“የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች” /ዮሐ.12÷24/
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ማርያምን ነሥቶ ፍጹም ሰውነታቸንን የተዋሐደው ስለ ስለ እኛ ለመሞት መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ በተለያየ ጊዜያትና ምሳሌያት ይገልጽላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሞት የሰው ሁሉ ፍርሃት በሆነበት ሁኔታ የቃሉ ምሥጢር ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱንም ተስፋ ያስቆርጣቸው ነበር፡፡ ሞት በሁሉ ላይ ነግሦ ሲገዛ እንደ ነበር ተጽፏል፡፡ /ሮሜ.3÷14/ መቼም “ነበር” ብሎ ለመናገር የተለወጠ ነገር መኖር አለበትና ሞት ሁሉን ሲገድል ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሳው፡፡ በመሆኑም “ሞት ሆይ፣ መውጊያውስ የት አለ? ሲዖል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?” ተብሎ እንደ ተጻፈው የትንሣኤው ኃይል ሞትን ታሪክ አደረገው፡፡ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ፣ እነሆም ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና ሲዖል መክፈቻ አለኝ” /ራእ.1÷13/ ፡፡
ከዚያም እውነት የተነሣ ጌታችን ባስተማረው በምሳሌ ትምህርቱ ላይ “እውነት እውነት እላችኋላሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” አለ፡፡ ጌታ በምሳሌው ላይ ያነሣው የስንዴ ቅንጣት ስለ ብዙዎች ብትሞት ብዙ እንደምታፈራ፣ ካልሞተች ግን ብቻዋን እንደምትቀር ነው፡፡ ስለዚህ ይህች ቅንጣት የምትጠበቀው እንድትሞት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለመብዛት መሞት አስፈላጊ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ይገርማል! እየኖሩ እንዲህ እየሞቱ መብዛትን የሰው አእምሮ አይገንዘበውም፡፡ ይሁን እንጂ ዓለም እንኳን በክብር መዝገብ ላይ ስማቸውን የምትጽፍላቸው ስለሌሎች መሥዋዕትነት ለመክፈል የሞቱትን ነው፡፡
እስኪ አንድ ታሪክ ለንሳ! ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው ክፍለ ዘመን ፋርሶች ግሪክን ወረሩና ማራቶን በምትባለው የግሪክ ከተማ ላይ ተከማቹ፡፡ ማራቶን ከግሪክ ዋና ከተማ ከአቴንስ ዐርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ፋርሶች ከግሪኮች ይልቅ የበረቱ ስለነበሩ ግሪኮች ጦርነቱን ብቻቸውን ማሸነፍ እንደማይችሉ ተረድተው የጎረቤት አገሮችን እርዳታ ለመጠየቅ መልእክተኞችን ወደ ጎረቤት አገሮች ላኩ፡፡ የግሪክ ጎረቤቶችም ጥያቄውን ተቀብለው ጦራቸውን ወደ ግሪክ ላኩላቸው፡፡ ግሪኮችም ባገኙት እርዳታ በመታገዝ ፋርሶችን ማራቶን በምትባለው ከተማ ላይ ጦርነትን ገጥመው አሸነፏቸው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ስለ ድሉ የአቴንስ ሕዝብ ሳይውል ሳያድር መስማት ስለነበረበት ፊዲፒዲስ /ኢዩክለስ /የተባለው ወታደር ድሉን እንዲያበሥር ያንኑ ዕለት ወደ አቴንስ እንዲሄድ ታዘዘ፡፡
ይህ ሰው ከጦርነት ውሎው በኋላ ያለ ምንም ዕረፍት ከማራቶን እስከ አቴንስ ያለውን ዐርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት በመሮጥ በጭንቀት የጦርነቱን ወሬ ይጠባበቅ ለነበረው ለአቴንስ ሕዝብ ድሉን ካበሠራቸው በኋላ ወዲያውኑ ወድቆ ሞተ፡፡ እንግዲህ ዘመናዊው የማራቶን ሩጫ ዐርባ ሁለት ኪሎ ሜትር (42 ኪ.ሜ ከ195 ሜትር) የሚሮጠው በዚህ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይህ የሩጫ ውድድርም በአንዱ ጀግና መሞት የተገኘ በመሆኑ በዓለማችን ላይ ብዙዎች የሚናፍቁትና የሚሳተፉበት ሁኗል፡፡ እንግዲህ በመሞት መብዛት ማለት ይህ ነው፡፡ የቅንጣቷም ምሳሌ ከዚህ ጋር የተገናዘበ ነው፡፡
ለአንድ ገበሬ አንዲት የስንዴ ቅንጣት አሳይታችሁት ይህች ምንድን ናት? ብትሉት አንዲት ፍሬ ስንዴ ሳይሆን ዘር ናት ይላችኋል፡፡ እርሱ ባለሙያ ስለሆነ በመሬት ላይ ብትጣልና ብትሞት ብዙ እንደምታፈራ ያውቃልና፡፡ እግዚአብሔርም “ሊቀ ማእምራን” ስለሆነ እኛ ለመኖር ብንሞት በውስጣችን ብዙ ፍሬ እንዳለ ያውቃል፡፡ “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖች ሁሉ አንድስ እንኳ ሳይኖር በመጽሐፍ ተጻፈ” /መዝ.138÷6/፡፡ ማንኛውም ሥራ ከመሠራቱ በፊት በሠሪው ዘንድ ያለቀና የተጨረሰ ማንነት አለው፡፡ የሰው ልጅም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በፈጠረው በእግዚአብሔር ዘንድ መጨረሻው የታየና የተመዘገበ ነው፡፡ አንዳንዶች “እግዚአብሔር እኔን አያውቀኝም” ቢሉም እነርሱ እንደሚያውቃቸው አለማወቃቸው እንጂ እንኳንስ የሰውን ልጅ እርሱ የማያውቀው ቅጠል እንኳን አልበቀለም፡፡
በአንድ ወቅት አምላካችን እግዚአብሔርና አበ ብዙኃን አብርሃም በሐሳብ አልተገናኙም ነበር፡፡ አብርሃም ስለ አንድ ልጅ ሲያወራ እግዚአብሔር ደግሞ ሊቆጠር ስለማይችል ሕዝብ ይነግረዋል፡፡ አብርሃም የሚያውቀው ባዶነቱን ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በውስጡ ዘር እንዳለ ያውቃል፡፡ ልዩነትን ልብ አልን ይሆን? ለዚህ ነው “ለእናንተ የማስባትን ሐሳብ እኔ አውቃለሁ” የሚለን /ኤር.23÷11/፡፡ በኃጢአት በመበላሸታችሁ፣ ሰው መሆን ባለመቻላችሁ እናንተም ሌሎች ተስፋ በእናንተ እናንተም በሌሎች ተስፋ ቆርጣችሁ ይሆን? የወዳጅ ክዳት፣ የሥጋ ለባሽ ክፋት አንገት አስደፍቷችሁ ይሆን? ነገር ግን ይህ ሁሉ የደረሰባችሁ በግል ጉዳያችሁ ወይስ ለሌሎች በምትከፍሉት መሥዋዕትነት ይሆን? እውነታው ደግሞ ለሌላው የሚተርፍ ማንነት ከሌለን ለራስ ብቻ መኖርም ሆነ መሞት ትርጕም የለውም፡፡
ከእኛ የሚያንሰው የስንዴ ቅንጣት በመሞት ዘሩን የሚያበዛ ከሆነ እኛማ ይልቁን እንዴት? በእርግጥም መብዛት መሞትን ይጠይቃል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ስለ ጌታችን ቤዛነት ሲናገር “ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው /ኢሳ.53÷10/፡፡ ራሱ ባለቤቱ “እኔ ሕይወት እንድሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” ብሏል /ዮሐ.10÷10/፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ሕይወቷን ለኃጥአን ነፍስ ቤዛ ይሆን ዘንድ መስጠቷን (ማረፏን) በተመለከተ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰላምታው ላይ “ወልድኪ ነፍሳተ ሶበ አርአየኪ በእሳተ ኵነኔ ዘሐሙ፣ ማርያም ትብሊ በእንቲአሆሙ፣ ቅትለኒ ለቤዛሆሙ ሰላም ለኪ፤ ልጅሽ በፍርድ እሳት መከራ የሚቀበሉትን ነፍሳት ባሳየሽ ጊዜ ሰላምታ የተገባሽ ማርያም ሆይ ለምትካቸው ስለእነርሱ እኔን ግደለኝ ትይዋለሽ” በማለት ለሌላው የሚተርፍ ማንነቷን ተናግሯል፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ የኖረበት የኑሮ ደረጃ ወገኖቹ ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡ እርሱ በመኳንንት ወግ፣ በቤተ መንግሥት ችግር የሚባል ነገር ሳይነካው፣ ግፍ የሚባል ነገር ሳይደርስበት፣ መብቱ በሚገባ ተጠብቆ፣ ከቅንጦትና ከድሎት አንዳች ነገር ሳይጎድልበት፣ የፈርዖን ልጅ እየተባለ የኖረ ሰው ነበር፡፡ በተቃራኒው ግን ወገኖቹ ሰው ሊደርስበት የሚችለውን የመጨረሻ መከራ እየተቀበሉ፣ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ ህልውናቸው በሌሎች ፈቃድ እየተወሰነ፣ ፈንግል እንደ ያዘው ዶሮ ሞታቸው የሰዓታት ጉዳይ እየሆነ መኖር ራሱ ቅጣት ሆኖባቸው ነበር፡፡ ሙሴ ግን ምንም እንኳ ንጉሣዊ ሕይወትን ቢያጣጥምም ከወገኖቹ ጋር ለመሞት ወሰነ፡፡ ስለዚህም ዐርባ ዓመት ሙሉ ከኖረበት ምቹ ቤተ መንግሥት ወጥቶ የእስራኤላውያንን የድኅነት መንደር ተቀላቀለ፡፡ “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፡፡ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ እግዚአብሔር መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና፣ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልከቷልና” /ዕብ.11÷24-26/፡፡
እኛ የሙሴን ታሪክ በጣዕም እንተርካለን፡፡ የሙሴን ሕይወት ግን መኖር ይከብደናል፡፡ ሙሴ ቤተ መንግሥት እንደተወ እንናገራለን፡፡ እኛ ግን እንኳን ጥቅማችንን የሚጎዳንን ኃጢአት መተው አንፈልግም፡፡ ታላቁ ባለ ቅኔ መንግሥቱ ለማ “የተለመደ ነው የመጣ ከጥንት፣ ከተጠቂው መራቅ አጥቂን መጠጋት” እንዳሉት የሀብታም፣ የባለሥልጣን፣ የታዋቂ ሰው ወገን፣ ዘመድ መባል ከጥንትም የነበረ ነው፡፡ አጥቂው ወገን ሆኖ ከተጠቂው ጋር መቆም፣ የተከበረ ወገን ሆኖ ከተዋረዱት ጋር መሰለፍ፣ ከባለ ሥልጣን ወገን ሆኖ ከተራው ሕዝብ ጋር መሰለፍ ግን እንደ አልማዝ ብርቅ የሆነ ነገር ነው፡፡ ይህ ዓለም ሞተንም የሚያልፍ፣ ቆመንም የሚያልፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር በዕለቱ ሲጠራንና ሥራችንን ፈጽመን ስንሄድ ግን ሞት የሠርግ ያህል ነው፡፡ “ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና”፡፡ /መዝ.62÷3/፡፡ ምሕረት ያለው ሞትን ነው፣ ሁላችንም እንሚገባን አዳም በበደለ ጊዜ ወደዚህ ዓለም የተላከው ለግዞት ነው፡፡ ሰው በሞት ሲጠራ ምሕረት ተደረገለት ማለት ነው፡፡
ቅዱሳን ሁሉ በዚህ ዓም ላይ ስመ እግዚአብሔር ሲዘለፍ፣ ሃይማኖት ሲነቀፍ እና ሥርዓት ሲዛነፍ ዝም ባለማለታቸው በከሃድያንና በዐላውያን ነገሥታት የተገረፉት፣ የቆሰሉት እና የሞቱት ይህን እውነት ምርኩዝ በማድረጋቸው እንጂ እንዲሁ ያለ ዋጋ አይደለም፡፡ “አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፣ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” /2ኛ.ቆሮ.6÷8-10/፡፡ ሰዎች የሚሉንን እግዚአብሔር ስለማይለን በዚህ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እርሱ የሚወደን በራሱ ፈቃድ እንጂ በሰዎች ፍቅር ላይ ተመሥርቶ አይደለምና፡፡ እግዚአብሔርን ብቻ ምስክርና ደጋፊ አድርጎ ለሐሰት ሞቶ ለእውነት መኖር “መብዛት” ነው፡፡
በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ጠርጡለስ በዘመኑ የነበሩ አላውያን ነገሥታት ያደርጉት የነበረውን የጭካኔ ተግባር በተመለከት ባስተማረው ትምህርቱ ላይ “አሰቃዩን፣ ስቀሉን፣ ንቀፉን፣ ኮንኑን፣ አቃጥሉን፣ የእናንተ ክፋት ግፍና ጭካኔ የኛ ንጽሕና ማረጋገጫ ነው፡፡ እናንተ በወገራችሁንና በቆረጣችሁን ቁጥራችን እልፍ ይሆናል፤ የሰማዕታት ደም የክርስቲያኖች ዘር ነው” እንዳለው ቅዱሳን ሰማዕታት በሕይወት ሳሉ ከሚያስተምሩትና ወደ ክርስትና እምነት ከሚያስገቡት የሰው ብዛት ይልቅ በመሞታቸው የሚማርኩት ይበልጣል፡፡ የችግራችንን ብዛት፣ የስብራታችንን ጽናት ያዩ ሁሉ አሁንስ አይኖሩም ብለው ተስፋ ቆርጠውብን ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሚኖሩ የሚመስሉትን ሙታን የምናጽናና፣ የተፍገመገሙትን የምንደግፍ፣ ሕይወት ለመረረባቸው የምናጣፍጥ ነን፡፡ ሞተው ይቀራሉ ስንባል ተነሥተን እንለመልማለን፡፡ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ብዙዎቹን እናፈራለን፡፡ ደክመን ማበርታታችን፣ ዝለን ማሳደዳችን፣ የሚታይ ነገር ሳይኖረን ሁሉን ገንዘብ ማድረጋችን ለዚህ እውነት ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ለማግኘት መልፋት፣ ለማሸነፍም መሸነፍ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለመኖርም መሞት ያስፈልጋል፡፡ እየሞቱ ማነስ እንዳለ ሁሉ እየሞቱ መብዛትም አለና፡፡
ገበሬ በጭቃ፣ በማጥ፣ በዶፍ ውስጥ ሰኔ ላይ ዘሩን ይዘራል፡፡ ነፋስ፣ ብርሃን፣ መኸር የሞላበት የጥርን ወር እያየ ይታገሣል፡፡ ስንዴውም ሆነ ሌላ የእህል አይነት የሚዘራው በስብሶ እንዲቀር ሳይሆን እንዲበዛ ነው፡፡ ዘሩ ጭቃ ላይ ወድቆ ከበሰበሰ በኋላ ብዙ ሆኖ ይበቅላላ፡፡ የሰው ልጅም ፈተና ላይ የሚወድቀውም ሆነ የሚሞተው ወድቆ ወይም ሞቶ ለመቅረት ሳይሆን በሞቱ ለመብዛት ነው፡፡ ጭቃን የተጸየፈ ገበሬ መኸር እደሌለው ሁሉ መከራን የተሰቀቀ ክርስቲያንም ሕይወት የለውም፡፡ ክርስትና ጣዕም የሚኖረው በመከራ እሳት ሲጠበስ ነውና፡፡ እኛም የክርስቶስን ክብር ብቻ ሳይሆን ሞቱንም ልንካፈል ተጠርተናል፡፡ቅዱስ አውግስጢኖስም “የክርስቶስን ትምህርትና ሕይወት የማይቀበል ሰው ክርስቲያን ነኝ አይበል” በማለት ክርስቶስን ባስተማረው ትምህርትና በሕይወቱ መምሰል እንደሚገባን ይጠቁመናል፡፡ “በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ” /ፊልጵ.3÷11/፡፡ ይኸውም እውነተኛ እምነታችን የሚፈተንበትና በእርሱ የማመናችን ምልክት ነው፡፡ ቸሩ አምላካችን እስከ ሞት ድረስ የታመንን ሆነን የብዙዎች መኖሪያ የሆነችውን መንግሥቱን እድንወርስ ይርዳን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከአባ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ
አዲስ አበባ