Archives

All posts for the month November, 2016

ክፍል ሁለት

 ጽርሐ ጽዮን

ጽርሐ ጽዮን ማለት ትርጒሙ የጽዮን አዳራሽ ማለት ሲሆን የመጀመርያዋ የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የዚህች ስፍራ (ቤት) አገልግሎት ጌታ ባረገ ጊዜ ሐዋርያትን «ኃይልን ከአርያም እስክትለብሱ ድረስ በእየሩሳሌም ከተማ ቆዩ» ብሎ ባዘዛቸው አምላካዊ ቃል መሠረት በታቦት የምትመሰል እመቤታችንን ከመሐል አድርገው በጸሎት በመትጋት የተነገራቸውን ተስፋ ሲጠባበቁባት የነበረችው የማርቆስ እናት ቤት ናት ጽርሐ ጽዮን፡፡ ሉቃስ 24፥49 የሐዋ 12፥12፡፡

በዚህች ስፍራ በጸሎት ሲተጉ ጌታ ባረገ በአስረኛው ቀን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በእሳት አምሳል አድሏቸዋል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያን ልደት (መመስረት) እንደሆነ የቤተክርስቲያናችን አባት የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስረድቷል (ገልጧል)፡፡

ቤተ ክርስቲያን በአይሁድና በአሕዛብ መካከል

ጌታ በሠላሳ ዓመቱ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ሳይውል ሳያድር 40 መዓልትና 40 ሌሊት ከቆመ ሳይቀመጥ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ፣ ከጾመ በኋላ በኢየሩሳሌም ማስተማር ጀመረ፡፡ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መረጠ፡፡ በመዋዕለ ስብከቱም ልዩ ልዩ የሆኑ ትአምራትን በማድረግ ድውያንን ፈወሰ፡፡ ሙታንን አስነሣ፣ የአይሁድ ካህናት ግን የሚደረግላቸውን ተአምራት አይተው የሚያስተምረውን ትምህርት ሰምተው በማመን ፈንታ ተቃወሙት፡፡ 3 ዓመት ከ3 ወር ከአስተማረ በኋላ በማዕከለ ቀራንዮ በኢየሩሳሌም ተሰቅሎ ሞተ፡፡  ሞቶም አልቀረም በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል ተነሥቶም ለሐዋርያት መጽሐፈ ኪዳን አስተምሮ ተስፋ ገባላቸው ‹‹ እነሆም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም  ከተማ ቆዩ›› ሉቃስ 24፡49 ብሏቸው ተስፋቸውን ነግሯቸው ዐረገ፡፡

በዓለ ሃምሳ /ጰራቅሊጦስ/

ደቀመዛሙርቱ  ተሰብስበው ሳለ በቅዱስ ጴጥሮስ አሳሳቢነት ጌታን በካደው በይሁዳ ፈንታ ሌላ ሐዋርያ እንዲተካ ጠየቀ፡፡ በሐሳቡ ሁሉም ሐዋርያት ስለተስማሙ ፍጹሙን እንዲመርጥ ወደ እግዚአብሔር ከጸለዩ በኋላ ለዩሴፍና ለማትያስ ዕጣ ቢጥሉ፣ ዕጣው ለማትያስ ስለወጣ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ተጨምሮ እንዲቆጠር ሆኖ ተሾመ፡፡ ሐዋ.1÷23-26

ጌታ በሚያርግ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ‹‹አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከትለብሱ ኃይለ እምአርያም ›› ብሏቸው ዐርጎ ነበርና ተናግሮ የማያስቀር ምሎ የማይከዳ ነውና በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በዐረገ በ10ኛው ቀን በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ግንቦት 18 ቀን በዕለተ እሑድ ለመቶ ሃያው ቤተሰብ በአምሳለ እሳት ወርዶ አድሮባቸዋል፡፡ የሚያውቁት ጸንቶላቸው የማያውቁት ተገለጸላቸው በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የእግዚአብሔርን ክብር ይናገሩ ጀመር፡፡ በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ባደረገው ስብከት ብዙ ሕዝብ ስለአመነ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ክርስትናን ተቀብለው ተጠመቁ፡፡ የሐዋ. ሥራ 2÷37-42

ለምን በዐረገ በ10ኛው ቀን ጰራቅሊጦስን ሰደደላቸው ቢሉ

 1. አዳም በ40 ቀን አግኝቶ ያጣትን ልጅነት እንዲመለስ ለማጠየቅ
 2. በ10ኛ ማዕረግ የገባን እኛ ነበርንና ወደቀደመው ክብራችን ወደ ማዕረጋችን እንደመለሰን ለማጠየቅ
 3. አሥርቱን ትዕዛዛት ቢጠብቁ ቢፈጽሙ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ መሆኑን ለማጠየቅ
 4. 10 ቁጥር የምሉዕ የፍጹምነት ምሳሌ በመሆኑ

ለምን በተነሣ በኃምሳኛው ቀን አደረገ ቢሉ ትንቢቱና ምሳሌውን ለመፈጸም

ትንቢቱ፡- ኢዩኤል 2፡ 28  ‹‹ እሰውጥ እምነ መንፈስየ ዲበ ኵሉ ዘሥጋ ›› መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ ብሎ በነቢዩ ኢዩኤል አድሮ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ

ምሳሌ፡- ዘሌ 23፡19 ‹‹ የወዘወዛችሁ ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ

ሰባት ቀን ቀጠሩ፡፡ እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ ሃምሳ ቀን ቁጠሩ አዲሱን የእህል ቁርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ፡፡

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ተቀብለው ለተወሰኑ ወራት ያህል በኢየሩሳሌምና አካባቢዋ ብቻ ወንጌልን አስተማሩ ነገር ግን ‹‹ ሑሩ ወመሀሩ ኩሎ አሕዛበ›› ባለው መሠረት ወንጌል በአንድ ቦታ ተወስኖ መቅረት የለበትምና በቅዱስ እስጢፋኖስ እረፍት ምክንያት ሁሉም ሲሰደዱ በምድረ አሕዛብ ወንጌል ትሰበክ ጀምር በዚህ ጊዜ ነበር ከአይሁድ በተመለሱት ክርስቲያኖችና በሐዋርያት መካከል የሐሳብ ልዩነት የተፈጠረው በቅድሚያ ችግሩን ከማየታችን በፊት አይሁድ እና አሕዛብ እነማን እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

አይሁድ፡- ማለት የቃሉ ትርጉም ታማኞች እውነተኞች ማለት ነው፡፡ ለጊዜው የይሁዳ ነገዶች ብቻ

የሚጠሩበት የብዙ ቁጥር ስም ነው ለመጀመሪያ ቃሉ በይሁዳ የሚኖሩትን ሰዎች ያመለክታል 2ኛ ነገሥት 16፡5 በኋላ ከምርኮ ከተመለሱ ይበልጡን ከይሁዳ ነገድ ሰለሆኑ እንደዚሁም ወደ ይሁዳ አገር ስለተመለሱ  ለያዕቆብ ዘሮች ሁሉ መጠሪያ ሆነ ኤር 34፡9

በሃይማኖት ረገድ ግን አይሁድ ማለት በአንድ አምላክ በማመን የታወቁ የአብርሃምና የሣራ ልጆች ማለት ነው፡፡ አብርሃም የነበረው ከጌታ ልደት በፊት ሁለት ሺህ ዓመት ሲሆን በአንድ አምላክ በማመኑ ምክንያት እግዚአብሔር ዘሩን እንደሚያበዛለት ቃል ኪዳን ከገባለት በኋላ ራሱ አብርሃም በኋላ ልጆቹና ቤተሰቦቹ እንዲገዘሩ አዘዘው፡፡ ዘፍ 15÷5፣ ሮሜ 4÷22

ይህም ትእዛዝ አብሃርም በአንድ በእግዚአብሔር ለማመኑና ለመታዘዙ ምልክት እንድትሆነው ነው፡፡ በአብርሃም የተጀመረችው ግዝረት ለዘሮቹ ሁሉ ተላለፈች፡፡ ግዝረት ለእስራኤል ከአብርሃም ለመወለዳቸው ምልክት ብቻ ሳትሆን የአብርሃምን ሃይማኖት ለመያዛቸውም መታወቂያ ነበረች፡፡ ከዚህም የተነሳ ከቆላፋን አህዛብ ጋር በጋብቻ አይቀላቀሉም ነበር፡፡ የመሲህ ክርስቶስ መምጣት ለቤተ

አይሁድ ብቻ ልዩ አስተያየት እንደሚያደርግላቸው ይጠብቁ ነበር፡፡ አሕዛብ ሊገቡበት የማይፈቅዱት የራሳቸው የሆነ ቤተ ጸሎትም ነበራቸው፡፡

አሕዛብ ማለት የቃሉ ትርጉም ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ዘፍጥ .10፡5 በመጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ በተለይ ከእሥራኤል ወገን ላልሆኑ ተነግሯል፡፡ ኢሳ 11፡10

በሃይማኖት ረገድ ግን አሕዛብ ማለት ነው፡፡ ዘፍጥ 10፡5 በመጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ በተለይ ከእሥራኤል ወገን ላልሆኑ ተነግሯል ፡፡ኢሳ. 11፡10

በሃይማኖት ረገድ ግን አሕዛብ ማለት ትንቢት ያልተነገረላቸው ሱባዔ ያልተቆጠረላቸው በተለያዩ አማልክት ሲያመልኩ የሚኖሩ የግዝረትና የመመሪያ ሕግ የሌላቸው የተበታተኑ ተስፋ የሌላቸው አሕቦች ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ አይሁድና አሕዛብ ይለያያሉ። አይሁድ ከአሕዛብ ጋር በምንም ዓይነት መንገድ አይተባበሩም እንዲያውም በጦርነት  እየተነሱ ብዙ ጊዜ ስለሚያሰቃያቸው አረማዊ የሚል ስም አውጥተውላቸው ነበር፡፡

አረማውያን ማለት እስራኤላዊ ያልሆነ ሥርዐትና ሕግ የሌላቸው መደዴ ያልሰለጠነ ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ልክ ግሪኮች ግሪክ ያልሆነውን ሁሉ በርባኖርስ እንዲሉት፡፡

እንግዲህ የሚንቋቸው የሚጠሏቸው አሕዛብ በሐዋርያ ትምህርት አምነው ወደ ምኩራባቸው ሲገቡ አብረው ሲበሉና ሲጠጡ አሕዛብ አረማዊ ከእስራኤላዊ ጋር መተባበር ተደርጎ የማይታወቅ ነው በማለት አዲሱቱን ቤተክርስቲያን ያውኳት ጀምር በአሕዛብ ምክንያት በሐዋርያትና ከቤተ አይሁድ በተመለሱት ክርስቲያኖች መካከል እንዳይካረር በማለት ሐዋርያትና ሌሎችም አርድእት የአይሁድን ሕግና ሥርዓት አልፎ አልፎ ሲሠሩበት ነበር፡፡

ለምሳሌ፡-

– ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ሲያስከትል ገዝሮ አስከትሎታል፡፡ ሐዋ. 16፡3

–  እንዲሁም በአይሁድ ሥርዐት መሠረት ስለቱን ለማድረስ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ይላጭ ነበር፡፡  ሐዋ. 18፡18

ሐዋርያትም ሆኑ አርድዕት ይህን ቢፈጽሙ አሻፈረኝ አሉ። ይልቁንም ከእርሱ ተሻልን ያሉት ምንም እንኳ አረማውያን ከእሥራኤል የተለዩ ቢሆንም ለመዳን ከሆን ወንጌል ያለ ኦሪት ጥምቀት ያለ ግዝረት ክርስቶስ ያለ ሙሴ ሊያድን አይችልም በማለት ቢጽ ሐሳውያን ያስነግሩ ጀመር። ነገሩ እንዳይከር በማለት ሐዋርያት ሲኖዶስ እንዲደረግ አዘዙ፡፡

የሐዋርያት ሲኖዶስ

በቤተክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያ የሃይማኖት ሲኖዶስ በሐዋርያት አማካኝነት ከ 49-50 ዓ.ም መካከል በኢየሩሳሌም ከተማ  በያቆብ እኁኁ ለእግዚእ ሊቀመንበርነት ተደረገ፡፡

በሲኖዶሱም ላይ ሐዋርያት የገጠማቸውን ችግር ሁሉ ከአስረዱ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላለፉ፡፡

 1.  ከአሕዛብ የሚመለሱት ክርስቲያኖች ከዝሙት እንዲጠበቁ
 2.  አሕዛብ ደግሞ ደም አንቆት የሞተውን እንዳይበሉ፣
 3.  ለጣዖታት የተሰዋውን እንዳይበሉ፣
 4.  አሕዛብን መምከርና ማስተማር እንጂ የሙሴን ሕግና ሥርዓት ጠብቁ ብሎ ማወክና ተስፋ ማስቆረጥ አይገባም የሚል ውሳኔ አስተላለፉ፡፡
 1.  ስለ ነገረ ቤተክርስቲያን ፣ ስለ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ስለ ካህናት አገልግሎት፣ ስለ ምእመናን ድርሻ አብጥሊስ ግጣ ዲድስቂልያ

በተሰኘ መጽሐፋቸው ወስነዋል፡፡

ዛሬም በሐዋርያት መሠረትነት የታነጸች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን መሠረት አድርጋ በዓመት ሁለት ጊዜ  የጎበጠውን የምታቀናበት የጎደለውን የምትሞላበት የሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ (የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ)  ታደርጋለች፡፡

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሕይወት

በ12ቱ ሐዋርያት የተጀመረች ጉባኤ ወደ 120 ቤተሰብ አድጋ እንደገናም በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ማኅበረ ክርስቲያን ወደ 3000 ሲደርሱ በኋላም በቅዱስ ጴጥሮስና በቅዱስ ዮሐንስ ተአምራት አምስት ሺህ ምእመናን አመኑ፡፡

በኢየሩሳሌም ውስጥ የተመሠረተችው ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች ምእመናን ቁጥር እየበዛ ሄደ፡፡ ይኽውም በክርስቲኖች  መካከል የነበረው የእርስ በርስ ፍቅር በዙሪያቸው የሚኖሩ ያላመኑ አሕዛብን አስቀኗቸው፡፡ ‹‹አደነቁም? አያችኋቸው ?እነዚህ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ሲፋቀሩ›› ይሉ ነበር፡፡ በመፋቀራቸውም የክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን አስመሰከሩ፡፡

እነዚህም የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች፣

1ኛ. ክርስቲያኖች ከሰዓት በኋላ ጊዜ ወስነው በኢየሩሳሌም ኤጴስ ቆጶስ በያዕቆብ

መሪነት በማርቆስ እናት በማርያም ቤትና ሌሎችም ቦታዎች እየተሰበሰቡ

የሐዋርያትን ትምህርት ይሰሙ ነበር፡፡/የሐዋ. ሥራ 12÷12

2ኛ. በየጊዜው የጌታን  ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በአንድነት እየተቀበሉ ይኖሩ ነበር፡፡ ዮሐ. 6÷54

3ኛ.በወንድማማችነት መንፈስ የተሳሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ ሁሉም በአንድነት በአንድ ማዕድ ላይ     ተቀምጠው ይበሉ ነበር፡፡

ይኽውም የሐዋርያት ማዕድ (አጋፔ) ይባል ነበር፡፡

4ኛ. ክርስቲያኖች በመካከላቸው ችግረኛ እንዳይኖር ንብረታቸውን እያመጡ ለሐዋርያት ማኅበር ይሰጡ ነበር፡፡ እንደዚሁ ያለውን ርዳታ

ካደረጉት መጀመሪያው ሰው ከቆጵሮስ የሄደው አይሁዳዊ በርናባስ / ዮሴፍ / ነበር፡፡ የሐዋ. ሥራ 2÷42-47 ፣4÷32-37 ይህ ዓይነት

የክርስቲያኖች ዕርዳታ ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለአይሁዳዊውም ሆነ ለአረማዊ ልዩነት ሳይኖር ይሰጥ ነበር፡፡ ከዐራተኛው መቶ

ክፍ  ዘመን ጀምረው በአሕዛብ ምድር የነበሩ ኤጴስ ቆጶሳት ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮም በኩል ያላትን ድርሻ ለመፈጸም

በቤተክርስቲያን  አካባቢ የድኩማን መርጃዎችን፣ የሙት ልጆችን ማሳደጊያ ፣ የሽማግሌዎ መጦሪያ ፣ የህሙማን ማስታመሚያዎችን

ያዘጋጁ ነበር፡፡

ለምሳሌ ፡- ቅዱስ ባስልዮስ የቂሣሪያ ኤጴስ ቆጶስ በስሙ የሚጠራ የሕሙማን ማስታመሚያ አሠርቶ ነበር፡፡

5ኛ.አይሁድ ክርስቲያኖችን ገሊላውያን፣ ናዝራውያን ይሏቸው ነበር፡፡ ክርስቲያኖችን ግን ወንድሞች ፣ ደቀመዛሙርት እየተባባሉ ይጠራሩ

ነበር፡፡ የሐዋ.  ሥራ 1÷15፣ ክርስቲያን መባል ግን በኋላ በአንጾኪያ የተጀመረ ነው፡፡ ዮሐ.ሥራ 11÷26 የአሕዛብን ትዕቢትና ኩራት

የክርስቲያኖች ኃይል አፈራረሰው፡፡ የአሕዛብን የአመንዝራነት ኃይል የክርስቲያኖች ቅድስና አሸነፈው፡፡

7 ዲያቆናት ምርጫ

ዓለምን ያስደነቀው በነገሩ የመጀመሪያ ክርስቲያኖች መካከል ታላቅ ሐሜትና መነቃቀፍ ስለተነሣ ሐዋርያት ሀሳብ አቅርበው ዲያቆናት እንዲመረጡ ተደረገ፡፡

በዚህም መሠረት በመልካም የተመሠከረላቸው ጥበብን የተሞሉ የጋለ መንፈሳዊ ቅናት ያላቸው መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ሰባት ሰዎች ምረጡ አሏቸው ሐዋርያትም ሰባቱን እጃቸውን ጭነው በጸሎት ሾሟቸው እነርሱም፡- 1. እስጢኖፋኖስ 2. ፊልጶስ 3. ጵሮኮሮስ 4. ኒቃሮና 5. ጢሞና 6. ጰርሜና 7. ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረው የአንጾኪያው ኒቆላዎስ ናቸው፡፡ የሐዋ. ሥራ 6÷5

ከእነዚህ መካከል ታሪካቸው በመጻሕፍትም ሆነ በተለያዩ ነገሮች ጎላ ብሎ የሚገኘውን የሁለቱን ዲያቆናት ታሪክ እንመለከታለን፡፡

ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ

እስጢፋኖስ ማለት በግሪክ ቋንቋ አክሊል፣ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው መብራት ማለት ነው፡፡ አባቱ ስሞዖን እናቱ ሐና ሲባሉ፣ የተወለደው ጥር 1 በእስራኤል ሀገር ውስጥ በብፅዐት /በስዕለት/ ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ ወደ ኦሪት ምሁር ገማልያል ዘንድ በመሄድ ብሉይ ኪዳንን፣ በኋላም ከመጥምቁ  ቅዱስ ዮሐንስ ሐዲስ ኪዳንን ተምሯል፡፡

እስጢፋኖስ ጥቅምት 17 ቀን በዋናነት ሊቀ ዲያቆናት ተብሎ ተሾመ፡፡  ቅዱስ እስጢፋኖስ ፍጹም እምነት ያለውና የጋለ መንፈሳዊ ቅናትና ተአምር የማድረግ ጸጋ ነበረው፡፡ የሚናረገውና የሚያስተምረው በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ስለነበር፣ በመቃወም ይከራከሩት የነበሩትን መልስ ስላሳጣቸው በቅናት መንፈስ በመመራት ይህ ሰው የሙሴን ሕግ ይነቅፋል እግዚአብሔርን ይሰድባል ብለው የሐሰት ምስከሮች አሰነሱበት፡፡ የሐዋ. ሥራ 6÷13-14 ያን ጊዜ የተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ ትኩር ብለው በተመለከቱት ጊዜ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበር፡፡ የካህናት አለቃው ለተጠየቀው መልስ እንዲሰጥ ቢጠይቀው ስለተከሰሰበት መልስ በመመለስ ፋንታ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የቅዱሳት መጻሕፍት ጽሑፍ በሚገባ ተረከላቸው፡፡ በዚህም ጉባዔ 8000 ሰዎችን አሳመነ፡፡ እነዚህም ማኅበረ እስጢፋኖስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ለአይሁድም  ቅዱስ እስጢፋኖስ የተገለጠለትን ምሥጢር እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ ‹‹እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦ አያለሁ›› የሐዋ. ሥራ 7÷55 አይሁድ እነዚህን ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ ስድቦች በመቁጠር እንደ ክረምት በረዶ በላይ ላይ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱበት ‹‹ ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው›› የሐዋ. ሥራ. 7÷60 ሲል ጸለየላቸው ፡፡ ከዚህ በኋላ ይህንን ተናግሮ አረፈ፡፡ ዕረፍቱም ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ዕረፍቱም ልደቱም አንድ ቀን ነው፡፡ በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት በተለያዩ ሀገሮች የተሰደዱት ክርስቲያኖች በየሄዱበት ስላስተማሩ ይህ ስደት ክርስቲያኖችን በማጥፋት ፋንታ ለክርስትና መስፋፋት በጣም ጠቀመ፡፡

ዲያቆኑ ፊልጶስ

ፊልጶስ የተመደበው በቂሣርያ የወደብ ከተማ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም በነበረችው ቤተክርስቲያን በቅዱስ እስጢፋኖስ ዕረፍት ምክንያት ክርስቲያኖች በየሀገሩ ሲበተኑ ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ መጥቶ ብዙ ሰዎችን አስተምሮና ተአምራት አድርጎ አጠመቀ፡፡ በጥንቆላ ሥራው ሰዎችን ያታልል የነበረው ሲሞን መሠርይ ሰዎች እየተውት ወደ ቤተክርስቲያን በመመለሳቸውና ብቻውን በመቅረቱ የፊልጶስም ትምህርትና ተአምራት ስለአስገረመው አብሮ ከሕዝቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ፡፡ የሐዋ. ሥራ 8÷13-24

ፊልጶስ ከሰማርያ ወደ ጋዛ እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስ ስለአዘዘው ወደዚያ ሄደ፡፡ በዚያም መንገድ ላይ የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የሆነ በሰረገላ ተቀምጦ አግኝቶት አስተምሮ ከነ አጃቢዎቹና ተከታዮቹ አጥምቆታል፡፡ የሐዋ. ሥራ 8÷27-40 ቀጥሎም ፊልጶስ በአካባቢው የነበሩትን ሀገሮች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቆይቶ ወደ ሀገሩ በመመለስ የሐዋ . ሥራ 21÷8-9 በቂሣርያ ለብዙ ዓመታት ካስተማረ በኋላ በዚያም አርፎአል፡፡ ብዙ ጸሐፊዎች ፊልጶስን ከዲያቆኑ ፊልጶስ ጋር አንድ ያደርጉታል ነገር ግን አይደለም፡፡

ይቀጥላል

 

 

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ

 

 

 

ክርስቶስ ሲወለድ ምድረ ፍልስጥኤም እንደሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የሰሜን አፍሪካና የታናሽ እስያ አገሮች በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች፡፡ በውስጥዋ የነበሩ ሕዝቦችም የተከፋፈለ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድን ነበራቸው፡፡ ከእነዚህም የሃይማኖት ቡድኖች ዋና ዋናዎቹ እሴዎች፣ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያን ነበሩ፡፡

ፈሪሳውያን

ፈሪሳዊ ‹‹ፖራሽ›› ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የተለየ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች አፍአዊ ትዕዛዛትን ብቻ በመጠበቅ የሕግ ፈጻሚ መስለው የሚታዩ እንደነርሱ አመለካከት (ወይም እምነት) የማይሄደውን የሚወቅሱ፣ የሚከሱ ነበሩ፡፡ ፈሪሳውያን ምንም የቅኝ አገዛዝ ቀንበር መላልሶ ቢያደቃቸውም ባህልና ልማዳችን ጭራሽ አይነካም የሚሉ ነበሩ፡፡ ማቴ. 15፥1-20።

በሃይማኖት በኩልም የሙሴ የሕግ መጻሕፍትንና የነቢያትን የትንቢት መጽሐፍ የምንቀበል እኛ ብቻ ነን፣ ፈጻሚዎቹ እኛ ነን ይላሉ፡፡ ከአይሁድ ዘር ውጭ የሆነ ከማንኛውም ጎሣና ዘር ጋር በባህልና በሥልጣኔ መቀራረብን እንደመርከስ ሕግን እንደመተላለፍ ይቆጥሩ ነበር፡፡ እንዲሁም የመሲህን መምጣት ነቅተው ተግተው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ከትንሣኤ ሙታን በኋላም ሥጋዊ ኑሮ አለ ብለው ቢያምኑም ነገር ግን ትንሣኤ ሙታንን ያምናሉ፡፡ በኑሯቸውም መካከለኛ ኑሮ የሚኖሩ     መጠነኛ እውቀትና ብዙ ሀብትም የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የመሲህን መምጣት ይጠባበቁ የነበሩት የጦር ኃይል አቋቁሞ የጦር አበጋዝ ሆኖ ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ያወጣናል ብለው ያስቡናል ይመኙ ነበር፡፡

  ሰዱቃውያን

ሰዱቃውያን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ማየየፈሪሳውያን ተቃራኒ ናቸው፡፡ ቡድኑም የሀብታምና የካህናት ቡድን ነው፡፡ ስለ ሥነ-ሥርዓትና ስለ ሃይማኖት ግድ የለሾች ነበሩ፡፡ ከቅኝ ገዥዎችም ጋር ተስማምተው ከእነርሱ ሥልጣን ለመጠቀም ብቻ የሚፈልጉ ነበሩ፡፡ ከሃይማኖት መጻሕፍትም የሙሴን ሕግ ብቻ ይጠቀሙ ነበር፡፡ በራሳቸው አስተያየትም ይተረጒሙት ስለነበር በትንሣኤ ሙታን፣ በመናፍስትና በሚመጣው ዓለም ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይቀበላል የሚለውን አይቀበሉትም አያምኑበትም ነበር፡፡ ማቴ 22:23-33፣ ዘዳ 25:5-10፣ የሐዋ ሥራ 23:8፣ ማር 12:19፣ ሉቃስ 20:28

ኤሳዎች /ኤሲያውያን/

እነዚህ ወገኖች ደግሞ የመናንያን ማኅበር ነበሩ፡፡ ከፈሪሳውያን ጋር በአስተሳሰብ ተጣልተው ከፈሪሳውያን የተገነጠሉ ነበሩ፡፡ ኩምራን በምትባለው ቦታ በሙት ባህር /ጨው ባህር/ የሎጥ ባህር አካባቢ ገዳም ገድመው ክርስቶስ ሲመጣ በተአምራት ከጠላቶቻችን እጅ ነፃ ያወጣናል ባዮች ነበሩ፡፡ በገዳማቸውም ውስጥ በጾም በጸሎት በትህርምት ተወስነው የሚኖሩ ነበሩ፡፡

የመሲህ መምጣት ተስፋ

ትንቢተ አብርሃም፦ “በዘርእከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር” የሚል ተስፋ ተነግሮት ስለነበረና የክርስቶስን ሰው መሆን ሥጋን ለብሶ መታየቱን ደጅ ይጠና ስለበረ “በመዋዕልየኑ ትፌኑ ወልደከ፣ ወሚመ አልቦ” ልጅህን በእኔ ዘመን ትልከዋለህን ወይስ በሌላ ጊዜ? ብሎ ምኞቱን በትንቢት ገልጿል። ዘፍ. 12፥3፣22፥18

ትንቢተ ሙሴ፦ “ነቢየ ያነሥእ ለክሙ እግዚአብሔር እምአኀዊክሙ ዘከማየ ወሎቱ ስምእዎ ” እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ ወገን እንደኔ ያለ መምህር /ነቢይ ያስነሳላችኋል ብሎ የተነበየውን ምሳሌውንም በነበልባልና በሐመልማል አምሳል አይቷል።  ዘጸ. 3፥4

ትንቢተ ዳዊት፦ “ ተዐውቀ እግዚአብሔር በይሁዳ፣ ወዐብየ ስሙ በእሥራኤል” እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ ስሙም በእሥራኤል” ከፍ ከፍ አለ። ይልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ በቤተልሔም እንደሚወለድ ገልጾ “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ፣ ወረኩበናሁ ውስተ ጾመ ገዳም እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ በዱርም ምድረ በዳ አገኘነው በማለት ተንብዮአል። መዝ∙75፥1፣131፥6።

ትንቢተ ኤርምያስ፦  “ለሊሁ ኢየሱስ አምላክ ወልደ አምላከ ይመጽእ ወየኀሪ ዐሠርተ ወክኤልተ ሐዋርያተ  ወይከይድ ውስተ ደብረ ዘይት ዘአነ ርኢኩ ሥግወ ”እርሱ ኢየሱስ አምላክ የእግዚብሔር አብ የባህርይ ልጅ ወደዚህ አለም ይመጣል ። አምላክ  12 ሐዋርያትን ይመርጣል።  ሰው ሆኖ  ደብረ ዘይት ሲመላለስ አየሁት   በማለት ተንብዮአል  (ተረፈ ኤርምያስ 11፥51-52)

ትንቢተ ዕዝራ፦ “አንበሳ ተንሥአ እመ ገዳም ውእቱኬ ወልድ ውእቱ” አንበሳ ከገዳም ተነሣ ይኸውም ወልድ ነው። መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 11፥37

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ነቢያት በምሳሌ የመሰሉትንና የተናገሩትን  ትንቢት ከዐበይት ነቢያት አንዱ  የሆነው ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሰባት መቶ ሃምሳ ዘመን ላይ “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዪዮ ስሞ አማኑኤል” እነሆ ድንግል  ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ብሎ አምልቶ፣ አስፍቶ አጉልቶ ገልጾታል። ኢሳ. 7፥14

ዓለም በዚህ በተመሰቃቀለ ማኅበራዊ ኑሮ ሲኖር ከቶ ደስ ብሎት በኑሮው አምኖበት የሚኖር ማንም አልነበረም፡፡ ብዙ ነቢያት ስለ መሲህ መምጣት ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ ይህ ትንቢት የተጠቀሰው በእስራኤል ተስፋ ብቻ በመሆኑ የእስራኤል ተስፋ አሁንም መሲህ መጥቶ ከአለባቸው ችግር እንዲያድናቸው ከሮማውያን የባርነት ግዛት ነፃ እንዲያወጣቸው በተስፋ ይጠብቁ ነበር፡፡

አረማውያን ደግሞ የሰውን ጨካኝነት የክፋቱን ብዛት ከቀን ወደ ቀን እየባሰ መሄዱን አይተው ከአምላክ አንድ ምሕረት ካልተላከ በቀር በሰው ኃይል ድኅነት ሊደረግ የማይችል እንደሆነ ያውቁ ነበር፡፡

የእስራኤል ተስፋ ሙሉ ቢሆንም መሲህ እንደሚመጣ ተስፋ ቢያደርጉም የመሲህን መምጣት ይጠባበቁ የነበረው አንድ መሲህ ተነስቶ አገሯን ከባዕድ አገዛዝ ነፃ አውጥቶ የዳዊት የሰሎሞንን መንግሥት መልሶ በሰላም የሚያስተዳድር አድርገው ያስቡ ነበር እንጂ አምላክ ወልደ አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሆኖ ዓለምን እንደሚያድን አያምኑም ነበር፡፡

የሰው ወገን የሆነ ሁሉ ደክሞት  እና መኖር ሰልችቶት ሁሉም በየበኩሉ ይቆዝም ነበረ፡፡ ሀብታሙ በሀብቱ ደስታን ለመሸመት አልሆንለት ብሎ መበለታትን ወዴት ወደቃችሁ የሚላቸው አልነበረም፡፡ በሽተኞችና ረሀብተኞች ጥርኝ ውኃ  ኩባያ ጥሬ የሚላቸው አጥተው በረኃብ ያልቁ ነበር፡፡

ዓለም በዚህ መልክ በሚገኝበት ወቅት በጭንቀት ጊዜ የቤተክርስቲያን መሥራች፣ የአሕዛብ ብርሃን የእስራኤል ዘነፍስ ክብር፣ የዓለሙ መድኃኒት የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም /ወላዲተ አምላክ/ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር በነበረች በፍልስጥኤም ልዩ ስሟ ቤተልሔም በምትባል በዳዊት ከተማ ክፍል በሥጋ ተገለጠ ማለት ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ ሉቃ.20፥10። እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች “ኢሳ. 14 ሕፃን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የሰላም አለቃ ነው። ኢሳ. 9፥6  መዝ. 72፥11- ዘካ 9፥2።

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የዘመነ ሥጋዌ ጉዞ ብሥራት፡-:

እግዚአብሔር መንፈሱን የሚያሳርፍበት የበቃ ሰው ባልነበረበት ጊዜ በነፍስም በሥጋም  ንጽሕት ድንግል የሆነች የእግዚአብሔርን ቃል በማኅፀኗ ለመሸከም የበቃች በናዝሬት ከተማ የምትኖር አንዲት ድንግል ነበረች፡፡ የዚህችም ድንግል ስሟ ማርያም ነበር፡፡ ሉቃስ 1፥27፡፡ እግዚአብሔር የዓለሙ ድኅነት ፈቃዱ ስለሆነ ለዚህ ዓለም ድኅነት ምክንያት ይህችን ድንግል መረጠ፡፡ ስለዚህም በፊቱ የሚቆመውን ባለሟሉን  መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤልን የምሥራች ይናገር ዘንድ ወደ እርሷ ላከ፡፡ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብር ኤልም  ወደዚያች ድንግል በደረሰ ጊዜ «ደስ ይበልሽ ጸጋ  የሞላብሽ ሆይ  ጌታ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው: አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት» ሉቃስ 1፥28 ቅድስት ድንግል ማርያም እውነተኛ ስለነበረች በውዳሴ ከንቱ አልተጠለፈችም፡፡ ስለዚህ ወዲያውኑ አልተቀበለችውም ነበርና እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ«ወንድ የማላውቅ ስሆን ይህ እንደምን ይሆናል?» ብላ ጠየቀችው፡፡ መልአኩም የተላከበት ታላቅ መልእከት ነውና በብዙ አስረጂ

 1.  መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ ወዘኒ ይትወለድ እምኔኪ

ቅዱስ ውእቱ ወልድ  እግዚብሔር ልዑል:: «መንፈስ ቅዱስ በአንች ላይ ይወርዳል የልዑል ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደወ

ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል»::

 1.   ወናሁ ኤልሳቤጥኒ እንተ እምአዝማድኪ ይእቲኒ ፀንሰት ወረከበት ወልደ በልህቃቲሃ ወበርስአቲሃ

ወናሁ ሳድስ ወርኀ ለአንተ ይብልዋ መካን

«እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች። ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህው ስድስተኛ ወር ነው»::

 1. እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም በማለት አበሠራት።»

አላት፡፡ ቅድስት ማርያምም «በእርግጥ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና እነሆ የእግዚአብሔር ገረዱ  አለሁኝ እንደቃልህ ይሁንልኝ» አለችው፡፡ ሉቃስ 1፥37፡፡ በዚህ ጊዜ አካላዊ ቃል ቃለ እግዚአብሔር ወልድ  የሰው ሕሊና ሊወስነው በማይችለው ፍጥነት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በማኀፀኗ ተቀረፀ። ይኸም በላይ ሳይጐል  በታች ሳይጨምር ነው፡፡

የኤልሳቤጥ ምስክርነት፡-

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመልአኩን ብሥራት እንደሰማች ወዲያውኑ አክስቷ ኤልሳቤጥ ወደምትገኝበት ወደ ይሁዳ ሄደች፡፡ ሉቃስ 1፥39፡፡ ከኤልሳቤጥም ዘንድ ደርሳ ሰላምታ እንደተሰጣጡ በኤልሳቤጥ ላይ መንፈስ ቅዱስ ሞላባትና የመልአኩ ቅዱስ ገብርአልን ቃል በመድገም «አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ የማህፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው» ብላ ብፅዕናዋን ቅድስናዋን የጌታም እናት መሆኗን ተናገረች፡፡ ሉቃስ 1፥41-45፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሰማያውያን መላእክት የመልአኩ ቅዱስ ገብርአልን ከሰብአ ዓለም የቅድስት ኤልሳቤጥን ከሁለቱም ወገን ምስክር ስላገኘች ለፈጣሪዋ ለልጃ ምስጋና አቀረበች፡፡ ሉቃስ 1፥46-55፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፡-

በሮማ አውግስጦስ ቄሣር በነገሠ በሶርያም ቄሬኔዎስ ገዥ በነበረበት ጊዜ በኢየሩሳሌምና በአውራጃዋም ሄሮድስ በነገሠ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እንዲቆጠር /እንዲጻፍ/ ቄሣር በሰጠው አዋጅ የእመቤታችንና የቅዱስ ዮሴፍ አገር ይሁዳ /በተልሔም/ ነበርና በአዋጁ መሠረት ሊቆጠሩ እንደመጡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወለደ፡፡ ሉቃስ 2፥1፡፡ ለቆጠራው የመጣው ሰው በዝቶ ቦታውን ይዞት ስነበር እመቤታቸንና ዮሴፍ ማደሪያ አጥተው በአንድ በረት እንደሠፈሩ የጌታችን ልደት በዚያው በበረት ሆነ፡፡ ሆኖም አምላክ ነውና እንደ አምላክነቱ ከእንስሳት ወገን ላህምና አህያ እስትንፋሳቸውን ገበሩለት፡፡ ሉቃስ 2፥8-20፡፡ የሰማይ ሠራዊት ደግሞ «ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ» እያሉ በምስጋና ተቀበሉት፡፡ ተቋርጦ የነበረው ሥራቸው ተጀምሯልና፡፡ እረኞችም ከብርሃኑ ብዛት ከሰማይ ሠራዊትም ምስጋና ድምጽ የተነሳ ይደነቁና ምስጋናም ያቀርቡ ነበር፡፡ ሉቃስ 2፥8-20፡፡

እንዲሁም የጥበብ ሰዎች ከምሥራቅ ረጅም ጉዞዋቸው መጥተው ሰገዱለት ወርቅ ለመንግሥቱ ዕጣን ለክህነቱ ከርቤም ለሞቱ ምሳሌነት አድርገው ገበሩለት፡፡ ማቴ 2፥1-12፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የሆነውን ሁሉ ታስተውል በልብዋም ትጠብቅ ነበር፡፡ ታላላቅ ተአምራት ሲያደርግ አይታለችና፡፡ ይኸውም በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና መውለድ፣  የሰማይ ሠራዊት መጥተው ምስጋና አቅርበውለታል። ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር እያሉ ሉቃ 2፥19፡፡ ወተመይጡ ኖሎት እንዘ ይሴብሕዎ ወየአኵትዎ ለእግዚአብሔር በእንተ ኵሉ ዘርእዩ ወሰምዑ ይህን መሠረት በማድረግ ኢትዩጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ርእይዎ ኖሎት አእኰትዎ መላእክት ለዘተወልደ እምቅድስት ድንግል ብሎ ዘምርል

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግን እየፈጸመ ማደጉን

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስምንተኛው ቀን ተገረዘ፡፡ ሉቃስ 2፥21፡፡ በዐርባ ቀንም ወደ ቤተ መቅደስ ተወሰደ፡፡ እዚያም ስምዖን አቀፈው ሐናም አየችው፡፡ ሉቃስ 2፥21-38፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶ ስደት ወደ ግብፅ

የምሥራቅ ሰዎች  የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው የተወለደው እያሉ የክርስቶስን ንጉሥነት እየመሰከሩ ስለመጡ ማቴ 2፥14 ርጉም ሄሮድስ ጌታን ንጉሥ ከሆነማ «ንጉሥ ሳይገድል አይነግሥም በኔ ላይ የሚሰለጥን እንዴት ያለ ንጉሥ ተወለደብኝ» በማለት ጌታን ይገድል ዘንድ አሰበ፡፡ ስለዚህም ወደ ግብጽ እንዲሰደዱ ምክሩን የሚለግስ መልአክ ከእግዚአብሔር ታዘዘ፡፡  እርሱም በሌሊት በራዕይ ለዮሴፍ ታየው፡፡ ተናገረውም እንዲህ ሲል ተነሣና «እናቱንና ሕፃኑን ይዘህ በሌሊት ወደ ግብፅ ሽሽ ሄሮድስም ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና» አለው፡፡ ዮሴፍ  እንደ ታዘዘው ቅድስት ድንግል ማርያምንና ሕፃኑን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ ተሰደደ፡፡ ማቴ 2፥13-15 ሆሴዕ 11፥1፡፡ ከዚያም ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር 3 ዓመት ከመንፈቅ ቆየ ርጉም ሄሮድስ እንደሞተ ያው መልአክ ለዮሴፍ ከግብፅ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለስ አመለከተውና ስለሆነም ወደ ናዝሬት ሄዶ ጌታም በዚያ አደገ፡፡ ማቴ 2፥23፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ የክርስቶስ የሕፃንነቱ ጊዜ

ከግብፅ ስደት ከተመለሱ በኋላ ጌታችንና ቤተሰቦቹም መኖሪያቸው ናዝሬት ነበር፡፡ ማቴ 2፥23፡፡ ናዝሬትም የገሊላ አውራጃ ከተማ ነበረች፡፡ እንደሌሎች አውራጃ ከተሞች ዝነኛ አልነበረችም፡፡ ስለዚህ አረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ የዕለት ምግቡን ያገኝ የነበረው እንጨት እየጠረበ ለቤት አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን እየሠራ በመሸጥ ነበር፡፡ ጌታችንም በዚህ በናዝሬት አደገ ጥበብን እየተሞላ በመንፈስ እየጠነከረ ይሄድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ግዕዘ ሕፃናትን አላፋለሰም፡፡ እንደማኝኛውም ሕፃን ቀስ በቀስ እያለ ነው ያደገው፡፡

በ12 ዓመቱ ከዘመዶቹ ጋር ለበዓል ኢየሩሳሌም ሄዶ እንደነበር እናገኛለን፡፡ ሉቃስ 2፥41-51፡፡ ምክንያቱም እመቤታችንና ዮሴፍ በእየዓመቱ እንደ አይሁድ ሥርዓት /ልማድ ለበዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበርና፡፡  በዓመት ሦስት ጊዜ በእናንተ ዘንድ ያለ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ትል ስለነበር፡፡ ኦሪት ዘፀ 23፥14-17፡፡

በዚያም በኢየሩሳሌም በሊቃውንቱ መካከል ሆኖ ሲጠይቃቸውም ሲሰማቸውም ተገኝቷል፡፡ ሉቃስ 2፥46-48፡፡ ይህም ማለት የዕብራውያንን ሥርዓት በመከተል የዕብራውያንን ትምህርት እየተማረ እንዳደገ ያስረዳል፡፡ አባ ሕርያቆስ ይህን ሲያስረዳ «የዕብራውያንን ሕግ ተማረ» ብሏል፡፡ ስለዚህ የዕብራውያን ሕግ የፀና ሆነ፡፡ ጌታችንም በዚህ በናዝሬት እየኖረ በጥበብም በቁመትም አደገ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስን አገኘ ቤተዘመዶቹን ይታዘዝ ያገለግልም ነበር፡፡ ሉቃስ 2፥25፡፡ እስከ ሠላሳ ዓመት ዕድሜው  በዚያው በናዝሬት ኖረ፡፡ በዚህም ዘመን ሰው የሚሠራውን ሁሉ ከኃጢአት በቀር ሠራ፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ከኃጢአት ብቻ በቀር የሰውን ሕግ ሁሉ ፈጸመ እንዳለ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ የክርስቶስ ጥምቀት

ጌታችን የሕፃንነቱን ዘመን ፈጽሞ ልክ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው የይፋ ሥራውን ለመሥራት ከናዝሬት ወጣ ወደ ይሁዳም ሄደ፡፡ የይፋ ሥራውንም በጥምቀት ጀመረ፡፡ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ምድረ በዳ «ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት» ንስሓግቡ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና እያለ እያስተማረ ወደ እርሱ የሚመጡትን ሁሉ የንስሐ ጥምቀት እያጠመቀ የክርስቶስን መንገድ እየጠረገ እያዘጋጀም መጣ፡፡ ክርስቶስ ከዮሐንስ ጋር በተገናኘ ጊዜ እንዲያጠምቀው ጠየቀው ዮሐንስ ግን «እኔ በአንተ ልጠመቅ እወዳለሁ እንጂ አንተ ከኔ እንዴት ትጠመቃለህ» ሲል አይሆንም አለው፡፡ ጌታችን ግን አንድ ጊዜ ተው የምልህን ስማ አለው። አብረው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዱ ዮሐንስ አጠመቀው ጌታችንም ተጠመቀ፡፡ ማቴ 3፥13-17 ማር 1፥9-11 ሉቃስ 3፥21-23 ዮሐ.1፥32-34 ኢሳ. 40፥3፡፡

ጌታችንም ተጠምቆ ከውኃ እንደወጣ ከሰማይ ቃል መጣ፡፡ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር «ይህ ነው የምወደው ልጄ» የሚለውን መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ ታየ፡፡ በዚህን ጊዜ ሦስትነቱ ተገለጠ ማለትም ወልድ ሲጠመቅ አብ በሰማይ ሆኖ ድምጽን ሲያሰማ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ሲያርፍበት፡፡

 የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ የክርስቶስ ጾም

ክርስቶስ እንደተጠመቀ ወዲያውኑ በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፡፡ በዚያም 40 መዓልት 40 ሌሊት ጾመ፡፡ ከዚህ በኋላ ተራበ፡፡ ፈታኙ ሰይጣንም እንደተራበ ባየ ጊዜ አዳምን በመብል እንዳሳትኩት ክርስቶስንም በምግብ አስታለሁ ብሎ «የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እነዚህን ድንጋዮች ኅብስት እንዲሆኑ እዘዝ» አለው፡፡ ክርስቶስ ግን ለፈቃዱ አልታዘዘለትም እንዲያውም «ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ከእግዚአብሔር በሚወጣው ቃልም ነው እንጂ» ሲል መለሰለት ማቴ. 4፥4 ዘዳ 8፥3 ሁለተኛም ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ  «ከዚህ ዘለህ ውረድ ስለ አንተ መላእክትን ያዛቸዋል በጎዳናህ ሁሉ እንዲጠብቁህ እግርህም እንቅፋት እንዳትሰናከል የሚል ጽሑፍ አለና» አለው፡፡ ጌታችንም መልሶ  «ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አትፈታተን» የሚለውን መለሰለት፡፡ ማንኛውም የማይገባውን እየሠራ እግዚአብሔር ይህን ያደርግብኛል የሚለው ሁሉ የማይረባ መሆኑን ጠቅሶ አስረዳው፡፡ ማቴ 4፥5-7 መዝ. 90፥11-12፡፡ ሦስተኛ እንደገና ከረጅም ተራራ አወጣውና የዓለምን መንግሥታት ክብራቸውን አሳይቶ  «ለኔ ብትታዘዝ ብትሰግድልኝ ብታመልከኝ ይህን ሁሉ ለአንተ እሰጥሀለሁ» ብሎ በሚያስጎመጅ ሁኔታ ገለጠለት፡፡ ጌታችን ግን ከክብር ዙፋን የወረደው ወደ እዚህ ዓለም የመጣው ለሰው ድኅነት እንጂ ለራሱ ክብር አይደለምና ሰይጣን ባላጋራዬ ወግድ ከኋላዬ ሲል ለአምላክ የአምልኮ ስግደት መስገድና አምላክን ብቻ ማምለክ እንደሚገባ አስረድቶ ለጊዜው  ሰይጣን ከሱ ራቀ፡፡ የፈጣሪ መላእክቱም ሊያገለግሉት መጡ፡፡ ማቴ. 4፥11፡፡

 የቅዱሳን የሐዋርያት መጠራት

 • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ለሊሁ ኢየሱስ አምላክ ወልደ አምላክ ይመጽእ ውስተ ዓለም ወየኃሪ ፲ወ ፪ ሐዋርያተ ወይከይድ ውስተ ደብረ ዘይት ዘአነ ርኢኩ ሥግወ» ብሎ በነቢዩ ኤርምያስ «እርሱ ኢየሱስ አምላክ የእግዚብሔር አብ የባህርይ ልጅ ወደዚህ አለም ይመጣል ። አምላክ 12 ሐዋርያትን ይመርጣል።  ሰው ሆኖ  ደብረ ዘይት ሲመላለስ አየሁት   በማለት ተንብዮአል  (ተረፈ ኤርምያስ 11፥51-52)
 • ወናሁ ይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር ወየኃሪ ፲ወ፪ተ ሐዋርያተ ዕፀወ ባሎጥ ብሎ በነቢዩ ቅዱስ ኤልሳ ያናገረውን ትገቢት ለመፈጸም፤
 • ጌታ ባሕርየ መላእክትን ባሕርይ ሳያደርግ የአዳምን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ሾመ። ኢነሥኦ ለዘነሥኦ እመላእክት ዘእንበለ ዳዕሙ እምዘርአ አብርሃም ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ።
 • ክርስቶስ ጾሙን ከፈጸመ በኋላ በደዌ የገባውን ሰይጣን በታምራት በክህደት የገባውን ሰይጣን በትምህርት ያወጡ ዘንድ 12 ሐዋርያትን (ደቀ መዛሙርቱን) ጠራ፤ ሾመ። ገሚሱን በዓሣ አጥማጅነት ተሰማርተው ሲሠሩ እነ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ እንድርያስ፣ ቅዱስ ያዕቆብ፣ ወልደ ዘብዴዎስ፣ ወንድሙ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ማቴ. 4፥8-22 ማር. 1፥20 ሉቃስ 5፥2-11/ ሌላውም እንዲሁ ከመቅረጫው ቅዱስ ማቴዎስ ወልደ እልፍዮስ ማቴ. 9፥9 ማር. 2፥14 ሉቃስ 5፥27፡፡ ሌላውም እንዲሁ በመንገድ እያለ የክርስቶስ ጥሪ የደረሰውና ለመከተል ፈቃደኛ ሆነው ቤተ ሰዎቻቸውን እየተሰናበቱ ተከተሉት፡፡ ዮሐ. 1፥34-53፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጸመው ከጾሙ በኋላ ባሉት ቀናት ባደረገው ትምህርት ነው፡፡ ማር. 3፥13-19 ሉቃስ 6፥14-16፡፡

የመጀመሪያው ተአምር

በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ተአምር ሆነ፡፡ በዚያም ጌታችን ተገኝቶ የመጀመሪያውን ተኣምር አደረገ፡፡ በሠርጉ ላይ እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 12ቱም ሐዋርያት ተገኝተዋል፡፡ ሠርገኞች በግብዣውም የወይን ጠጅ ባለቀባቸው ጊዜ በእመቤታችን አማላጅነት ዘመዷ የሠርጒ ባለቤት የሆነው ዶኪማስን ልጇን ጌታችንን  በአማላጅነቷ ለምና ከውርደትና  ከሽሙጥ አድናዋለች፡፡ዮሐ. 2፥1-11፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት

 አንቀጸ ብፁዓን

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንት ብፁዓን እለ ንጹሓን በፍኖቶሙ (በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ) ወእለ የሐውሩ በሕገ እግዚአብሔር (በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ) ብፁዓን  እለ የኀሡ ስምዖ (ምስክሩን የሚፈልጉ ምስጉኖች ናቸው) መዝ 118 (119)  እያለ በነቢያት ያናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ  ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አምላክ ወሰብእ ፍጹም ሰው ፍጹም  አምላክ ሆኖ በላይ ሳይጐድል በታች ሳይጨምር በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ አንቀጸ ብፁዓንን አሰተምሯል፤ በመሆኑም። የተራራው ስብከት በመባል የሚታወቀው እንደ ቤተክርስቲያናችን ስያሜ አንቀጸ ብፁዓን እየተባለ የሚጠራውን እንደ መጀመሪያ አዋጅ አድርጎ «ብፁዓን ብፁዓን» እያለ እውነተኛውን የክርስትና ትምህርት በዚህ መልክ አስተማረ፡፡ እመቤታችንም እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል አለች፡፡ሉቃ.1፥48 ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው ይላል ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የሐ ሥራ.20፥35።

ይህ ትምህርት ፍጹም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ የፍጹምነት ትምህርት ነው፡፡ የክርስትናውም አርነት ፍጹም ነውና አንድ የመንግሥት መሪ መንግሥት እንደያዘው የሚያውጀው የመንግሥቱን ዓላማ ነው፡፡ ክርስቶስ በመጀመሪያው የክርስትናውን ዓላማ ይህንንና ይህን ሠርቶ የፈጸመ ብፁዕ ነው በማለት እውነተኛውን ክርስቲያናዊ ትምህርት አስተማረ ምንም በተለያዩ ቦታዎች ብፁዓን ቢጠሩም በዚህ በተራራው ትምህርት ጊዜ የተገለጡት እንደ ቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ ዘጠኝ ናቸው፡፡  ማቴ.5፥3-12፡፡

ትምህርቱ በምሳሌ

ጌታ ከጥንት «እከሥት በምሳሌ አፉየ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት» (በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ መዝ 77፥2 በማለት በነቢዩ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ያናገረውን በዘመነ ሥጋዌው ተግባራዊ አድርጐታል። በመሆኑም ጌታችን  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲሁ ቢገባው ይግባው ካልገባውም ይቅር በማለት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሁሉንም በሚገባው በምሳሌ ያስተምር ነበር፡፡ ለምሳሌ ገበሬዎችን በእርሻ «ናሁ ወጽአ ይዝራእ ዘይዘርእ ወእንዘ ይዘርእ ቦ ዘወድቀ ውስተ ፍኖት፤ ወቦ ዘወድቀ ዲበ ኰኲሕ ፤ ወቦ ዘወድ ውስተ ሦክ ወቦ ዘወድቀ ውስተ ምድር ሠናይ /እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ ሲዘራ  በመንገድ ዳር የወደቀ አለ፤ በጭንጫ ላይ የወደቀ አለ፤ በእሾህ  መካከል የወደቀ አለ፤ በመልካም መሬት ላይ፤ የወደቀ አለ» ፤እያለ አስተማረ።

ሴቶችን፦« ትመስል መንግሥተ ሰማያት ብኍአ ዘነሥአት ብእሲት ወአብኀአቶ ውስተ ሠለስቱ መሥፈርተ ሐሪጽ ወአብኅአ ኩሎ (መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈርያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።

ነጋዴዎችን፦ ትመስል መንግሥተ ሰማያት ብእሴ ሠያጤ ዘየኃሥሥ ባሕርየ ሠናየ (መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች።

ዓሣ አጥማጆችን ፦ ትመስል መንግሥተ ሰማያት ገሪፈ እንተ ተወድየት ውስተ ባሕር ወአሰተጋብአት እሞኵሉ ዘመደ ዓሣት (መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች በማለት እየመሰለ አስተምሯል፡፡ ማቴ. 13፥1-58፡፡ እንዲያውም ያለምሳሌ አላስተማረምም አልተናገረምም፡፡ ማቴ. 13፥35፡፡ እንግዲህ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዓላማ ለማስተማር ስለሆነ ሁሉንም በሚገባው መልክ አስተምሯል፡፡

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት

ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ እንዲሁም ድውያነ ሥጋን በተአምራት ይፈውስ ነበር፡፡ ከተአምራቱም በጥቂቱ ኅብስት አበርክቶ ማብላቱ ማቴ. 15፥32-38 ሕሙማንን መፈወስ ዮሐ. 5፥5-10 ዕውራንን መፈወስ ዮሐ 9፥1-12 ሙት ማንሣት ዮሐ. 11፥11-34 በአጠቃላይ ብዙ ገቢረ ተአምራትን ፈጽሟል፡፡ ግን ድውይ በመወሱ ተአምራትን ሁሉ በማድረጉ ሰንበትን ሻረ ተብሎም ተከሷል፡፡ ሰይጣንን በሰይጣን አለቃ ያወጣል ተብሎ ተከሷል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅበራዊ  ኑሮ

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ፤ ወልድ ዋሕድ፤ ሰው የሆነው  ከኃጢአት በቀር ሰው በሄደበት ሄዶ ለማስተማር ነው፡፡ በሰዎች ማኅበራዊ ኑሮ እየገባ የደስታቸውም የኃዘናቸውም ተካፋይ ሆኗል፡፡ በመጀመሪያ ጊዜ በገሊላ ቃና ተአምራትን ያደረገው በሠርግ ቤት በመገኘት የሰዎች የደስታ ተካፋይ ከመሆኑ የተነሣ ነው፡፡ ዮሐ. 2፥1-12፡፡

ከቅዱስ ማቴዎስ ቤት ጀምሮ በነአልዓዛር ስምዖን ዘለምጽ ቤት ግብዣ እየተጋበዘ ገብቷል፡፡ በእነዚህም ቤቶች ቀዳሚ የሆኑ ትምህርቶችን ሰጥቷል፡፡ ሉቃስ 10፥38-42፡፡ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ የጸሎቱ ተካፋይ ለመሆን ከ12 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ ፈጽሟል ሉቃስ 2፥42-50፡፡ እኔ አምላክ ነኝና እኔ ያለሁበት ነው ቤተመቅደስ አላለም፡፡ ይህም ሰው እምነቱን ሥርዓቱን አክብሮ  በቤተ ክርስቲያን በማኅበር ጸሎት በተወሰነው ቦታና ጌዜ መገኘት ግዴታው መሆኑን ያስረዳል፡፡ በሐዘን ቤት ተገኝቶ  አልቅሷል፡፡ ይኸውም በአልዓዛር ሞት ጊዜ ነው፡፡ በዚያም ከመገኘቱ የተነሣ አልዓዛርን ከሞት አሥነሥቶታል፡፡ ዮሐ. 11፥11-34፡፡ በዚህም መልክ እንደማንኛውም ሰው ሆኖ ከኃጢአት በቀር የሰውን ችግር እየተካፈለ እግረ መንገዱን ግን እያስተማረ ኖረ፡፡ ሲያስተምር ይውላል፡፡ ሌሊት ግን ወደ ደብረ ዘይት እየወጣ ያድር ነበር፡፡ ሉቃስ 21፥37፡፡ ምግብ የሚያዘጋጅለት ደከመህ እረፍ የሚለው ዘመድ አልነበረውም፡፡ ሲያስተምር ውሎ «ልጆች የሚበላ አለን?»እያለ ይጠይቅ ነበር፡፡ ማቴ. 15፥32-38 ፡፡

 የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሐሙስ እራት

ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር ፍስሐን /የፋሲካን/ በዓል በማክበር ራት ኅብስቱን አንሥቶ ባረከ ፈተተ ለደቀመዛሙርቱም «እንኩ ብሎ ይህ ሥጋዬ ነው ነገ በመልዕልተ መስቀል የሚቆረሰው›› ብሎ ሰጣቸው፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ እንዲሁ ባረከ እንኩ ሁላችሁ ጠጡ ይህ ነው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ለዓለም ኃጢአት ማስተሰርያ ሆኖ ነገ የሚፈሰው ሲል ሰጣቸው ማቴ. 26፥26-29፡፡ በዚህ ጊዜ ሥርዓተ ቁርባንን አሳያቸው፡፡ ምስጢረ ቁርባንን መሠረተላቸው፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ሳያቋርጥ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ይቀጥላል 1ኛ ቆሮ. 11፥26 ቅዱስ ሥጋውን መብላት ክቡር ደሙን መጠጣት ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያስገኝ  መሆኑን አስረዳ፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱን ይዞ ለጸሎት ወደ ጌቴ ሰማኒ ሄደ፡፡ ማቴ. 26፥36-49፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መያዝ

ጌታችን በጌቴሰማኒ ሆኖ ሲጸልይ ከቀመዛሙርቱ አንዱ የነበረ ይሁዳ ወደ ካህናቱ አለቃ ሄዶ ነገር ሠራ፡፡ ያስይዘውም ዘንድ ሠላሳ ብር ተቀብሎ የጭፍሮቹ መሪ ሆኖ ድንገት እርሱ ክርስቶስ ነውና ተባብራችሁ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ነበርና ይሁዳ ሄዶ «መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን» ሲል እጅ ነሳው፡፡ በዚህ ጊዜ ተረባርበው ያዙት፡፡ ክርስቶስ ግን «ይሁዳ በመሳም ልታሲዘኝ መጣህን» ሲል የሰላም ቃል ተናግሮ እጁን ሰጠ እንጂ «አልያዝም» ብሎ አልታገለም፡፡ ወዲያውም ጭፍሮቹ እያዳፉ እያጋፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት ማቴ.26፥47-57፡፡

ደቀመዛሙርቱ ግን ለራሳቸው ፈርተው ተበተኑ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ብቻ የሚሆነውን ሁኔታ ሁሉ ለማየት ከኋላ ከኋላ እየተከተሉ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ አብረው ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን እስከ መጨረሻውም ቢሆን አልተለየውም፡፡ ስለዚህ በመስቀሉም ጊዜ በአንጻሩ ሆኖ ሲያለቅስ ውሏል፡፡ ማቴ. 26፥58 ዮሐ. 19፥26፡፡ ሊቀ ካህናቱም አጣድፎ የበኩሉን ምርመራ ፈጸመና በክርስቶስ ላይ ሊሞት የሚያስችለውን ውሳኔ አስወስኖ ወደ ጲላጦስ ወሰደው፡፡ ጲላጦስ ግን ነገሩን መላልሶ በማጥናት ምንም በደል ያልተገኘበት መሆኑን ተረድቶ ሊለቀው ፈልጎ ነበር፡፡ ዮሐ.19፥19።

ነገር ግን የካህናቱ አለቃ የሕዝብ ሽማግሌዎችም በአንድ ድምጽ ሆነው «ስቀለው ስቀለው» እያሉ ጮሁ፡፡ በመቀጠልም «ይህን ሰው ከአዳንከው የቄሣር ታማኝ አይደለህም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ሰው የቄሣር ጠላት ሰው፡፡ ለቄሣር ሰዎች ግብር እንዳይከፍሉ ከልክሏል፡፡ ሲሉ ከቄሣር ጋር እንደሚያጣሉት አስፈራሩት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሕጋችን ሞት ይገባዋል ብለው የነበረውን ሕግ ስለጠቀሱበት እንደ ሕጋችሁ ወስዳችሁ ስቀሉት ብሎ ክርስቶስን አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ጲላጦስ ግን ከነገሩ ንጹሕ እንደሆነ ተናገረ፡፡ ማቴ. 27፥15-26፤ ሉቃስ 23፥1-25 ዮሐ. 18፥29፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ክፉ አድራጊ ተሰቀለ፡፡ በመስቀል ተሰቅሎ የሞተ ሁሉ ርጕም  ይባል ነበርና የርግማንን ውርደትን ከሰው ለማራቅ ሲል በእንጨት ተሰቀለ፡፡ ወንጀሉንም ከፍተኛ ለማድረግ በነፍሰ ገዳዮችና በልዩ ልዩ ወንጀል ከተፈረባቸው ሁለት ወንበዴዎች ጋር በመካካል ተሰቀለ፡፡

ክርስቶስ በሰው ዘንድ እንደ ክፉ አድራጊ ቢቆጠርም ሌላው ግዑዝ ፍጥረት ሁሉ ለአምላክ ለመመስከር ወደ ኋላ አላለም፡፡ ስለዚህ ፀሐይ ጨለመ፤ ጨረቃ ደም ሆነ፤ ከዋክብት ከሰማይ ወደምድር ረገፉ፤ አዕባን ተፈተቱ፤  መቃብራት ተከፈቱ፤ ሙታን ተነሡ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ፡፡ ማቴ 27፥45-54 ማር. 15፥33 ሉቃስ 23፥44-45፡፡

እንዲሁም በሰው በኩል የሚቻለው የክፋት ሥራ ሁሉ እስከ ሞት ድረስ ነበር፡፡ በእርሱ ሁሉ ተፈጸመ፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ሁሉም ተፈጸመ ሲል የመጨረሻውን ቃል ተናግሮ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በሥልጣኑ ለየ፡፡ ዮሐ. 19፥30፡፡ የክርስቶስ ሞትም በእናቱ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ በኩል መራራ ሐዘን ሆነ፡፡ በጸሐፍት ፈሪሳውያንና በሊቀ ካህናቱ በኩል ግን ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መቀበር

ንጉሥ የሰቀለው አንበሳ የሰበረው ይፈራልና በመስቀል ተሰቅሎ የሞተውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመቅበር የተረፉት አበጋዞች ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የተባሉ ሽማግሌዎች ጥያቄ አቀረቡ። ጲላጦስም እንደሞተ በሰማ ጊዜ ተደነቀ፡፡ በመስቀል ሳለ የተደረገውን ተአምራት ሰምቶ ስለነበር በእውነት ይህ ሰው ታላቅ ነው ብሎ ጌታን በመስቀሉ ተጸጽቶ ነበርና ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በጠየቁት መሠረት እንዲቀብሩት ተፈቀደላቸውና ጌታችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ሕያው፤ ዘኢይመወት፤ (የማይሞት የማይለወጥ አምላክ) እያሉ  እንዲገንዙት በአዘዛቸው መሠረት በአዲስ በፍታ ገንዘው ማንም ወዳልተቀበረበት ቦታ ወስደው ዮሴፍ ለራሱ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ ቀበሩት፡፡ ማቴ. 27፥56-61 ማር 15፥42 ሉቃስ 23፥50-56 ዮሐ. 19፥38-42፡፡ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ከክብሩ አልተለየምና ዓለምን ይገዛ ያስተዳድር ነበር፡፡ መቃብር ጠባቂዎቹ ተመድበው /ማቴ. 25፥62-66/ በመቃብሩ ቁልፍ ተደርጎለት በማኅተም ታትሞ ይጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን መቃብሩን ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በሦስተኛው ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ማቴ. 28፥7 ማር.16፥6 ሉቃስ 24፥5 ዮሐ. 20፥16፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ

ክርስቶስ በተቀበረ በሦስተኛው ዕለት በመንፈቀ ሌሊት ሲነሣ የመቃብር ጠባቂዎች ደነገጡ በድንም ሆኑ፡፡ ክርስቶስን ከልደት እስከ መስቀል ሞት ድረስ እንደሰው ብቻ ይመለከቱት ነበር፡፡ ነገር ግን ትንሣኤው ዕፁብ አምላክነቱን አሸናፊነቱን አሳመነ፡፡ ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን የለውምና ይዞም ሊያስቀረው አልቻለም፡፡ ማቴ. 28፥4፡፡ በክርስቶስ ሞት ያዘኑት  ቅዱሳን ሐዋርያትና ቅዱሳት አንስትም ሰላም ሳያገኙ ሰንብተው ነበር፡፡ በዚህ ቀን ግን በየበኩላቸው ወደ መቃብር እየሄዱ ከመቃብር አካሉን ስላላገኙ በበለጠ አዘኑ፡፡ ሴቶች ደግሞ ከመመላለሳቸው የተነሳ መልአኩ «እንዴት ሕያውን ከሙታን  መካካል ትፈልጉታላችሁ እርሱ ተነሥቷል ከዚህ የለም» የሚል የሚያስደስትም የሚያሳዝንም ቃል ሰምተው ተመለሱ፡፡ እያዘኑም ሲሄዱ ክርስቶስን በመንገድ አገኙት እጅም ነሱት /ሰገዱለት/፡፡ ማቴ 28፥9፡፡

እርሱ ግን ሂዱና ለደቀመዛሙርቱ እንደተነሣሁ ንገሯቸው» አላቸው፡፡ በክርስቶስ መነሣት በደቀመዛሙርቱ በኩል ፍጹም ደስታ ሲሆን በሊቃነ ካህናቱና በጸሐፍት ፈሪሳውያን በኩል ደግሞ ሐዘንና ፍርሀት ሆነ፡፡ ስለዚህም ትንሣኤው ለሕዝብ እንዳይነገር እኛ ተኝተን ሳለ ደቀመዛሙርቱ መጥተው ሰርቀው ወሰዱት ተብሎ እንዲነገር አስደረጉ፡፡ ማቴ 28፥13፡፡ እንዲሁም ከነርሱ ጋር እየወጣና እየወረደ እንደቀድሞው እየበላና እየጠጣ ዐርባ ቀን አብሯቸው ቆየ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት

ጌታችን የለበሰውን ሥጋ እንደያዘ  ከተነሣ በኋላ በዚህ ዓለም መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማረ፤ በዝግ ቤት  ገብቶ አብሮ እየበላ እየጠጣ በመንገድ በጉባኤ እየተገለጠ የእግዚብሔርን መንግሥት እየነገራቸው እና እያስተማረቸው 40 ቀን አብሯቸው ኖረ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደላከው ወደ አብ ዐረገ የሐዋ ሥራ 1፥1-4፡፡ ደቀመዛሙርቱ ተሰብስበው ባሉበት ጊዜ  የማጽናኛ ቃል እናንተ ግን ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በእየሩሳሌም ከተማ ቆዩ ብሎ ተናግሮ ዐረገ ሉቃ 24፥48-52፡፡

ደቀመዛሙርቱም እጅ ነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ሉቃ 24፥50-52፡፡ 120 የሚያህሉ ቤተሰቦች ሳይለያዩ የተስፋውን ቃል ይጠባበቁ ነበር፡፡ የሐዋ 1፥15፡፡ 120 ቤተሰብ ሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት 72ቱ አርድት 36ቱ ቅዱሳት አንስት ነበሩ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ከነዚህ ሁሉ አልተለየችም ነበር፡፡

 ይቀጥላል

አባ ሳሙኤል

በኢትዩጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

አዲስ አበባ