነትን (ነፍስንና ሥጋን) በነፍስ ተክቶ ይናገራል፡፡ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና፡፡…” ማቴ. 2÷20፡፡ እዚህ ላይ የሕፃኑን ነፍስ የሚለው ራሱ ሕፃኑን ሙሉ ሰውነት ማለት ነው እንጂ ሥጋውን ለይቶ ነፍሱን ብቻ ማለቱ አይደለም እንዲሁም “ኢትቅትል ነፍሰ” እንዲል ነፍስ አትግደል ሲል ነፍስ የምትሞት ሆና አይደለም ለሥጋ ሰጥቶ መናገሩ ነው፡፡ “ዳይኮቶሚስቶች፤ ትራይኮቶሚስቶች” የሚያቀርቡትን የተለያዩ መረጃዎች ትርጉማቸውንና ሐሳባቸውን በማስተካከል ውድቅ ያደርጓቸዋል፡፡ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን አስተምሮ ለዕብራውያን የጻፈውን መልእክት እንመልከት፡፡ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሠራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው “ወይፈልጥ ነፍሰ እመንፈስ”፡፡ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪወጋ ድረስ ይወጋል ያለበት ምክንያት ቢረቅበት ነው ነገር ግን በሐልዮ በነቢብ በገቢር የተሠራውን መርምሮ ይፈርዳል ሲል ነው፡፡” ዕብ. 4÷12፡፡ ጅማትና ቅልጥም የሚዳሰስ መዋቲ የሥጋ ክፍል ወይም ሁለቱ በአንድነት ሥጋን ይገልጻሉ፡፡ አንድ ሥጋ ይባላሉ እንጂ ሁለት አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ነፍስና መንፈስ ደግሞ የማይታየውን ረቂቁንና የማይዳሰሰውን የሰውነት ክፍል የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

“እስመ ዘተወልደ እምሥጋ ሥጋ ውእቱ”

ከግዙፍ ሥጋ የሚወለድ ግዙፍ ነውና ከረቂቅ መንፈስ የምትወለድ ነፍስ ረቂቅ ናትና ከመንፈስ ቅዱስ የሚወልዱት ልደት እንዲህ ነውና መንፈስ በወደደው ረድኤቱን ያሳድራል “ወቃሎ ትስምዕ” ትንቢት ሲያናግር ሱባዔ ሲያስቆጥር ትሰማዋለህ “ሀብተ ሙሴ በኢያሱ ሀብተ ኤልያስ በኤልሳዕ ሲያድር አታውቅም ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱት ልደትም እንዲህ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በወደደው ያድራል ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጉም ትሰማዋለህ ይላል”፡፡ ዮሐ. 3÷6፡፡

መንፈስ ቅዱስ ምእመናንን ንስኃ እንዲገቡና በክርስቶስ እንዲያምኑ ልብን ይለውጣል አማኝ የሆነ ሰውን ሥጋውን እንዲጾም እንዲጸልይ በሕይወቱ ሁሉ ይመራዋል እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ሮሜ. 8÷13፡፡

መንፈስ ማለት መንፈሳዊ ሥነ-ምግባር ነው፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ምጽዋት፣ ቸርነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ንጽሕና ነው፡፡ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ አሁንም በመንፈስ እንኑር በመንፈስም እንመላለስ ገላ. 5÷22፡፡ ኤፌ. 4÷30 – 1ቆሮ. 12÷13፡፡

 

አባሳሙኤል፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

አዲስአበባ

 

 

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

ከሰንደቅ ጋዜጣ

ለብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን – ሊቀጳጳስ የተደረገ ቃለ መጠይቅ!!

ሰንደቅ፡ኮሚሽኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያለውን አደረጃጀት ቢገልጹልን?

ብፁዕነታቸው፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በህግ ክፍል ማስታወቂያ 415/1964 በነጋሪት ጋዜጣ ከታህሳስ 26 ቀን 1964 ዓ.ም ጀምሮ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት በመሆን ተቋቁሞ ሲሰራ የቆየ  ሲሆን ፣ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲም ሪፖብሊክ መንግሥት የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጄንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት በኢትዮጵያዊ ነዋሪዎች በጐ አድራጐት ድርጅትነት በምዝገባ ቁጥር 1560 ተመዝግቦ የማህበራዊና የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ የበጐ አድራጐት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ፣ ቦርድና የአመራር አባላት ያሉት ኮሚሽን ነው፡፡

በመሆኑም የልማት ኮሚሽን የቤተክርስቲያኗ የወገን ደራሽነቷን ለማረጋገጥ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የነፍስ አድን እርዳታ በማድረግ ብሎም መልሶ በማቋቋም እና በልማት በማገዝ ፈርጀ ብዙ አገልግሎት ሲስጥ ቆይቶአልአሁንም እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሰንደቅ፡በአኹኑ ሰዓት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዋና ትኩረቶች ምንድን ናቸው?

ብፁዕነታቸው፡

 • የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚስፋፉበትን መንገድ መቀየስ፣
 • በገጠር የሚኖሩ ዜጐች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ፣ የሚሆኑበትን መንገድ የመቀየስና የመሥራት፣
 • የኤች አይቪ/ኤድስ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር ረገድ የተቀናጀና የተጠናከረ ሥራ መሥራት፣
 • በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ የበኩሉን የስራ ድርሻ ማበርከት፣
 • በእናቶች እና ሕፃናት ሥርዓት ምግብ ሥራ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ መሳተፍ፣
 • ስደተኞችን የመቀበልና ማስተናገድ ሥራን አጠናክሮ መቀጠል፣
 • ችግር ፈቺ የሆኑ የልማት ስራዎችን በማጥናት እና በፕሮጀክት በማካተት የሥራ አጥ ወጣቶች እና ችግረኛ ሴቶች ተጠቃሚ በማድረግ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኑሮአቸው የተሻሻለ እንዲሆን ማገዝ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ሰንደቅ፡በልማት የተለያዩ ዘርፎች በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራትና ተጨባጭ ውጤቶች ምን ምንድን ናቸው?

ብፁዕነታቸው፡

 • ኮሚሽኑ ከበርካታ አገር አቀፍና የውጭ በጎ አድራጐት ድርጅቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር በአገሪቷ በሚገኙ ክልልሎች ለሚኖሩ አያሌ ማህበረሰቦች ከአሉባቸው ችግሮች እንዲላቀቁ በማድረግ ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን በመሆን አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ይኸውም በበርካታ ወረዳዎች የገጠር ልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር በመስኖ ፤ በንፁህ መጠጥ ውሃ ፣ የተሻሻሉ ግብርና ዘዴዎችን በማስረጽ ፣ በገቢ ምንጭ ተግባራት ፣ በአቅም ግንባታ ፣ የአካባቢ ጥበቃ ፣ በማህበረሰብ የአደጋ ጊዜ መቋቋሚያና መጠባበቂያ ፈንድ ማህበራትን በመመስረትና በማጠናከር ፣ በስርዐተ ምግብ አጠቃቀም ፣ በሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ በኤች አይቪ እና በመሳሰሉት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል በኮሚሽኑ ሥር ባለው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች መምሪያ አማካኝነት ከጐረቤት ሀገራት ተሰደው የሚመጡትን እና ከስደት ተመላሾችን ኮሚሽኑ ባቋቋመው የስደተኛ ካምፖች በመቀበል አስፈላጊውን ሰብአዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ አድርጓል፡፡
 • ለዚህም ዐብይ አስረጂ የሚሆነው ልማት ኮሚሽኑ በተገበራቸው በዘላቂነታቸው በተረጋገጡ የልማት ተቋማት እና ለህብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት (CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ ኮሚሽኑ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በቀደምትነት አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም በቅቷል፡፡ በተጨማሪም የክልል ፣ የዞን እና የወረዳ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የልማት ኮሚሽናችን በተገበራቸው የልማት ሥራዎች በተጠቃሚው ሕብረተሰብ ላይ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በመመልከት ምስጋናና እውቅና እየቸሩን ይገኛሉ፡፡

ሰንደቅ፡በክርስቲያናዊ ተራኦ ረገድ ፣ ኮሚሽኑ የፈፀማቸው ጉዳዮች ቢዘረዝሩልን? ለምሳሌ፡- በአየር ንብረት ለውጥ (በድርቅ)…

ብፁዕነታቸው፡

 • ልማት ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት ለዓለም አስጊ ለሆነው የአየር ለውጥ ችግር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአየር ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉየልማት ስራዎችን በፕሮጀክት ጥናት በማካተት ተግባር ላይ እያዋለ ነው፡፡ ይኸውም ለተጠቃሚ አርሶአደሮች የአየር ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝሪያዎችን በማቅረብና በማከፋፈል፣ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ እና ጥበቃ ሥራን በማጠናከር የጎላ ተግባር እያከናወነ ነው፡፡
 • ልማት ኮሚሽኑ ለቤተክርስቲያን ደን ልማትና ጥበቃ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት የቤተክርስቲያ ደን ፕሮጀክት አጥንቶ በአጋርነት የሚሰራ ድርጅት በማግኘቱ በተመረጡ ገዳማት ላይ የደን ጥበቃና ማስፋፋት ሥራን መሠረት በማድረግ የተራቆቱ መሬቶች በደን የሚሸፈኑበትን ሁኔታ ለማስቻል ደረጃ በደረጃ እያከናወነ ይገኛል፡፡
 • በተጨማሪም ኮሚሽኑ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጅ እና የሶላር መብራት ተከላ በ15 ገዳማትያከናወነ ሲሆን ለወደፊቱም በሰፊው የሚሠራበት የልማት መስክ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
 • የልማት ኮሚሽኑ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተቋማትን በመገንባት እና የመስኖ ልማት በማስፋፋት ወደፊት በድርቅ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ለመቋቋም የሚያችል ስራዎችን በአፋር እና በሰሜን ሸዋ የአፋር አዋሳኝ ወረዳዎች እና በሌሎችም ላይ በሰፊው በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ሰንደቅ፡ በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች ውስጥ ፣ የሕዝቡ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ብፁዕነታቸው፡

 • ልማት ኮሚሽኑ ሥራውን እስከ ታች አውርዶ ለመሥራት የሚያስችል የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን በክልል እና በዞን ከተሞች ስላሉት በእነርሱ አማካኝነት ሥራው ማህበረሰቡን መሠረት አድርጎ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ በሚንቀሳቀስባቸው የፕሮጀክት ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሥራውን ለማስተዋወቅም ሆነ ከህዝብ ጋር ለመሥራት ምቹ መንገድ በመኖሩ እና የልማት ኮሚሽኑ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስላለው የማህበረሰቡ በልማት ተሳታፊነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የልማት ሥራዎቻችን በዘለቄታዊነት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የማህበረሰቡ ተሳትፎ የታከለበት በመሆኑ በግልጽ የሚታይ እውነት ነው፡፡

ሰንደቅ፡ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን ፣ መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላትና መልሶ ማቋቋም በኩል ኮሚሽኑ ሥራዎች ያገኙትን ውጤቶች ቢያብራሩልን?

ብፁዕነታቸው፡

 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ስደተኞችና ከስደት ተመለሾችን በመቀበልና አስፈላጊዉን እርዳታ በማድረግ በሀገሪቱ ቀደምት ታሪክ ያላት ስትሆን በዚህም ከአምት አስርት አመታት በላይ አገልግሎቱን እየሰጠች ትገኛለች፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያኗ የሀገሪቱ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለስደተኞችና ተመላሾች በተቀናጀ ሁኔታ አገልግሎት መስተጥ ሳይጀመሩ እሷ ይህን አገልግሎት በቀደመትነት መስጠቷን ያሳያል፡፡ በነበሩት የድጋፍ ጊዜያትም ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊ የሆኑና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ያማከለ ድጋፍና እርዳታ መስጠት ተችሏል፡፡
 • በሂደትም የቤተክርስቲያኗዋ ክንፍ የሆነዉ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን 1964 በህግ ሲቋቋም የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ እንደ አንድ የስራ ዘርፍ በማካተት በርካታ ተግባራትን ለመፈፀም በቅቷል፡፡
 • የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ መመሪያ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሥር በመሆንና የራሱን አስተዳደር በማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
 • በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ከመንግሥት ፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና እና ከልሎች አለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በበአዲስ አበባና ከተማ አካባቢዋ ባሉ ከተሞች እና በአራም ሀገሪቷ አቅጣጫ በሚገኙ 18 የመጠለያ ጣቢያዎች ማካኝነት ቁጥራቸው በየጊዜ የሚለያይ ቢሁንም በአሁኑ ሰዓት ከ801 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ ሀገር ስደተኞች ማለትም ከደቡብ ሱዳን ፤ ከሶማሊያ ፤ ከየመን ፤ ከኤርተራ ፤ ከኮንጎ፣ ከሱዳን ፣ ወ.ዘተ  ለመጡ ስደተኞች የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ይኽውም፡-

 • ኮሚሽኑ ለስደተኞች የመጠለያ ፣ የምግብ ፣ የአልባሳት ፣ የገንዘብ ፣ የጤና  ፣ የማህበራዊና የስነልቦና ምክር ፣ የትምህርትና የሙያ ክዕኖት ስልጠና ድጋፍ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ስደተኞች ቤታቸው እንዳሉ ሆነው እንዲሰማቸው ለማድረግ የሚኖሩበት መጠለያ አካባቢ ምቹ የሆነ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ ይኸውም የአካባቢ እክብካቤ ፣ የአካባቢና የግል ንጽሕና እንዲጠበቅ እንዲሁም የመጡበትን አዲስ አካባቢ እንዲላመዱ የማስተማርና የማሳወቅ ሥራዎች በሰፊው ይከናወናሉ፡፡
 • በመሆኑም ስደተኞች በሚሰጣቸው የትምህርት እና የሙያ ክዕኖት ድጋፍ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ሆነው የተለያዩ የገቢ ምንች የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እራሳቸውን ለማቋቋም ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ ስደተኞችን ከቤተሰብ ጋር በማገኛኘት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል፡፡
 • ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ስደተኞች የተለየዩ የቁሳቁስ ድጋፍ ፤ በኤች አይቪ ኤድስ ድጋፍና እንክብካቤ ፤ በግጭት አፈታት በፆታ ጥቃት ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ይሰራል፡፡

ሰንደቅ፡ ኮሚሽኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ከመሰል አገራዊና የውጭ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅትና መተባበር ምን ይመስላል?

ብፁዕነታቸው፡

 • የልማት ኮሚሽኑ በሚተግብራቸው የልማት ሥራዎች እና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት ከሌሎች ልቆ እስከ መሸለም ያበቃው ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር ተናቦ ፣ ተቀናጅቶ እና ተባብሮ በመሥራቱ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚቻለው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተባብሮ መስራት ሲቻል ነው፡፡
 • ኮሚሽኑ ይህን መርሆ በዋናነት በመከተል በግልጽነት እና በተጠያቂነት እየተንቀሳቀሰ በአነስተኛ በጀት ታላላቅ የልማት ሥራዎችን በመገንባት እውን እያደረገ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ በከፈታቸው የልማት የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችም ሆነ የፕሮጀክት ጽ/ቤቶች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ከሁሉም የልማት ባለድርሻ አካላት ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በፕሮጀክት ሥራ መልካምድራቸው አስቸጋሪ በሆኑ ሥፍራዎች ሁሉ የተለያዩ የልማት ተግባራትን በማከናወን እና ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የካበተ ልምድ ስላላቸው በየፎረሙም በተምሳሌነት የሚቀርቡ ሆነዋል፡፡

ሰንደቅ፡ የኮሚሽኑ ፕሮጀክቶች እና እንቅስቃሴዎች ፣ በሀገራዊ ሽፋን ያላቸው ስርጭት የተመጣጠነ ነው?

ብፁዕነታቸው፡

 • አዎን! በእኛ በኩል ሙሉ በሙሉ ባይሆን እንኳ ፕሮጀክቶች ያላቸው ስርጭት በአብዛኛው የተመጣጠነ እንደሆነ እምነታችን ነው፡፡ ኮሚሽኑ በአኹኑ ሰዓት በሚያካሂዳቸው27 የሚሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች እና በ18 የስደተኞች መቀበያ ካምብ አማካኝነት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የፕሮጀክት ወረዳዎች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይኸውም
 • በጋምቤላ ክልል፡ ጋቤላ ዙሪያ ወረዳ ፣ ፊኝዶ ፣ ተርኪዲ ፣ ኩሌ ፣ ሆኮቡ
 • በቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል፡ በከማሽ ፣በኩርሙክ ፣ በሸርቆሌ ፣ በባምፓሲ ፣ በቶንጎ
 • አፋር ክልል፡ በአርጎባ ልዩ ዞን፣ ሰሙ ሮቢ ፣ ዱለቻ
 • በኦሮሚያ ክልል፡በጉርሱም ፣ በጃርሶ ፣ በአርሲ ሮቤ ፣ በቄለም ወለጋ
 • በሶማሌ ክልል፡ በጂጂጋ ፣በሸደር ፣ በቀርቢበያህ ፣ በአውበሮ ፣ በኮቤ ፣ በመልካ ጂዳ ፣ በሔለወይኒ ፣ በቆልማንዩ
 • አማራ ክልል፡ በሊቦ ከምከም ፣ በአንኮበር ፣ በጊሼ ራቤል ፣ በዳወንት ፣ በበርኸት
 • ትግራይ ክልል፡ በክሊተ አውላዐሎ ፣ በእንደርታ ፣ሽመልባ ፣ አደ አርሹ ፣ እፀጽ
 • ደቡብ ክልል፡ ጉራጌ ፣ ሙዑር ፣ ቡታጀራ ፣ ወልቂጤ ፣ ሲዳማ ፣ ጌዲዮ ፣ ይርጋ ዓለም ፣ አለታ ወንዶ ፣ አላባ ፣ አርባ ምንጭ በ10 ወረዳዎች የኤች/አይቪ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ሥራዎች
 • ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች በ150 ወረዳዎች ላይ የኤች/አይቪ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ሥራዎች ያከናውናል፡፡

ሰንደቅ፡ ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች ሲያከናውናቸው የቆያቸው የልማት ፕሮጀክቶች እየተዘጉ እንደሆነ ይነገራል ፣ ፕሮጀክቶቹ የሚዘጉበት አልያም የሚቋረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?

ብፁዕነታቸው፡

 • ፕሮጀክቶች በተፈጥሮአቸው የጊዜ ገደብ አላቸው ይሁንና በኮሚሽኑ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች እስከ ታች የሚዘልቀውን የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን ፣ ፕሮጀክት ጽ/ቤቶችን እና የማህበረሰብ ማህበራትን በመጠቀም ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት በመከተል ሕብረተሰቡ የተለያዩ ሕግጋትን እና ደንቦችን እንዲያወጡ በማገዝ ፕሮጀክት በዘለቄታነት የሚቀትልበትን ሁኔታ እያመቻቸ በራሱ በህብረተሰቡ እየተመራ የሚከናወኑ የፕሮጀክት ዓይነቶች ናቸው፡፡
 • ይህንን ለማድረግ ፕሮጀክቶች ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲቀጥሉ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ተጋባራት ይከናወናሉ፡-
 • ተጠቃሚው ሕብረተሰብ በፕሮጀክት ጥናት ፣ እቅድ ፣ክንውን፣ ክትትልና ግምገማ እንዲሳተፉ ይደረጋሉ፡፡
 • በዕቅድ ዝግጅት ወቅት የሕብረተሰቡ ፣ ማህበራዊ ድርጅቶች ፣በየደረጃው የሚገኙ  የአካባቢ አመራሮች ወዘተ በፕሮጀክት ሂደት ውስጥ ያላቸው ድርሻ በግልጽ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡
 • የፕሮጀክት መጀመሩን የሚያበስር ዓውደ ጥናት ይዘጋጃል ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የእያንዳንዱ የሥራ ድርሻ በግልጽ ለውይይት ይቀርባል፡፡
 • የፕሮጀክት ተግባራትም እንደተጠናቀቁ በወቅቱ ለሚመለከተው ባለድረሻ አካላት በሕጋዊ የርክክብ ሰነድ ተረክቦ እንዲያስተዳድራቸው ይደረጋል፡፡

ሰንደቅ፡ ኮሚሽኑ በአኹኑወቅት ከለጋሾች ጋር ያለው ግንኙነትና የወደፊት ዕቅዱን በጠቁሙን?

ብፁዕነታቸው፡

 • የልማት ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር የላው ግንኙነት መላካም እና በተሸለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ዋናው ጉዳይ ለሚረዱን ድርጅቶች ፣ ለመንግሥት እና ለተጠቃሚ ማህበረሰብ ታማኝ ሆኖ በመገኘት የታለመለትን ፕሮጀክት በጥራትና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ በጽናት ማከናወን ነው፡፡
 • የልማት ኮሚሽኑም ዋነኛ ዓላማ የሕብረተሰቡ ኑሮ ተሻሸሎ ማየትና ለተሻለ እድገት ማብቃት በመሆኑ በዚሁ ረገድ ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ ግለፀኝነት እና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በየጊዜው ከለጋሽ ድርጅቶች አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝ ቆይቷል ፣ አሁንም እያገኘ ይገኛል፡፡
 • በተለይ ኮሚሽኑ የህፃናት ፖሊሲን ቀርፆ እና አፀድቆ በሥራ ላይ ማዋሉ እና የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አጋርነት (Humanitarian Accountability Partnership) ፍሬም ወርክ አዘጋጅቶ እና አፅድቆ በመተግበሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክሯል፡፡
 • ኮሚሽኑ በቅርቡ ሁሉንም የፕሮጀክት አጋሮች ተወካዮችን በመጋበዝ ባለን የጋራ አጀንዳ እና በቀጣይ ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት በተመለከተ ለመወያየት ዕቅድ በመያዝ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

ሰንደቅ፡ ኮሚሽኑበአኹኑሰዓትየራሱየሆነየገቢምንጭለማጠናከርምንእየሠራነው?ለወደፊትምንያቀደሠራካለቢያብራሩልንር?

ብፁዕነታቸው፡

 • ኮሚሽኑ ከውጪ ከሚያገኘው የእርዳታ ድጋፍ በተጨማሪ በገቢ ራስን ለማጠናከር እንዲቻል ዓላማው አድርጎ እየተንቀስ ነው፡፡ ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የውጭ እርዳታ በእጅጉ እየቀነሰ የመጣ ስለሆነ የተለያዩ የገቢ ምንጭ ዕቅድ ማዘጋጀትና መሥራት ግዴታ ሆኖአል፡፡ በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ ለገቢ ምንጭ መምሪያ አደራጅቶ ሥራ ጀምሯል፡፡
 • በቃሊቲ አካባቢ ከሚገኘው የኮሚሽኑ ጋራዥ እና መጋዘን እንዲሁም የከርሰ ምድር መቆፈሪያ ሪግ ማሽን ጨምሮ ለዚሁ ተግባር በመዋል የገቢ ምንች ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
 • ኮሚሽኑ በአኹኑ ጊዜ የገቢ ምንጩን በበለጠ ለማጠናከር እንዲያስችለው አንድ የሻማ ማምረቻ ፋብሪካ እና በሁለት ቦታዎች ላይ የታሸገ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም መሠረታዊ ጥናቶች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሰንደቅ፡ ኮሚሽኑ በእንጦጦ አካባቢ የሆስፒታል ግንባታ እቅድ እንዳለው ይታወቃል ፣ ሂደቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ ይቻላል?

ብፁዕነታቸው፡

 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከ46 ዓመት በፊት የልማት ኮሚሽኑን ሲያቋቁም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን ለመርዳት፣ አባት እናት የሌላቸውን እና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ምዕመናን ከውጪና ከውስጥ በሚገኝ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
 • ቤተክርስቲያኒቱ በገዳማት፣ በአድባራትና በአጥቢያ ቤተክርስቲያን አካባቢ ብዙ በጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት ስላላት መሬቱን በማልማት ገዳማቱና ህብረተሰቡ ከልማቱ ውጤት እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ እንዲሁም በየአካባቢው የትምህርት ቤትና የጤና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ከመንግስት ጋር በመተባበር መሠረተ ልማት ማካሄድ አንዱ ተግባፘ ነው፡፡
 • ይህን የጤና አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማዳበር በቅርቡ በእንጦጦ አካባቢ አንድ ራሱን የቻለ ከፍተኛ ሆስፒታል ተቋቁሞ በአይነትና በጥራት አገልግሎት እንዲሰጥ እቅድ ወጥቷል፡፡
 • ይህ የተጠቀሰው ሆስፒታል በአይነቱም ሆነ በባህሪው የተለየ ከመሆኑም ባሻገር የግንባታው ወጪ ከ370,000,000 የአሜሪካን ዶላር (ሦስት መቶ ሰባ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ) ሲሆን በኢትዮጵያ ብር ሲተመን ደግሞ ከ8.5 ሚሊሆን ብር (ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር) በላይ ግምት ተይዞለታል፡፡
 • ሥራው በሚጀምርበት ጊዜም ለ2100 ቋሚና ለ369 ጊዚያዊ በጥቅሉ ለ2469 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
 • በተመሳሳይ ሂደት ሆስፒታሉ የልዩልዩ በሽታዎች መታከሚያና ማገገሚያ ክፍሎችና መሳሪያዎች የሚኖሩት ሲሆን የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ የዲፕሎማቲክና የኤምባሲ ሠራተኞችን እና ከልዩልዩ አካባቢ የሚመጡ በሽተኞችን ለማከም ከ200 በላይ አልጋዎች ይኖረዋል፡፡
 • ቅድመ ጥናቱ እንደሚያሳየው ይህ በቀጥታ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና ከአሜርካን ሀገር ከሚገኝ ሌዠንደር ኮርፕ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በአጋርነት የሚቋቋመው ሆስፒታል የውጪ ምንዛሪን በማስገኘትና በአገሪቱ ውስጥ የቱሪዝምን አገልግሎት ለማስፋፋት እንደሚረዳ ይታመናል፡፡
 • የአሜሪካ መንግስትና በአሜሪካ ውስጥ ያሉ አበዳሪ ድርጅቶች ብድሩንም ሆነ ለብድሩ ዋስትና ለመስጠት ኃላፊ እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል፡፡
 • በኢትዮጵያ በኩል ግንባታውንና ከውጪ የሚገኘውን መዋዕለነዋይ እውን ለማድረግ በእንጦጦ አካባቢ ያለውና ለዚሁ ጉዳይ የተከለለውን መሬት ለዚሁ አገልግሎት እንዲውልከሚመለከተው አካል ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ እንገኛለን፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን!

 

 

አባሳሙኤል፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

አዲስአበባ

 

 

 

 

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ሰውሆይ ውኃ ሕይወታችን ነው!

 • ክቡራንና ክቡራት የክልሉና የአካባቢው የመንግሥት ባለስልጣናት
 • የተከበራችሁ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሠራተኞች
 • ክቡር የገዳሙ አስተዳዳሪና መነኮሳት በሙሉ
 • ክቡራን ተጋባዝ እንግዶችና
 • በአጠቃላይ የዚህ አካባቢ ማኅበረ ሰብእና ለዚህ የንጹሕ ውኃ መጠጥ ፕሮጀክት የምረቃ በዓል ጥሪ ተደርጎላችሁ የተገኛችሁ ሁሉ ውድ ጊዜ ያችሁንና ጉልበታችሁን መሥዋዕት አድርጋችሁ እዚህ በመገኘታችሁ በእራሴና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ስም የከበረ ሰላምታየን አቀርባለሁ፡፡

ከዚህ በመቀጠል ቸር እግዚአብሔር አምላክ ያሰብነውን የልማት ሥራ በሰላም አከናውኖ ለዚህ ዕለት ላደረሰን ክብር ምስጋና ይግባው፡፡ እናንተም እንኳን ደስ አላችሁ!

“ቀዳሜ ሕይወቱ ለሰብእ እክል ወማይ፤ ወይን ወስርናይ”

ለሰው የመጀመሪያ ሕይወቱ እህልና ውኃ፤ ወይንና ስንዴ ነው እንዳለ፡፡ሲራክ 29፡21

እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ሁሉን አዋቂ ነውና ለፍጥረቱ ሁሉ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር በሙሉ አሟልቶ ፈጥሯል፡፡ወኃ የተቀደሰ የምድራችን አካል እንደሆነ በመዝ. 69፥34 ተገልጻል ውኃ ለሕይወታችን በከፍተኛ ደረጃ አስፈላጊ ስለሆነነው፡፡

በመሆኑም ስለ ውኃ ጥቅም ገመግለጻችን በፊት ጥንታዊት፤ ታሪካዊት፤ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት እናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፈጣሪዋ የተሰጣትን ሀብትና ትዕዛዝ ጠብቃ የሰው ልጆች በሙሉ ሰላማዊ፤ ጤንነቱ የተሟላ፤ ሥነ-ምግባሩ ያማረ፤ እምነቱ የጸና፤ እርስ በእርስ የሚረዳዳና የሚተዛዘን፤ በፍቅር አብሮ የሚኖር፤ በወዙ በጉልበቱና በሙያው ሠርቶ ራሱን የሚጠቀምና ሌላውን የሚጠቅም፤ ትክክለኛና ፍትሐዊ የሆነ፤ፊት አይቶየማያዳላ፤ቅንናትሁት፤ኩሩ፤ለክብሩናለነጻነቱየተጋዜጋለማፍራትበብሉይናበሐዲስ ኪዳን መሠረት ላይ ቁማ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ ያስተማረችውንና በተግባር የፈጸመችውን በመጠኑም ቢሆን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡

ውሃ ለሕይወታችን ጠቃሚ ከሆኑት መካከል በዋነኝነት የሚጠቀስ እና የምድራችንን 70 በመቶ የሚሆነውን ክፍል የሚይዝ የዓለማችን አካል ነው፡፡ ከሰውነታችንም 70 በመቶው ውሃ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ ከደማችንም 90 በመቶው ውሃ ነው፡፡ ያለውሃ መኖር አይቻልም፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት 97 በመቶ የሚሆነው የውሃ አካል እጅግ ጨዋማ እና በውቅያኖሶች የሚገኝ ሲሆን ንጹሕ ተብሎ የሚገመተው 3 በመቶው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ መካከልም ለመጠጥ እና ለግብርና ሥራዎች የሚውለው አንድ በመቶ አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እጅግ ልንጠቀምበት የሚገባው እና እስከአሁን እንደሚፈለገው ያልተጠቀምነው ውሃ የከርሰ ምድር ውሃ ሲሆን ይህም 20 በመቶ የምድራችንን ውሃ ይሸፍናል፡፡

በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ንጽሕና በጎደለው ውሃ እና ከግል ንጽሕና አጠባበቅ ችግር ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ቁጥራቸው ከሁለት ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች በተቅማጥ በሽታ ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ ይህንን ለመከላከል ንጹሕ ውሃ መጠጣት ምትክ የማይገኝለት መፍትሔ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽናን የመናገሻ ማርያም ገዳምና የአካባቢው ኅብረተሰብ ያለበትን የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከገዳሙ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ብዙ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከብዙ ዓመታት በኋላ ችግሩ ሊቀረፍ ችሏል፡፡

ይህንየመጠጥውሃሥራእውንለማከናወንልማትኮሚሽኑ፡-

 1. አንድ 12ዐ ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በኮሚሽኑ የውኃ መቆፈሪያ መሳሪያ(ሪግ) በመቆፈር
 2. አስፈላጊውን ነዳጅ እና የባለሙያ ክፍያ በመሸፈን
 3. 125 ሜትር ባለ 4 ኢንች ፕላስቲክ ቧንቧ ጉድጓድ ውስጥ ለውኃ መግፊያ

የዋለና

 1. 6ዐዐ ሜትር ባለ 11/4 ኢንች የብረት ቧንቧ እና ሌሎች አስፈላጊ

መገጣጠሚያች ገዝቶ በማቅረብ እና ከምእመናን ድጋፍ የተገኘ የፕላስቲክ

ቧንቧ አንድ ክሎሚትር በመዘርጋት

 1. አንድ ከ22ዐ ሜትር በላይ ውኃ ሊገፋ የሚችል ፓምፕ ግዥ በመፈፀም
 2. ከመናገሻ ከንቲባ የተገኘ ድጋፍ ትራንስፎርሞር በዋጋ ሲተመ ንበድምሩ

1,000.000 (ከአንድ ሚልዮንብር) በላይ የሚደርስ ወጭ ያደረገ ሲሆን፤

በመሆኑም ይህንን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ዛሬ ሚያዝያ 26 ቀን 2ዐዐ9 ዓ.ም.በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ተመርቆ ሲከፈት ታላቅ እርካታ ይሰማናል፡፡ በቀጣይም መሰል ተግባራትን የንጹሕ ውሃ ችግር ባለባቸው ሥፍራዎች አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያበረታታን ተግባር ነው፡፡

የታቀደውን ዓላማ ለማሳካትም ኮሚሽኑ ያለውን አቅም ሁሉ በማሰባሰብ ሥራውን በማከናወን ለተጠቃሚ የገዳሟ መነኮሳትና ለአካባቢው ኅብረተሰብ ለማስረከብ በመቻሉ እግዚአብሔር አምላካችንን እና መሰግናለን፡፡

በድጋሜእንኳንደስአላችሁ!

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን!

ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ/ም

 

አባሳሙኤል፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

አዲስአበባ

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ  በመጀመሪያ ዲያቆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ ዞሮ ደወል ካሰማ በኋላ መቶ አምሳው ዳዊት ይታደልና ይደገማል፡፡ የሰባት ቀናት ውዳሴ ማርያምና አንቀጸ ብርሃን  እስከ ይዌድስዋ  ድረስ ታድሎ ይደገማል፡፡ ከዚያም “እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም ዓመ ከመ ዮም ያብጽሐኒ ያብጽሕክሙ አግዚአብሔር በፍሥሓ ወበሰላም” ተብሎ አቡነ ይደገምና  በዐራቱም ወንጌላት መሠረት ለእያንዳቸው በእየዕለቱና  ሰዓቱ የተመደበውን አቡን ካህናቱ በቀኝና በግራ እየተፈራረቁ  ይመራሉ፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም ይቀበላሉ፡፡ በመቀጠል፡-

ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡

አመኑኤልአ ምላኪየ ለከ ኃይል ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡

ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይልለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡

ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኩቴት (12) ጊዜ በመሐሉ አቡነ ዘበሰማያት እየተዜመና እየተደገመ ይባላል፡፡

ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለማሕየዊ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለዕበዩ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለመንግሥቱ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ስለልጣኑ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለኢየሱስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለክርስቶስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለሕማሙ  ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለመስቀሉ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

 

ክርስቶስ አምላክነ ዘመጽአ ወሐመ በእንቲአነ በሕማማቲሁ በዜወነ፡፡

በሌላኛው ወገን ንሰብሖ ወናልዕል ስሞ ኀቡረ እስመ ውእቱ ገብረ ምድኃኒተ በብዝኀ ሣህሉ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን (እግዚኦ ተሣሃል)፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  እብኖዲ(በቅብጥ አምላክ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ) ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ታኦስ (በጽርዕ አምላክ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ማስያስ (ቅቡዕ የተቀባ መሲሕ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኢየሱስ (መድኅን መድኃኒት) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ክርስቶስ (ዳግማይ አዳም ምሉአ ጸጋ ቀዳሜ በኩረ ልደት ለኩሉ ፍጥት) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ) ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን   አማኑኤል (ስመ ሥጋዌ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ትስቡጣ ናይናን  (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  እየተባለ  በአንድ ወገን 20 ጊዜ በሌላው ወገን 21 ጊዜ በጠቅላላው 41 ጊዜ

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  እየተባለ ይሰገዳል፡፡

 

በመጨረሻ ጊዜ፡-

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ (እናመልከው ዘንድ ለፈጠረን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል)፡፡

ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግእዝትነ ወመድኃኒትነ (እመቤታችንና መድኃኒታችን ለሆነች ለአምላክ እናት ለማርያም ምስጋና ይገባል)፡፡

ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ(ኃይላችን መጠጊያችን ለሆነ ድኅነት ለተገኘበት ለክርስቶስ ምስጋና ይገባል)፤፤ ጸሎተ ሃይማኖትን ሐመ  እስከ ሚለው ድረስ መድገም ነው፡፡

 

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0
ምንባብ ዘሰኑይ- የሰኞ

ምስባክ

የምስባክ ትርጉም
ሰኞ በ1 ሰዓት ዘመዓልት

1ኛ.  ምን. ዘፍ 1፥ 1-31፡፡

2ኛ.  ምን. ኢሳ 5፥1-9፡፡

3ኛ.  ምን.  ሲራ. 1፡፡

ወንጌል ማር.  11፥ 13-26፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል

ዘገብረ መንክረ ባሕቲቱ

ወይትባረክ ስመ ስብሐቲሁ

ምስባክ መዝ. 71 ፥ 18-19

የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን

ብቻውን ድንቅ ሥራ ያደረገ

የጌትነቱም ስም ይክበር ይመስገን

ሰኞ በ3 ሰዓት ዘመዓልት

1ኛ.  ምን. ኢሳ 5 ፥ 21-30፡፡

2ኛ. ምን.  ኢዩ 2 ፥ 21-32፡፡

3 ፥ 1-21፡፡

3ኛ.  ምን.  ኤር 9፥ 12-19፡፡

ወንጌል ማቴ.  21 ፥  18-22፡፡

ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር

ወቆማ እገሪነ ውስተ አዕጻድኪ ኢየሩሳሌም

ኢየሩሳሌም ሕንጽት ከመ ሀገር

ምስባክ መዝ. 121፥1-3

ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂዳለን  ባሉኝ ጊዜ ብለውኛልና ደስ አለኝ፡፡ ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮችሽ በዓጸዶችሽ ቁመዋልና ደስ አለኝ፡፡ ኢየሩሳሌም እንደ ሀገርነቷ የታነጸች ናት
ሰኞ በ6 ሰዓት ዘመዓልት

1ኛ.  ምን. ዘፀአ. 32፥ 7-15፡፡

1ኛ. ምን. ጥበብ 1 ፡፡

ወንጌል  ዮሐ. 2፥ 13-17

 

እስመ ህየ ዐርጉ አሕዛብ

ሕዝበ እግዚአብሔር ስምዐ እስራኤል

ከመ ይግነዩ ለስምከ እግዚኦ

ምስባክ መዝ. 121 ፥ 3-4

የብዙ ብዙ የሆኑ እስራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተዋል፡፡ ለእስራኤል ምስክር የሚሆኑ የእግዚአብሔር ወገኖች ናቸው፡፤ አቤቱ ለስምሕ ይገዙ ዘንድ
ሰኞ በ9 ሰዓት ዘመዓልት

1ኛ.  ምን. ዘፍጥ 2፥ 15-23፡፡

3፥ 1-24 ፡፡

2ኛ.  ምን. ኢሳ .40፥ 1-8፡፡

3ኛ.  ምን. ምሳ. 1 ፥ 1-9፡፡

ወንጌል ማቴ.21፥ 23-27፡፡

ስምዐነ አምላክነ ወመድኃኒነ

ተስፋሆሙ ለኩሎሙ አጽናፈ ምድር

ብፁዕ ዘኀረይኮ ወዘተወከፍኮ

ምስባክ መዝ. 64፥5-6

ድኅነት የምታደርግልን ፈጣሪያችን ልመናችንን ስማን

በምድር ዳርቻ ላሉት ሁሉ አለኝታቸው

የምትሆን አንተ ነህ፡፡ የመረጥረከውና የተቀበልከው የተመሰገነ ነው፡፡

ሰኞ በ11 ሰዓት ዘመዓልት

1ኛ.  ምን . ኢሳ.  50::

2ኛ. ምንኢሳ  26፥ 2-20::

3ኛ. ምን. ሲራ. 2::

4ኛ. ምን. ሆሴ  14፥ 2-10::

ወንጌል ዮሐ. 8፥ 51-59::

ምንባብ

ወትጼዕረኒ ልብየ ኩሎ አሚረ

እስከ ማእዜኒ ይትዔበዩ ጸላእትየ

ላዕሌየ ነጽረኒ ወስምዓኒ እግዚኦ አምላኪየ

ምስባክ መዝ. 12፥2

 

ልቡናየ ሁል ጊዜ ታስጨንቀኛለች

ጠላቶቸ እስከ መቸ ይታበዩብናል

አቤቱ ፈጣሪየ ስማኘረ ተመልከተኝም

           ዘሰሉስ – የማክሰኞ
ማክሰኞ በ1 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.   ምን. ዘፀአ 19፥ 1-8፡፡

2ኛ.  ምን. ኢዮ. 23፥ 24፡፡

3ኛ.  ምን. ኢሳ 1፥ 21-31፡፡

4ኛ.  ምን.ሆሴ.  4፥ 1-8፡፡

ወንጌልማቴ 26፥ 1-6፡፡

ለይትኀፈሩ ወይኅሰሩ እለ የኀሥሥዋ ለነፍስየ፤ ለይግብኡ ድኅሬሆሙ ወይትኀፈሩ እለ መከሩ እኩየ ላዕሌየ፤

ለይኩኑ ከመ ጸበል ዘቅድመ ገጸ ነፋስ፤

ምስባክ.መዝ. 34፥4

ሰውነቴን ለማጥፋት የሚሽዋት ሁሉ ይፈሩ፤ ይጎስቁሉም፤

በእኔ ክፉ ለአመጡብኝ የመከሩብኝ ሁሉ ወደኋላቸው ይመለሱ፤

ይፈሩ በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፡፡

 

ማክሰኞ በ3 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ. ምን. ዘዳግ. 8፥ 11-19፡፡

1ኛ. ምን ሲራ. 3፡፡

ወንጌል ማቴ 23፥ 37-38፡፡

ፍታሕ ፍትሕየ ወባልሐኒ

ወበእንተ ቃልከ አሕይወኒ

ርኁቅ ሕይወትየ እምኃጥኣን

ምስባክ መዝ. 118፥ 154

ፈርደህ ከመከራ አድነኝ

ሕግህንም ስለጠበቅሁ አድነኝ

ሕይወት እግዚአብሔር ከኃጥኣን የራቀ ነው፡፡

ማክሰኞ በ6 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

ኛ.  ምን.ሕዝ.  21፥ 3-17፡፡

2ኛ.  ምን. ሲራ .4፡፡

ወንጌል ዮሐ. 8፥ 12-20፡፡

አድኅነኒ እግዚኦ እምፀርየ፡፡

ወእምጸላትየ እስመ ይኄይሉኒ

ዘይባልሐኒ እምጸላጽየ ምንስዋን ወዘያዕሌኒ እምለቆሙ ላዕሌየ፡፡

ምስባክ  መዝ.58፥-1

አቤቱ ከጠላቶቸ አድነኝ፡፡ ከሚበረቱብኝም ጠላቶቸ አድነኝ፡፡ ጥፋተኞች ከሆኑ ጠላቶቸም የሚያድነኝ እሱ ነው፡፡ በጠላትነት ከተነሱብኝ ጠላቶቸ በላይ ከፍከፍ የሚያደርገኝ እሱ ነው፡፡
ማክሰኞ በ9 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን. ዘፍጥ.  6፥ 5-22::

2ኛ.  ምን. ዘፍጥ. 6፥ 21-24::

3ኛ.  ምን. ዘፍጥ.  8፥ 9-22::

4ኛ.  ምን. ዘፍጥ.  9፥ 1-7::

5ኛ.  ምን. ምሳ. 9፥ 1-12::

6ኛ.  ምን. ኢሳ. 20፥ 9-31፡፡

7ኛ.  ምን.ዳን. 6፥ 2-28፡፡

ወንጌል.ማቴ 24፥3-35፡፡

ኀቤከ እግዚኦ አንቃዕዶኩ ነፍስየ አምላኪየ

ወኪያከ ተወከልኩ ወኢይትኀፈር ለዓለም፤

ወኢይሥሐቁኒ ጸላእትየ

ምስባክ. መዝ. 24፥1

 

አቤቱ ፈጣሪየ በአንቃዕድዎ ልቡና ወዳንተ መልሸ ለመንሁ፡፡ በመከራ ለዘላለሙ እንዳላርፍ ባንተ አመንሁ፡፡

ጠላቶቸም አይዘብቱብኝም፡፡

 

ማክሰኞ

 

በ11 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን ኢሳ. 29፥ 5-21፡፡

2ኛ.  ምን. ኢሳ. 28፥ 16-26፡፡

3ኛ.  ምን. ምሳ 6፥ 20-35፡፡

ወንጌል ማቴ. 25፥14-46፡፡

46-54፡፡

 

በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግሥትከ

አፍቀርከ ጽድቀ ወዐመፃ ጸላእከ

ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን

ምስባክ  መዝ. 44፥ 6

 

የመንግሥትህ በትር የጽድቅ በጽር ነው፡፡

ጽድቅን ወደድህ፤ አመጽንም ጠላህ ፡፡

ለድኃና ለጦም አዳሪ የሚያስብ ንዑር ክቡር ነው፡፡

 

ዘረቡዕ – የሮብ
ረቡዕ በ1 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ. ምን. ዘፀአ. 17፥ 1-7፡፡

2ኛ. ምን. ኢሳ. 2፥ 1-11::

3ኛ. ምን. ምሳ. 3፥ 1-15፡፡

4ኛ. ምን. ሆሴ. 5፥ 13-15፡፡

ወንጌል ዮሐ. 11፥

እስመ ተማከሩ ኅቡረ ወዐረዩ

ላዕሌከ ተሰካተዩ ወተካየዱ

ተዓይኒሆሙ ለኤዶምያስ ወለይስማኤላውያን፡፡

ምስባክ መዝ. 82፥ 5

አንድ ሁነው በአንድነት ተካክለው ተማክረዋልና

በአንተ ላይ ፈጽመው ተማማሉ

የኤዶምያስና የእስማኤላውያን  ወገኖች

ረቡዕ በ3 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን. ዘፀአ. 13፥ 17-7፡፡

2ኛ.  ምን. ሲራ. 22፡፡

ወንጌል  ሉቃ. 22፥ 1-6፡፡

 

ይባዕ ወይርአይ ዘከንቶ ይነብብ

ልቡ አስተጋብአ ኃጢአተ ላዕሌሁ

ይወጽእ አፍኣ ወይትነገር ወየኀብር ላዕሌየ፡፡

ምስባክ  መዝ. 40፥ 6

ከንቱ ነገርን የሚናገር ገብቶ ይይ፡፡ ልቡናው ዕዳ የሚሆንበትን ኃጢአት ሰበሰበ፡፡ ወደ ውጭ ወጥቶ ኃጢአትን ይናገራል በእኔ ላይም ያስተባብራል፡፡
ረቡዕ በ6 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ. ምን. ዘፀአ. 14፥13-31::

2ኛ. ምን. ሲራ. 23፡፡

ወንጌል ሉቃ. 7፥ 36-50::

 

ጸላእትየሰ እኩየ ይቤሉ ላዕሌየ

ማእዜ ይመውት ወይሠዐር ስሙ

ይባእ ወይርአይ ዘከንቶ ይነብብ

ምስባክ መዝ.40፥5

ጠላቶቸ ግን በእኔ ላይ ክፋትን ይናገራሉ፡፡

መቼ ይሞታል  ስሙስ መቼ ይሻራል

ከንቱ የሚናገር ገብቶ ይመልከት

ረቡዕ በ9 ሰዓት  ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን. ዘፍጥ.  24 ፥ 1-9፡፡

2ኛ.  ምን. ዘኁ.  20፥ 1-13፡፡

3ኛ. ምን.  ምሳ. 1፥ 10-33፡፡

ወንጌል ማቴ.  26፥ 1-16፡፡

 

እስመ ናሁ ወውዑ ፀርከ

ወአንሥኡ ርእሶሙ ጸላእትከ

እስመ ተማከሩ ኅቡረ ወዐረዩ

ምስባክ መዝ. 82፥2

እነሆ ጠላቶችህ ደንፍተዋልና

ጠላቶችህ ራሳቸውን ነቅንቀዋልና

በአንድነት ተካክለው ተማክረዋልና፡፡

ረቡዕ በ 11 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን. ኢሳ.  58፥ 1-14፡፡

2ኛ.  ምን. ኢሳ. 59፥ 1-8፡፡

ወንጌል ዮሐ. 12፥ 27-36፡፡

 

ወፈውሰኒ እስመ ተሀውካ አዕፅምትየ

ነፍስየ ተሀውከት ፈድፋደ

ወኢትሚጥ ገጸከ እምኔየ፡፡

ምስባክ መዝ. 6፥2

 

አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ

ነፍሴም እጅግ ታወከች

ፊትህ ከእኔ አትመልስ፡፡

ሐሙስ በ1 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን. ዘፀአ 17፥ 8-16፡፡

2ኛ.  ምን. ግብ ሐ. ዘፀአ. 1፥ 15-20፡፡

ወንጌል  ሉቃ. 22፥ 1-14፡፡

 

ዘሐሙስ- ዘሐሙስ

ወጽሕደ እምቅብ ነገሩ፤

እሙንቱሰ ማዕበል ያሰጥሙ፤

ዓዲ

ሶበሰ ጸዐለኒ እምተዓገሥኩ ፤

ወሶበ ጸላኢ አዕበየ አፉሁ፡፡

ምስባክ መዝ. 54፥ 21/12

ነገሩ ከቅቤ የለዘበ ሆነ ፡፡  እነሱ ማዕበል ናቸው ያሰጥማሉ፡፡

ወይም

ጠላት ሰድቦኝ ቢሆን በታገሥሁት ነበር ፡፡ ጠላትም በእኔ ላይ አፉን ከፍ ቢያደርግ በተሸሸግሁ ነበር፡፡

ሐሙስ

 

በ3 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ. ምን. ዘፀአ. 32 ፥30-35፡፡

2ኛ. ምን. ዘፀአ. 33፥ 1-3፡፡

3ኛ. ምን.ሚክ 2 ፥3-13፡፡

ወንጌል  ማቴ. 26 ፥ 17-19፡፡

ወይንዕዋ ለነፍሰ ጻድቅ

ወይˆንን ደመ ንጹሐ

ወኮነኒ እግዚአብሔር ጸወንየ፡፡

ምስባክ መዝ. 93 ፥ 21

የጻድቁን ሰውነት ለጥፋት ይሽዋታል፡፡

ንጹሕን ደም የሚያፈስ

አግዚአብሔር ግን አምባ መጠጊያ ሆነኝ

 

ሐሙስ በ6 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.   ምን. ኤር. 7፥ 3-13::

2ኛ.  ምን. ሕዝ. 20፥ 39-44::

3ኛ.  ምን.   ሚክ. 2፥ 7-13::

4ኛ.  ምን. ሚክ 3፥ 1-8፡፡

5ኛ.  ምን ሶፎ 1፥ 7-18 ፡፡

6ኛ. ምን. ሲራ. 12፡፡

ወንጌል.ማር. 14፥ 12-16::

እስመ ሰማዕኩ ድምፀ ብዙኃን እለ ዐገቱኒ ዐውድየ

ሶበ ተጋብኡኅቡረ ላዕሌየ

ወተማከሩ ይምስጥዋ ላዕሌየ፡፡

ምስባክ መዝ . 30፥  13

 

በዙሪያየ የከበቡኝን የብዙዎችን ድምጽ ሰምቻለሁና

በእኔ ላይ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ

ሰውነቴን ሊጥቋት ተማከሩ፡፡

ሐሙስ በ9 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.  ምን. ዘፍጥ. 22፥ 1-19፡፡

2ኛ. ምን. ኢሳ. 61፥ 1-7፡፡

3ኛ. ምን.  ኢዮ. 27፥ 1-23፡፡

4ኛ. ምን. ኢዮ. 28፥ 1-13፡፡

5ኛ. ምን ሚል 1፥ 9-14፡፡

6ኛ. ምን. ሚል. 2፥ 1-8፡፡

ወንጌል ሉቃ 22፥ 1-13፡፡

ትነዝሀኒ በአዛብ ወእነጽሕ

ተኀጥፅበኒ እምበረድ ወእጻዐዱ

ልበ ንጹሐ ፍጥር ሊተ እግዚኦ

ምስባክ መዝ. 50፥7

 

በአውባን /በሂሶጵ ቅጠል ትረጨኛለህ

እኔም ንጹሕ እሆናለሁ

ታጥበኛለህ እኔም እንደ ከበረዶ ይልቅ ንጹሕ  እሆናለሁ

አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፡፡

 

ሐሙስ

ሐሙስ

በ9 ሰዓት ውስጥ፡፡

ሀ.የኅፅበተ እግር ምንባብ

1ኛ.  ምን. ዘፍጥ  18፥ 1-33::

2ኛ.  ምን. ዘፀአ. 14፥ 29-34::

3ኛ.  ምን.   ኢያ. 3፥ 13-17::

4ኛ. ምን. ኢሳ 4፥ 2-7::

5ኛ.  ምን. ኢሳ 55፥ 1-13::

6ኛ.  ምን. ሕዝ. 11፥ 17-21::

7ኛ.  ምን. ሕዝ 46፥ 2-9፡፡

8ኛ.  ምን. ምዝ ፥ 51፡፡

9ኛ.  ምን. መዝ ፥ 54፡፡

10ኛ. ምን. መዝ. ፥ 69፡፡

11ኛ.  ምን. ጢሞ ቀዳ. 4፥ 9-16፡፡

12ኛ. ምን ጢሞ. ካል 5፥ 1-10፡፡

ወንጌል ዮሐ.13፥ 1-20::

ለ የኀዕበተ እግር መጨረሻ ምዕዛል፡፡

መዝሙር፥ 150

እግዚአብሔር ይሬእየኒ ወአልቦ ዘየጥአኒ

ውስተ ብሔር ሥዑር ህየ የኀድረኒ

ወኀበ ማየ ዕረፍት ሐፀነኒ

ምስባክመዝ . 22፥1

 

እግዚአብሔር ይጠብቀኛል፤ የሚያሳጣኝም ነገር የለም፡፡

በለመለመ መስክ በዚያ ያኖረኛል

ዕረፍት በአለበት ውኃም አነጻኝ፡፡

 

ሐሙስ ስለ ቁርባን፡፡

1ኛ.  ምን ቆሮ ቀዳ. 11፥ 23-34፡፡

2ኛ. ምን ጴጥ ቀዳ  2፥ 11-25፡፡

3ኛ. ምን ግብ ሐዋ 8፥ 26-40፡፡

ወንጌል ማቴ.  26፥ 20-30፡፡

ምስባክ መዝ. 23፥5-6

 

ሐሙስ በ11 ሰዓት ዘመዓልት፡፡

1ኛ.   ምን. መዝ. 150፡፡

2ኛ.  ምን. ኢሳ 52፥ 13-15፡፡

3ኛ.  ምን. ኢሳ. 53፥ 1-12፡፡

4ኛ.  ምን. ኢሳ. 54፥ 1-8፡፡

5ኛ.  ምን. ኤር 31፥ 15-26፡፡

6ኛ.  ምን. ኢሳ .31፥ 1-9፡፡

7ኛ.  ምን. ኢሳ 32፥ 1-20፡፡

8ኛ.  ምን. ኢሳ.33፥ 1-10፡፡

ወሠራዕከ ማእደ በቅድሜየ

በአንጻሪሆሙ ለእለ ይሣቅዩኒ

ወአጽሐድክዋ በቅብ ለርስየ

ምስባክ መዝ. 22፥ 4

ዘይሴሰይ እክልየ አንሥአ ሰኮናሁ ላዕሌየ

አንተ እግዚኦ ተሣሀሊ ወአንሥአኒ እፍድዮሙ

በእንተዝ አእመርኩ ከመ ሰመርከኒ፡፡

ምስባክ መዝ.  9

በፊቴ ማእድን ሠራህ

በሚያስጨንቁኝም ፊት

ራሴንም በዘይት አለዘብኽ(ቀባህ)

እንጀራየን የሚመገብ ( ግብረ በላየ) ተረከዙን በላዬ አነሣብኝ፡፡

አቤቱ አንተ ይቅር በለኝ

ፍዳቸውን እከፍላቸው ዘንድ አንሣኝ

በዚህ እንደ ወደድከኝ አወቅሁ፡፡

ዓርብ – ዘዓርብ

 

ዓርብ በ1 ሰዓትዘመዓልት  (ዘነግህ)

1ኛ.    ምን ዘዳግ. 8፥ 19-20::

2ኛ.   ምን. ዘዳግ. 9፥1-24::

3ኛ.   ምን.   ኢሳ. 1፥1-9::

4ኛ.   ምን. ኢሳ 33፥ 5-22::

5ኛ.   ምን. ኤር. 20፥1-18::

6ኛ.   ምን. ኤር. 12፥ 1-8::

7ኛ.   ምን. ጥበብ 1፡፡

8ኛ.   ምን.ዘካ. 11፥ 11-14፡፡

9ኛ.   ምን. ሚክ. 7፥ 1-8፡፡

10ኛ.  ምን. አሞ 2፥ 1-16፡፡

11ኛ. ምን. አሞ. 3፥ 1-7፡፡

12ኛ.  ምን. ሆሴ. 10፥ 32-8፡፡

ወንጌል.ማቴ 27፥ 1-14፡፡

ማር .15፥ 1-5፡፡

ሉቃ. 22፥ 65-71፡፡

ዮሐ. 18፥28-40፡፡

ይበል መራሒ፡- ነአምን ነአምን ነአምን ሕማሞ ለዘኢየሐምም ርግዘተ ገቦሁ ነአምን ወቅንዋተ እደዊሁ ነአምን ዬ፡ ዬ፡ ዬ፡ ነአምን ሞቶ ወትንሣኤሁ፡፡ በመቀጠልም በግራና በቀኝ እየተቀባበሉ ይህን ይበሉ፡፡ ከዚያም ለከ ኃይል ይበሉ፡፡

እስመ ቆሙ ላዕሌየ ሰማዕተ ዐመፃ፡፡

ወሐሰት ርእሰ ዐመፃ፡፡

ዓዲ

ተንሥኡ ላዕሌየ ሰማዕተ ዐመፃ

ወዘኢየአምር ነበቡ ላዕሌየ

ፈደዩኒ እኪተ ህየንተ ሠናይት፤  ምስባክ. መዝ. 34፥ 11

1.     ምራት፡- ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት ይስቅልዎ ለኢየሱስ ዲበ ዕፀ መስቀል፡፡

2.    ምራት፡- ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት አውጽእዎ አፍአ ለኢየሱስ ውስተ ዓውደ ምኩናን፡፡

3.    ምራት፡- ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት ሐመይዎ ለኢየሱስ ወመጠውዎ ለጲላጦስ፡፡

4.    ምራት፡-ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት  አውጽእዎ አፍአ ለኢየሱስ ወነበረ ዐውደ ሶቤሃ፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት፡፡

 

መሪው፡፡- የማይታመመውን ጌታ ሕማሙን እናምናለን እናምናለን እናምናለን ፤ የጎኑን በጦር መወጋት እናምናለን፤ እጆቹ በችንካር መቸንከራቸውን እናምናለን፡፡ ወዬው ወዬው ወዬው ሞቱንና ትንሣኤው እናምናለን በማለት ግራና እየተቀባበሉ  ይበሉ፡፡

ከዚያም እንደተለመደው ለከ ኃይል ይበሉ

 

ምስባክ

የሐሰት ምስክሮች በጠላትነት ተነሥተውብኛልና

ሐሰትም የዓመፃ  አበጋዝ ናት/

ወይም

የሐሰት ምስክሮች በጠላትነት ተነሡብኝ፡፡

በእኔ ላይም የማላውቀውን ነገር ተናገሩብኝ፡፡

1.     ሊቃነ ካህናት ኢየሱስን በመስቀል ላይ ይሰቅሉት ዘንድ በጧት/በነጋ ጊዜ ተማከሩ፡፡

2.     ሊቃነ ካህናት ኢየሱስን ወደ መስቀል አደባባይ ይወስዱት  ዘንድ በጧት/በነጋ ጊዜ ተማከሩ፡፡

3.     ሊቃነ ካህናት ኢየሱስን አስረው ለጲላጦስ አሳልፈው ይሠጡት ዘንድ በጧት/በነጋ ጊዜ ተማከሩ፡፡

4.     ሊቃነ ካህናት ኢየሱስን ያን ጊዜ ወደ ውጭ አውጥተው በፍር አደባባይ ያቆሙት ዘንድ በጧት/በነጋ ጊዜ ተማከሩ፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን፡፡

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ በዮርዳኖስ የተጠመቀ፤ በመስቀል የተሰቀለ፤ አቤቱ ይቅር በለን፡፡

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ፡፡ ብሎ ብቻ ያቆማል፡፡

 

ዓርብ በ3ኛ ሰዓት ዘመዓልት (ዘሠለስት)

1ኛ.  ምን. ዘፍጥ.  41፥ 1-22::

2ኛ.  ምን. ኢሳ.  63፥1-19::

3ኛ.  ምን. ኢሳ. 64፥ 1-4::

4ኛ.  ምን. ኢሳ. 4፥ 8-16::

5ኛ.  ምን. ኢሳ. 50፥ 4-11::

6ኛ.  ምን. ኢሳ. 3፥ 5-15::

7ኛ.  ምን. ሚክ. 7፥ 9-20::

8ኛ.  ምን. ኢዮ. 29፥ 21-25::

9ኛ.  ምን. ኢዮ. 30፥ 1-14፡፡

10ኛ.  ምን. መዝ. 35፡፡

ወንጌል ማቴ.  27፥ 15-26፡፡

ማር.  15፥ 6-15፡፡

ሉቃ. 23፥ 13-25፡፡

ዮሐ 19፥ 1-12፡፡

 

ይበል መራሒ፡- አርዑተ መስቀል ፆረ፤ አርዑተ መስቀል ፆረ፤ ይስቅልዎ ሖረ ፡፡ ዬ፤ ዬ፤ ዬ፤ ከመ ኪያነ ይቤዙ እግዚኦ ኮነ ገብረ፡፡

በጧት የተባለውን ምቅናይ ለከ ኃይልን ከዚህ በል፡፡

ዲያቆን፡-  መዝ. 34 በውርድ ንባብ ይበል፡፡

ካህን፡- ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒ፤ ጽብኦሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ፤ነግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍዑኒን  በዜማ ይበል፡፡ ሕዝቡም ይቀበሉት፡፡

ዐገቱኒ ከለባት ብዙኃን፤

ወአኀዙኒ ማኅበሮሙ ለእኩያን፤

ዐገቱኒ ከለባት ብዙኃን፡፡          

ምስባክ መዝ. 21፥ 16

v ምራት፡- ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት አኀዝዎ  ለኢየሱስ ወወሰድዎ ይስቅልዎ፡፡

v ምራት፡- ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት   አሕየወ ሎሙ በርባንሃ ወወሀቦሙ ኢየሱስሃ ይስቅሉ

v ምራት፡- ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ወሰድዎ ለኢየሱስ ውስተ ምኩናን፡፡

v  ምራት፡-  ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ቀሰፎ ጲላጦስ ለኢየሱስ ወመጠዎሙ ይስቅልዎ፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ይበል፡፡

 

ዓርብ በ6 ሰዓትዘመዓልት (ዘቀትር)፡፡

1ኛ.   ምን. ዘኊል.  21፥ 1-9::

2ኛ.  ምን. ኢሳ. 53፥ 7-12::

3ኛ.  ምን.  ኢሳ. 13፥ 1-10::

4ኛ.  ምን. ኢሳ. 50፥ 10-11::

5ኛ.  ምን. ኢሳ. 51፥1-6::

6ኛ.  ምን. አሞ. 8፥ 8-14::

7ኛ.  ምን. አሞ 9፥ 1-15፡፡

8ኛ.  ምን. ሕዝ. 37፥ 15-22::

9ኛ.  ምን. ገላ.  6፥ 14-17::

ወንጌል ማቴ.  27፥ 27-45::

ማር.  15፥ 16-33፡፡

ሉቃ. 23፥ 27-44፡፡

ዮሐ. 19፥ 13-27፡፡

 

ይበል መራሒ፡- ተሰቅለ ፤ተሰቅለ፤ ተሰቅለ ወሐመ ቤዛ ኩሉ ኮነ፡፡  ዬ፤ ዬ፤ ዬ በመስቀሉ በዜወነ እሞት ባልሐነ እያለ ሲመራ በግራና በቀኝ ያሉ ሁሉ እየተቀባበሉ ይህን ይበሉ፡፡

በጧት የተባለውን ምቅናይ ለከ ኃይልን ከዚህ በል፡፡

ዲያቆን፡- በውርድ ንባብ ኦ መኑ ዝንቱን  ያንብ፡፡

ካህን፡-  ለመስቀልከ ንሰግድ ኦ ሊቅነ ወለትንሣኤከ ቅደስት ንሴብሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ የሚለውን ያዚም ሕዝቡም እየተቀባበሉ ይበሉ፡፡

ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ፤

ወኁለÌ ኩሉ አዕፅምትየ፤

ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ፤        ምስባክ መዝ. 21 16

v ምራት፡- ጊዜ ስድስቱ ሰዓት አልበስዎ አልባሲሁ ለኢየሱስ ወወሰድዎ ይስቅልዎ፡፡

v ምራት፡- ጊዜ ስድስቱ ሰዓት ዐበጥዎ ለስምዖን ከመ ይፁር መስቀሎ፡፡

v ምራት፡- ጊዜ ስድስቱ ሰዓት ሰቀልዎ ለኢየሱስ በቀራንዮ መካን፡፡

v  ምራት፡- ጊዜ ስድስቱ ሰዓት ቀትር ሶቤሃ ሊቃነ ካህናት ሰቀልዎ  ለኢየሱስ መዕከለ ክልኤ ፈያት፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ይበል፡፡

መሪው፡- ተሰቀለ፤ ተሰቀለ፤ ተሰቀለ፤ ታመመም የሁሉ ቤዛ መድኃኒት ሆነ፤ ወዬው  ወዬው ወዬው በመስቀሉ አዳነን ከሞትም አዳነን እያለ ሲመራ በግራና በቀኝ ያሉ ሁሉ እየተቀባበሉ ይህን ይበሉ፡፡

በጧት የተባለውን ምቅናይ ለከ ኃይልን ከዚህ በል፡፡

ዲያቆን፡- በውርድ ንባብ ኦ መኑ ዝንቱን  ያንብ፡፡

ካህን ፡- ሊቅ ፈጣሪያችን ሆይ ለመስቀልህ እንሰግዳለን፡፡

ቅድስት የሆነች ትንሣኤህንም ዛሬም ዘወትርም እናመሰግናለን፡፡

እግሬን እጄን ቸነከሩኝ

አጥንቶቸንም ሁሉ ቆጠሩ

እግሬን እጄን ቸነከሩኝ

v ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስን ልብሱን አልብሰው ይሰቅሉት ዘንደ ወሰዱት፡፡

v ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ ስምዖንን አስገደዱት፡፡

v ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ያን ጊዜ ቀትር ነበር፡፡ የካህናት አለቆች ኢየሱስን በቀራንዮ ሰቀሉት፡፡

v ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ የካህናት አለቆች ጌታ ኢየሱስን በሁለት ወንበዴዎች መካከል ሰቀሉት፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን፡፡

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ በዮርዳኖስ የተጠመቀ፤ በመስቀል የተሰቀለ፤ አቤቱ ይቅር በለን፡፡

v ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ፡፡ ብሎ ብቻ ያቆማል፡፡

 

በ9 ሰዓትዘመዓልት (የተሲያት)

1ኛ.    ምን. ኢያ. 5፥ 10-12፡፡

2ኛ.   ምን. ሩት. 2፥ 11- 14::

3ኛ.  ምን.   ኤር. 18፥ 18-23::

4ኛ.  ምን. ኤር. 12፥ 1-13::

5ኛ.  ምን. ኢሳ.  24፥1-23::

6ኛ.  ምን. ኢሳ. 25፥ 1-12::

7ኛ.  ምን. ኢሳ. 26፥ 1-8፡፡

8ኛ.  ምን. ዘካ. 14፥ 5-11::

9ኛ.  ምን. ኢዮ. 16፥ 1-22::

10ኛ.  ፊልጵ.  2፥ 1-18::

ወንጌል ማቴ.  27፥ 46-50::

ማር. 15፥ 34-27፡፡

ሉቃ. 23፥ 45-46፡፡

ዮሐ. 19፥ 28-50፡፡

በዜማ ማኅዘኒ፡-

v አምንስቲቲ ብሂል በዕብራይስጥ ተዘከረነ በዓረብኛ በሥውር የነበርህ  ማለት ነው፡፡

v ሙኪርያ ብሂል በዕብራይስጥ እግዚኦ  በዓረብኛ ብሂል ነዳዊ ማለት ነው፡፡

v ሙዓግያ ብሂል በዕብራይስጥ ቅዱስ በዓረብኛ ብሂል እሳታዊ ማለት ነው፡፡

v ሙዳሱጣ ብሂል በዕብራይስጥ  ሊቅ በዓረብኛ ብሂል ነበልባላዊ ማለት ነው፡፡

v አንቲ ፋሲልያሱ ብሂል በዕብራይስጥ በውስተ መንግሥትከ በዓረብኛ  ብሂል ወዮ ጌታዬ እኔ ልሙትልህ ማለት ነው፡፡

ዲያቆን፡- በውርድ ንባብ ተዘከረነን ሲያነብ  ካህናቱም  ተዘከረነን ሲያዜሙ ሕዝቡ እተቀበለ አብሮ ያዜማል፡፡

ዲያቆኑ፡- በውርድ ንባብ ለትቅረብ ስእለትየን ሲያነብ ካህናቱም  ኦ ዘጥዕመ ሞተን   ሲያዜሙ ሕዝቡ ይቀበላል፡፡

ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ፤

ወአስተዩኒ ብሂአ ለጽምእየ፤

ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ፤

ምስባክ መዝ. 68፥21

v ምራት፡-ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት  ጸርሐ ኢየሱስ በቃሉ ወይቤ ኤሎሄ ኤሎሄ

v ምራት፡-ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት  ገዐረ ኢየሱስ በቃሉ ወወጽአት መንፈሱ ሶቤሃ

v ምራት፡-ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት  ከልሐ ኢየሱስ በቃሉ ወአማኅፀነ ነፍሶ ሶቤሃ

v ምራት፡-ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት   አጽነነ ርእሶ ኢየሱስ ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት … ብሂለከ ፈጽም፡፡

 

አሳዛኝ በሆነ ዜማ፡-

v አምንስቲቲ ማለት በዕብራይስጥ ተዘከረነ በዓረብኛ በሥውር የነበርህ  ማለት ነው፡፡

v ሙኪርያ ማለት በዕብራይስጥ እግዚኦ  በዓረብኛ  ነዳዊ ማለት ነው፡፡

v ሙዓግያ ማለት በዕብራይስጥ ቅዱስ በዓረብኛ  እሳታዊ ማለት ነው፡፡

v ሙዳሱጣ ማለት በዕብራይስጥ  ሊቅ በዓረብኛ  ነበልባላዊ ማለት ነው፡፡

v አንቲ ፋሲልያሱ ማለት በዕብራይስጥ በውስተ መንግሥትከ በዓረብኛ  ወዮ ጌታዬ እኔ ልሙትልህ ማለት ነው፡፡

ዲያቆን፡- በውርድ ንባብ አቤቱ ይቅር በለንን ሲያነብ  ካህናቱም አቤቱ ይቅር በለንን    ሲያዜሙ ሕዝቡ እተቀበለ አብሮ ያዜማል፡፡

ዲያቆኑ፡- በውርድ ንባብ ልመናየን ተቀበልን ሲያነብ ካህናቱም     ሞት የማይገባው አምላክ ምትን ቀመሰ እያሉ ሲያዜሙ ሕዝቡም  ይቀበላል፡፡

በምግቤ ውስጥ ሐሞትን ጨመሩ፤

ጥማቴንም ለማርካት መፃፃውን አጠጠኝ፤

በምግቤ ውስጥ ሐሞትን ጨመሩ፡፡          ምስባክ መዝ. 68፥21

v በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ኤሎሄ ኤሎሄ አለ

v በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ጮኸ፤ ያን ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡

v በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ፤ያን ጊዜ ነፍሱን አደራ ሰጠ፡፡

v በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ራሱን ዘንብል (ዘለስ) አድርጎ ሁሉ ተፈጸመ አለ፡፡

በየምራቱ መጨረሻ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ፡-

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ …  ብሎ እንደላይኛው መድገም ነው፡፡

 

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ  በመጀመሪያ ዲያቆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ ዞሮ ደወል ካሰማ በኋላ መቶ አምሳው ዳዊት ይታደልና ይደገማል፡፡ የሰባት ቀናት ውዳሴ ማርያምና አንቀጸ ብርሃን  እስከ ይዌድስዋ  ድረስ ታድሎ ይደገማል፡፡ ከዚያም “እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም ዓመ ከመ ዮም ያብጽሐኒ ያብጽሕክሙ አግዚአብሔር በፍሥሓ ወበሰላም” ተብሎ አቡነ ይደገምና  በዐራቱም ወንጌላት መሠረት ለእያንዳቸው በእየዕለቱና  ሰዓቱ የተመደበውን አቡን ካህናቱ በቀኝና በግራ እየተፈራረቁ  ይመራሉ፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም ይቀበላሉ፡፡ በመቀጠል፡-

ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡

አመኑኤልአ ምላኪየ ለከ ኃይል ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡

ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይልለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡

ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኩቴት (12) ጊዜ በመሐሉ አቡነ ዘበሰማያት እየተዜመና እየተደገመ ይባላል፡፡

ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለማሕየዊ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለዕበዩ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለመንግሥቱ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ስለልጣኑ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለኢየሱስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለክርስቶስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለሕማሙ  ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ለመስቀሉ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

ክርስቶስ አምላክነ ዘመጽአ ወሐመ በእንቲአነ በሕማማቲሁ በዜወነ፡፡

በሌላኛው ወገን ንሰብሖ ወናልዕል ስሞ ኀቡረ እስመ ውእቱ ገብረ ምድኃኒተ በብዝኀ ሣህሉ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን (እግዚኦ ተሣሃል)፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  እብኖዲ(በቅብጥ አምላክ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ) ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ታኦስ (በጽርዕ አምላክ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ማስያስ (ቅቡዕ የተቀባ መሲሕ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኢየሱስ (መድኅን መድኃኒት) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ክርስቶስ (ዳግማይ አዳም ምሉአ ጸጋ ቀዳሜ በኩረ ልደት ለኩሉ ፍጥት) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ) ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን   አማኑኤል (ስመ ሥጋዌ) ናይናን (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ትስቡጣ ናይናን  (መሐር ኪያነ፤ መሐረነ)  ኪርያላይሶን ፡፡

ኪርያላይሶን  እየተባለ  በአንድ ወገን 20 ጊዜ በሌላው ወገን 21 ጊዜ በጠቅላላው 41 ጊዜ

ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  እየተባለ ይሰገዳል፡፡

 

በመጨረሻ ጊዜ፡-

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ (እናመልከው ዘንድ ለፈጠረን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል)፡፡

ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግእዝትነ ወመድኃኒትነ (እመቤታችንና መድኃኒታችን ለሆነች ለአምላክ እናት ለማርያም ምስጋና ይገባል)፡፡

ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ(ኃይላችን መጠጊያችን ለሆነ ድኅነት ለተገኘበት ለክርስቶስ ምስጋና ይገባል)፤፤ ጸሎተ ሃይማኖትን ሐመ  እስከ ሚለው ድረስ መድገም ነው፡፡

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

፰. መዝሙርዘሆሣዕና፦ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ

   ምስባክ፦ እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ፤

   በእንተ ጸላዒ፤ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ።

  (መዝ. 8፥2-3)

  ምንባብ፦ ማቴ 21፥1-17

‹‹ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት፣ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፣ ሆሣዕና በአርያም፤››   ‹‹ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም፤ (ማቴ 21-9)።

 image-78eea9e6b1b5290ba79bbf4d0ebe98a6a39b1bbe067f333681cdf18ab15a09bf-V

ይህ መዝሙር የእሥራኤል ሕዝብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ እሱን በደስታና በዕልልታ ሲቀበሉ የዘመሩት መዝሙር ነው።‹‹ሆሣዕና››ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ እባክህን አድነን፤›› ማለት ሲሆን፣ ‹‹ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት›› ማለት ደግሞ ‹‹የዳዊት ልጅ እባክህ አድነን፣›› ማለት ነው።አይሁድ (የእስራኤልሕዝብ) ይህንን መዝሙር የሚዘምሩትመሢሕ እንዲወርድላቸው በመጠባበቅ ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ነው። ይህንን መዝሙር የሚዘምሩት በዓመት ለ7 ቀናት በሚያከብሩት በዳስ በዓል (በበዓለ ደብተራ) ጊዜ ነው። በዚህ በዓል ይህንን መዝሙር በየቀኑ ይዘምሩታል።

የእስራኤል ሕዝብ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩት በታላቅ ክብርና ድምቀት ነው። ሕዝቡ ይህን በዓል ለማክበር ከየሀገሩ ከሳምንት አስቀድሞ ይሰበሰቡ ነበር።

ጌታችንም ወደ ምድር መጥቶ በሚያስተምርበት በመጨረሻው ዓመት የፋሲካን በዓል ለማክበርና ሕዝቡን ለማስተማር ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ። በነቢዩ በዘካርያስ ትንቢት(9፥9)እንደተነገረውወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ በአህያ ላይ ተቀምጦ ነበር የወጣው። ይህም ፍጹም ትሕትናውን ያሳያል። የሚገርመው ጌታ በአህያ ተቀምጦ ሲመጣ መላዋ ኢየሩሳሌም በድንጋጤና ተውጣ ነበር። በፈረስና በሠረገላ ቢመጣማ ኖሮ የባሳ ድንጋጤናሽብር በተፈጠረ ነበር። ይህም ሁሉ ያለ ማመን ውጤት ነው። የክርስቶስ እምነት የጐደለው ሁሉ ምንጊዜም ከመሸበርና ከድንጋጤ ነጻ ሆኖ መኖር አይችልም።

ከእንስሳት ሁሉ አህያ የተመረጠችበት ምክንያት ራሱንየቻለ ምሥጢር አለው። ይኸውም  አህያ ትዕግሥተኛ፣አደጋንና መከራን ቻይ፣ ትህትና ያላትና በጣም የዋሂት ናት። እነዚህምገጸ ባህርያት ለጥሩ ክርስቲያኖች ያስፈልጋሉ። ስለዚህትህትናት፣ ትዕግሥትንና የዋህነትንሁሉ ገንዘብ አድርገን ብንገኝ የምሕረት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት እስራት ሊፈታን ቅዱስ ፈቃዱ ነው።image-0-02-04-831ec0fa29051c4aa511f72f9e694188b829e908eb2be00a7a5ddaa74ef4e40f-V

 

ከሩቅ አገር (ከውጭ አገር)የመጡት ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር ስለነበረው ትምህርትና ያደርጋቸው ስለነበሩት ተአምራት ሰምተው ስለነበረ እሱን ለማየትና ትምህርቱን ለመስማት እጅግ ይጓጉ ነበር። እነዚህከውጭ አገር የመጡ የአይሁድ ሕዝብ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣቱን ሰምተው እርሱን ለመቀበል ገና ወደ ኢየሩሳሌም ሳይደርስ ከሩቅ ቦታ ጀምሮ በታላቅ ሆታና ዕልልታሊቀበሉት ወጡ። ጌታ በሚሄድበት ቦታ ሁሉ ሕዝቡየወይራ ዛፍና የዘንባባ ቅርንጫፎች እያውለበለቡና ልብሳቸውን በሚሄድበት ምድር ላይ እያነጠፉ፣ የዘንባባም ቅርንጫፎች እየጐዘጐዙ፣ እንዲሁም ‹‹ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት››የሚለውን መዝሙር እየዘመሩ ተቀበሉት። የእስራኤል ሕዝብ የወይራ ዛፍና የዘንባባ ቅርንጫፎች እያውለበለቡ በታላቅ ክብር ይቀበሉ የነበረው አንድን የሀገር መሪ ወይም ንጉሥ ሲቀበሉ ነበር። በተለይምimage-0-02-04-b52ebc1311a9a5459bdb4a60bc1d5ea99dd409f020fcc18b5d8bc841302ed2e8-V

‹‹ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት››ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር› የሚለውን መዝሙር ይዘምሩ የነበረው ይመጣል ብለው ለሚጠብቁት መሢሕ ነበር እንጂ ለሌላ ሰው አልነበረም። ጌታን ሲቀበሉ ይህን መዝሙር የዘመሩት በብዛት ሕፃናት ነበሩ። አይሁድ ጌታን መሢሕ ነው ብለው ስላላመኑበት ይህ መዝምር ለእሱ መዘመሩን ሰምተው እጅግ ተቈጥተው ነበር። ኢየሱስንም ሕዝቡንና ሕፃናቱን ዝም እንዲያሰኝ ጠየቁት። ጌታም  ‹‹ እነሱ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይዘምራሉ፤››አላቸው። በዚያን ጊዜም በተአምር ድንጋዮች አፍ አውጥተው እንደዘመሩ የአባቶች ትውፊት ይነግረናል።

ቤተ መቅደስን ማጽዳትጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ በቀጥታ ወደ ቤተ መቅደስነበር የሔደው። በዚያም ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ እንደገባ በጸሎት ፈንታ የማይገባ ሥራ፣የንግድ ሥራ ሲሠራ ጌታችን ኢየሱስ ይመለከታል። የተለያዩ ነጋዴዎች ተሰብስበው የወይፈኖች፣ የበግና የፍየል ጠቦቶች እንዲሁም  የርግቦች ንግድ ተጧጥፎ ነበር። የእነዚህ ከብቶች ንግድ የተጧጧፈበት ምክንያት ከእስራኤል ሀገር ውጭ በልዩ ልዩ ሀገሮቸ የሚኖሩና ከሩቅ አውራጃዎች ይመጡ የነበሩት አይሁድ ከብቶቹን ለምሥዋዐት ይፈልጉአቸው ስለነበረ ነው።

image-0-02-04-a1fbc0ddf89df87bd856ef233926029b40330635562a7a21d62049d0634daed5-V

 

እንዲሁም ቤተ መቅደስን ለመርዳት የአስተዋጽኦ ገንዘብ ለመስጠት የእስራኤል ገንዘብ ሼክልያስፈልግ ስለነበረ ከውጭ አገር ያመጡትን የውጭ ገንዘብ የሚመነዝሩ ገንዝብ ለዋጮችም ጠረጴዛዎቻቸውን ዘርግተው በንግድ ሥራ ላይ ተጠምደው ነበር። ጌታም ይህንን የንግድ ሥራ በቤተ መቅደስ አካባቢ ሲኪያሄድ በተመለከተ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ ‹‹ ቤቱ የጸሎት ቤት ይባላልእናንተ ግን የሌቦችዋሻ አደረጋችሁት፤››በማለት በዚያ በንግድ ሥራ የተሠማሩትን ሁሉ በጅራፍ እየገረፈ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አስወጣቸው።

እኛም እኮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን ከጸሎት ሌላ ዓለማዊ ጭውውትና ሌላ ተግባር የምንሠራ ከሆነ ጌታ በሥውር ጅራፍ ስለሚገርፈንና ስለሚቀሥፈን መጠንቀቅ አለብን። ቤተ ክርስቲያን የጸሎት  ቦታ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ከጸሎት በስተቀር ሌላ ጭውውትና ሌላ  ነገር ማድረግ የለብንም። በዕርግጥ በቤተ ክርስቲያን መልካም ሥራ መሥራት፣ የተጣሉ ሰዎች ማስታረቅ ተገቢ ነው። በዛሬው ቀን አይሁድ ‹‹ሆሣዕና በአርያም፣ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፣››እያሉ በመዘመር፣ ልብሳቸውን ጌታበሄደበት መንገድ ላይ በማንጠፍና የወይራ ዛፍና የዘንባባ ቅርንጫፎች በማውለብለብ ጌታንበዕልልታና በሆታ ተቀብለውታል። እኛስ ዛሬ ክርስቶስን እንዴት ነው የምንቀበለው? እኛ ክርስቶስየምንቀበለው በልባችን ውስጥ እንዲመላለስ፣በቤታችንና በኅብረተሰባችን ውስጥ እንዲመላለስ በማድረግ መሆን አለበት።

ክርስቶስን በቤታችንንና ውስጥ መቀበል አለብን። እንግዲህ ክርስቶስን ለመቀበል ልባችንንናቤታችንን ማጽዳትአለብን። ልባችንን ቤታችንን ካላጸዳን ክርስቶስ በቤታችንና በልባችን ሊያድር፣ ሊመላለስ አይፈቅድም። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶሱ ሰዎች ሲጽፍ ‹‹ እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆናችሁንና የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ መኖሩን አታውቁምን?››

(1ቆሮ.3፥16) ይላል። ስለዚህ ልባችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለሆነ ልባችንንና በአጠቃላይ መላ ሰውነታችንን በንጽሕና መጠበቅ አለብን። ታዲያስ ልባችን ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከኃጢአት ንጹሕ ነው?አለበለዚያ ጌታችን በኢየሩሳሌም እንዳደረገው ዛሬም ጅራፉን ይዞ ሊመጣብን ስለሚችል መጠንቀቅ አለብን።

በዚያን ጊዜ የነበረውን የእስራኤልን ሕዝብ ሁኔታ ስንመለከት የሰው ጠባይ ምን ያህል ተለዋዋጭ እንደሆነ እንገነዘባለን። አይሁድ የሆሣዕና ዕለት ጌታን ‹‹ ሆሣዕና በአርያም!እያሉ በሆታና በዕልልታ እንደተቀበሉት ተመልክተናል።ነገር ግን እነዚሁ ሕዝቦች ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥጲላጦስን ጌታን ‹‹ስቀለው! ስቀለው!›› እያሉ ጮሁ። እኛም ሰዎች እንዲሁ ነን። ዛሬ ወደ እግዚአብሔር  እንቀርባለን፣  ነገ ደግሞ ከእርሱ እንርቃለን።‹‹ስቅለው ስቀለው!›› ባንልም ከክርስቶስ የሚያርቅ ተግባር እንፈጽማለን። ኃጢአት እንሠራለን፣ ከወንድማችን ጋር እንቀያየማለን። ጌታ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ቂም በቀልን አይወድም፣ ሆኖም ልዑል እግዚአብሔር ቸር መሐሪ ስልሆነ ተመልሰን ንስሓ ከገባን ይቅር ይለናልና ንስሓ መግባት አለብን። የሚመጣው  ሳምንት በጌታ ላይ የደረሱትን ሥቃይና መከራ፣ ስቅለትና ሞት የምናስብበት ሳምነት (ሕማማት) ስለሆነ የንስሐ ጊዜ ነውና ሰውነታችንን አጽደተን እንጠብቅ። ልዑል እግዚአብሔር ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድረሰን። አሜን!!

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበበ

 

 

Please follow and like us:
0
Please follow and like us:
0

 

፯.  መዝሙር ዘኒቆዲሞስ፦ ሖረ ኀቤሁ

    ምስባክ፦  ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤ አመከርከኒ

    ወኢተረክበ ዐመፃ በላዕሌየ፤ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ

    እጓለ እመሕያው (መዝ 16፥3-4)።

   ምንባብ፦ ዮሐንስ. 3፥1-12

ዳግም ልደት«ሰው ዳግመኛ/እንደገና ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም»  (ዮሐ. 3፥3)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከተባለ የኦሪት ሕግ ሊቅና መምህር ጋር ያደረገውን ውይይት ነው። ኒቆዲሞስ የኦሪት ሕግ ሊቅና መምህር ከመሆኑም በላይ የአይሁድን ሕዝብ በበላይነት ያስተዳድሩ የነበሩት 70 ምሁራን ሊቃውንት የሚገኙበት ታላቅ ሸንጎ አባል ነበር። የአይሁድ ሸንጎ አባላት የአይሁድ እምነት፣ ሕግና ባህል እንዳይፈርስና እንዳይጣስ ጠንቅቀው መጠበቅና ማስጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት ነበረባቸው። ስለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድን እምነትና ባህል ይነቅፍ ስለነበረ፣ አይሁድና የአይሁድ  ሸንጎ  አባላት እሱንና ትምህርቱን ሁሉ አይቀበሉም ነበር።

ሆኖም ኒቆዲሞስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርትና ያደረጋቸው የነበሩትን ተአምራት ስምቶ በልቡ ይደነቅ ነበር። ስለሆነም ሁሉንም ጠንቅቆ ለማወቅ በነበረው ታላቅ ፍላጎት ወደ ጌታ ሄዶ ቃል በቃል ሊያነጋግረውና ሁሉንም ከእርሱ ለመረዳት ይፈልግ ነበር። ነገር ግን ጌታ ኢየሱስን የሚከተልና ትምህርቱን የሚቀበል እሱንም መሲሕ መሆኑን የሚያምን ሰው ሁሉ ከአይሁድ ማኀበር እንዲለይና እንዲወገዝ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ወስነው ነበር። ኒቆዲሞስም ይህንን በመፍራት በተለይም እሱ ራሱ ከባለሥልጣኖቹ አንዱ ስለነበር፣ በይፋ ወደ ጌታ ለመሄድ አልፈለገም። ስለዚህ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ የሄደው በሥውር ማት በሌት ነበር። በሌሊት የሄደበትም ሌላው ምክንያት ምሥጢራትንና በተለይም የሃይኖት  ተምህርትን ጠንቅቆ ለማወቅና ለመረዳት ምቹ ጊዜ ሌሊት ስለሆነ ነበር። አእምሮም የሚሰበሰበው ሌሊት ነው።

ውይይቱ፦ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሌሊት ሄዶ ሰፊ ውይይት አደረገ።  በውይይቱም ጊዜ ኒቆዲሞስ «መምህር ሆይ! እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር እነዚህን  አንተ የምታደርጋቸውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል ማንም የለምና አንተ መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር እንደመጣህ እናውቃለን፤» አለው

ጌታችን ኢየሱስም «እውነት እውነት እልሃለሁ ሰውዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊያይ አይችልም፤» አለውይህም ማለት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ማለት ነው። «እንደገና መወለድ፤» « ዳግመኛ መወለድ» የሚለው አነጋገር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ አነጋገር ለኒቆዲሞስም እጅግ የረቀቀ አነጋገር፣ የረቀቀ ምስጢር ነበር የሆነበት። ይህ ለኒቆዲሞስ ሊገባው አልቻለም። ስለዚህም ኒቆዶሞስ «ታዲያ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኀፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን? ብሎ ጌታ ጠየቀው።
የሦስት  ፫ ዓይነት መወለድበመንፈሳዊ ትምህርትና በአባቶች ትምህርት መሠረት አንድ ሰው ሦስት ዓይነት ልደት አለው። 1ኛ/ አንድ ሰው በተፈጥሮ ሕግ መሠረት ከእናትና ከአባቱ ይወለዳል፤ ይህ በተፈጥሮ ሕግ የሚገኝ ልደት ነው።

፪ኛ ሁለተኛው ልደት ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ  ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ሲል ገልጦ ለኒቆዲሞስ መለሰለት፦ «እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።» ይህ ከላይ እንደተገለዐው ጥምቅት ነው። ሰው በሕፃንነቱም ሆነ ከአደገ በኋላ ጥምቀትን ከተቀበለ (ክርስትና ከተነሣ) አዲስ ሰው ሆነ ማለት ነው፤ እንደገና ተወለደ ማለት ነው።  በጌታ አነጋገር ኒቆዲሞስ የዱሮውን ሥርዐትና እምነት ትቶ በክርስቶስ አዲስ ሰው መሆነ ነበረበት። በክርስቶስ አምኖ መጠመቅ ነበረበት። አዳም የጌታን ትእዛዝ አፍርሶ አትብላ የተባለውን ዕፅ በለስን በመብላቱ የእግዚአብሔር ትእዛዝ በማፍረሱ ከእግዚአብሔር ርቆ ነበር። በዚህም እንደሞተ ተቆጥሯል። የሰው ከባዱ ሞት ከእግዚአብሔር ፊት መለየት፣ ከእግዚአብሔር ፊት መራቅ ነው። አዳም የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፣ ነገር ግን በበደለ ጊዜ፣ ኃጢአት ከሠራ በኋላ የእግዚአብሔር ልጅነትን አጥቶ ከእግዚአብሔር ርቆ ነበር። ያንን ያጣውን የእግዚአብሔር ልጅነት መልሶ የሚያገኘው በጥምቀት ነው። ስለዚህ በምንጠመቅበት ጊዜ ያንን ያጣነውን የእግዚአብሔር ልጅነት እንደገና እናገኛለን። ስለዚህ ነው ጥምቀት አዲስ መወለድ፣ አዲስ ልደት የሚባለው።

፫. አንድ ሰው ያልተስተካከለ ሕይወት በኃጢአት የተጨማለቀ ኑሮ የሚኖር ከሆነ፣ ይህ ሰው በእግዚአብሔርም ዘንድ በኀብረተሰቡም ዘንድ እንደሞተ ነው የሚቆጠረው። ይህ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት፣ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚችለው የቀድሞውን የተበላሸ ሕይውት፣ የቀድሞውን የተበላሸ ሕይውት የቀድሞውን በኃጢአት የተጨማለቀ ኑሮ እርግፍ አድርጎ በመተው መለወጥ ያስፈልገዋል። አንድ ኃጢአተኛ ሰው፣ አንድ ያልተስተካከለ ኑሮ የሚኖር ስው የቀድሞ መጥፎ ሥራውን ትቶ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ እንደሆነ ወደ ኅብረተሰቡም ትመልሶ መልካም ሕይወት መኖር ከጀመረ የሀ ሰው እንደገና ተወለደ ይባላል። አዲስ ሰው ሆነ ይባላል። በኅብረተሰቡም አነጋገር  « እገሌ እኮ አዲስ ሰው ሆኗል፤ አዲስ ፍጡር ሆኗል፤ ይባላል።

ጌታችን  «ሰው ዳግመኛ ካልተወለድ  በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤» ያለው ለኒቆዲሞስ ብቻ አይደለም። ጌታችን ሁላችንንም «እንደገና ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም፤»  ይለናል። ምናልባት ክፉ ሥራ በመሥራት፤ የኃጢአት ሥራ በመሥራት እግዚአብሔር አስቀይመነው ይሆናል። ጎረቤቶቻችንን፤ ወንድሞቻችንን፤ እህቶቻችንን  አስቀይመን ይሆናል ይሆናል። ቂም በቀልም ይዘን ይሆናል። እንግዲህ ክፉ ሥራችንን እርግፍ አድርገን በመተው፤ ያስቀየምነውንም ይቅርታ በመጠየቅ፣ እኛንም ያስቀየመንን ይቅር በማለት ወደ እግዚአብሔር ከተመለስን አዲስ ሰዎች፣ አዲስ ልጆች እንሆናለን ማለት ነው። መለወጥ አለብን፤ እንደገና መወለድ አለብን። አዲስ ሰዎች መሆን አለብን። ይህን ከአደረግን ልዑል እግዚአብሔር ይቅር ባይና መሐሪ ስለሆነ  ይቅር ብሎ ይቀበለናል።

ጌታም በማቴዎስ ወንጌል « ተመልሳችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ ምንግሥተ ሰማያት መግባት አትችሉም፤» (ማቴ. 18፥2) ይለናል። ሕፃን የዋህ ነው፤ ንጹሕ ነው፤

ተንኮልንም አይሠረም። ሕፃን ቂም በቀል አይዝም፤ ክፉት ተንኮል የለበትም። በአባቱም ላይም ታላቅ እምነት አለው። እኛም እንደ ሕፃናት መሆንአለብን፤ ከቂም በቀል፤ ከክፉት፤ ከተንኮል መራቅ አለብን። ይህን ያደረግን እንደሆነ የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን። ወደ እግዚአብሔር መንግሥትም በቀላሉ እንገባለን። ስለ ሕፃናት ቂም በቀል አለመያዝ አንድ ታሪክ ልንገራችሁ።

በአንድ መንደር ሁሉት ቤተሰቦች ነበሩ። ሁለቱም ቤተሰቦች በዕድሜ የተስተካከሉ ሁለት ልጆች ነበሯቸው። አንድ ቀን ሁለቱ ልጆች ሲጫወቱ  ተጣልተው አንዱ ልጅ ሌላውን ልጅ ጥቂት ያቆስለዋል። በዚህ ምክንያት ሁለቱ ቤተሰቦች ይጣሉና ይኳረፉሉ። መኳረፉቸውንም የሰሙ ጐረቤቶች ሁለቱን ቤተሰቦች ሊያሰማሙና ሊያስታርቁ ሽምግልና ይቀመጣሉ። ሽማግሌዎች ለማስታረቅ በሚጥሩበት ጊዜ ሁለቱ ቤተሰቦች አንታረቅም በማለታቸው ሽማግሌዎቹ ጥቂት ተቸግረው ሳለ፣ ሁለቱን ልጆች ሩቅ ሆነው ሲጫወቱ ይመለከታሉ። አንዱ ሽማግሌ የሚጫወቱት ልጆች እነማን እንደሆኑ  ለማወቅ በዕድሜ አነስተኛ የሆነውን ሽማግሌ ይልከዋል። ሰውዬውም ሄዶ ሲመለከት የሚጫወቱት ልጆች እነዚያ የተጣሉት ልጆች መሆናቸውን ይረዳል። ተመልሶ ለተሰበሰቡት

ሰዎች «እኛ ከልጆቹ ያነስን ነን፤ እነሱ በታላቅ ፍቅር ይጫወታሉ። መጣላታቸውንም  ፈጽሞ ረስተውታል። ታዲያ እናንተ ምን እንሁን ነው የምትሉት?» ብሎ ከነገራቸው በኋላ፣ ሁሉም ተገርመው ታርቀው ተለያዩ ይባላል።

የእግዚአብሔር ባለሟል የነበረው ንጉሡ ዳዊት ወደ አምላኩ ሲጸልይ « አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፤ የቀናውንም መንፈስ በውጤ አድስልኝ፤» (መዝ. 50፥10) ሲል ጸልዮአል። ኒቆዲሞስ ይህንን መዝምር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ኒቆዲሞስ ሊቅ ስለነበር ነው ጌታ «አንት የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን እንዴት አታውቅም?» ያለው።

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሰው ሁሉ የተበላሸ ሕይወት፤ በኃጢአት የተጨማለቀ ሕይውት ሊኖረው አይችልም። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው ስለዚህ ጉዳይ አበክሮ ሲናገር  «ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአት ፈጽሞ አይሠራም፤ ሊሠራም አይችልም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ባሕርይ በውስጡ ስለሚኖርና ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ ነው፤» ይላል ( 1ኛ.ዮሐ 3፥9)። ቀጥሎም ይኸው ሐዋርያ እንዲህ ይላል «ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ የዲያብሎስ ልጅ ነው፤ ይለናል።(3፥8) የዲያብሎስ ልጅ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ይገኛል? በዕርግጥ የዲያብሎስ ልጅ ለመሆን የሚፈልግ ማንም የለም። መቼም ክፉ ነገር ስንሠራ፣ ኃጢአት ስንሠራ የምንሠራው ሥራ ሁሉ ክፉ መሆኑን፣ ኃጢአት የምንሠራ መሆኑን እናውቃለን፤ እያወቅን እኮ ነው ኃጢአት የምንሠራው። እንግዳህ በክፉ ሥራችን፣ በኃጢአታችን ልዑል እግዚበሔር  እንዳይፈርድብን ክፉ  ከመሥራት ኃጢአት ከመሥራት ራሳችንን መከልከል አለብን። አዲስ ሰዎች መሆን አለብን። እንግዲህ ልዑል እግዚአብሔር የሚወደውን ምልካም ሥራ ሠርተን የእግዚአብሔር ልጆች ለመባል ያብቃን!! ሰማያዊ መንግሥቱንም ለመወረስ ይርዳን። አሜን!!

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበበ

Please follow and like us:
0