እውቀትና ጥበብ መገኛው ከእግዚአብሔር ነው!!
ማስተዋልን አብልጦ የሰጠው ለሰሎሞን ነው፡፡ ይህንም የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ፡፡ 1ኛ ነገ. 3÷4-12
ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሚታየው ንጉሥ ሰሎሞንን የሚያክል ማንም አዋቂና ብልህ ሰው የለም፡፡ ከእርሱም በፊት አልነበረም፡፡ ከእርሱም በኋላ አልተነሳም፡፡ ወደ ፊትም አይነሳም፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንን የሚበልጠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የሚበልጠው አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ አምላክ በመሆኑ ሁሉን ያውቃል፡፡ ሰሎሞን ግን ፍጡር ነውና ሁሉን ማወቅ አይችልም፡፡ ክርስቶስ ከሰሎሞን እንደሚበልጥ የተናገረውም ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡
ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ተውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፡፡ የሰሎሞንም ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፡፡ እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ ማቴ. 12÷42
መንፈሳዊ ፍልስፍና የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል በመከተል እውቀትን፤ ማስተዋልን፤ ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር እንደሆነ ሲያስተምር የሥጋዊ ፍልስፍና ሐሳብ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሥጋዊ ፍልስፍና በመጀመሪያ እንዲህ አይነቱን ከፍ ብሎ በተጠቀሰው የቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሰፈረውን ታሪክ እውነት ነው ብሎ አይቀበለውም፡፡ የተነገረው የታሪክ ከቶ አልተፈጸመም በማለት እንደ ልብ ወለድ ታሪክ ሊመለከተው ይፈልጋል፡፡ ስለ ፈርኦንና ስለ ናቡከደነፆር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የታጻፈው ታሪክ እውነት ቢሆን ኖሮ ይላል ሥጋዊ ፍልስፍና የግብፅና የባቢሎን ታሪክ ጸሐፊዎች በመዘገቡት ነበር፡፡ ስለሌላው ሁሉ ነገር ሲጽፍ ይህኛውን የሚተውበት ምክንያት አይኖርም ነበር በማለት ሥጋዊ ፍልስፍና ታሪኩን ያናንቀዋል፡፡ የተባሉት ነገሥታት ያን የመሰለ ሕልም አልመው ነበር ተብሎ ቢታመንበት እንኳ ይላል ሥጋዊ ፍልስፍና ሕልማቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ማያያዙ ስሕተት ነው ይላል፡፡ ሁለቱም ነገሥታት ስለ መንግሥታቸው እድሜ አዘውትረው እስካሰቡት አንዳንድ ስጋትም እስከ ደረሰባቸው ድረስ ተኝተው የሚያስፈራ ሕልም በእንቅልፍ ልቡናቸው ሊመጣባቸው ይችላል ይላል፡፡ ሕልማቸውንም ለማስፈታት ፈልገው በሀገሩ ውስጥ ላሉት ሕልም ተርጓሚዎችና ጠቢባን ሕልማቸውን ቢነግሯቸውና እነዚህም ሕልሙን መፍታት ቢሳናቸው ይህን ማድረግ ያልቻሉና ምስጢሩ ከእግዚአብሔር የሚገለጥላቸው ሌሎች ሰዎች ስላሉ ነው ወደሚለው ሐሳብ እንድንሄድ አያደርገንም ይላል፡፡ የግብፅና የባቢሎን ሕልም ተርጓሚዎችና ጠቢባን ለማግኘት ያልቻሉትን የሕልም ትርጉም ዮሴፍና ዳንኤል አገኙት ቢባል እንኳ ከቀሩት የተሻሉ ሆነው ተገኙ ወይም በዚያ በተወሰነ ሕልም ላይ እንዳጋጣሚ ሆኖ የፍችው ሐሳብ ስለመጣላቸው ፈጸሙት ይባላል እንጂ የተለየ ኃይል ስለወረደላቸው ፈጸሙት ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይሆናል በማለት ያናንቀዋል፡፡ ሕልም በአጠቃላይ በቀን ሲያስቡት ሲመኙት ወይም ሲፈሩት ከነበረ ነገር ላይ የሚነሳ ስለሆነ የተባሉት ነገሥታት ሕልምም ሆነ የሌላ ሰውሕልም ከዚህ የተለየ ትርጒም ሊሰጠው አያስፈልግም ሲል ይከራከራል፡፡
ሥጋዊ ፍልስፍናንና መንፈሳዊ ፍልስፍናን የሚያጋጨው ሌላም ጥያቄ አለ፡፡ እውቀትና ጥበብ ምን አገልግሎት መስጠት አለበት? እውነተኛ እውቀትንና ጥበብን ከሐሰተኛ እውቀትና ጥበብ የሚለየው ምንድን ነው? በሌላ አነጋገር አንደኛውን ከሌላው ለመለየት የምንጠቀምበት መስፈርት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ ሁለቱን ፍልስፍናዎች ይለያቸዋል፡፡ ከሥጋዊ ፍልስፍና አንፃር እውቀት ጥበብ ሰዎችን ለሥጋዊ ሕይወታቸው ከሚያስገኝላቸው ጥቅም ያለፈ ሌላ የሚፈለግበት ነገር የለም፡፡ እውነት ሰዎችን ያበላቸዋል ያኖራቸዋል፡፡ ለችግራቸውም መፍትሔ እንዲያገኙለት ይረዳቸዋል፡፡ ይህን ካደረገ ሥራውን ተወጥቷል በአንፃሩ እንደ መንፈሳዊ ፍልስፍና አካሄድ እውቀት ጥበብ ሰውን ከዚህም በላይ ማገልገል አለበት እንደ መንፈሳዊ ፍልስፍና አቋም እውቀት ጥበብ ማስተዋል በሰው ልቡና ውስጥ መንፈሳዊ አስተሳሰብን ማነፅ መቻል አለበት፡፡ በመንፈሳዊ ፍልስፍና አካሄድ እውቀት ጥበብ ሰውን በፀባዩና በአስተሳሰቡ ከበፊቱ ጊዜ የተሻለ ሰው ሊያደርገው መቻል ይኖርበታል፡፡ መንፈሳዊ ፍልስፍና ከሁሉም በፊት የፈሪሃ እግዚአብሔርን ስሜት በአንደኛ ደረጃ ያስቀምጠዋል ይህን ስሜት ለመፍጠርና ለማዳበርም እውቀት ጥበብ በመንፈሳዊ ፍልስፍና ዐይን እውቀትና ጥበብ ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍልስፍና ከዚህ ላይ ኦሪታዊና ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ለተባለው ሐሳብ በማስረጃነት ከቅዱሳት መጻሕፍት የሚጠቅሳቸው ቃሎች ይጠቀሳሉ፡-
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ ምሳ. 1÷7 ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር አምላክ የለም ይላል፡፡ መዝ. 13÷1
በመንፈሳዊ ፍልስፍና መሠረት እውነተኛ እውቀትና ጥበብ የሚገለጥበት ሌላም መንገድ አለ፡፡ እውነተኛ እውቀትና ጥበብ ሰውን አስተዋይ ያደርገዋል፡፡ ልቡና ይሰጠዋል፡፡ በሚደርስበት ክፉ ነገር ሁሉ እንዲታገስ ብርታት ይሰጠዋል፡፡ ከአንደበቱ ክፉ ቃል እንደይወጣ ይጠብቀዋል አሁንም መንፈሳዊ ፍልስፍና (ኦሪታዊና ክርስቲያናዊ ፍልስፍና) ይህን ሐሳብ የሚያጠናክርባቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች የሰነፍ ሰው ቊጣ ቶሎ ይታወቃል ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል መጽ. ምሳ. 12÷16 ቊጡ ሰው በስንፍና ይሠራል አስተዋይ ግን ይታገሣል መጽ. ምሳ. 14÷17
ሰውን ጠቢብ አእምሮ ከቁጣ ያዘገየዋል፡፡ ምሳ. 9÷11 ሰነፍ ሰው ቁጣውን ሁሉ ይናገረዋል ጠቢብ ግን በልቡ ያስቀረዋል መጽ. ምሳ 29÷11
እውነተኛ እውቀትና ጥበብ እንደ መንፈሳዊ ፍልስፍና መንገድ ሌላም የሚለይበት ጠባይ አለው የአዋቂዎችንና የመልካም ሰዎችን ምክርና ትዕዛዝ ለመስማትና ለመፈጸም ለሰው ልቡና ይሰጠዋል፡፡ በአንፃሩ ማስተዋልና ጥበብ በልቡ ያልሠረጸው ሰው የነዚህን ሰዎች ምክር ይንቃል፡፡ ትዕዛዛቸውንም እሺ ብሎ አይቀበልም፡፡
በልቡ ጠቢብ የሆነ ሰው ምክርም ትዕዛዝም ይቀበላል መጽ. ምሳ. 10÷8 የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል ምሳ. 12÷15 ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድም ወደ ጠቢባንም አይሄድም መጽ. ምሳ. 15÷12 ምክር በሰው ልብ እንደጠሊቅ ውኃ ነው፡፡
አእምሮ ያለው ሰው ግን መልካሙን ሁሉ ይቀዳዋል (መጽ. ምሳ. 20÷5) ያስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች፡፡ ምሳ. 18÷15 ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሳፅን ይንቃሉ፡፡ ምሳ. 1÷7
ከዚህ በላይ ለተጠቀሰው በቅዱስ መጽሐፍ ላይ ስለተመሠረተው መንፈሳዊ ፍልስፍና ሥጋዊ ፍልስፍና በበኩሉ ምን መልስ አለው የሚለውን ጥያቄ አንስተን እንመልከት ቅዱስ መጽሐፍና መንፈሳዊ ፍልስፍና ለእውቀትና ለጥበብ እግዚአብሔርን መፍራት ሰውን ማክበር ትዕግስተኛ መሆንና የመሳሰለውን እንደመስፈርት አድርገው የሚጠቅሱትን ሐሳብ ሥጋዊ ፍልስፍና አይስማማበትም፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት፤ ሰውን ማክበርና የመሳሰለው የሃይማኖትና የምግባር ጥያቄ እንጂ የእውቀት፤ የጥበብና የችሎታ ጥያቄ አይደለም ይላል፡፡ አንድ ሰው በጎ ጠባይና ምግባር ስላለው ብቻ እውቀትና ችሎታ አለው ብሎ መደምደም ስሕተት ነው ሲል ይከራከራል፡፡ በአንዳሩ ሌላው ሰው ክፉ ፀባይና ምግባር ስላለው ብቻ እውቀትና ክህሎት እንደሌለው አደርጎ ማሰብ አይቻልም ይላል፡፡ አንድን የሒሳብ ወይም የፍልስፍና ጥያቄ ለመፍታት ሲፈለግ ለዚህ የሚያስፈልገው ሃይማኖትና ምግባር ሳይሆን ትምህርት፤ እውቀት፤ ችሎታ ነው ይላል፡፡ ትሑት መሆን፤ ትዕግሥተኛ መሆን እግዚአብሔርን መፍራት ባጭሩ መንፈሳዊነት ስለተባለው ጥያቄ መልስ ግኝት አንዳችም የሚሰጠው ጥቅም የለውም ይላል፡፡ መንፈሳዊ ሰው መሆን ጥያቄውን እንድትፈታ አያስችልህም፡፡ ጥያቄውን ለመፍታት ከቻልክም ይህ የተሳካልህ መንፈሳዊ ሰው ስለሆንክ ሳይሆን ችሎታ ስላለህ ብቻ ነው ይላል፡፡
በአንጻሩ ክፉ ፀባይንና ምግባርን ማሳየት ከእውቀትና ከማስተዋል እጥረት እንደመጣ አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው ሲል አሁንም ሥጋዊ ፍልስፍና አጥብቆ ይከራከራል፡፡ ክፉ ፀባይና በጎ ፀባይ ስለ አንድ ሰው እውቀትና ችሎታ ምንም የሚገልፀው ነገር የለም ይላል፡፡ በአንድ በኩል በጎ ፀባይና ምግባር በሌላ በኩል እውቀት ፀባይና ችሎታ እንዲሁም ክፉ ፀባይና ምግባር በንድ በኩል እውቀትና ሙያ የለሽ መሆን በሌላ በኩል ሁለት የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ አንደኛው ከሌላው ጋር መነጻጻርና መደባለቅ እንደሌለበት ሥጋዊ ፍልስፍና ያስገነዝባል፡፡ ሁለቱ ነገሮች የተለያዩ በመሆናቸው ምክንያት አንድ ሰው በፀባዩና በምግባሩ ክፉ ሆኖ ሳለ በጣም አዋቂና ጠቢብ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል ይላል፡፡ በአንጻሩ፤ ቀና በጎ መንፈሳዊ ሰው ሆኖ ሳለ እውቀትና ችሎታ የሚጎድለው ገልቱ ሰው ሊሆን ይችላል በማለት ይከራከራል፡፡ አዋቂዎችና ጠቢባን ሆነው ሳሉ በጠባያቸውና በምግባራቸው ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ሰካራሞች፣ አመንዝራዎች፣ ከሃዲዎች ወዘተ… የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ ይላል፡፡ በአንጻሩ እውቀትና ችሎታ የሌላቸው ሆነው ሳሉ በጠባያቸውና በምግባራቸው ቀናዎች፣ ትሑታን፣ ሰው አክባሪዎች፣ ደጋግ ሰዎች ሞልተዋል ይላል፡፡
ሥጋዊ ፍልስፍና ከመንፈሳዊ ፍልስፍና ጋር ከብዙ ቦታ ላይ የማይጣጣም ሐሳብ እንዳለው በማየት ቅዱስ ጳውሎስ አጥብቆ ይነቅፈዋል፡፡ ለፍልስፍናው መጠሪያ አድርጎ የሚጠቀምባቸው ቃሎች ዋንኞችም የዚህ ዓለም ጥበብ፣ የሰው ጥበብ፣ የጥበቦች ጥበብ፣ የአስተዋዮች ማስተዋል፣ የሚያባብል ጥበብ፣ ከንቱ ጥበብ የሚሉት ናቸው፡፡ በአንጻሩ መንፈሳዊ ፍልስፍና የክርስቲያን ሃይማኖትንና በእሱም ላይ የተመሠረተውን፣ በእሱም ላይ የተመሠረተውን ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ማለት ነው) የእግዚአብሔር ጥበብ ነው ሲል ይጠቅሰዋል 1ኛ ቆሮ. 1÷18-27/2፥8÷3 -18÷20)፡፡
ሐዋርያው ሥጋዊ ፍልስፍናን ሥጋዊ እውቀትንና ጥበብን ሲያወግዝ በተለይ በሀሳብ ውስጥ ያለው የግሪኮች ፍልስፍና ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የግኖስቲክ ፍልስፍና ዋንኛው ነው፡፡ ሐዋርያው የግሪክች ፈላስፎችንና መምህራንን አፍራሽ አመለካከት በምሬት ያስታውሰዋል፡፡ በተለይም ክርስቶስን ላለመበቀል ባሳዩት ግትር አቋማቸው ምክንያት በጽኑዕ ነቅፏቸዋል፡፡ በወቅቱ የነበረውንም ሥጋዊ እውቀትንና ጥበብን ከመንፈሳዊ እውቀትና ጥበብ ጋር እያነጻጻረ በሰፊው የተናገረው ቃል ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ የዚህም ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፣ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ብሎ ተጽፏልና፡፡ ጥበበኛ የትታለ ጸሐፊስ የትአለ የዚህች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበቧ ስላላወቀችው በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗልና፡፡ መቼም አይሁድ ምልክትን ይሻሉ፡፡ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይለምናሉ፡፡ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይኽም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፡፡ ለተጠሩት ግን አይሁድ ቢሆኑም የግሪክ ሰዎችን ቢሆኑም የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሚሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና 1ኛ. ቆሮ. 1÷18-25
እኔም ወንድሞቼ ሆይ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ በእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርኩ አልመጣሁም፡፡ በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና፡፡
እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበር እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን ቃሌም ስብከቴም መንፈስና ኃይልን በመግለጥ ነበር እንጂ፡፡
በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም፡፡ በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም፡፡ የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምስጢር እንናገራለን ከዚች ዓለም ገዢዎች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፡፡ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፡፡ 1ኛ. ቆሮ. 2÷1-8 ማንም እራሱን አያታልል ከናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና በእርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ ደግሞ ጌታ የጥበበኞችን ሃሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፏልና 1ኛ. ቆሮ. 3÷18-20
ሐዋርያው ስለዚህ ዓለም ጥበበኞች የሃሳብ ከንቱነት ሲናገር በብሉይ ኪዳን የተጻፈውን በማስመልከት የተጠቀሰው ሓሳብ ሲሆን ቃሉም በትንቢተ ኢሳያስ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል የሚመለከት ነው፡፡ ቃሉም ራሱ እግዚአብሔር በነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ አፍ የተነገረው ቃል ነው፡፡
ሁሉን የፈጠርኩ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ? የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፡፡ የሟርተኞችንም አሳብ …… ፡፡ ጥበበኞችቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ፡፡ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ ኢሳ. 44÷24-25
በሃይማኖት በመንፈሳዊ ፍልስፍና ውስጥ የእሞቱ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የሃይማኖቱና ፍልስፍናው የተሳሰሩ ስለመሆናቸው፡፡
በመግቢያው ላይ ስለ ፍልስፍና አከፋፈል አንስተን ስንናገር ፍልስፍና ከሁለት ቦታ ሊከፈል ይችላል በአንድ በኩል ስለ ሥጋዊ ፍልስፍና በሌላ በኩል ስለ መንፈሳዊ ፍልስፍና መናገር እንደሚቻል ተመልክቶአል፡፡
አንደኛው ዓይነት ፍልስፍና መንፈሳዊ ፍልስፍና ሊባል የቻለበት ምክንያት በሃይማኖት ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ሃይማኖታዊ ጠባይ ያለው በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑም መጠን ሃይማኖት የሚሰብከው ሐሳብ ሁሉ በራሱ በፍልስፍናው ውስጥ ይንፀባረቃል፡፡ ይህ ስለሆነም በመንፈሳዊ ፍልስፍና ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት መናገር ዐቢይ ቦታ አለው፡፡ በመንፈሳዊ ፍልስፍና ውስጥ የሰው በጎነት እና ድኅነት የሚገኘው ለእግዚአብሔር ታዛዥ በመሆን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚሄድ ሥራ በጎ ሥራ ሲሆን ከዚህ የወጣ ሥራ ግን ክፉ ሥራ መሆኑንና በእግዚአብሔርም ዘንድ ያስቀጣል፡፡