Archives

All posts for the month December, 2016

                                                        ክፍል ሦስት
 ዘመነ ሐዋርያትና ዘመነ ሐዋርያነ አበው
ዘመነ ሐዋርያት እና ዘመነ ሐዋርያነ አበው /ከ1-160 ዓ.ም/
ይህ ምንባብ በሁለት ዐበይት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን እነርሱም
1.ዘመነ ሐዋርያት ሲባል ይህም ዘመን 1-70 ዓ.ም ያለው ሲሆን
2.ዘመነ ሐዋርያውያነ አበው ሲባል ደግሞ ይህም ዘመን ከ70-160 ያለው ዘመን ነው።
1. ዘመነ ሐዋርያት 1-70 ዓ.ም
መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዘመኑ በማየ ዮርዳኖ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ 40 መዐልት 40 ሌሊት ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ
ሳያጥፍ ከጾመ በኋላ የማዳን ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የመጀመሪያ ሥራውን ያደረገው ደቀመዛሙርትን መምረጥ ነበር። እነዚህም
ደቀመዛሙርት ሐዋርያት ይባላሉ፡፡ ማቴ 10፡25 አንድም በሌላ አንፃር የንጉሥ እንደራሴ ፊት አውራሪ ጃንደረባ አፈቀላጤ
ማለት ነው፡፡
የሐዋርያት አጠራር
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁን ተመልከቱ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች ኃይለኞች የሆኑ ብዙዎች ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፡፡ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፡፡ እግዚአብሔር የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር መረጠ 1ኛ ቆሮ 1፡26 እንዳለ ሐዋርያትን ከተለያዩ ከተናቁ ከተጠሉ ቦታዎችና ከአምስት ከምናምንቴ ግብሮች/ ሥራዎች ፣ ጠርቷቸዋል፡፡
1. ከአናምያን /ከሽመና/ በዚህ ግብር ሲተዳደሩ ከነበሩት መካከል ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ታዴዎስ ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ ናቸው፡፡
2. ከአናጽያን/ከግንበኝነት/ ከዚህ ግብር ከተጠሩበት መካከል ለምሳሌ ሐዋርያው ቶማስ
3. ከመጸብሓን /ከቀራጭነት/ ቀራጭ በአይሁ የተጠሉ የተናቁ ይልቁንም እንደ ኃጢአተኛ የሚቆጠሩ ነበር ከዚህ ግብር የተጠራው ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ
4. ከመስተገብራን /ከግብርና ;/ከግብርና ሥራ እየኖሩ ሳለ ከተጠሩት መካከል ቅዱስ በርተሎሜዎስ ቅዱስ ናትናኤል፡፡
5. ከመሠግራን /ከዓሣ አጥማጅነት/ በዚህ ግብር የሚተዳደሩ ነገር ግን ለሐዋርያነት ክብር ከተጠሩት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስ እንድርያስ ቅዱስ ዮሐንስን ወንድሙን          ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስን ነበር፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታዲያ ለምን ሐዋርያትን ሲመርጥ አሥራ ሁለት አድርጎ መረጣቸው? ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡
ትንቢቱ፡- ተረፈ ኤር 11፡52 ላይ‹‹ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም ይገባል እኔ ሰው ሆኖ ያየሁት ከባሕርይ አባቱም ወደዚህ ዓለም የተላከ ሰው ሆኖም ወደዚህ ዓለም የመጣ እርሱ አብሯቸው ይታይ ዘንድ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትን ለሱ አገልጋዮች ሊሆኑ ይመርጣል›› ያለው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ፡
ለምሳሌው፡-
1.ያዕቆብ ሶሪያ ወርዶ አሥራ ሁለት ልጆች ወልዷል ጌታችንም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በመንፈስ ወልዷቸዋል፡፡
ዕብ 2፡16
2.በኢያሱ መሪነት አሥራሁለቱ ነገደ እሥራኤል ምድረ ርስት እንደገቡ ሁሉ በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መሪነት ምእመናን ርስተ
መንግሥተ ሰማያት ይገባሉና
3.ቤተ እስራኤል ሥትመሠረት 12ቱ አበው እየተባሉ በሚጠሩት ከያቆብ አብራክ በተከፈሉ የአሥራ ሁለቱ ዘንድ አባቶች እንደ ነበር ሁሉ አሁንም ጌታ የእሥራኤል           ዘነፍስ ማኅበር ቤተክርስቲያን ሥትመሠረት በ12ቱ ሐዋርያት ትሆን ዘንድ አምላክ ፈቀደ፡፡
ጥምቀተ ሐዋርያት
የሐዋርያት ጥምቀት በብዙ ሊቃውንት ዘንድ አከራካሪ ቢሆንም እኛ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተረዳነው ጥምቀታቸውን የፈጸሙት ገና ሁሉን ትተው የተከተሉት ወቅት ቢሆንም ይህ በስውር የተፈጸመ ነበር። ነገር ግን በግልጥ የሐዋርያት ጥምቀት የተፈጸመው በምሴተ ሐሙስ የሐዋርየትን እግር በማጠብ አንድም ትህትና ሲሠራ አንድም ጥምቀታቸውን ሊፈጽም ነበር፡፡ ዮሐ. 12
ሐዋርያት መቼ ቆረቡ
ከጥምቀት በኋላ ሥጋ ወደሙ በመቀበል እንዳለብን ሲያሳየን ኅብስቱን ከአሥራ ሦስት (ፈትቶ) ቆርሶ ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ ጽዋውንም አንስቶ አመሰግኖም ሰጣቸው እንዲሁም አለ ሁላቸው ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡ ብሎ አቁሩቧቸዋል፡፡ ማቴ 26፡26
ለአንድ ወታደር ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ለጦርነት የሚያስፈልገውን ሙሉ ትጥቅ እንደሚዝ ሁሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላት ድል ይነሱበት ዘንድ ተአምራት ያደርጉ ዘንድ
ጋኔን እንዲያወጡና ለምጽ እንዲያነጹ ሙት እንዲያሥነሡ የሥልጣን /ትጥቅ/ ሰጣቸው ሲያስተምሩም መከራና ሞትን እንዳይፈሩ በማስተማራቸውም ምክንያት በተከሰሱ ጊዜ ጠበቃ እንዳይፈልጉና ራሳቸውም በሚናገሩበት ጊዜ የሚናገሩበትን ነገር አስቀድመው እንዳያስቡና እንዳይጨነቁ የሚያበረታታና የሚያጽናና ቃል ነገራቸው፡፡ ማቴ 10፥8-11 18፡19
የሐዋርያት ትምህርት
ክርስተና የተሰበከው በሐዋርያት በመሆኑ ትምህርተ ሐዋርያት ከክርስቶስ የተገኘ የቤተ ክርስቲያን እምነት መነሻ ነው፡፡ የሐዋርያት ትምህርት በዓይን ያዩት በጆሮ የሰሙት በእጅ የዳሰሱት በኋላም በመንፈስ ቅዱስ የተረዱት በመሆኑ እውነተኛነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ ‹‹ ሂዱና አስተምሩ›› ተብለው የተላኩ መልእከተኞች ናቸውና መልእክተኛነታቸው የታመነ ነው፡፡ የእነዚህን ሐዋርያት ትምህርት ቤተክርስቲያን በትውፊትና በመጽሐፍ አግኝታዋለች፡፡ ማር.16፥15
1.በትውፊት፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁን ያያችሁን እነዚህን አድርጉ››
ፊሊጵ 4፡9 በማለት እንደተናገረው ሐዋርያት ትምህርታቸውን ያስተማሩት በመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ከኑሮአቸው ከተግባራቸው
ከገድላቸው እና ከትሩፋታቸው ጭምር በመሆኑ ቅድስት ቤተክርስቲያን በሐዋርያት ትውፊት ትጠቀምበታለች፡፡
2. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በቃል ብቻ ሳይሆን ያስተማሩት መጻሕፍት በመጻፍ ጭምር እንጂ ይህን
እውነተኛ ትምህርት ጠብቃ በመያዝ ለዓለም አበርክታዋለች፡፡ ሐዋርያት ወንጌልንና መልእክታትን የጻፉት፤ ያስረከቡትም
ለቤተክርስቲያን ነው፡፡ የሚገኘውም በቤተክርስቲን ውስጥ ነው የመጽሐፍ ቅዱስም ባለቤት ቅድስት ቤተክርስቲያን ናት። ስለዚህ
ሐዋርያት የጻፉትን መጻሕፍትን በመቀበል ለትውልድ ሁሉ ታወርሳለች፤ ታቆያለች፡፡
1ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ /ስምዖን፣ ኬፋ/
ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባህር ዳር በምትገኘው በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ የአባቱ ስም ዮና ይባላል፡፡ ጌታን ከመከተሉ በፊት ከአምስት ዓምት ጀምሮ ያደገው በቅፍርናሆም ከተማ ሲሆን በጉልማሳነቱ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባህር ዓሣ አጥማጅ ነበር፡፡ ማር. 1÷16 -18 /ለደቀመዝሙርነት ሲመረጥ ዕድሜው 55 ዓመት እንደነበር ይነገራል፡፡ ዜና ሐዋርያት ገጽ 3-15/ የመጀመሪያ ስሙ ስምዖን ሲሆን ጌታችን ጴጥሮስ ብሎታል፡፡ በላቲን ቋንቋ ዐለት ማለት ነው፡፡ በአርማይክ ደግሞ ኬፋ ይባላል፡፡ ማቴ 16÷17 በዚህም ቃል የመንግሥተ ሰማይ ቁልፍ ተሰጥቶታል፡፡
 በጥብርያዶስ ባህር ላይ ለመሄድ ሞክሮ መስጠም ስለጀመረ ጌታ ከመስጠም አድኖታል፡፡ ማቴ.14÷31 (እምነት) /አንተ እምነት የጎደለህ ስለሞን ትጠራጠራለህ፡፡
 የሮም ጭፍሮች ጌታን ለመያዝ ሲጠጉ የሊቀ ካህናቱን ባርያ/ማልኮስን /በሰይፍ ጆሮውን ቆርጦታል፡፡ ዮሐ. 18÷ 10
 ጌታ በአይሁድ እጅ ተይዞ ሳለ የገባውን ቃል አጥፎ ሦስት ጊዜ ጌታን አላውቀውም ብሎ ካደ፡፡ ማቴ. 26÷69-75
 በኋላ ግን በንስሓ በመመለሱ ጌታ ግልገሎቼን አሰማራ ጠቦቶቼን ጠብቅ በጎቼን አሰማራ በማለት አደራ ሰጥቶታል፡፡ዮሐ. 21÷15
 ቅዱስ ጴጥሮስ የበዓለ ሃምሣ ዕለት አስተምሮ በአንድ ጊዜ ሦስት ሺህ ሰዎችን አሳምኗል፡፡ የሐዋ.ሥራ 2÷41
 በቂሣሪያ የነበረውን አረማዊ/ አሕዛብ/ የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስን ከነቤተሰቡ አጥምቋል፡፡ የሐዋ. ሥራ 10 ÷48
 ቅዱስ ጴጥሮስ በፍልስጥኤም፣ በልዳ፣ በኢዮጴ፣ በቂሣሪያ፣ በሶርያ፣ በጳንጦን፣ በገላትያ፣ በቀጶዶቅያ በቢታንያና ሮሜ በተባሉ ሀገሮችና በሌሎችም እየተዘዋወረ              አስተምሯል፡፡ ብዙ ተአምራትን አድርጓል፡፡
 የቤተክርስቲን መዛግብት ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ መልክና ቁመት ሲገልጹ ፊቱ ሰፋ ያለ ሲሆን ሪዛምና መካከለኛ ቁመት የነበረው ራሰ በራ ሰው በማናቸውም ነገር ፈጣንና    ቀልጣፋ ነበር ይሉታል፡፡
በመጨረሻም ይህ ሐዋርያ ቅድስ ጴጥሮስ በሮም ንጉሠ ነገሥት ኔሮን ቄሳር ዘመነ መንግሥት በክርስትያኖች ላይ በተነሳው ስደትና መከራ ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀል የቁልቁል ተሰቀለ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ በሰማዕትነት ሐምሌ 5 ቀን 67 ዓ.ም ዐረፈ፡፡በ1ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ በቫቴካን ኮረብታ፤ ጰውሎስ በኦስቴያ መንገድ መቀበራቸውን መስክሯል፡፡ ቅዱስት ቤተክርስቴያንም የረፍታቸውን መታሰቢያ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ታከብራለች፡፡
2ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ
ቅዱስ ዮሐንስ ሀገሩ በገሊላ አውራጃ ሲሆን ከወንድሙ ከቅዱስ ያዕቆብ ጋር ዓሣ ያጠምድ ነበር፡፡ ማር. 1÷19-20 ለሐዋርያነት ክብር ሲጠራ እድሜው 20 ዓመት ነበር። አባቱ ዘብዴዎስ እናቱ ማርያም /ባውፍልያ/ ይባላሉ። ዮሐንስ ማለት ፍስሐ ሰላም ተድላ ማለት ነው፡፡ ማቴ 4፡21
ቅዱስ ዮሐንስ የሚጠራባቸው ስሞች
1. ፍቁረ እግዚእ/ጌታን የሚወድ/ ፡- በሕይወቱ እና በኑሮው ጌታን ለመምሰል ይጥር ስለነበር ጌታም ይወደው ነበር። እንዲያውም የጌታችን መታጠቂያውን ጠፍር           ቢታጠቅ ፍትወት ሥጋዊ ወደማዊ ጠፍቶለት ኑሮውም ሁሉ እንደ መላእክት ሆኖለታል፡፡
2. ወልደ ነጎድጓድ /ቦኤኔርጌስ/፡-
3. ነባቤ መለኮት /ታኦጎሎስ/ ፡- ነገር መለኮትን ከሌሎች ሐዋርያት አብልጦ አምልቶና አስፍቶ በመጻፍ ነባቤ መለኮት ተሰኘ፡፡
4. ቊጹረ ገጽ /ፊቱ በሐዘን የተቋጠረ/፡- በዕለተ ዓርብ ከእግረ መስቀሉ ስር ተገኝቶ የጌታችን መከራ መስቀል በማየቱ ከዚያች ዕለት ጀምሮ ለሰባ ዘመን ያህል ሳይስቅ       ፊቱ በሐዘን ተቋጥሮ ይኖር ስለነበር፡፡
5. አቡቀለምሲስ/ባለ ራዕይ/፡- ኃላፊያትንና መጻእያትን በራእዩ ገልጦ ስለተናገረ ይህ ስም ተሰጠው፡፡
6. ወልደ ዘብዴዎስ
7. ዮሐንስ ወንጌላዊ
የቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያዊ ጉዞ
ቅዱስ ዮሐንስ እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ለውለታው እመቤታችን በእናትነት ካገኘ
በኋላ እርሱም ለ16 ዓመት በእርሱ ቤት የተቀመጠች ሲሆን እመቤታችንን ከማረፏ በፊትም ሆነ ካረፈች በኋላ ብዙ ሥራዎችን ፈጽሟል፡፡
– የጌታችን ሥዕል ለጢባርዮስ ቄሣር የሳለ የመጀመሪያው አባት ነው። ሥዕሉም በ37 ዓመት እንደተሳለ ይገመታል፡፡
– እመቤታችን ካረፈች በኋላ ዋና መንበሩን ኤፌሶን አድርጉ የተለያዩ ሀገሮች አስተምሯል፡፡
– ከደቀመዝሙሩ ከአብሩኮሮስ ጋር በመሆን የአሕዛብ እመቤት ሮምናን ከነቤተሰቧ አጥምቋል፡፡
– የአርጤምስስን ቤተመቅደስ /ቤተጣኦትን/አፈራርሷል
ወንጌልን ሦስት መልእክታትን በመጨረሻም በጭካኔው በሚታወቀው በድምጥያኖስ ቄሣር ዘመነ መንግሣት 81-96/15/ ዓመታት በግዞት ተግዞ ሳለ ራዕዩን ጽፎ       አምላኩ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ሞት ሳያይ በ99 ዓመቱ ጥር 4 ቀን ተሰውሯል፡፡
3ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ /ወልደ ዘብዴዎስ/
ቅዱስ ያዕቆብ የዮሐንስ ወንድም ሲሆን የመጀመሪያ ሥራው ከአባቱ ጋር ዓሣ ማጥመድ ነበር፡፡ ማር. 1÷19 ያዕቆብ ማለት አኃዜ ሰኩና /ተረከዝ ያዥ/ ማለት ነው፡፡ በሌላ አንፃር ታላቁ ያዕቆብ እየተባለ ይጠራል፡፡ እንደሌሎቹ ሐዋርያት ለማስተማር ዕጣ ቢጣጣሉ ለዚህ አባት የደረሰችው ሀገር ፍልስጤኤም ሕንድ በስፔንም ሀገር እንደሰበከ የሚናገሩ አንዳንድ መዛግብት ተገኝተዋል፡፡ በእነዚሁ ሀገሮች ጣዖታትን ሰባብሮና ሽሮ ወንጌልን ሰብኳል/አንጿል/። በመጨረሻም በንጉሥ ሄሮድስ ትዕዛዝ በ44 ዓ.ም ሚያዝያ 17 ቀን በሰይፍ ተመትሮ ሰማዕት ሆኗል፡፡
አዕማድና የምሥጢር ሐዋርያት
በተከታታይ ከላይ የጠቀስናቸው ሦስቱ ሐዋርያት ማለት ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ እነዚህ አዕማድ ሐዋርያትና የምሥጢር ሐዋርያት ይባላሉ፡፡
አዕማድ ካሰኛቸው ዐበይት ምክንያቶች 1ኛ. ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ 2፡9 ላይ አዕማድ ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ 2ኛ. የኢየሩሳሌምን ቤተክርስቲያን በዋናነት ያስተባብሩ ስለ ነበር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ሐዋርያት የምሥጢር ሐዋርያት እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ምክንያቱም፡-
1. በደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮቱን ሲገልጽ
2. በወለተ ኢያኢሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ
3. በጌቴሴማኒ ሲጸልይ ከሌሎች ለይቶ ይዟቸው ሄዶ ነበርና
በተጨማሪም የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁን የሰማችሁትን ለማንም አትናገሩ ብሎ ይነግራቸው ስለነበር የምሥጢር ሐዋርያት ተባሉ፡፡ ማቴ 17፡9
4ኛ. ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ
ቅዱስ እንድርያስ የቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም ሲሆን ትውልዱም በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ በዓሣ ማጥመድ ተግባር ላይ ሳለ በጌታ ቃል በመጀመሪያ የተጠራ ሐዋርያ ነው፡፡ ዮሐ. 1÷34-35 ፡፡ ጌታን ከመከተሉ በፊት የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዝሙር ነበር፡፡ ዮሐ. 1÷41
ቅዱስ እንድርያስ የሚጠራባቸው ቅጽል ስሞች
ፕሮቶክሌቶስ፡- የተጠራ ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በዚህ ስም ይጠሩበት ነበር፡፡ አስቀድሞ ለሐዋርያነት ስለተጠራ
ሳይሆን አይቀርም፡፡
አስተባባሪ ሐዋርያ፡- ከሰው ጋር የመግባባት ችሎታ ስለነበረው በሐዋርያት ዘንድ እንደ አስተባባሪ ሐዋርያ ይቆጠር ነበር፡፡
የወጣቶች ሐዋርያ፡- ጥብርያዶስ ባሕር ሲማር ለቆየው ሕዝብ ቅዱስ እንድርያስ አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘውን ወጣት
አቅርቦ አስባርኮታል። ጌታም የአምስት ገበያ ሕዝብን በበረከት አጥግቧል፡፡ ዮሐ 6፡6-7
የአሕዛብ ወዳጅ ሐዋርያ፡- ጌታችን ለማየት የፈለጉትን ከአሕዛብ ወገን የነበሩትን ግሪኮች ተቀብሎ ከጌታ ጋር በማቅራረቡ በማገኛኘቱ፡፡
ዮሐ 12፡20
የቤተሰብ ሐዋርያ፡- የጌታችንን ማደሪያ ካየ በኋላ ተመልሶ ለወንድሙ ለቅዱስ ጴጥሮስ በመናገሩ እና የወንጌልን ምሥራች ለቤተሰቡ በማብሠሩ የቤተሰብ ሐዋርያ ይባላል፡፡
ቅዱስ እንድርያስ መጀመሪያ የስብከት ሥራውን በፍልስጥኤም ጀመረ፡፡ የቤተክርስቲያን ጸሐፊ የነበረው አውሳብዮስ እንደገለጠው እንድርያስ በሩስያ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ ቀጥሎም በቢታንያ፣ በገላትያ፣ በሩማንያ፣ በመቄዶንያ፣ በታናሽ እስያ፣ በግሪክ አገር አስተምሯል፡፡ የቁስጥንጥንያን ቤተክርስቲያን የመሠረተና የቁስጥንጥንያ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ መሆኑ ይነገራል፡፡ በመጨረሻም ግሪክ ውስጥ ምትራ /ጳጥሪስ/ በምትባለዋ ሀገር ሲያስተምር በጣኦት አምላኪዎች እጅ የሚመስል ቅርጽ ባለው በመስቄል ተሰቅሎ በድንጋይ ተወግሮ ታኅሣሥ 4 ቀን በ60 ዓ.ም. በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
5ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ
ቅዱስ ፊልጶስ ሀገሩ ቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ዮሐ ሥራ. 1÷14 ትውልድ ነገዱም ዛብሎን ነው፡፡ ጌታ ተከተለኝ ባለው ጊዜ ወዲያውኑ ጥሪውን በመቀበል ጌታን ከመከተሉም በተጨማሪ ቅዱስ ናትናኤልን ወደ ጌታ ያቀረበ/የጠራ/ እሱ ነው፡፡ ዮሐ. 1÷46 -47 ፡፡ ጌታችንን ለማየት የፈለጉትን ከአሕዛብ ወገን /ነገድ/ የነበሩት ግሪኮች ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርበው የተማሩት በቅዱስ ፊልጶስና በቅዱስ እንድርያስ አቅራቢነት ነበር፡፡ ዮሐ. 12÷20-22፡፡ ቅዱስ ፊልጶስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ አብን አሳየንና ይበቃናል›› ብሎ በጠየቀው እኔን ያየ አብን አየ … እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን›› በማለት ምስጢረ ሥላሴን አስረዳው፡፡ ዮሐ. 14÷8-11 ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ወንጌልን በትንሿ እስያ ውስጥ በምትገኘው በፍርግያ አስተምሯል፡፡ በመጨረሻም በታናሽ እስያ ውስጥ ሲያስተምር በተቃዋሚዎች እጅ ቁልቁል ተሰቅሎ ኅዳር 18 ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
6ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ /ዲዲሞስ/
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ትውልድ ነገዱ አሴር ሲሆን ትንሣኤ ሙታን የለም ብለው ያምኑ ከነበሩት ከሰዱቃውያን ወገን ነበር። ቶማስ በዕብራውያን አረማይክ ቋንቋ ዲዲሞስ በሕንድ ቋንቋ ማድረስ ማለት ሲሆን ትርጉሙም መንታ ማለት ነው፡፡
 የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የተወጋ ጎኑን የተቸነከሩ እጆቹንና እግሮቹን ካልዳሰስኩ አላምንም ብሎ ነበርና በስምንተኛው ቀን ቶማስ ባለበት እጅህን     አምጣና ዳሰኝ ብሎት ቢዳስሰው ከእሳት እንደገባ ጅማት ዐሥሩም ጣቶቹ ኩምትርትር ብለዋል።
 የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገትን ያየና ያበሠረ ሐዋርያ ነው፡፡
 ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ቤተመንግሥት የሠራ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የደረሰችው ሀገር ህንድ ሲሆን በዚሁ ሀገር የህንዶችን ጥንታዊና ባህላዊ እምነታቸውን ወደ ክርስትና እምነት ለመለወጥ ከፍተኛ ተጋድሎ           አድርጎ በመጨረሻም በ66 ዓ.ም ጣዖት አምላኪዎች ቆዳውን ገፈው በሰውነቱ ጨው ነስንሰው በማሰቃየት ግንቦት 26 ቀን ለሞት አብቅተውታል፡፡
7ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ
ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ ስሙ በሐዲስ ኪዳን ላይ የተገለጠው በሐዋርያት ዝርዝር ላይ ብቻ ሲሆን ታሪኩ ተጽፎ አይገኝም ፡፡ ጌታን ከተከተለ በኋላ የወንጌልን ትምህርት በአረብ አገር፣ በሕንድና በአርመንያና በአካባቢዋ አስተምሯል፡፡ የአርመንን መንበር ያቋቋመው በርተሎሜዎስ ነው፡፡ ቅዱስ በርተሎሜዎስ በአርመንያ አካባቢ ኤልዎስ በተባለው ቦታ አንድ የወይን ባለጸጋ እባብ ነድፎት ለሞት ስላበቃው ወዳጅ ዘመዶቹ ለለቅሶ ተሰበሰቡ፡፡ በርተሎሜዎስ ግን ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበርና ከሞት አሥነሣው፡፡ በዚህም ተአምር ሕዝቡ፣ መኳንንቱና መሣፍንቱ ሁሉ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ ብዙ ክርስቲያኖችን በማፍራቱም በቅንዓት ሰዎች ተነስተውበት መስከረም 1 ቀን አሸዋ በተሞላ ከረጢት ውስጥ ከተውት ከነሕይወቱ ባህር ውስጥ ወረወሩት፡፡ በዚያም ዐረፈ፡፡ በነጋታው ምእመናን ከባህር አውጥተው ቀበሩት፡፡
8ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ/ ሌዊ/
ቅዱስ ማቴዎስ የመጀመሪያ ስሙ ሌዊ ነው፡፡ ማር. 2÷14 ማቴዎስ የሚባለውን ስም ያወጣለት ጌታ ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ የቀድሞ ሥራው ቀራጭ /ግብር ሰብሳቢ/ ነበር፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ የቀረጥ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ጌታ ጠጋ ብሎ ተከተለኝ አለው፡፡ ወዲያውም በቤቱ ታላቅ ግብዣ ለጌታ አድርጎ ጓደኞቹ የነበሩትን ቀራጮችን ወደ ጌታ አቅርቦ ካገናኛቸው በኋላ ሁሉንም ትቶ ተከተለው፡¨ሉቃ. 5÷27-32 በዚህም አባቶቻችን ቅዱስ ማቴዎስን የቁም ተዝካሩን አውጥቶ ጌታን የተከተለ ሐዋርያ ይሉታል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በዕጣ የደረሰችው ሀገር ምድረ ፍልስጥኤም ስትሆን ቀጥሎ በኢትዮጵያ ፣ በፋርስ፣ በባቢሎን አካባቢ እንደሰበከ ይነገራል፡፡ / ገድለ ሐዋርያት ገጽ 101÷18/ ሩፊኖስና ሶቅራጥስ የተባሉና በዓለም የታወቁ የታሪክ ጸሐፊዎች ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን ስብኳል ሲሉ ጽፈዋል፡፡
በሌላ መልኩ ከ317 እስከ 419 ዓ.ም የነበረው የላቲን ቤተ ክርስቲያን አባት ተብሎ የሚጠራው ጆሮም የኢትዩጵያ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ ነው ሲል ጽፏል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ነው በማለት በጽሑፍ አረጋግጧል። ወደ ሕንደኬ (ሕንድ) ከመሔዱ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ነበር የመጣው በማለት የተጠቀሱት ሦስቱ ሐዋርያት በኢትዮጵያ ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስ ማቴዎስ የአይሁድና የአረማውያንን ትምህርት እየተቋቋመ ድውያንን ሲፈውስ ፣ አጋንንትን ሲያወጣ ልዩ ልዩ ተአምራትን ሲያደርግ ዜናው በከተማው ሁሉ በመዳረሱ በዚህ የተናደዱ መኳንንት በቅዱስ ማቴዎስ የሞት ፍርድ ፈረዱበትና ጥቅምት 12 ቀን አንገቱን በሠይፍ ተሰይፎ ዐረፈ፡፡
9ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ /ወልደ እልፍዬስ/
ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ ትውልደ ነገዱ ከነገደ ጋድ ሲሆን በሌላ አጠራር ታናሹ ያዕቆብ ይባላል፡፡ ወንጌልን ለማስተማር የደረሱት አኅጉራት ኢየሩሳሌምና ፍልስጥኤም ሲሆኑ በነዚሁ ሀገር አሚነ ክርስቶስን አስተምሮ ሕዝቡን ከአምልኮት ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ከሕገ ጣዖት ወደ ሕገ ወንጌል ከዲያብሎስ ቁራኝነት ወደ መንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት ቢመልስ ጣዖት አምላኪያን የሐሰት ምሥክሮችን አቁመ ውና አጣልተው በድንጋይ ተወግሮ የካቲት 10 ቀን በ62 ዓ.ም በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
ነገር ግን አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስን ከጌታ ወንድም /እኁ ለእግዚእነ/ ጋር አንድ አድርገው ይጽፋሉ፡፡ ይህ ግን ስሕተት ነው እንደ ቤተክርስቲያናችን ትምህርት እስቲ በሠንጠረዥ ለይተን እናስቀምጠው፡፡

 

ስም

 

አባት

 

የትውልድ ነገድ

   ሰማዕትነት የተቀበሉበት            የሚለያዩበት ነጥቦች
 

ያዕቆብ

 

 

ወልደ

እልፍዮስ

 

ነገደ ጋድ

 

የካቲት 10

በፍልስጤም ወንጌልን እንደሰበከ ይነገራል እንጂ ታሪኩ ጐላ ብሎ አይታወቅም
 

ያዕቆብ

 

ወልደ ዮሴፍ

 

ነገደ ይሁዳ

/ቤተዳዊት/

 

ሐምሌ 18

የጌታ ወንድም መሆኑ የያዕቆብን መልእክት መጻፉና የሃይማኖት ሲኖዶስ /49-50/ ላይ የጉባኤው ሊቀመንበር መሆኑ

 


10
/ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል

የተወለደው በናዝሬት በምትገኘው በቃና ዘገሊላ ነው፡፡ ዮሐ. 21÷2 የመጀመሪያ ስሙ ስምዖን ሲሆን ናትናኤል ብሎ የጠራው ጌታ ነው፡፡ ትውልድ ዘመኑ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ሄሮድስ የቤተልሔም ሕፃናትን በሚያስፈጅበት ጊዜ እናቱ ከበለስ ሥር ደብቃ አትርፋዋለች፡፡ ጌታም ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ሥር ሳለህ አውቅሃለሁ ያለው ለዚህ ነው፡፡ ወደ ጌታ የጠራው ፊልጶስ ሲሆን ናትናኤል ምሁረ ኦሪት ነበርና ከናዝሬት መልካም ነገር አይወጣም በማለት የነቢያትን ቃል መጽሐፍን በማወቁ ተናገረ፡፡ ዮሐ. 1÷44-52

ቅዱስ ናትናኤል ለሐዋርያነት ከመጠራቱ በፊት ለሕገ ኦሪት ቀናተኛ ስለነበር ቀናተኛ ተባለ ፡፡ ማር 3÷19 ሐዋርያው ስምዖን ወንጌልን በሶርያ፣ በባቢሎን በግብጽ እና ሊቢያ እየተዘዋወረ አስተምሯል፡፡ ማቴ. 10÷4 በመጨረሻ በግብጽ ሲያስተምር ሕዝቡ በትምህርቱ አምነው በመብዛታቸው አረማውያኑ ስለቀኑበት ለግብፅ ንጉሥ እንድርያኖስ ከሰው በሠራዊት አስይዘው በማምጣት በንጉሡ ትዕዛዝ ሐምሌ 10 ቀን በሠይፍ አስገደለው፡፡ / ስንክሳር ሐምሌ 10 ቀን የሚነበበው/

11ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ / ልብድዮስ/
የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ በመባል ይታወቃል፡፡ የሐዋ. ሥራ 1÷13፣ሉቃ. 6÷16 ታዴዎስ ልብድዮስ እየተባለ ይጠራል፡፡ ማቴ. 10÷4
-የሐዋርያው ታዴዎስ ሀገረ ስብከት ሶርያ ነው፡፡ በአንድ ቀን ያለጊዜው እህልን ዘርቶ ለጐተራ አብቅቷል
-አንዲት ዘማዊት ሴትን በነፋስ አውታር አንድትንጠለጠል አድርጓል
-በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን ቃል በተግባር ፈጽሞ ያሳየ አባት ነው፡፡ ማቴ 19፡24
-በመጨረሻም ወንጌል በተለያዩ ሀገሮች አስተምሮ ሐምሌ 2 ቀን በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት አርፏል፡፡
12ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ
ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ጌታን በሸጠው በአስቶሮቱ ይሁዳ ምትክ የተሾመ ሐዋርያ ነው፡፡ የሐዋ. ሥራ 1÷15-26፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊነቱ የታወቀው አውሳብዮስ ቅዱስ ማትያስ ከሰባው አርድእት አንዱ እንደነበር ጽፏል፡፡/አውሳብዮስ 1÷13-31/
-በላዒተ ሰብእ በተባለች ሀገር ገብቶ አስተምሯል
-በደማስቆም አስተምሮ በመጨረሻም በይሁዳ ከተሞች እየተዘዋወረ አስተምሮ በዚህ ዕለት መጋቢት 8 ፊላኦን በተባለች ቦታ በሰላም
አርፏል፡፡
13ኛ/ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተወለደው ጠርሴስ ከተማ ነው፡፡ ዘሩ ከዕብራውያን ከብንያም ነገድ ነው፡፡ በ15 ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ ከገማልያል የአይሁድን ሕግና ሥርዓት ተማረ፡፡ በ30 ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አካል ሆኖ ተቆጠረ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ አባልነት ለሁለት ዓመት በሠራበት ወቅት ለኦሪት እምነት ቀናተኛ ፈሪሳዊ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማናቸውም ምክንያት ይቃወም ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ክርስትናን በማስተማሩ በአይሁድ ሸንጎ ሲቀርብ የተከራከረው እርሱ ነበር፡፡ ኋላም በድንጋይ ሲወገር የወጋሪዎችን ልብስ ይጠብቅ የነበረው እርሱ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ ያሉ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የፈቃድ ደብዳቤ ከሊቀ ከህናቱ ተቀብሎ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት በመንገድ ሲሄድ ከከተማ ሳይገባ ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን ወጥቶ አካባቢውን አበራው። ጳውሎስም ወደ መሬት ወደቀ፡፡‹‹ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?›› የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ‹‹ ጌታ ሆይ ማነህ?›› ብሎ ጠየቀ ‹‹ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡ ›› የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል ብሎ ጌታችን ተናገረው ፡፡ ጳውሎስም የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ከተነገረው በኋላ ደማስቆ እንዲገባ አስታወቀው፡፡ የሐዋ. ሥራ 9÷11
የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቤተክርስቲያን መጠራት
ጌታ በራዕይ ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ መመረጥ ሐናንያ ለተባለው ሰው ነገረው፡፤ ሐናንያ ግን ጳውሎስ የክርስቲያኖች አጥፊ ነው ብሎ ጌታን ተከራከረው ፡፡ ጌታም ‹‹ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፣ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና›› በማለት ሐናንያን ወደ ጳውሎስ ዘንድ ላከው፡፡
ሐናንያም ሄደ ወደ ቤቱ ገባ እጁንም ጭኖበት ‹‹ ወንድሜ ሳውል ሆይ ጌታ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፡፡ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይመላብህ ዘንድ ላከኝ›› አለ፡፡ ወዲያውም እንደቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፡፡ ያን ጊዜም ደግሞ አየ ተነሥቶም ተጠመቀ፡፡ መብልም በልቶ በረታ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሐናንያ ከተጠመቀና ከተማረ በኋላ ወደ ዓረብ ሀገር መሄዱን ራሱ ተናግሯል፡፡ ገላ. 1÷17፡፡ በቆጵሮስ ዳፋ ሳውል የሚለው ስሙ ተቀይሮ ጳውሎስ ማለት ብርሃን፣ መዶሻ ንዋይ ኅሩይ/ምርጥ እቃ/ ማለት ነው፡፡
የሐዋያው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ጉዞ
የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያደረጋቸው ጉዞዎች ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጉዞ ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ በልዑል ሥራ 13 ÷1-3
በዚህ ጉዞአቸው በጠቅላላ ወደ 2000 ኪ.ሜ የሚደርስ መንገድ በእግር ተጉዟል፡፡ ጉዞው የተከናወነው በ46 ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ ይህን ጉዞ ያደረገው ከሲላስ ጋር ነው፡፡ በጉዞው ከ14 የማያንሱ ሀገሮች ተሸፍነዋል፡፡ ሁለተኛውን ጉዞ ያደረገው በ50 ዓ.ም ገደማ ነው፡፡ ይህን ጉዞ ያደረገው ከሲላስ ጋር ነው፡፡ በጉዞው ከ18 የማይንሱ ከተሞች የተሸፈኑ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል ገላትያ፣ ጤሮአዳ፣ ኤፊሶን፣ ቆሮንቶስ፣ ልስጥራ፣ ኢየሩሳሌምና አንጾኪያ ይገኙበታል፡፡ በዚህኛው ጉዞ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ክርስቲያኖች የሰበሰበውን ዕርዳታ ለኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ይዞ ሲመለስ በኢየሩሳሌም የፋሲካ በዓል ስለነበር ከየሀገሩ የመጡ አይሁድ ቅዱስ ጳውሎስን ተቃወሙት። ተቃውሞውን ለመግታት በአይሁድ ሕግ በቤተ መቅደስ የመንጻት ሥርዓት መፈጸም ጀመረ፡፡ ነገር ግን ከአሕዛብ ወገን የነበረውን ደቀመዝሙሩን ጥሮፊሞስን ወደ መቅደስ ያስገባው መስሏቸው ተቃውሟቸው በረታ፡፡ በዚህ የተነሳ ከተማዋ ታወከች፡፡ የሐዋ. ሥራ 22÷29 በሁከቱ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ በ58 ዓ.ም ለሮም እስር ዳርጎታል፡፡ ሁለት ዓመት በቁም እስር ቆይቶ ከሮም ሕግ ጋር የሚቃወም ወንጀል ስላልተገኘበት በነጻ ተለቋል፡፡
ከዚህም በኋላ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያልተመዘገበውን ጉዞውን ያደረገው፡፡ ጉዞውንም ያደረገው በመታሰሩ ያዘኑትን ክርስቲያኖችን ለማጽናናትና የጀመራቸውን ሥራዎች ፍጻሜ ለማየት የተደረገ ጉዞ ነው፡፡ በመጨረሻም በኔሮን ቄሣር ዘመን ለሮም ከተማ መቃጠል ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ የሞት አዋጅ ታውጆ ስለነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኔቆጶልዮን ከተማ ሲያስተምር በ65 ዓ.ም ተይዞ 2 ዓመት ከ6 ወር በጨለማ ቤት በእስር ከቆየ በኋላ በ74 ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ በአስትያ መንገድ አንገቱን በሠይፍ በ67 ዓ.ም. ሐምሌ 5 ቀን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
ክብረ ሐዋርያት በቤተክርስቲያን
ቅዱሳን ሐዋርያት ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ለቅድስት ቤተክርስቲያንን የሰጡ በትምህርታቸው በኑሮአቸው በተግባራቸው ቤተክርስቲያን ያስጌጡ ስለ ቤተክርስቲያንም ሲሉ ልዩ ልዩ መከራን የተቀበሉ የተሰው በመሆናቸው ቤተክርስቲያን እነዚህን ከዋክብቶቿን ያላትን ፍቅር አክብሮት ለመግለጽ ሰማዕትነታቸው በሚመጣው ትውልድ ልቡና ተቀርጾ ከዘመን ወደ ዘመን እንዲሸጋገር ስማቸውና ታሪካቸው ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል በማሰብ በልዩ ልዩ መንገድ ስታከብራቸው ትኖራለች፡፡ ለምሳሌ፡-
1.ትምህርታቸውን ሳታዛባ በመጠበቅ
ብዙዎች በልዩ ልዩ ዘመን ከእውነተኛው ትምህርተ ሐዋርያት አፈንግጠው በራሳቸው መንገድ በገዛ ፍልስፍናቸውና ምኞታቸው እየተመሩ ስሕተት እየገቡ ባለንበት         ዘመን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን የሐዋርያትን እውነተኛ ትምህርትና ትውፊት ጠብቃ እስከ ዛሬ ኑራለች።ወደፊትም እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ትቆያለች፡፡               ገላ 1፡ 8-9
2.ገድላቸውን በመመስክር
አበው ሐዋርያት የክርስትና ኑሮ ፋና ወጊዎች በመሆናቸው ከከሀድያን፣ ከመናፍቃን ከአረማውያን ከትዕቢተኛ መኳንንትና መሳፍንት ከዚህ ዓለም የዲያብሎስ አሸክላ     ጋር ተጋድለው በደማቸው ቀለም በአጥንታቸው ብዕር ነው ክርስትናን የጻፉት፡፡ ጽፈውም ብቻ ሳይሆን ኑረው ቀምሰው አሳይተውናል፡፡ ስለ ወንጌል ክብር ስለ            ርትዕት ሃይማኖት የተሰው የቅድስት ቤተክርስቲያን መዓዛ የሆኑት ሐዋርያት ቤተክርስቲያን ገድላቸውን በመመስከር ታከብራቸዋለች፡፡
3.በዓላቸውን በማክበር
‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ›› መዝ 88፡3 ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ ብሎ ለቅዱሳኑ ቃል ኪዳን እንደገባላቸው ሁሉ ቅድስት የኢትዮጵያ             ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን አውቃ የቅዱሳን ሐዋርያትን የሰማዕትነታቸውን ቀን/ ከቅዱስ ዮሐንስ በስተቀር የእርሱን የተወለደበትን ቀን ይከበራል/            በዓላቸውን በደመቀ ሁኔታ በውዳሴ በቅዳሴ በማኅሌት ታስባቸዋለች፤ ታከብራቸዋለች፡፡
4.በአማላጅነታቸው በመተማመን
የቅዱሳን አማላጅነት በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርትና በቤተክርስቲያን ታሪክ በተለያዩ ቦታዎች ተገልጦ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ምእመናን አስቀድመው                    የልብሳቸውን ዘርፍ እየነኩ በጥላቸው ላይ እየተኙ ይፈወሱ እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም በስማቸው ቤተክርስቲያን በማነጽ በስማቸው በመጠራት ሥዕላቸውን በማክበር      ልጆቿ ድኅነተ ነፍስ ድኅነተ ሥጋ ያገኙ ዘንድ በስማቸው ጸልዩ እያለች ታስምራለች፡፡

አባ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ