Archives

All posts for the month August, 2016

እግዚአብሔር ሰውን አክብሮና አልቆ በመልኩ በምሳሌው ፈጠረው፡፡ ሰው ግን እግዚአብሔር ባስቀመጠው የክብር ሥፍራ አልተገኘምና ተዋረደ፡፡፡ ከኃጢአቱም የተነሣ ደሃ ሆኗልና ሰው ሆኖ መፈጠር /መወለድ/ የምሬት ርእስ ሆነ፡፡ ሁሉን አይቶ ሁሉን ማጣት የሰው ልጅ የማይለምደው የኑሮ ጥቁር መልኩ ነው፡፡ ሁሉን ያጣ ሁሉን ሲያገኝ የዕድገት ሕግ ያለው፣ የሚናፈቅ ደስታና ሊተርኩት የሚያስቸኩል የኑሮ ገድል ነው፡፡ ሁሉን አይቶ ሁሉን ማጣት ግን የሚያንደረድር የቁልቁለት ጉዞ፣ ጉልበትን እያዛለ ከዕይታ የሚሠውር፣ ልታይ ልታይ ያለውን ሰብእና ደብቁኝ የሚያሰኝ፣ የማይለምዱትና የማይደፍሩት ሥፍራ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ሀብት ጨብጣችሁ አግኝቶ እንደማያውቅ ብትቸገሩ ሌሊቱን ያመጣ ቀኑን ያመጣልና በርቱ፡፡ ሀብት በማጣታችሁ ስትበሳጩ ሀብት የማያመጣውን ጤና እንደምታጡ አስቡ፡፡ ወልዳችሁ ሞት ልጆቻችሁን ነጥቋችሁ ከሆነ ማዳን ብቻ ሳይሆን መግደልም የእግዚአብሔር ሥልጣን እንደሆነ በመረዳት ከከንቱ አእምሮ ራቁ፡፡ ሊነጋ የጨለመ እንጂ ጨልሞ ሊቀር የመሸ ሌሊት ስለሌለ በእምነታችሁ ጽኑ! ጌታችን ድል ለነሡ ሽልማት የሚሰጥ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ለወደቁትም ትንሣኤ የሚሆን አምላክ ነውና፡፡

በሥነ ፍጥረት ተመራማሪነቱ የሚደነቅ አንድ የሥነ ሕይወት ሊቅ በባሕር ዳርቻ ዳክዬዎችን እያየ ይመሰጥ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ የሚያያቸው እነዚህ ዳክዬዎች በሽታ ገባባቸውና ማለቅ ጀመሩ፡፡ እርሱም መድኃኒት ነበረውና ለማዳን ሲቀርባቸው ይሸሹታል፡፡ ከዚህም የተነሣ ዓይኑ እያየ፣ መድኃኒቱንም በእጁ እንደጨበጠ ዳክዬዎቹ  በሙሉ አለቁ፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ ‹‹ዳክዬ ብሆን ዳክዬዎቹን አድናቸው ነበር›› ብሎ ቁጭቱን ተናገረ ይባላል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ባልሆንኩ ለሚሉት የሰውነትን ዋጋ ሊገልጥ፣ ሰው የለኝም ለሚሉት ጥሩ ሰዋቸው ሊሆን፣ ሰው በሆንኩ ለሚሉትም ሰው ሊያደርጋቸው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ፣ ሰውነታችንን ተዋሕዶ ሰው ሆነ፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ . . .  ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ››  እንዲል /ዮሐ.1÷1/፡፡

ይኸውም እኛን ከሞት አድኖ የሕይወትን ትንሣኤ ሊሰጠን ነው፡፡ ከጌታችን ሰው መሆን በፊት የነበሩ ጻድቃን ሰዎች ቢኖሩም ከጠባያቸው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮአቸውም በውርስ ኃጢአት ስለተያዙ /ከእመቤታችን በቀር/ እኛን ሊያድኑን አልቻሉም ነበርና፡፡ ሊቁ አቡሊደስ ‹‹ከሰው ወገን ማንም ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር፣ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲዖል ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው?  ብሎ እንደተናገረ /መዝ.8÷8/፡፡ ራሱን ማዳን ያልቻለው ሌላውን ማዳን እንደምን ይችላል? አንድ ራሱን ሊያድን ያልቻለስ ዓለምን ሁሉ ሊያድን እንደምን ይችላል? ኃጢአት በሰው አድሮ ይኖር ነበርና፤ ሞትም ይከተለው ነበርና/መዝ.8÷9/ ብሏል /ሃይ.አበው ገጽ 145/፡፡

የሠለጠነው ዓለም እንኳ ሰውን በቤተ ሙከራ ለመፍጠር ሲያስብ የሞት ማስወገጃን ለመሥራት ግን ዕቅድ እንኳን የለውም፡፡ ለምን? ቢባል የንጉሡም የምሁሩም አእምሮ ሞትን የሚገዛ ሳይሆን ለሞት የተገዛ ነውና፡፡ ሞት ሁለት ዓይነት መልክ አለው፡፡ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየትና የነፍስ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት የሚሉት ናቸው፡፡ የሰው ትልቁ ሞት ሕይወት ከሆነው ከእግዚአብሔር አንድነት መለየቱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወተ ሥጋ ያሉትን ኃጢአተኞች ‹‹ሙታን›› በማለት የሚጠራቸው ለዚህ ነው /ኤፌ.2÷1/፡፡ መንፈሱ የሞተ ሰው ከእግዚአብሔር  ጋር ያለውን አንድነት ያፈረሰ በመሆኑ የባከነ ሕይወት ይኖራል፡፡ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይም ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ፊት በእሳት ባሕር ይጣላል፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ አምነው በሕግ በአምልኮ እርሱን የተከተለ፣ በክርስቲያናዊ ምግባር እርሱን የመሰለ ግን ይህ የሞት ኃይል በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተጽፎ እንደምናገኘው ሞት ለብዙ ዘመናት ኤልያስን አሳዶት ነበርና ሞትን ከለመኑት መካከል አንዱ ነው፡፡ /2ኛ ነገ.4÷35/፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኤልያስ ሞትን አቅም አሳጥቶታል/1ኛ ነገ.17÷22/፡፡ በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር መንግimage-0-02-01-2980bbe6bd90ef23328b91120246b672dbccccf83b98515d72bd86c86eb77c32-Vሥቱን በማስፋፋት ውስጥ ትልቅ ድርሻ (ሓላፊነትን) የተጣለባቸው እነ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም በተሰጣቸው የጸጋ ሥልጣን በሞት ላይ መራመድና ሙታንን ማስነሣት ችለዋል /ሐዋ.5÷1-11፣9÷40/፡፡ ታዲያ በጸጋ ያደረባቸው ቅዱሳን ከጌታችን ተአምር ጋር የሚነጻጸር ይህን ያህል ድንቅ ነገር ካደረጉ በማይወሰነው ፍጹም አካሉ እርሱ ባወቀው ድንቅ ጥበቡ ያደረባት እመቤታችንማ ተአምሯ እንዴት ከዚህ አይልቅ? የእርሷ ሞትና ትንሣኤ ከልጅዋ ሞትና ትንሣኤ ጋር ይነጻጸራል ቢባልስ ምን ይደንቃል? ዳሩ ግን በዕውቀት /በመረጃ/ ያልታገዘ እምነት ጠቀሜታው አመርቂ አይደለምና የጌታችንና የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ ሲነጻጸር /የሚመሳሰልበትንና የማይመሳሰልበትን ምክንያት/ በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡ እመብርሃን ምሥጢሩን ትግለጥልን፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥድሳ አራት ዓመቷ በእግዚአብሔር ፈቃድ ጥር ሃያ አንድ ቀን ዐርፋለች፡፡ ሐዋርያትም ሥጋዋን ገንዘው ተሸክመው ሊቀብሩ ሲወስዱ አይሁድ አይተው ለምቀኝነት አያርፉምና ቀድሞ ልጇን ከመቃብር ሰርቀው ወስደው ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ ያውኩናል፤ ዛሬ ደግሞ እናቱን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? ብለው ሥጋዋን ለማቃጠል ወሰኑ፡፡ ከዚያም ታውፋንያ የሚባለውን ሰው ከመካከላቸው መርጠው ‹‹አንተ ሂድና ሥጋዋን ከመሬት ላይ ጣለው፣ እኛም ወስደን እናቃጥለዋለን›› ብለው ላኩት፡፡ እርሱም ተደፋፍሮ ሥጋዋን ከመሬት ላይ ለመጣል አጎበሩን ሲጨብጥ የእግዚአብሔር መልአክ ተቆጥቶ ሁለት እጁን ቆርጦታል፡፡ ወዲያው የእመቤታችንን ሥጋ ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ቅዱሳን መላእክት እየዘመሩ ወደገነት አሳርገውታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም ዮሐንስ ያየውን ምሥጢር ለእነርሱም እንዲያሳያቸው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ጾም፣ ጸሎት ለማድረግ ሱባኤ ያዙ፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሐዋርያት በወረሰችው ትውፊት መሠረት ለጾመ ፍልሰታ ሥርዓት ሠርታ፣ ከሰባቱ አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መገለጫ ጾም ትጾማለች፡፡ ልክ እንደ ሐዋርያቱ የእመቤታችንን ምሥጢረ ትንሣኤና ዕርገት ይገለጥላቸው ዘንድ በመሻት ሕፃናት፣ ጎልማሶችና አረጋውያን በመንፈሳዊ መነቃቃት ሱባኤ ይገባሉ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጾማቸውን በጀመሩ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ ከገነት አምጥቶ ሰጥቷቸዋል፡፡

እነርሱም አክብረው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ ከዚያም በተቀበረች በሦስተኛ ቀኗ ተነሥታ በቅዱሳን መላእክት እና በክቡራን ሐዋርያት ዝማሬ ታጅባ ዐርጋለች፡፡ ከዚህም የተነሣ በመቅድመ ተአምረ ማርያም ላይ እንደተገለጸው አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሦስቱን በዓላቶቿን እንደ እሑድ ሰንበት እንድናከብር ሲያዝዙን የትንሣኤዋንና የዕርገቷን በዓል በተመለከተ ‹‹ወአመ 16 ለወርኃ ነሐሴ ፍልሰተ ሥጋሃ ሰዱሰ መዋዕለ ይግበሩ በዓለ ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ በነሐሴ 16 ሥጋዋ የፈለሰበት ነውና እስከ 21  ድረስ ለስድስት ቀናት እንደ ልጇ ትንሣኤ አድርገው ያክብሩ›› በማለት ሥርዓት ሠርተዋል፡፡

‹‹እንደ›› የሚለው አገባብ መመሳሰልን ለመግለጥ፣ ኃይለ ቃሉን ለማጉላት እና በአጽንኦት ክብርን ለመስጠት ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ አበበ እንደ ከበደ ጎበዝ ተማሪ ነው ብንል የአበበ ጉብዝና የከበደን ያህላል /ይመስላል/ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ምሳሌ «ዘየሐጽጽ፤ ከሚመሰልለት ነገር የሚያንስ» ቢሆንም የእመቤታችን ትንሣኤ ከጌታችን ትንሣኤ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን እንደሚያስገነዝብ ልብ ይሏል፡፡ በመሆኑም የእመቤታችንን ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ አድርገን እንድናከብር የታዘዝንበትን ምክንያት በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

ሀ. የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው በመቃብር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ቆይቶ እንደተነሣው ሁሉ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምም ሥጋ ሐዋርያት ከቀበሯት በኋላ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር ቆይታ ተነሥታለች፡፡

ለ. ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ሲነሣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በኅቱም መቃብር እንደተነሣ እመቤታችንም እንዲሁ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል በኅቱም መቃብር ተነሥታለች፡፡

ሐ. ጌታችን ሦስት ሌሊትና መዓልት በከርሠ መቃብር ሲቆይ ሥጋውን ሙስና መቃብር እንዳላገኘው ሁሉ እመቤታችንም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ስትቆይ ሥጋዋን ሙስና መቃብር ሳያገኘው ተነሥታለች፡፡

መ. ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣበት ሳምንት ማለትም እስከ ዕለተ ጰራቅሊጦስ ባሉት ቀናት ውስጥ የሚደረሰው ስብሐተ እግዚአብሔር እና የሚሰጠው ትምህርት ሁሉ በሞቱ፣ በትንሣኤው እና በዐርገቱ ላይ እንደሚያተኩረው ሁሉ እመቤታችን ከተነሣችበት ነሐሴ ዐሥራ አራት እስከ ዐሥራ ስድስት ድረስ ያው ሥርዓትና ትምህርት ስለሚከናወን ነው፡፡

ሠ. ጌታችን ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳይጠብቅ ዳግመኛ ሞት በማያስከትል በሐዲስ ሥጋ እንደተነሣ ሁሉ እመቤታችንም ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ ዳግመኛ ሞት በሌለበት በሐዲስ ሥጋ ተነሥታለች፡፡ እንዲሁም ጌታችን ወደ ሰማይ ያረገው ሞትን ድል ነሥቶ ነው፡፡ እነ ሄኖክና ኤልያስ ሲያርጉ እንዲሁ ሳይሞቱ ነው፤ እመቤታችን ግን ያረገችው እንደ ልጇ ሞት ድል ከተነሣ በኋላ ነው፡፡ ደግሞም ሄኖክና ኤልያስ ቢያርጉ ዕርገታቸው ሞት አለበት፡፡ መሬታዊ ባሕርይ ካለው ፍጥረት ሞትን የማያይ፣ የማይታመምና የማይለወጥ የለምና፡፡ ሆኖም ግን ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ ከሰው ሁሉ ምስኪኖች ይህ ምሥጢር ተሠውሮባቸው ‹‹ዛሬ እንብላ እንጠጣ ነገ እንሞታለን›› በሚል ብቻ እምነታቸውን የወሰኑ ናቸው /1ኛቆሮ.15÷33/፡፡

ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድራዊ ሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው ቅዱስ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ ‹‹ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለወሰደው አልተገኘም፡፡ ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና›› እንዲል /ዕብ.11÷5/፡፡ ይሁን እንጂ ሄኖክና መሰሎቹ በሐሳዊ መሲህ ዘመን በአካል ተገኝተው በርትዕት ሃይማኖት ክርስቲያኖች እንዲጸኑ፣ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት በመመሥከርና የመሲሑን ስሑትነት በመግለጥ በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ሄኖክ ቢያርግ የገባው ገነት ነው፤ ኤልያስም ቢያርግ የገባው ብሔረ ሕያዋን ነው፡፡ እመቤታችን ግን ብታርግ የገባችው መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕርገቷን በዜማው ‹‹እመቤታችን በክብር ወደ ሰማይ ዐረገች›› ሲል ዘምሯል፡፡ ስለዚህ ትንሣኤዋም ሆነ ዕርገቷ እንደ ልጇ መሆኑን እናምናለን፡፡

የጌታችንና የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ ሲነጻጸር ይመሳሰላል ቢባልም ግን የሚለያይበትም ምክንያት አለው፡፡ ጌታችን ከመቃብር የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አልፎ አልፎ ‹‹እግዚአብሔር አስነሣው›› የሚል ቃል ይገኛል /ሐዋ.2÷32፣3÷15፣ሮሜ.4÷24፣10÷9፣1ኛ ቆሮ.15÷15/፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቅድስት ሥላሴ በሥልጣን አንድ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው እንጂ ጌታችን እንደ ፍጡር አስነሺ የሚሻ ሆኖ አይደለም፡፡ ራሱ ባለቤቱ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አስነሣዋለሁ›› ብሏልና /ዮሐ.2÷19/፡፡ እንዲሁም «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፡፡ ስለዚህ አብ ይወድደኛል እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላስነሣት ሥልጣን አለኝ›› ብሏል /ዮሐ.10÷17-18/፡፡ ስለዚህ ጌታችን በራሱ፣ በባሕርይ አባቱ በአብ፣ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ከሙታን ተነሣ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከሙታን ተለይታ የተነሣችው በልጇ በወዳጅዋ በፈጣሪዋ በአምላኳ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን በመሆኑ አሥነሽ ትሻለች /ሽቷታል/፡፡ ጌታችን በኩረ ትንሣኤ በመሆኑ ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ሁሉ እርሱን አብነት አድርገው በእርሱ ሥልጣን ይነሣሉ፡፡ እመቤታችን ግን ከጌታችን ቀጥላ ልጇን ወዳጅዋን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጋ ተነሥታለች፡፡ ሌላው የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በፊት ከሰው ልጆች ሁሉ ቀድማ መነሣቷ ነው፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ ሰፊ ምክንያትና ትንታኔ ያለው ሲሆን ለአብነት ያህል ግን ሁለቱን እናያለን፡፡

ሀ. የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ጥበበኛው ሰሎሞን ከመዝሙራት ሁሉ በሚበልጠው መዝሙሩ ላይ ‹‹ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይትየ ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኰኵሕ ቅሩበ ጥቅም፤ ወዳጄ ሆይ፣ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግቤ ሆይ፣ ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና›› /መኃ.2÷14/ ሲል አባቱ ዳዊት ደግሞ ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› ብሎ ነበር /መዝ.131÷8/፡፡

አቤቱ ክርስቶስ ሆይ! ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት  በከርሠ መቃብር አድረህ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል በኅቱም መቃብር በራስህ፣ በአባትህና በሕይወትህ ሥልጣን ከሙታን ተለይተህ ለምእመናን ትንሣኤ /ዕርገትን/ ወደምትሰጥበት ወደ መንግሥተ ሰማያት ተነሣ፡፡ አንተ ብቻህን አይደለም፤ የመቅደስህ ታቦት ማለት የሰውነትህ ማደሪያ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስን ተዋሕደህ ፍጹም ሰው ሆነህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አንተ ጽላት ማኅፀኗን ታቦት አድርገህ ያደርክባት ቅድስት እናትህ ድንግል ማርያም ሌሎች በትንሣኤ ዘጉባኤ እንደሚሉት ማለትም መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል በኅቱም መቃብር በአንተ ሥልጣን ተነሣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ከጌታችን ቀጥላ ዳግም ምጽአትን ሳትጠብቅ ተነሥታለች፡፡

ለ. የአዳም ዘር በሙሉ በዚህ ዓለም ለሠራው ደግም ሆነ ክፉ ሥራ ዋጋውን ለመቀበል በጌታችን ፊት ይቆማል /እንቆማለን/፡፡ ‹‹ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን»፤ ‹‹መልካምም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ እያንዳንዱ በሥጋው የሠራውን ብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል›› እንዲል /ሮሜ.14.10፣2ኛቆሮ.5.10/፡፡ እመቤታችን ግን የፈራጁ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ በመሆኗ፣ ክብሯም ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ስለሆነ በልጇ የፍርድ ወንበር ፊት አትቆምም፡፡ ስለዚህ እርስዋ ለአምላክ እናትነት የተመረጠችና የከበረች ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ እንተ አልባቲ ሙስና ናትና በልጇ የፍርድ ወንበር ፊት መቆም ስለማይገባት ትንሣኤዋ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት መጠበቅ አላስፈለገውም፡፡

ይልቁንም ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች» በማለት ፍርድን ለመቀበል ሳይሆን ምሕረትን ለማሰጠት ስለእኛ እንደምትማልድ መስክሯል /መዝ.44.9/፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ በትንሣኤ ዘጉባኤ የእርስዋ ግብር መነሣት/መቆም/ ሳይሆን የልጇን ፍርድ ማየትና ማድነቅ መሆኑን ልናስተውል ይገባል፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ በሃይማኖት በምግባር ጸንተን፣ ጌታችንን በሕግ በአምልኮ ተከትለን፣ እመቤታችንንም ተማጽነን እርስዋ ያለችበትን መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጣዕሟን በአንደበታችን፣ ፍቅሯን በልቡናችን ታሳድርብን፤ አሜን፡፡

 

                  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ከአባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ

የእመቤታችን መገኘቷ ሥርወ ልደቷ ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግሥት ነው፡፡

እመቤታችን ስለ አንቺ የተደረገ ነገር ሁሉ ድንቅ ነው፡፡ “በኪዳነ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ ነው”፡፡ ከኖኅ እስከ አብርሃም፣ ከአብርሃም እስከ ሙሴ ከዳዊት፣ እስከ ኢያቄም ወሓና ድረስ እመቤታችን በተለያዩ ህብረ ምሳሌ በበትረ አሮን፣ በደመና፣ በሰዋሰው በድልድይ፣ በመርከብ፣ በተራራ እየተመሰለች ስትነገር ኑራለች፡፡ ማቴ. ፩÷፩

እግዚአብሔር በወርቅ በዕንቍ ከተሠራው ቤተ መንግሥት ይልቅ በጭቃ፣ በጨፈቃ፣ የተሠራውን ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር ይወዳልና፡፡

በእመቤታችን አማላጅነት ያመኑ “እምነ ጽዮን” እመቤታችን ይሏታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እናታችን መንፈሳዊ ልደትን በ40 በሰማንያ 80 የተወለድንባት፡፡

እግዚአብሔር ወልድ አባታችን መድኃኒታችን አምላካችን ነው፡፡image-0-02-01-44863ce8f34e4487c873886bdb116e6705a8df835a41775e27e87493cf839b26-V

በትረ ሙሴ፣

ይህች በትር ከየት የተገኘች ትሆን? ሙሴ አንድ ዐመፀኛ ግብጻዊን ገድሎ ከግብጽ ኰብልሎ ምድያም በገባ ጊዜ በዮቶር ቤት ተስተናገደ፡፡ ዮቶር የአታክልት ቦታ ነበረው ለሙሴ ሲያስጐበኘውም በአትክልቱ መካከል ሙሴ አንዲት የተለየች ዕፅ አየና ባለቤቱን ዮቶረን “ይህች ነገር ምንድንናት?” ሲል ሙሴ ጠየቀ፡፡ ዮቶርም “ይህች የተለየ ታሪክ ያላት ናት” ይህች ብትር የዮሴፍ ነበረች ዮሴፍ በሞተ ጊዜ ንብረቱ ሁሉ በንጉሡ በፈርኦን ዕቃ ግምጃ ቤት ነበር፤ እኔም የንጉሡ የፈርኦን ካህነ ጣኦት ነበርሁ ወደ ሀገሬ ለመመለስ ንጉሡን ሳስፈቅድ ይህችን ብትር አየኋትና ደስ አለችኝ፤ ስለዚህም ንጉሡን አስፈቅጄ አመጣኋት አሁን ካለችበት ቦታ ይዤ ደገፍ ስልባት ከዚያው ተተከለች ተጣበቀችም፡፡ እነቅላለሁ ብዬ ብሞክር የማይቻል ሆነ፡፡ በምድያም አሉ የሚባሉ ኃያላን ቢሞክሩም አልሆነላቸውም፡፡ ይኸውም እንደምታያት አለች አለው፡፡

በዚህ ጊዜ ሙሴ ብትርዋን እየተመለከተ ማድነቅ ጀመረ፤ ዮቶርም ምንድነው የምታደንቀው አሁን ከነገርኩህ ሌላ የተለየ ታሪክ አገኘህ እንዴ? በማለት ጠየቀው ሙሴም “አዎን ሌላ ታሪክ አለ” በማለት ታሪኩን እንዲህ ሲል ቀጠለ “እግዚአብሔር በዕለተ ዐርብ ከፈጠራቸው ዐሥር ፍጥረታት አንዷ ይህች በትር ነበረች፡፡ እግዚአብሔር ከሁሉ አብልጦ ለሚወደው ለአዳም ሰጠውና አዳምም ለልጁ ለሴት ሰጠው፤ ሴትም ለኖሕ ሰጠው፣ ኖሕም ለሴም ሰጠው ከሴምም ለአብርሃም ደረሰች፣ አብርሃምም ለይስሐቅ ሰጠው፣ ይስሐቅም ለያዕቆብ ሰጠው፣ ያዕቆብም ለሚወደው ልጁ ለዮሴፍ ሰጠው” በማለት ሲተርክ ዮቶር እንዴ! እንዴ! ምንድነው የምትለው? አሁን የምትናገረው ማን አምኖ ይቀበልሃል? አለው፡፡ ሙሴም “አሉ የተባሉ የምድያም ኃያላን ሰዎች ሊነቅሉ ሞክረው እምቢ አላቸው ብለህ የለ?” አለው፡፡ እሱም “አዎ አለ፤ ሙሴም እንግዲያውስ አሳይሃለሁ” አለና በእጁ ሳብ ቢያደርገው ከአሸዋ እንደተወተፈ ሸንበቆ ውልቅ አለችና ከእጁ ገባች፡፡

“ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ”

ነቢዩ ኢሳይያስ “ትወፅእ በትር እምሥርወ እሴይ፡- ከእሴይ ሥር ብትር ትወጣለች” ማለቱ ያች አስቀድማ በምሳሌ የታየች ብዙ ተአምራት የታዩባት ብትር አሁን በግልጽ ከእሴይ ሥር ትወጣለች ከእሴይ ዘር ትወለዳለች ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ ይህን የነቢዩን የኢሳይያስን ትንቢት ሲተረጐም በትር የተባለችው ድንግል ማርያም ናት፣ ጽጌ የተባለውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት አብራርቶታል፡፡ እሴይ የዳዊት አባት ስለሆነ እመቤታችን ወለተ ዳዊት ንጉሥ ትባላለች፡፡ ስለዚህም ነው ወንጌላዊው ማቴዎስ ማቴ. ፩÷፩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም ያለው ኤር. ፳፫÷፭፣ ሉቃ. ፩÷፴፪፣ ማቴ. ፱÷፳፯፣ ራዕ. ፳፪÷፲፮”፡፡

ከእሴይ ዘር የተወለደው ኢያቄም ከአሮን ልጆች ዘር የምትወለድ ቅድስት ሐናን አገባና ሁለቱም ደጋግ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩና ትእዛዙን የሚያከበሩ ሁነው ልጅ ሳይወልዱ ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር አመለከቱና እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ መልአኩን ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ የተለየች ልጅ እንደሚወልዱ አበሠራቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል አይታበልምና ያች ከእሴይ ሥር ትወጣለች የተባለች ሙሴና አሮን እየተቀባበሉ እስራኤልን ነጻ ያወጣባት በትር አሁን በገሐድ ከእሴይ ግንድ በቀለች፣ ለመለመች አበበች አፈራች፡፡ “ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ”፡- ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች የተባለው የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጸመ፡፡ ኢሳ. ፲፩÷፩

ቅዱስ ያሬድ ይህን በተመለከተ ሲዘምር “ዕፅ ዘበቈለት ኀበ መኀዘ ማይ፡- ውኃ በሚወርድበት (በውኃ ዳር) የበቀለች ዛፍ፣ ፍሬሃ ሠናይ፡- ፍሬዋ የሚያምር፣ አዳም ለርእይ በዓይን ለማየት ደስ የምታሰኝ፣ በምድር ሥጋውያን ምእመናን በአንድነት ተሰብስበው “ሰዓሊ ለነ ቅድስት” በማለት ይጸልዩባታል፤ በሰማይ ደግሞ ምእመናነ ነፍስ ከእርሷ በተገኘው ጸጋ መንግሥተ ሰማያትን ወርሰው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይኖሩባታልና፡፡

ከአዳም እስከ ኖሕ፣ ከኖሕ እስከ አብርሃም፤ ከአብርሃም እስከ ዳዊት፤ ከዳዊት እስከ ኢያቄም ያለውን መሠረቷ በተቀደሱ ተራሮች ነው ያሏት ለዚህ ነው፡፡ ሉቃ. ፫ ፳፫÷፴፯፤ መመልከት ይቻላል፡፡ ማቴ. ፩÷፩-፲፰፡፡

ኢያቄምና ሐና ኑሮአቸው በእግዚአብሔር ፊት ቅንና ግልጽ በሰውም ፊት የዋሃንና ስሕተት የማይታይባቸው ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሀብታቸው በሦስት ክፍል የተመደበ ነበር፡፡ ይኸውም፡-

 • አንዱ ክፍል ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት
 • ሁለተኛው ክፍል ለድኾችና እንግዶች መቀበያ
 • ሦስተኛው ክፍል ለራሳቸው ለቤተሰባቸው አገልግሎት

በዚህ ሁኔታ በሰውና በእግዚአብሔር የተመሰገኑ ደጋግ ሰዎች ልጅ ሳይኖራቸው 20 (ሃያ) ዓመታት አለፉ፡፡

ስለዚህም ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጣቸው መላ ዘመኑ ቤተ እግዚአብሔርን የሚያገለግል እንዲሆን ቃል ገብተው ተሳሉ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ በዓል ሲከበር ኢያቄም ከጐረቤቱቹ ጋር መባዕ ይዞ በዓሉን ለማክበር ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ በጊዜው የነበረው ሊቀ ካህናት ይሳኮር (ሮቤል) ይባላል፡፡ ኢያቆም መሥዋዕት ይዞ መምጣቱን አይቶ ወደ እርሱ ሄደና “ልጅ ሳይኖርህ (መኻን) ሁነህ እንዴት ወዲህ ትመጣለህ መባንስ እንዴት ታቀርባለህ?” እግዚአብሔር እኮ የመኻኖችን መባ አይቀበልም አለና ከለከለው፡፡ ስለዚህ ኢያቄም በከፍተኛ ሐፍረትና ሐዘን ተመለሰ፡፡ ዘፍ. ፲፭÷፪-፮፣ ፩ሳሙ. ፫÷፲፪፡፡

ኢያቄም በከፍተኛ ሐዘንና ሐፍረት እያለ ታላቅ ብርሃን የተጐናጸፈ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ከፊቱ ቆመ እንዲህም አለው፡፡ ኢያቄም! እኔን በማየት አትፍራ አትጨነቅም፡፡ እኔ ጸሎትህ የተሰማ ምጽዋትህ ቅድመ እግዚአብሔር የደረሰ መሆኑን ልነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወዳንተ የተላክሁ የእግዚአብሔር መልአክ ነኘና ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ የብዙዎችን ማህፀን ይዘጋል፤ ይከፍታል፡፡

(ቅድመ አያት) ሣራ እስከ ሰማንያ ዓመት ዕድሜዋ መኻን ሁና በኋላ የይስሐቅ እናት ሆነች፡፡ እንደዚሁም ራሔል የእግዚአብሔር ወዳጅ ሁና መኻን ነበረች በኋላ ደግሞ የዮሴፍ እናት ሆነች፡፡ የእግዚአብሔር የቅርብ ወዳጆች የነበሩት የሳምሶንና የሳሙኤል እናቶች ሆኑ መኻኖች ነበሩ፡፡ መሳ.  ፲፫÷፩-፳፬፣ ሳሙ. ፩÷፳

ስለዚህ ሚስትህ ሐና ሴት ልጅ ትወልድልሃለች ስሟንም ማርያም ብለህ ትጠራታለህ በእናትዋ ማሕፀን ውስጥ ሳለችም መንፈስ ቅዱስ ያድርባታል አለው፡፡ ከዚያ መላኩ ወደ ሐና ሄደ፡፡

ከዚያ በኋላ መላኩ ኢያቄምን ተሰናብቶ ወደ ሐና ሄደና አትፍሪ ወይም እኔን አይተሽ ሌላ መንፈስ ያየሸ አይምሰልሽ!! እኔ ጸሎትሽንና ምጽዋትሽን ከእግዚአብሔር ፊት የማቀርብ መልአክ ነኝና አሁንም የመጣሁት ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትሆን ማርያም የምትባል ልጅ የምትወልጂ መሆንሽን ልነግርሽ ነው በማለት አበሠራት፡፡ በዚሁም እውነት ከአባትዋ ከኢያቄምና ከእናትዋ ከሐና ነሐሴ 7 ቀን 5484 ዓ.ኲ. ተጸነሰች፡፡ ግንቦት 1 ቀን 5485 ዓ.ኲ. ተወለደች፡፡ ስለዚሁም ነው ሊቁ አባ ሕርያቆስ “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ” ድንግል ሆይ በሥጋ ፈቃድ የተፀነሽ አይደለሽም “አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ” ብዝኁ ወተባዝኁ ባለው በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ ያለው፡፡ (ቅ.ማ)

 • ሙሴ በኃቅለ ሲና ያያት ነበልባለ እሳት የተዋሓዳት
 • የእግዚአብሔር ቃል የተጻፈባት የሙሴ ጽላት
 • ደብተራ ኦሪት
 • በትረ አሮን
 • ሕዝቅኤል ያያት ቤተ መቅደስ በአጭሩ እነዚህን ብቻ ብንመለከት እንኳን!!
 1. ሙሴ ከግብጽ ወደ ምድያም ተሰዶ የአማቱን የዮቶርን በጎችና ፍየሎችን ይጠብቅ በነበረበት ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ነበለባል ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ እሳቱ ዛፉን ሳያቃጥለው፣ ወይም ሐመልማሉ እሳቱን ሳያጠፋው አንድ ሁኖ አየና ቀርቤ ነገሩን ማወቅ አለብኝ ብሎ ወደዚያ ሲጠጋ ልዑል እግዚአብሔር እሳት ከተዋሐዳት ሐመልማለ ዕፅ ሁኖ “ሙሴ ሙሴ የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች (የተለየች) ናትና ጫማህን አውልቅ” በማለት ካዘዘው በኋላ በግብፃውያን አገዛዝ ተጨንቀው የነበሩትን እስራኤላውያንን ነጻ ማውጣት የሚችልበትን መመርያ ሰጠው፡፡ እዚህ ላይ ምሳሌው እንዴት ነው? ቢባል ሐመልማል የእመቤታችን ነበልባል (እሳት) የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ የግብጻውያን አገዛዝ ከባድ ቀንበር የተጫናቸው እስራኤላውያን ከአዳም ጀምሮ እስከ ዕለተ ዐርብ ድረስ በዲያብሎስ አገዛዝ ሥር ወድቀው የነበሩት ነፍሳት ነጻነትን ጉዳይ ያመለክተናል፡፡ ሉቃ. ፳÷፴፯፣ ማር. ፲፪÷፳፮፣ ዘዳ. ፴፫÷፲፮፣
 2. የሙሴ ጽላት፡- ጽላቱ የእመቤታችን በጽላቱ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር በሙሴ ጽላት ዐድሮ ሙሴን ያነጋግር እንደነበረ አሁንም የእግዚአብሔር ቃል በድንግል ማርያም ማሕፀን ዐድሮ ሰው ሁኖ አድኖናልና፡፡ ዘጸ. ፳፭÷፳፪፣ ዘኁ. ፩÷፩፣ ዘዳ. ፯÷፩-፮
 3. ደብተራ ኦሪት (ቅድስተ ቅዱሳን) የቃል ኪዳን መኖርያ እንደነበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅደረ መለኮት ሁናለችና ዘጸ. ፩÷፩-፴፮፣
 4. በትረ አሮን የአሮን በትር ሳይተክሉአት፣ ውኃን ሳያጠጧት ለምልማ፣ አብባ፣ አፍርታ እንደተገኘች እመቤታችንም ያለ ዘርዐ ብእሲ የእግዚአብሔርን ቃል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልዳለችና፡፡ ዘኁ. ፲፯÷፰፣ ዕብ. ፱÷፬
 5. ሕዝቅኤል ያያት ቤተ መቅደስ፣ ሕዝቅኤል ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደሆነው ወደ መቅደሱ በር መልሶ አመጣኝ፣ ተዘግቶም ነበር፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፣ ይህ በር እንደተዘጋ ይኖራል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና እንደተዘጋ ይኖራል እንጂ አይከፈትም አለኝ ይላል፡፡ ሕዝ. ፵፬÷፩-፭፡፡ ይህም ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና የተነገረ ምሳሌ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ እመቤታችን ከመፅነስዋ በፊት ከፀነሰችም በኋላ፣ ከመውለድዋ በፊት ከወለደችም በኋላ ድንግል ናትና፡፡ ሉቃ. ፩÷፴፭-፴፱፣ ማር. ፩÷፳፬፣ ፭÷፯ ማቴ. ፩÷፲፰፡፡

ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልእተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ

“ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና” “ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” ሉቃ. ፩÷፳፰፡፡ ይህንን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መነሻ በማድረግ እንደ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር የተመረጡ ወንጌልን የሰበኩ ሐዋርያውያን አበው እመቤታችን የደስታችን መገኛ የሐዘሃችን መጽናኛ መሆኗን ሲመሰክሩ “እኔ ሐዋርያው የሆንኩ ወንጌልን የማስተምርለት የጌታዬ እናቱ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ከተወለደ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽን ያለ መለወጥ የጠበቀውን አማኑኤልን የወለድሽው ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ” ብለዋል፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ጌታ በቤተልሔም በከብቶች በረት ሲወለድ መላእክት ያቀረቡትን የደስታ ዝማሬ መነሻ በማድረግ “የመላእክት ደስታቸው የሚሆን ጌታን የወለድሽው ደስ ይበልሽ” በማለት አመስግኗታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በበኩሉ “ተፈሥሒ አ ሙኀዘ ፍትሐ የተድላና ደስታ መፍሰሻ ሆይ ደስ ይበልሽ” ብሏታል፡፡

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ሰዎች ሲላክ የመጀመሪያው አይደለችም፤ ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ዳንኤልን ሲያነጋግረው ነቢዩ ደንግጦ ከምድር ላይ መደፋቱን ሲመሰክር “… ሲናገረኝም ደግሞ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ፡፡ እርሱም ዳሰሰኝ ቁጭ አድርጎ አቆመኝ” ብሏል ዳን. ፲÷፲፭-፲፯፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ጥበብንና ማስተዋልን የተመላ ነቢይ ነው፡፡ ነገር ግን መልአኩ ራእዩን ሲገልጥለት ዳንኤል ከፍርሐት የተነሣ በግንባሩ ከመደፋቱ ውጪ ያቀረበለት ሰላምታና ምስጋና የለም፡፡ የድንግል ማርያምና የመልአኩን የብሥራት ሁኔታ ስንመለከት ግን ለድንግል ማርያም የተለየ ምስጋና ክብር አቅርቦላታል፡፡ “ጸጋ የመላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” ብሏታል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ምስጋና ምን ክብር አለ?

ድንግል በኅሊናኪ ወድንግል በሥጋኪ

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ከተናገረው ቃል የተወሰደ ነው ሉቃ. ፩÷፳፯

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ከዚህ የጸና አቋም በመነሣት “የምንጊዜም ድንግልናዋንና ንጽሕናዋን ሲመሰክሩ” “በጊዜው ሁሉ ንጽሕት ድንግል የምትሆን አምላክን የወለደች ማርያም” ብለዋታል፡፡ በመሆኑም “በሐሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ” የተባሉት ቃላት የተወሰዱት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል ሉቃ. ፩÷፳፯፣ ማቴ. ፩÷፳፫፡፡

እመ እግዚአብሔር ጸባዖት ሰላም ለኪ

እመቤታችንን፣ “የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናት ሰላምታ ይገባሻል” በማለት ስናመሰግናት መነሻችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የልጇን ኃያልነት ወይም አሸናፊነት ሲመሰክር “ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፣ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፣ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” ብሏል ኢሳ. ፱÷፮-፯፡፡

ነቢዩ “አለቅነት በጫንቃው የሆነ፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ብሎ የጠራውን አምላክ የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ የድንግል ማርያምን እመ እግዚአብሔርነት (የእግዚአብሔር እናትነት) የዕንቆራው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሲመሰክር “በድንግልና ሳለች ከእርሷው ተወልደ፣ድንግል ማርያምን እናቴ አላት” ብሏል፡፡ የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስ በበኩሉ “ከማይመረመር ልደቱም በኋላ ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም፣ ስለዚህ ወላዲተ አምላክ እንደሆነች አመን” ብሏል፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ” ሉቃ. ፩÷፵፫  ቅድስት ድንግል ማርያምን “እመእግዚአብሔር ጸባዖት የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናት ሰላምታ ይገባሻል፡፡

ቡርክት አንቲ እም አንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ

እመቤታችንን “ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽ ፍሬ የተባረከ ነው፤ ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” አላት ሉቃ. ፩÷፳፰፡፡ የሚለው እና ቅድስት ኤልሳቤጥ “አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” ሉቃ. ፩÷፵፲ የሚለው ቃለ ወንጌል ነው፡፡ ይህንን የምስጋና ቃል ነው፡፡

ስለሆነም አበው ነቢያት የተነበዩት ሓዋርያት የሰበኩት ስለ እመቤታችንና ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረውን የተስፋ ቃል ፍጻሜውን ለማየት ቢመኙም ዐረፍተ ዘመን ስለገታቸው “ጌታችን” እስመ ብዙኃን ነቢያት ወጻድቃን ፈተው ይርዓዩ አንትሙ ዘትየእዩ ወኢርእዩ ወፈተው ይስምዑ አንትሙ ዘትሰምዑ ወኢሰምው፡፡

ብዙ ጻድቃንና ነቢያት እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኙ፡፡ ነገር ግን አላዩም የምትሰሙትንም ለመስማት ፈለጉ ነገር ግን አልሰሙም ሲል ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡ ማቴ. ፲፫÷፲፮

ከአባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ

 

‘‘በምትጾሙበት ጊዜ ግብዞች እንደሚያደርጉት አታድርጉ’’ 

           ማቴ 6-14

ጾም በመንፈሳዊ ሕይወት የሚያድግና ልብላ ልጠጣ የሚለውን የሥጋን መሻትና ፍላጐት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጐ ማቅረቢያ መንገድ ነው፡፡ ጾም ማለት ከሆነ ነገር መከልከል ማለት በመሆኑ ጾም ለአዳም የተሰጠው የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፡፡ ዘፍ 2፥17 ጾም እግዚአብሔርን የመፍራትና ፊትን ወደ እርሱ የማዞር ምልክትና የእግዚአብሔር ገጸ ምሕረት መለመኛ ነው፡፡ ‘‘እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ’’ እንዲል 2ኛ ዜና. 20፥3 እንዲሁም ጾም የነፍስ ቁስል የሚድንበትና የሚጠገንበት፤ በመልካም ሥነ ምግባር ላይ የቆመ ትውልድ የሚታነጽበትም መሣሪያ ነው፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ‘‘ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል’’ እንዳለው በሀገርና በወገን ላይ የተላለፉት አዎንታዊ ጠባሳዎች ያፈረሷቸው ስፍራዎችና መልካም ነገሮች ሁሉ የሚጠገኑትና ተመልሰው የሚሠሩት በጾም ነው፡፡ ኢሳ. 58፥6-14 ጾም የሌለበት ሰውነት የአጋንንት መኖሪያ ቤት እንጂ የእግዚአብሔር መቅደስ አይደለም፡፡ በተሐደሶ ሰዎችና በመሰሎቻቸው እያደረ ‘‘ዘመነኛ’’ በሚል ሽፋን ሰይጣን የሚሰብከውን ጾም የለሽ ስመ ክርስትና ብቻ እንጠንቀቅበት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘‘በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ’’ ያለው ሆድን ወድዶ ጾምን ጠልቶ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ስለማይቻል ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ‘‘ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለ እርሱ አልኋችህ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ፣ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ አሳባቸውም ምድራዊ ነው’’ የተባሉት ናቸውና ፊለ. 3፥18-19፡፡

ስለ ጾም አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ ‘‘የእውቀት ዛፍ  በተባለችው ተሸንፈን መጾምን እንቢ በማለታችንና ጾምን በማፍረሳችን ከዚያ በኋላ በደረሰብን መከራ በግድ ጾምን፡፡ የጾም ሕግ አስቀድሞ የተሰጠንም ለነፍሳችን ትምህርት ለጸሎትና እርሱ ለሚያመጣው ዕዳ አርቆ ማጣሪያና መጠበቂያ  እንዲሆነን ነበር፡፡ ስለዚህም ዛሬ ከጥንቱ ከመጀመሪያው የጾምን ሕግ ባለመጠበቃችን ምክንያት ያጣነውን ነገር መልሰን እናገኝ ዘንድ ጾም እንድንጾምና ለጾም እንድንገዛ አደረገን’’ ብሏል ትምህርት ካልዕ በእንተ ትንሣኤ ቁ.28

የኢትዮጵያ ሕዝብ በጾሙ በጸሎቱ በሃይማኖቱ የተወደደ ለመሆኑ እግዚአብሔር በየጊዜው በሚያደርገው ትድግና የተመሰከረለት ነው፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሚጾሙት ጾም በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረው ከቸርነት፤ ከምጽዋት ከጸሎትና ከስግደት ከንጽሕና እና ከSt.Maryቅድስና ጋር ስለሆነ እግዚአብሔር ለመቀበሉና ምሕረቱን ለአገራችን ለመስጠቱ በሩቅ በታሪክ በቅርብ በዓይን እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት በተጋድሏቸው እንደፈጣሪያቸው ስስትን፤ ትዕቢትን፣ ፍቅረ ንዋይን ድል የነሡና የሃይማኖት አበጋዞች በመሆን የተራበውን የሚያበሉ፣ የተጠማውን የሚያጠጡ፣ ቆርሰው የሚያጐርሱ፣ ቀደው የሚያለብሱ፣ ገንዘባቸውን ለነዲያን ከፍለው ምጽዋት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ በጾማቸው እንደ እነ ዮዲት እንደ እነ አስቴር ጠላትን ድል ነሥተውበታል፣ ሀገርን ጠብቀውበታል፣ እንደ ሰብአ  ነነዌ ከመቅሰፍት ድነውበታል፣ አንድ አንድ አገሮች እንደ ሰብአ ትካት በውኃ ሲጠፉ እንደሰብአ ሰዶም በእሳት ሲቃጠሉ እንደነ ዳንታንና አቤሮን ከመሬት ሲሰጥሙ እንደ ሰብአ ሰናዖር በነፋስ ሲሙቱ ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ መቅሰፍት ተጠብቃ የምትኖረው በቅዱሳን ካህናትና ምእመናን ጾምና ጸሎት በመናኝ ገዳማውያን አባቶች ቅጠል በጥሰው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጸብአ አጋንንትን ግርማ ሌሊትን ታግሰው በምናኔ ሕይወት በሚኖሩ ቅዱሳን አባቶች ጸሎት መሆኑ የታመነ ነው፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ቤተ  ክርስቲያን የሚመጡ የምእመናን ቁጥር እየጨመረ የሚሄደውም ጾም ጸሎቱ የሠመረለት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራችን ለዘመናት በነጻነት ተጠብቃ የኖረችውም በሌላ ኃይል ሳይሆን በጾምና በጸሎት እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ በመኖሯ ነው፡፡ መዝ. 67፥31

“ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ” ጾመ ድጓ ቅዱስ ያሬድ

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችው! እያልን

በእየዕለቱ የሚነበቡ ምንባባትና  የሚሰበክ ምስባክ ማውጫ (ዘቅዳሴ)

 

ቀን ምንባብ ምስባክ

 

ትርጉም
ነሐሴ 1 1ኛ ጢሞ 5፥1-121

1ኛ ዮሐ 5፥1-6

የሐ.ሥራ 5፥26-34

ሉቃ.1፥39-57

በጽሑ መላእክት ወቦሙ መዘምራን፣ ማእከለ ደናግል ዘባጥያተ ከበሮ በማኅበር ባርክዎ ለእግዚአብሔር መዝ .67፥25

 

አለቆች ለምስጋና ደረሱ መዘምራንም አሏቸው። ከበሮን በሚመቱ በቆነጃጅት መካከል። እግዚአብሔርን በማኅበር አመስግኑት።
ነሐሴ 2

 

1ኛ ጢሞ 2፥8-ፍም

1ኛ ጴጥ 5፥1-7

የሐ.ሥራ 16፥13-19

ሉቃ 18፥1-15

ወይሰግዳ ሎቱ አወልደ ጢሮስ በአምኃ፣ ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ  ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን፣ መዝ 44፥9

 

የጤሮስ ሴት ልጆች እጅ መንሻ ይዘው ይሰግዱለታል። የምድር ባለጠጐች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ። ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው።
ነሐሴ 3 1ኛ ተሰሎ 3፥1-ፍም

1ኛጴጥ 3፥10-15

የሐ.ሥራ 14፥20-ፍም

ማቴ 25፥1-14

አዋልደ ንግሥት ለክብርከ፣ ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፣ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፣ መዝ.44፥9

 

የእመቤታች የመንፈስ ቅዱስ ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው። በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና

እመቤታችን በቀኝህ ትቀመጣለች።

ነሐሴ 4 ሮሜ 12፥16-ፍም 1ኛ ጴጥ 5፥5-12

የሐ.ሥራ 17፥23-28

ዮሐ. 12፥24-26

ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግለ ድኅሬሃ፣ ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ፣ ወይወስድዎን በትፍሥሕት ወበሐሤት መዝ .44፥14 በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ በደስታና በሐሴት ይወስዷአቸዋል።
ነሐሴ 5 2ኛ ቆሮ 12፥10-17

1ኛ ዮሐ 5፥14-ፍም

የሐ.ሥራ 5፥14-ፍም

ሉቃ 13፥10-18

እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፣ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን።

መዝ 83፥

 

የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳል የአማልክት አምላክ በፅዮን ይታያል
ነሐሴ 6 1ኛ. ቆሮ 3፥10-22

1ኛ.ጴጥ 3፥1-7

የሐ.ሥራ 16፥13-19

ማቴ. 2፥9-16

ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፣ እዜከሮን ለረዐብ ወለባቢሎን እለ የአምራኒ፣ ወናሁ ኢሎፍሊ ወጢሮስ ወሕዝበ  ኢትዮጵያ መዝ 86 ፥3 የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ባንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው።

የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸውዋለሁ፡፡ እነሆ ኢሎፍሊን ጢሮስን የኢትዮጵያንም ሕዝብ አስባቸዋለሁ።

ነሐሴ 7 ዕብ 9፥1-11

2ኛ ጴጥ 2፥6-18

ዮሐ ሥራ 10፥1-30

ማቴ 1፥1-17

መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፣ ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን፣ እምኵሉ ተዓይኒሁ ለያዕቆብ መዝ 86፥1 መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው። ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል።
ነሐሴ 8 ሮሜ 9፥24-ፍም

1ኛ ጴጥ 4፥12-ፍም

የሐ.ሥራ 16፥35-ፍም ሉቃ 10፥38 -ፍም

ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቀፍዋ፣ ወተናገሩ በውስተ ማኅፈዲሃ፣ ደዩ ልበክሙ ውስተ ኃይላ፣

መዝ 47-12

ጽዮንን ክበብዋት በዙሪያዋም ተመላለሱ። በቤቷ ሁናችሁ ጸልዩ። ታድነናለች ልባችሁም በእሷ ላይ እመኑባት።
ነሐሴ 9 ፊልጵ 1፥12-24

2ኛ ዮሐ 1፥6-ፍም

የሐ.ሥራ 15፥19-25

ሉቃ 23፥26-31

እስመ ኃረያ እግዚአብሔር ለጽዮን፣ ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ፣ ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለም፣

መዝ 131፥13

እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና፣ ማደሪያው ትሆን ዘንድ ወዷታልና እንዲህ ሲል፦ ይህች ለዘለዓለም ማሪፊያዬ ናት
ነሐሴ 10 ዕብ 12፥22- ፍም

1ኛ ጴጥ 1፥6-13

የሐ ሥራ 4፥31-ፍም

ሉቃ 16፥9-17

ተዘከር ማኅበረከ ዘአቅደምከ ፈጢረ፣ ወአድኀንከ በትረ ርስትከ ፣ደብረ ጽዮን ዘኀደርከ ውስቴታ

መዝ 73-2

አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን። የተቤዥሃትንም የርስትህን በትር። በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ።
ነሐሴ 11 1ኛ ቆሮ 5፥11-ፍም

1ኛ ዮሐ 2፥14-20

የሐ.ሥራ 12-፥18-ፍም

ሉቃ 6፥20-27

ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ፣ወትሠይሚዮሙ መላእክተ ለኵሉ ምድር፣ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ መዝ 44፥16 በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ። በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ።

ለልጁ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ።

ነሐሴ 12 1ኛ ቆሮ 9፥17-ፍም

ይሁዳ 1፥8-14

የሐ ሥራ 24፥1-22

ማቴ 8፥10-15

ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክቲሁ፣ ሰምዐት ወተፈሥሐት ጽዮን፣ ወተሐሥያ አዋልደ ይሁዳ መዝ 96፥8 መላእክቱ ሁሉ ይሰግዱለታል አቤቱ ስለፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት። የይሁዳ ሴት ልጆች ደስ አላቸው።
ነሐሴ 13 ዕብ 11፥23-30

2ኛ ጴጥ 1፥15-ፍም

የሐ.ሥራ 7፥44-51

ማቴ. 17፥1-19

ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአክ ይትፌሥሑ፣ ወይሴብሑ ለስምከ፣ መዝራዕትክ ምስለ ኀይል  መዝ 88፥12

 

ታቦርና አርሞንኤም በስምህ  ደስ ይላቸዋል። ስምህን  ያመሰግናሉ። ስልጣንህ ከኃይልህ ጋር ተደረገላቸው።
ነሐሴ 14 1ኛ ቆሮ 1፥10-19

ያዕቆብ 1፥12-22

የሐ. ሥራ10፥31-44

ሉቃ 1፥39-57

ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር፣ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፣ እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ መዝ 147፥1 ኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች ጽዮን ሆይ ለአምላክሽ እልል በይ። የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና።
ነሐሴ 15 1ኛ ቆሮ 1፥18-ፍም

ይሁዳ 1፥17-ፍም

የሐ.ሥራ 1፥12-15

ማቴ 10፥1-15

ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ፣ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ፣ ወውስተ ፀሐይ ሴመ ጽላሎቶ፣ መዝ 18፥4 ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። በእነርሱ ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ።
ነሐሴ 16 ሮሜ 8፥31-ፍም

2ኛ ዮሐ 1፥1-7

የሐ.ሥራ 1፥12-15

ማቴ 26፥26

ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል፣ እግዚአብሔር ውስተ ማእከላ ኢትትሀውክ፣ ወይረድኣ እግዚአብሔር ፍጽመ መዝ 45፥4 ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ። እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም። እግዚአበሔር ፈጥኖ ይረዳታል።

                                           

                  ስብሐት ለእግዚአብሔር

  ለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

 

ከአባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

አዲስ አበባ