Archives

All posts for the month February, 2017

 

 

፪.  መዝሙረ ዘቅድስት ግነዩ ለእግዚአብሔር

       መሰባክ፥ እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፤ አሚን

           ወሠናይ ቅድሜሁ፤ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ

   መቅደሱ መዝ (955-6)

    ምንባብ ማቴ 616-24

 

‹‹በምትጾሙበት ጊዜ ግብዞች እንደሚያደርጉት ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ እነርሱ ጾመኞች መሆናቸውን ሰው እንዲያውቅላቸው መልካቸውን ያጠወልጋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ እነርሱ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፤ ቊ.16።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አርአያ ለመሆን፤ እኛን ለማስተማር የጾመው አርባ ጾም ባለፈው ሳምንት እንደተነጋገርነው ያለፈው ሳምንት ዘወረደ ነው የሚባለው።

እንግዲህ ጾም የምንጾመው ከእግዚአብሔር በረከትን፤ ረድኤትንና ቸርነትን ለማግኘት ነው። ከቃሉ እንደ ተረዳነው ለታይታ መጾም የለብንም። በእውነት መጾማችንን እግዚአብሔር አውቆ ዋጋችንን እንዲሰጠን ብቻ ነው መጾም ያለብን። ጾም እግዚአብሔር ያዘዘው ስለሆነና እርሱም ለእኛ አርአያ ለመሆን የጾመው ስለሆነ እኛም መጾም ይገባናል።

የጥንት የብሉይ ኪዳን አባቶች አንድ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ጾም ይጾሙ ነበር። ነቢያት፣ በኋላም ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታትም የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከት ለማግኘይ ጾምን ጸመዋል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ 40 ቀን ጾሞ ዐሠርቱ ትእዛዛትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብሏል (ዘፀ 24፥12-18)። የእስራኤልም ሕዝብ 40 ዘመን በሲና በረሃ (ገዳም) ከኖሩ በኋላ ወደ ምድረ ርስት (እስራኤል) ገብተዋል። (ይህም 40 ዘመን እንደ ጾም ተቈጥሮላቸዋል)። ነቢዩ ኤልያስም እንዲሁ ከጾመ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረጎ ገነት ገብቷል፤ (1ነገ 1፥8)። ምእመናን ጾምን ቢጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ ሲሉ አባቶች በአስተማሩት መሠረት እኛም ይኸው እንጾማለን እንጸልያለን።

ጾም ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ብቻ  ሳይሆን ለሥጋዊ  ሕይወታችንም ጭምር እጅግ አድርጎ ይጠቅመናል። ከዚህ ቀጥሎ በጥናት የተደረሰባቸውን ጾም የሚሰጣቸውን ጥቅሞች እንመልከት፦

፩ኛ.  የጥንቱ ግብጻውያን ጾም ይጾሙ ነበር። ጾም ይጾሙ የነበረው ግን ሙሉ ጤናማዎችና

      ወጣቶች ለመሆን ወጣቶችም ለመምሰል ነበር የጥንቱ የግብጽ ምሁራንና ዐዋቂዎች

      በጥናት እንደደረሱበት ጾም ሰውነትን ያድሳል እጅግም ወጣት ያደርጋል። ስለዚህም

      አዘውትረው ይጾሙ ነበር።

፪ኛ. የጥንት  ግሪኮች ደግሞ  በጥናትና በምርምር እንደደረሱቡት ጾም ሰውን እጅግ ንቁና

     ዐዋቂ፤ አእመሮንም ብሩህ ያደርገዋል። ስለዚህም ጥበብንና ዕውቀትን ለማግኘት

     እንዲሁም ፍልስፍናን በጥልቀት ለማግኘትና ለመራቀቅ ጾምን አዘውትረው ይጾሙ

      ነበር።

፫ኛ. የመጀመሪዎቹ የአሜሪካ ነዋሪዎች ሕንዶች ጉብዝናን፣ ጉልበትንና ጥንካሬን ለማግኘት

     አዘውትረው  ይጾሙ ነበር። ሕንዶች በሕይወት ተመክሮአቸው እንደ ደረሱበት

     አብዝተው  የአማረ ምግብ የሚበሉ፣ ሥጋና ጮማ የሚቆርጡ ሰዎች  ሳይሆን ቅጠላ

     ቅጠል፣ ጎመንና  ፍራ -ፍሬ የሚበሉ (የሚመገቡ) ነበር  ጎበዞችና ጀግኖች ሆነው

     በጦርነት ጊዜ ድልን ይቀዳጁ የነበሩት።

፬ኛ. የሩስያ ሠዓሊዎች ደግሞ ጥሩ ሥዕል ለመሣል ይችሉ የነበሩት ጾን በሚጾሙበት ጊዜ

     ስለሆነ፣ አዘውትረው ይጾሙ ነበር።

፭ኛ. በሁሉተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በእንግሊዝ አገር ከባድ የምግብ እጥረት (ረሃብ)  ስለደረሰ፣ የእንግሊዝ መንግሥት ለሕዝቡ በግዢም ሆነ በስጦታ ለምግብ የሚያገለግሉ ቈሳቁሶችን ለምሳሌ ስንዴና በቆሎ  ይሰጡ የነበረው በመቀነስ (በጥቂቱ) ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ግን በቂ ምግብ  በመገኘቱ ሕዝቡ የፈለገውን ያህል ምግብ (ስንዴና በቆሎ ወዘተ) ያገኝ ጀመር። ታዲያ የጤና ባለሙያዎች አጥንተውና ተመራምረው እንደደረሱበት መቊነን  በሚሰጥበት ዘመንና ምግብ እንደ ልብ በሚገኝበት ዘመን የነበረውን የሕዝቡን ጤንነት ሲገመግሙና ሲመረምሩ መቊነን በሚሰጥበት ዘመን የሕዝቡ ጤንነት እጅግ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ የሚያመለክተው ጾም መጾም ለጤንነትም  ለአእምሮ ነፃነት መራቀቅን ጠቃሚ መሆኑን ነው።

፭ኛ  ዛሬም እኮ ቅባት፣ ሥጋና ጮማ መብላት ለጤና ጠንቅ መሆኑን ሐኪሞች አዘውትረውና አበክረው ይናገራሉ፣ ይመክራሉ። በተለይም የስኳር በሽታ፣ የደም ብዛት፣ ሌላም ሌላም በሽታ ያለባቸው ሕመምተኞች ከቅባት፣ ከሥጋ በተለይም ከጮማ እንዲከለከሉ ሐኪሞች አጥብቀው ይመክራሉ። መመሪያም ይሰጣሉ።

ስለዚህ የመንፈሳዊ ሕይወታችንንና ሥጋዊ ሕይወታችን ሕይወታችን እንዲሁም ጤንነታችነ በመልካም ሁኔታ ተጠብቆ እንዲኖር ጾም ማዘውተር እጅግ ጠቃሚ ነው። ይህም መሆን ያለበት በጾም ወራት ብቻ ሳይሆን  በሌላም ጊዜ መጾሙ ለጤንነታችን እጅግ ጠቃሚ ነው።

እንግዲህ የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች! ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾም ጾሙን የልማድ ጾም ማድረግ የለብንም። መጠንቀቅ ያለብን ከላይ የተጠቀሱት ለጤና፣ ለውፍረት መቀነሻ ተብሎ የሚጾም ከእግዚአበሔር ሕግና ከሃይማኖት በበረከት ከጽድቅ ጋር ግንኝነት የለውም ስለዚህ እውነተኛ ጾም ከልብ መጾም አለብን። በዚህ በጾም ወራት ራሳችንን ማወቅና በጥንቃቄ መመርመር አለብን። ከእህልና ከመጠጥ፣ ከቅባትና ከሥጋ ብቻ መከልከል ብቻ በቂ አይደለም። ከማናቸውም መጥፎ ነገር ከማናቸውም የኃጢአት ሥራ ከማናቸውም የተንኮል
ሥራና ተግባር፣  ከቂም ከበቀል፣  ከምቀኝነት ከትዕቢት፣ ከስርቆት፣  ከስካር፣ ከዝመት በሐሰት ከመመስከር ወዘተ ራሳችንን መከልከል አለብን።

የጾም ጊዜ የንሰሓ ጊዜ መሆን አለበት። ስለዚህ በጾም ጊዜ (ሀ) በፊት የሠራነውን መጥፎ ሥራዎች እያስታወስን በመጻጸት ንስሐ መግባት አለበን።  (ለ)  ከማናቸውም መጥፎ መንገድ ወይም ክፉ ሥራ ከልብ መመለስ ይኖርብናል። (ሐ) እንዲሁም መጥፎ ጠባያችንን ማረምና ለሌሎችም መልካም አርያአና ምሳሌ እንድንሆን ያስፈልጋል። (መ) በጾም ጊዜ ማዘንና ማልቀስ እንዲሁም ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን አጥብቆ መጸለይ ያስፈልጋል።

እግዚአብሔር መዋዕለ ጾሙን በሰላምና በጤና አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን ቅዱስ ፊቃዱ ይሁንልን! አሜን።

 ይቆየን —

 አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበበ

 

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ እንደተጠመቀ አልዋለም አላደረም ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ወደሚባል ሥፍራ ወይም በረሀ ገባ፡፡

 • በዚያም ፵ ቀን ፵ ሌሊት ጾመ፣ ጾሙም እኛ እንደምንጾመው በቀንና በሌሊት ባለው ክፍለ ጊዜ በመብላትና በመጠጣት ሳይሆን ፵ውን ቀን ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ እንደ አንድ ቀን አድርጎ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ እንደጾመ መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡
 • ሆኖም ጾሙን በመጾም ላይ እንዳለ ሰይጣን መጥቶ በሦስት አርእስተ ኃጣውእ ፈተና አቀረበበት፤ የፈተናዎቹም ዓይነቶች ስስት፣ ትዕቢት እና ፍቅረ ንዋይ (ገንዘብን መውደድ) ነበሩ፡፡
 • ዲያበሎስ (ሰይጣን) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእነዚህ አርእስተ ኃጣውእ ለመፈተን ኀይለ ቃሉን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ያደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥቅሱን በጥቅስ እየመለሰ በመለኮታዊ ኀይሉ እየደመሰሰ ድል አድርጎታል፡፡
 • ሰይጣን በመጀመሪያ ጌታችንን የእግዚአብሔርስ ልጅ ከሆንህ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ እና አንተም እኔም ርቦናል እንብላ አለው፡፡ እርሱ ጌታ ግን “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፣ ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ ተብሎ ተጽፎአል ሲል ገሠጸው”፡፡

ሰይጣን ስሙ እንደ ኃጢአቱ ብዙ ነው፡፡ ይኸውም የወደቁት መላእክት አለቃ፣ የመልካም ነገር ተቃራኒ ዲያብሎስ ብዔል ዜቡል፣ ቤልሆር አብዩን አጶልዮን፣ ወንድሞች ከሳሽ ባለጋራ፣ የዓለም ሁሉ ከሳሽ ታላቁ ዘንዶ፣ የቀድሞው እባብ፣ ክፉው ነፍሰ ገዳይ የሐሰት አባት እየተባለ ይነገርለታል፡፡ ጌታችን ሰይጣን በጠየቀው ጥያቄ አሳፍሮ ከመለሰው በኋላ እንደገና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ቅድስት ከተማ ሔደ፡፡ ሰይጣንም ደግሞ መጥቶ በአጠገቡ ቆሞ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፡፡ እግርህንም እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔርስ ልጅ ከሆንክ ራስህን ወደታች ወርውር አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰይጣንን ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፎአል ሲል አዋርዶና አሳፍሮ ሰደደው፡፡ ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደረጅም ተራራ ሔደ፡፡ ሰይጣንም ተከትሎት ሔደ፡፡ በለመደው ትዕቢቱና ትምክህቱ ተሞልቶ ምትሐቱን አዘጋጅቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውን፣ ከተማቸውን በወርቅ፣ በአልማዝ በዕንቁ ለብጦ አስገጦ አስውቦ አሳምሮ አሳየው፡፡

ጌታችንንም እንዲህ አለው ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ ክብር በወርቅና በአልማዝ በዕንቁና በከበረ ድንጋይ የተጌጠውን የተዋበውን ከተማ እሰጥሃለሁ ሲል በአምላክነቱ ሊፈትነው ሞከረ፡፡ ጌታችን ግን ሰይጣንን ሒድ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና ብሎ በማያዳግም በትረ ግሣጼው ቀጣው፤ አሳፈረው፣ አባረረው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰይጣን እንደጢስ ተኖ እንደ ትቢያ በኖ ከፊቱ ጠፋ፡፡ (ማቴ. ፬÷፩-፲፩)

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ፈተናዎች ማለት ሰይጣን በስስት ሲመጣበት በትዕግሥት፣ በትዕቢት ሲመጣበት በትሕትና በአፍቅሮ ንዋይ ቢመጣበት በጸሊአ ንዋይ ዲያብሎስንና ሠራዊቱን በሙሉ ድል እንዳደረጋቸው ሁሉ እኛም በሕይወታችን ዘመን በጾማችንና በጸሎታችን፣ ጊዜ ትዕግሥትን፣ ትሕትናን ጸሊአ ንዋይን ገንዘብ አድርገን ብንጸና ፈቃደ ሥጋችንና ፈቃደ ሰይጣንን ድል ለማድረግ እንደምንችል ይታመናል፡፡ በነዚህ መንፈሳውያን መሣሪያዎች እንድንጠቀምም አስተምሮናል፡፡

ፈተና ቢደርስብን እንኳ የእግዚአብሔር መላእክት መጥተው እንደሚቆሙልንና እንደሚረዱን፣ እንደሚያጽናኑንና እንደሚያ- በረታቱንም አንጠራጠርም፡፡ ድል ለመንሣት ኀይል፣ ጽንዕ እንደምናገኝም በሙሉ ልብ እናምናለን፡፡ እንተማመናለን፡፡ ይኸውም “ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤ ለእለ ይፈርሕዎ ወያድኅኖሙ፤ ጠዐሙ ወታእምሩ ከመኄረ እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአልና ይህም ማለት እግዚአብሔርን በሚፈሩና በሚያከብሩ ምእመናን ዙሪያ መላእክት ይከትማሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ደግ ቸር መሆኑን በአዳኝነቱ፣ በደግነቱ ልትተማመኑ እንድትችሉ በእርሱ ወደ እርሱ ተጠጉ ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ተናጋሪውም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ “ወሰቦ ትጸውሙ ኢትኩኑ ከመ መደልዋን” በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ “አንትሙሰ ሶበ ትጸውሙ ቅብኡ ርዕሰክሙ” እናንተስ ስትጾሙ ራሳችሁን ተቀቡ፡፡ ማለትም ጾመኛ ጸሎተኛ ተብላችሁ በውዳሴ ከንቱ ምክንያት ዋጋችሁን እንዳታጡ፡፡ ማቴ. ፮÷፲፮

በጊዜውም ያለ ጊዜውም አካሔዳቸውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ሰዎች ከጥንት ጠላታቸው ከዲያብሎስ የኃጢአት ቀምበር ነፃ ናቸው፡፡ በተለይም በጾም በጸሎት ቅኑት እንደገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ሆነው ሌት ተቀን የሚተጉ አማንያን ሁሉ ጠላትን ድል ነሥተውት ይኖራሉ፡፡ ከሕፃንነት ዘመኑ አንሥቶ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቶ ከመኖሩም በላይ በጾም በጸሎት ተወስኖ ይኖር የነበረው ነቢዩ ዳንኤል ከወገኖቹ ጋር ተማርኮ ወደ ባቢሎን ከተወሰደ በኋላ በአምልኮቱና በበጎ ምግባሩ ጸንቶ በመገኘቱ ከመጣበት ፈተና ሁሉ እንደዳነ ከመጽሐፈ ትንቢቱ እንረዳለን፡፡ ት.ዳን. ፱÷፫-፲፡፡

ነቢየ ልዑል ዳንኤል የነገሥታት ዘር ነበር፡፡ ዐዋቂ፣ ነገር አርቃቂ በዐራቱ ነገሥታተ ባቢሎን ነበረ፡፡ በእምነተ ጽኑዕነቱና በአምልኮቱ፣ በጸሎቱና በጾሙ በነገሥታቱም በሕዝቡም ዘንድ ታዋቂ ነበር፡፡ በዚሁም ምክንያት መኳንንቱና የንጉሡ አማካሪዎቹ ሁሉ የዳንኤልን በንጉሡ ዘንድ መወደድ አይተው ያልፈጸመውን ኃጢአትና ወንጀል ተብትበው ንጉሡ ከዳንኤል ጋር የሚጋጭበትንና የሚለያይበትን፣ የሚጣላበትንና ከፊቱ የሚርቅበትን እንዲያውም በተራቡ አናብስት ተበልቶ የሚጠፋበትን መንገድ አዘጋጁ፡፡ ይህም ፈተና በአምልኮተ እግዚአብሔር ምክንያት የመጣበት ነበር፡፡

 • ንጉሡ ናቡከደነጾርም ለጊዜው መስሎት በዳንአል ላይ ተቈጣ፡፡ ዳንኤል ግን ንጉሡን አንተ ብትቈጣ ንጉሥ ሆይ እኔ ከሕፃንነቴ ጊዜ ጀምሮ የማመልከው የአባቶቼን አምላክ እግዚአብሔርን ስለማመልክ የተለመደውን የዘወትር ጸሎቴን ከመጸለይ ፈጽሞ አላቋርጥም ብሎ ነገረው፡፡
 • ንጉሡም እጅግ ከመናደዱና ከመበሳጨቱ የተነሣ ከእጄ የሚያድንህ ሰው ከኔ የበለጠ ኃያል ፈጣሪም ሆነ ፍጡር ካለ አያለሁ ብሎ አማካሪዎቹ በጥላቻ መልኩ ያዘጋጁትን የውሳኔ ሀሳብ ጽሑፍ ወይም ቃለ ጉባኤ አጽድቆ ወዳጁ ዳንኤልን ወደተራቡት አናብስት ጉድጓድ ውስጥ ይዞ ወረወረው፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ዳንኤል ይወደው ስለነበረ ሌሊቱን ሙሉ እህል ሳይቀምስ ሳይተኛና ሳያርፍ፣ ሲበሳጭና ሲያዝን አደረ፤ ዳንኤል እነዚህ ሁለት ቀን ሳይበሉ የሰነበቱት አናብስት ጅራታቸውን እንደለማዳ የቤት እንስሣ እየወዘወዙ ከእግሩ በታች ወድቀው የእግሩን ትቢያ እየላሱ ተቀበሉት እንጂ ምንም አልነኩትም፡፡
 • ዳንኤልም በአናብስት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ፣ ከአናብስት መካከል ቆሞ “ኢትመጥወነ ለግሙራ በእንተ ስምከ፣ ወኢትሚጥ ኪዳነከ፣ ወኢታርሕቅ ምሕረተከ እምኔነ፣ በእንተ አብርሃም ፍቁርከ፤ ወበእንተ ይስሐቅ ቁልዔከ ወበእንተ እስራኤል ቅዱስከ”፡፡
 • ስለስምህ ብለህ ለጥፋት አሳልፈህ አትስጠን ከእኛ ዘንድ ምሕረትን አታርቅብን፣ ኪዳንህንም አትመልስብን፣ አትርሳንም ስለወዳጆችህ፣ ስለአብርሃም፣ ስለይስሐቅና ስለያዕቆብ ብለህ አስበን እያለ ጸለየ፡፡ (ዳን. ፮÷፲፱-፳፯)

ንጉሡ ዳርዮስም ዳንአል ወደ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ በመጣሉ አዝኖአልና፤ በነጋታው ከተቀመጠበት ተነሣ፤ ወደአናብስት ጉድጓድ ለመሄድ ዝግጅት አድርጎ ማልዶ ተነሣ፡፡ መኳንንቱን፣ መሣፍንቱን ራስ ቤትወደዶቹን አማካሪዎቹንና ባለሟሎቹን አስከትሎ ነቢዩ ዳንኤል ወደተወረወረበት የአናብስት ጉድጓድ ሄደ፡፡ ጉድጓዱ የታሸገበትን ማኅተም ቀደደ፡፡ በሩን ከፈተ ወደ ጉድጓዱም ተመለከተ እነሆ ዳንኤልም በጉድጓዱ ውስጥ በአናብስት መካከል በሕይወት ቆሞ ሲጸልይ አገኘው፡፡ በዚሁ ጊዜ ንጉሡ ዳርዮስ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክ እግዚአብሔር ከአናብስት አፍ ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው”፡፡

 • ዳንኤልም ንጉሡ ዳርዮስን “ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ ቅንነት ተገኝቶብኛልና አንተንም ደግሞ ንጉሥ ሆይ አልበደልሁህምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአናብስትን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልነኩኝም ብሎ መለሰለት”፡፡
 • ንጉሡም ዳንኤልን ከጉድጓድ አውጥቶ የዳንኤልን ጠላቶች የእርሱን አማካሪዎች አምጥቶ አናብስት ለእናንተ ደግሞ እንደ ዳንኤል ይሰግዱላችሁ እንደሆን ወደ ጉድጓዱ ውረዱ ብሎ ቢወረውሯቸው ገና ሳይወርዱ አናብስቱ እየዘለሉ ይዘው ቀለጣጥመው ሰባብረው ዋጡአቸው፡፡ በሠፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርምና የሥራቸውን አገኙ፡፡
 • ከዚህ በኋላም ንጉሡና ቤተሰቡ፣ እንዲሁም በግዛቱ ውስጥ ያሉ ያገሩ ሕዝብ ሁሉ በዳንኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንዲያምኑ አዋጅ አስተላለፈ፡፡ ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት አምኖ፣ ተቀብሎ በአምልኮቱ ጸና፡፡ (ዳን. ፮÷፲፮-፳፰)
 • ስለዚህ እኛም ሰማይንና ምድርን ጥቃቅኑንና ግዙፋን ፍጥረታትን የፈጠረ እውተኛ ፈጣሪ አምላክ የሆነው እግዚአብሔርን በእውነት ማምለክና የተቀደሰ ሥራን መሥራት በጾም፣ በጸሎት መትጋት፣ በትእዛዛቱ መጽናት፣ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በሰላም በትህትና አብሮ መኖር ይገባናል፡፡ መንገዳችንና አካሄዳችን እንዲሁ የቀና ከሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ከመጣብን አስደንጋጭና ክፉ ፈተና ሁሉ እንደሚያድነን የታመነ ነው፡፡ ይህኑም ተረድተን ከከንቱ አምልኮ ተጠብቀን በጾም በጸሎት ተወስነን በሥጋው ወደሙ ጸንተን ከቈየነው ለተስፋ መንግሥተ ሰማያት እንደሚያበቃን አንጠራጠርም፡፡ ለዚሁም እንድንበቃ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ (የሐ.ሥ. ፲÷፫-፬፣ ፲÷፴-፴፩) ይቆየን

   ከአባ ሳሙኤል

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 

  ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳ

  አዲስ አበባ 

   

ዐቢይ ጾም

ዘወረደ

ዘወረደ ማለት ፦ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸው ‹‹ ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚኩሉ  ዘየሐዩ በቃሉ  (ከሰማየ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ ሁን ብሎ የማዳነ ሥልጣን ያልው  የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም) በማለት ከሰማየ  ሰማያት ወረዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለሙን ያዳነበት ምስጢር የሚነገርበት ሳምንት ማለት ነው (ድጔ ዘአስተምህሮ)

                 ፩  መዝሙር፦ተቀነዩ ለእግዚአብሔር

                     ምስባክ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤

                     ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ፤ አጽንዕዋ     

                    ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር (መዝ 211-12)

                    ምንባብ ዮሐ.310-20

ይህ የዛሬው እሑድ ዐቢይ ጾምን የምንቀበልበት እሑድ ነው። ቅበላ ይባላል። ከነገ ሰኞ ጀምሮ የምንጾመውን ጾም የምንቀበልበት እሑድ ነው። ይህ ነገ የምንቀበለው ጾም በልዩ ልዩ ስሞች ይታወቃል፦ዐቢይ ጾም ይባላል፤ ዐቢይ ጾም ማለት ትልቁ ጾም  ማለት ሲሆን ዐቢይ የተባለበትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ስለሆነ ነው  (አርባ) ጾም ይባላል፤ ‹‹ከዚህም በኋላ  ጌታ ወደ ምድረ በዳ  (ቆሮንቶስ ገዳም) ሄዶ አርባ  ቀንና አረባ ሌሊት ጾመ፤ (ማቴ 4፥1 )

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዓብይ ጾም የምትሠጠው ክብር በማንም አገር ጥንትም ሆነ ዛሬ አልታየም። በጾሙ ስምንት እሁዶች አሉ። ለስምንቱ ሁሉ የተለያየ ስያሜ አላቸው። ስያሜውም ሐዲስ ኪዳንንና ማሕሌተ ያሬድን መሠረት ያደረገ ነው። የመጀመሪያው እሁድ ዘወረደ ይባላል። ጾሙ ሰኞ ሊጀመር መንፈሳዊ አገልግልቱ በጾም ሥርዓት ከወደዚህ ባለው ቅዳሜ ይጀመራል። “ዘወረደ እምላእሉ አይሁድ ስቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ” ትርጉሙ “ከለይ ወርዶ ሥጋ የለበሰውን አካላዊ ቃል አይሁድ ሰቀሉ፣ ሁሉን የሚያድን ሁሉን  የሚያኖር መሆኑን ግን አላውቁም” የሚለው መሐትው በዓቢይ ጾም ዋዜማ ቅዳሜ ጧት ከቅዳሴ በኋላ ይቆማል መሐትው የሚለው ቃል ዋዜማ ድራር ከሚለው ቃል ጋር ይመሳሰላል። ድራር ማለት “ራት” ማለት ሲሆን ከሌላ ቃል ጋር ከተናበበ ግን እንደ ዋዜማ ያገለግላል፣ ዋዜማና መሐትው የአቀራረብ ጊዜአቸው ይለያያል። ዋዜማ ለሚቀጥለው ቀን ክብረ በዓል በሠርክ የሚካሄደው መንፈሳዊ አግለገልት ነው። መሐትው ደግሞ  ለምሳሌ ሰኞ አንድ ክብረ በዓል ቢኖር እሁድ ጧት ከቅዳሴው ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ምንፈሳዊ አገልግልት ነው። “ሐተወበራ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ ማሕቶት ይወጣል፣ ማሕቶት ሲበዛ መሐትው ይባላል። በጥንት ዘመን በክብረ በዓሉ ዋዜማ በዓሉን ለማብሠር መብራትብ  የማብራት ልምድ ነበር። በዚሁ ነው መሐትው የተባለው።

መሐትው ፍሲካ መሐትው ዮሐንስ። … ከተባለ በዋዜማው የሚዘመረውን መዝሙር መግለጹ ነው።

ከዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት እስከሚቀጥለው ሳምንት ዘወረደ ይባላል። ቅዱ ያሬድ ምሥጢረ ትስብእትንና ሥነ ስቅለትን እያገናዘበ የዘመረው መዝምር ለስያሜው ዋና መነሻ ነው። በአንዳንዱ የዜማ ሊቃውንት  ይህ ስሙን መዋዕለ ሙሴኒ ይሉታል። ከዘወረደ ሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ያምስቱ ቀን የጾምድጔው ዕዝልም ሆነ እስመለአለም አብዛኞቹ በዘፀአት 24፥5 እስከ መጨረሻው እንድተገለጸው ሙሴ በደብረ ሲና ስድስት ቀን ከቆየ በኋላ እግዚብሔር እንዳነጋገረው በሚተርከው መሠረት የተሰጠ ስያሜ ነው። ባንድንድ የፍትሓ ነገሥት በዚህ ሰሞን እስከ 12 ሰዓት ድረስ መጾም እንዳለበትና በተቀሩት ሌሎች ሳምንታት  ከሕማማት በቀር እስከ 11 ሰዓት ብቻ መጾም እንዳለበት ተመዝግቧል።

ከነገ ሰኞ ጀምሮ ዐቢይ ጾምን እንጀምራለን። ዛሬ መነጋገር ያለብን ይህን ዐቢይ ጾም እንዴት አድርገን እንደምንጾመው ነው። ስለ አራት ነገረሮች ማሰብ አለብን፦

 1. ጾም በምንጾምበት  ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ  ይገባናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል እንደሚያስጠነቅቀን ጾም ስንጾም ጾማችን ለተርእዮ፣ ሰው እንዲያመሰግነን ማድረግ የለብንም። ከልዑል እግዚአብሔር ዋጋ እንድናገኝበት መሆን አለበት እንጂ። አንዳንድ ሰዎች እስከ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚጾሙ ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ በጥሬ ብቻ እንደሚጾሙ ይናገራሉ። ይህ ሁሉ ጥሩ ነው። ነገር ግን ይህ ለውዳሴ ከንቱና ለተርእዮ እንዳይሆንብን መጠንቀቅ አለብን። እንደዚህ መጾማችንንም ለሰው መንገር የለብንም። ለተርእዮ ወይም ሰዎች እንዲያውቁን የምናደርገው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ አያሰጥም  (ማቴ 6፥16-18)
 2. ጾም በምንጾመበት ጊዜ ከምግብ ብቻ መከልከል የለብንም። የምንጾማቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች አሉ የአልክሆል መጠጦችንም መጾም አለብን። እንዲያውም የተለያዩ ኃጢአቶችን እንዳንሠራ ያለመጠን ከመጣጣት መቆጠብ አለብን። በመሆኑም ከሚያሰክሩ መጠጦች መከልከል ያለብን በጾም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ከአልኮሆል መጠጦች አዘውትሮና አብዝቶ ከመጠጣት መከልከል አለብን። 2. በተጨማሪ ክፉ ነገር ከማየት፣ ክፉ ነገር ከመናገር፣ መጥፎ ነገር ከመስማት ወደ መጥፎ ቦታም ከመሄድ መከልከል አለብን። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለ ጾመ ሲዘምር ‹‹ይጹም ዓይን ይጹም ልሳን፣ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሱም እምተናግሮ፤›› (ዓይን ይጹም፤ አንደበትም ይጹም፤ ጆሮም ክፉ ነገር ከመስናት ይጹም) ይላል።
 3. ጾም በምንጾምበት ጊዜ የምንጾመውን ምግብ ማለት ቊርሳችንን ወይም ምሳብ የምንበላው ማታ ከሆነ ምሳችንን ጭምር አጠራቅመን ወይንም በቊርሳችን በምሳችን ጊዜ የምንመገበውን በገንዝብ ተምነን ለእግዚብሔር (ለቤቱ ክርስቲያን) ወይንም ለበጎ አድራጎት ድርጅት ወይንም ለነዳያን መስጠት አለብን። የምንጾመውን ምግብ በገንዘብ ለውጠን ለቤተ ክርስቲያንና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ እንዲሁም ለነዳያን እንዲውል ከአደረግን በውኑ ጾማችን እውነተኛ ጾም ይሆናል። ይህን ያደረግን እንደሆነ ነው ጾም ጾምን ማለት የምንችለው።
 4. የጾም ጊዜ የንስሓ ጊዜ ነው። ስለዚህ በጾም ጊዜ በፊት የሠራነውን የስሕተት ሥራዎችን እያስታወስን በመጸጸት ንስሓ መግባት 2. ከመጥፎ መንገድ ወይም ከክፉ ሥራ ሁሉ ከልብ መመለስ፤ 3. ጠባያችንን ማረም እና  መ. ኃጢአታችን በደላችን የእግዚአብሔር ሕግ በመተላለፋችን እያስብን ማዘንና ማልቀስ እንዲሁም ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን አጥብቆ መጸለይ ያስፈልጋል።

እንግዲህ ልዑል እግዚአብሔር መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስጀመረ በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃን ትንሣኤው በሰላምና በጤና ያድርሰን። አሜን!

 

 

መሪነት በመንፈሳውያን ሰዎች

በአንድ ወቅት አንድ አባት ለአንድ ሰው ሲመክሩት “በትናንሽ እግሮችህ ዙሪያ ያሉትን ስሕተቶች ለማየት ትህትና የሚረዳህ አይደለምን?” ብለውት ነበር፡፡ ወዳጆቼ መንፈሳዊ ሕግጋት ምን ያህል ትክክለኛ እንደኾኑ እና በዙሪያችን ያሉትን ስሕተቶቻችንን መርምረን በከንቱ የመጣልንን በከንቱ ካለመናገር እንደሚሻል እንድረዳ ያደርጉናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ በተጨባጭ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ሕግጋትን በመልእክቱ ጽፎልናል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስን ሕይወት በምናይበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ምን ነገሮችን ማሟላት እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ታላላቆቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከዓመታት በኋላ ነው ወደ መሪነት ብቃት የመጡት፡፡ በእርግጠኛነት የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ እድገት በክርስትና ሕይወት ምልልሶቹ ውስጥ ያገኛቸው ናቸው፡፡

የእርሱ ታማኝ አገልጋይነት የዘርና የባህል ተጽዕኖዎችን ሁሉ ተቋቁሞ እንዲያልፍ ረድቶታል፡፡ የዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳን እርሱን ያሳስበዋል፡፡ የአንድ ሰው ባለጠግነት ወይንም ድኅነት ወይንም በማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ ይገኝ በየትኛውም የትምርት ደረጃ ይሁን ቅዱስ ጳውሎስ ስለሰው ልጆች መዳን እንዳይሠራ የሚከለክለው አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ ከእርሱ ትምህርትና የሕይወት ተሞክሮ በተጨማሪ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘና የተመላ እንዲሁም የሥራ ሕይወት ስለነበረው ደስተኛ ነበር፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የመሪነት መመዘኛዎች ብሎ ያስተማረው ትምህርት ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከአሁን ድረስ እየተሠራበት ያለ መመዘኛ ነው፡፡ ስለዚህ እንደማይጠቅሙ እቃዎች አውጥተን የምንጥላቸው ወይንም እንደተጨማሪ ነገሮች ማጣቀሻ አድርገን የምንመለከታቸው አይደሉም፡፡

ወደ ጢሞቴዎስ የተላከውን መልእክት ስለመንፈሳዊ መሪዎች መመዘኛዎች የሚናገር ስናስታውሰው “የእግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደምታስተዳድር ታውቅ ዘንድ እጽፍልኃለሁ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የእውነት ዐምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤት ናት” ይለናል፡፡ (1ኛ ጢሞ. 3÷15)፡፡

መሪነትን የሚፈትነው

የዛሬዋ ዓለማችን ጧት ተሠርቶ ማታ የሚፈርስበትና በችግር የምትናጥበት ምስጢር የሽንገላ መቃብር ስለሆነች ነው፡፡ ሰጪም ይሁን ተቀባዩ፣ አሞጋሹም ተሞጋሹ እንኳን ያለውን የሌለውንም ፈጥሮ እንዲህ ነህ እኮ እንዲህ ነሽ እኮ የሚል ሓሳበ ውዳሴ ከንቱ ከአልጨመረበት ጆሮውን አይሰጥም፡፡ እንደቁም ነገር የሚታየው የሚዢጎደጎደው ከናፍረ ጉኁሉት (የሽንገላ ቃል) ነው፡፡

ነገር ግን ማንኛውም መሪ እንደ መሪ ራሱን የማያከብድና ይልቁንም ራሱን እንደ ታናሽ ሰው ይቆጥር የነበረ አስተዋይ መሪ ዳዊት በመዝ. 21÷6 ላይ “አንሰ ዕፄ ወአኮ ሰብእ ምኑን በኅበ ሰብእ ወትሑት በውስተ ሕዝብ ኰሎሙ እለ ይሬዕዩኒ ይትቃጸቡኒ፣ ይብሉ በከናፍሪሆሙ ወየሐውሱ ርእሶሙ” እኔ ትል ነኝ ሰው አይደለሁም፡፡ በሰው ዘንድ የተናቅሁ በሕዝብም ዘንድ የተዋረድሁ ነኝ ሲል ድምፁን አሰምቷል፡፡ የዳዊት አባባልም በብዙ የግለማችን በሳል ምሁራን መሪ ሰዎች እንዲሁም በገዳም የሚኖሩ መናንያን መነኮሳት አንደበት ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ለእኔ ጭንጋፍ ለሆንሁት ታየኝ” ሲል ተደምጧል፡፡ ይህ አባባል እውነተኛ አባባል ነው ሰው ደካማ ነውና በሥልጣን ለዘለዓለም የኖረ የለምና፡፡

ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ አገልግሎት

      መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የእጁ ሥራ ለሆነው የሰው ልጅ ሁለንተናዊ አገልግሎት ጠቀሜታ ተገልጿል፡፡ ሙሴ ድሆችን ስለመደገፍ መመሪያዎች ሰጥቷል፡፡ ይህ በዘፀአት ምዕራፍ 22ና 23 በግልጽ ተቀምጧል፡፡ እስራኤላውያን ድሆችን፣ ባልቴቶችን/ መበለቶችንና ወላጅ ያጡትን (ወላጅ አልባ) ልጆች እንዲረዱ ታዘዋል፡፡ እንዳያዳሉ የሌላውን ሀብት እንዳይመኙ እግዚአብሔር አስጠንቅቋቸዋል፡፡ የቃርሚያ ሕግን እንኳን በመስጠት ድሆች እንዳይራቡ ሥርዓትን አበጅቶላቸው ነበር፡፡ በዘሌዋውያን ምዕራፍ (25÷8-43) የኢዩቤልዩ ዓመትን በየሃምሳ ዓመት ሲያከብሩ የእስራኤል ሕዝብ አንዱ ሌላውን እንዳይጨቁን አሳስቦአቸው ነበር፡፡

እነኚህ ያየናቸው ጥቅሶች በአሁኑ  ዘመንም በዓለማችን በተለያዩ መልኮች ተግባራዊ እየሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍትህና እኩልነት ወዘተ… በሚሉ ቃላት ሁለንተናዊ አገልግሎት ይካሄዳል፡፡ ተግባራዊነቱ ባይለካም፡፡ የእግዚአብሔር ትእዛዛት በብሉይ ኪዳንም ይሁን በሐዲስ ኪዳን ወደ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር (እግዚአብሔር ተኮር) ወደጐን ደግሞ ከሰው ጋር (ሰው ተኮር) ግንኙነት እንድናደርግ ይጠበቅብናል፡፡ ዐሠርቱ ትእዛዛትን ስንመለከት እነኚህ ሁለት ገጽታዎች ይንፀባረቃሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት ትእዛዛት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረው የሚገባውን ግንኙነት ሲናገሩ፣ የቀሩት ስድስት ትእዛዛት ደግሞ ሰው ከሰው ጋር ስላለው ግንኙነት ይናገራሉ፡፡

ሁለንተናዊ አገልግሎት በአዲስ ኪዳን

በሐዲስ ኪዳን ሁለንተናዊ አገልግሎት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ሕይወትና ተግባር ይህንኑ የሰው ሕይወት መሟላት ያለውን ፍላጐት ያሳያል፡፡ በብሉይ ኪዳን የገለጠውን የእግዚአብሔር ዓላማ ይኸውም የሰውን የተሟላ ሕይወት አጠናክሯል፡፡ ስለድሆች ጌታችን ካስተማረው በተጨማሪ ሐዋርያትም ተመሳሳይ ትምህርት በመስጠት ድሆችን ስለመንከባከብ አስተምረዋል፤ መክረዋል፡፡ (2ኛ ቆሮ.8÷9) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው እግዚአብሔር ለድሆች የሚደረገውን ሥራ ከቶ እንደማይረሳ ይናገራል፡፡ (ዕብ.6÷10) የያዕቆብ መልእክት ለእግዚአብሔር ያለን አምልኮና ለሰው ያለን ምግባር የተቆራኙ መሆናቸውን ያስረግጣል፡፡ (ያዕ. 2÷14-17) ዮሐንስም በመልእክቱ ልባችንን ለድሆች መክፈት እንዳለብን ይናገራል፡፡ (1ኛ.ዮሐ.3÷17) ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን የተቸገሩትን መርዳት እንዳለባት በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን ማድረግ ለክርስቶስ ያላትን እምነት ይገልፀዋል፡፡ ለድሆች ሊኖር የሚገባው አገልግሎት በማቴዎስ ወንጌል (22÷37-40) በስፋት ተመልክቷል፡፡ የአንደኛዋ መቶ ክፍለ ዘመን ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ይህንን አገልግሎት በተግባር ትፈጽማዋለች፡፡ (ፊል.1÷1-6፣ 1ኛጢሞ.3÷8-13)

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበበ

 

“ወይቤሎሙ ዘይፈቅድ ይኩን ሊቀ ለያትሕት ርእሶ ለኩሉ” አለቃ ሊሆን የሚወድ ራሱን ለሁሉ ዝቅ ያድርግ ለሁሉም አገልጋይ ይሁን፡፡ (ማር. 9÷34)

“አንትሙ ውእቱ ፄዉ” ለምድር (ማቴ. 5÷13) እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፡፡ እናንተ ለሕዝቡ አብነት ካልሆናችሁ ማን አብነት ይሆናል። ‹‹ዘእንበለ ዘይገጽፍዎ በአፍአ››ሕዝቡ ከልቦናው ያወጣችኋል በልቡናው በሓሳባቸው ይነቅፏችኋል። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ‹‹ከማሁ ይብራህ ብርሃንክሙ በቅድመሰብእ››እንዲሁም ሥራችሁ ሁሉ በሰው ፊት ይብራ ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት የእናንተ ብርሃን በሰው ፊት ሁሉ ይብራ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ራስ ማነው?

እግዚአብሔር ከሰው ጋር የመሠረተው አንድነትና የአብሮነት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ሰው ስለ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚዘጋጅበት በምድር ላይ ያለች የአንድነት ጉባኤ (ሕብረት) ናት፡፡ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል በስምምነት የተመሠረተች ፍቅርን መተዛዘንን፣ የሰው ልጅ ሁሉ ለፈጣሪው ተገዥ እና ታዛዥ ውሉን (ሕጉን) ፈጻሚ፣ አስፈጻሚ ሆኖ የሚመላለስባት፣ እግዚአብሔር በበኩሉ በውሉ ውስጥ አንዱ ሆኖ ሕጉን በማስፈጸም እና ዋጋ በመስጠት የሚሳተፍባት ታላቅ እና በምድር ላይ ወሰን የለሽ የአንድነት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

እንግዲህ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንነት ስንናገር ከላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ የአንድነት ጉባኤ የባለቤትነት ድርሻ የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን ለምን እንዳስፈለገች? ለምንና በምን እንደተመሠረተች የባለቤትነት ድርሻ ተሳትፎ መብትና ግዴታ ምንን እንደሚመስል በአጠቃላይ የመሥራቹ እቅድ እና መሥራቹ ለመሠረታት ቤተ ክርስቲያን በአደራነት ታላቅ ኃላፊነት ለእነማን እንደሰጠ የሚገልጽ ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሰው እና በአምላክ መካከል የተመሠረተች ፍቅር የታወጀባትና በተግባር የተገለጠባት በደሙ የመሠረታት መንፈሳዊ አካል (ሰውነት) ናት፡፡ ይህም መንፈሳዊ ሰውነት በክርስቶስ ፈቃድ አዳኝነትና መሪነት መኖርን ያመለክታል፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል ቃል በክርስትና ሕይወት መኖር ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ማለት በሌላ አገላለጽ፡- የክርስቶስ ሰውነት ወይም የአማኞች ስብስብ ማለት ነው እንደዚሁም የእግዚአብሔር ቤት ወይም ሕንጻ ማለትም ይሆናል፡፡ በግእዝ ቋንቋ “ቤተ ክርስቲያን” ስንል የክርስቲያኖች ቤት ማለት ሲሆን፣ ይህም የክርስቲያኖች መገናኛና ልዩ የአምልኮ ሥፍራ ማለት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች መንፈሳዊት ተቋም ስትሆን የሰማያዊው መንግሥት የመንግሥተ ሰማያት አምሳል /Model/ ናት፡፡ ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ልናስታውስ የሚገባን ነገር ቢኖር ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር እንደገባንና ከቅዱሳን ጋር ሕብረት እንደፈጠርን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ማኅበር ናት፡፡ ቅዱስ ማለት የተለየ ማለት ነውና ከዓለማዊው ሕይወት ተለይተው በክርስቶስ ለተመሠረተው መንፈሳዊ ሕይወት ራሳቸውን የሰጡ ክርስቲያኖች ማኅበር ናት፡፡ የዚህ ማኅበር ወይም አንድነት መሥራች ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን ራስ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለሆነም የክርስቶስ አካል (ሰውነት) ትባላለች፡፡ (1ቆሮ.12÷12፣ ኤፌ.1÷23)

 • በክርስቶስ ደም የተዋጀች፤ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ በበዓለ ጰራቅሊጦስ የተቋቋመች የእግዚአብሔር መኖሪያ ናት፡፡ (ኤፌ.1÷20፣ 1ቆሮ.6÷19፣ የሐዋ. ሥራ 12÷12)
 • ምድር ላይ ኃይል እንዲኖራት የልዩ ልዩ ስጦታ ባለቤት የሆነች፤ በአግባብና በሥርዓት ልጆቿን እንድትመራ ጠባቂ መሪዎች የተሾሙላት፤ ወንጌልን ለሰዎች ሁሉ ለመስበክ ሓላፊነትን ወስዳ ለአማኞቿ ያስተላለፈች፤ (ለማውገዝ) ሆነ ለመፍታት ሥልጣን ያላት ናት፡፡ (ሮሜ.12÷3-8፣ ኤፌ.4÷11)
 • ቤተ ክርስቲያን በባሕርይዋ ቅድስት፣ ዓለም አቀፋዊት እና ሐዋርያዊት ናት፡፡ በድንበር፣ በዘር በቀለም በጾታ አትከፈልም፡፡ ዓለም አቀፋዊ አንድነታችን ይጠበቅ ዘንድ ሐዋርያዊ ውርስ ያስፈልገናል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባል በየትኛውም ቦታ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ሰው ባለበት ቦታ ከምትኖረው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ውርስ ያለው አገልግሎት ይጠበቅበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያትን ሥልጣን (ሓላፊነት) መሠረት ያደረገ መንፈሳዊ አገልግሎት ማከናወን ካልቻለች ቤተ ክርስቲያን ተብላ ልትጠራ አትችልም፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ተልዕኮ የሰው ልጆችን ፍላጎት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በመምራት ከእግዚአብሔር ጋር መንፈሳዊ አንድነት መመሥረት ነው፡፡ (ማር.16÷15፣ ማቴ.18÷15-20)

ሐዋርያዊ ውርስ

      ሐዋርያዊ ውርስ /Apostolic Succession/ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው፡፡ የእነኚህ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳት ተቀዳሚ አባቶች የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ከሆኑት እነርሱም የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ፡፡

ቤተ ክርስቲያንን እና (መንጋውን) ይጠብቁ ዘንድ ጌታ ለሐዋርያቱ እኩል ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል፡፡ በሐዋርያት መካከል የሥልጣን የበላይነት ጥያቄ በተነሣ ጊዜ እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እና በእነርሱም መካከል መበላለጥ እንደሌለ አስረድቷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሐዋርያቱ ተከታይ እና ወራሽ በሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት መካከልም የሥልጣን መበላለጥ የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊት መንግሥት ስትሆን መሥራቿ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያኗ ራስ እና አካሏ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የእርሱ አካሉ ናት፡፡ (ኤፌ.1÷23) በበላይነት የመምራቱን ሓላፊነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወስዶ ሐዋርያቱን የመንጋው ጠባቂ አድርጐ በተለያየ አቅጣጫ አሰማርቶአቸዋል፡፡ “ረዐይኬ ዓባግእየ” በጎቼን ጠብቅ ሐዋርያቱ የሚጠብቁት የራሳቸውን መንጋ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስም የተሰየመውንና የእግዚአብሔር የሆነውን መንጋ ነው፡፡ ስለዚህ ነው በታላቅ አደራ በመንጋው ላይ የተሾሙት ቤተ ክርስቲያኔን ትጠብቋት ዘንድ… ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ያለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በሥልጣኑ ከሞት የተነሣ የመጀመሪያው በኩር ነው፡፡ ሰው ደግሞ ሟች እና ወደ አፈር የሚመለስ ነው፤ ስለዚህ ሰው ለዘለዓለም የቤተ ክርስቲያን ራስ ለመሆን አይቻለውም በጊዜ ገደብ የተወሰነ ነው፡፡

ማስተዋል ያለብን!  

ቤተ ክርስቲያንን እና (መንጋውን) ይጠብቁ ዘንድ ጌታ ለሐዋርያቱ እኩል ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል፡፡ በሐዋርያት መካከል የሥልጣን የበላይነት ጥያቄ በተነሣ ጊዜ እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እና በእነርሱም መካከል መበላለጥ እንደሌለ አስረድቷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሐዋርያቱ ተከታይ እና ወራሽ በሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት መካከልም የሥልጣን መበላለጥ የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊት መንግሥት ስትሆን መሥራቿ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያኗ ራስ እና አካሏ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የእርሱ አካሉ ናት፡፡ (ኤፌ.1÷23) በበላይነት የመምራቱን ሓላፊነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወስዶ ሐዋርያቱን የመንጋው ጠባቂ አድርጐ በተለያየ አቅጣጫ አሰማርቶአቸዋል፡፡ “ረዐይኬ ዓባግእየ” በጎቼን ጠብቅ ሐዋርያቱ የሚጠብቁት የራሳቸውን መንጋ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስም የተሰየመውንና የእግዚአብሔር የሆነውን መንጋ ነው፡፡ ስለዚህ ነው በታላቅ አደራ በመንጋው ላይ የተሾሙት ቤተ ክርስቲያኔን ትጠብቋት ዘንድ… ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ያለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በሥልጣኑ ከሞት የተነሣ የመጀመሪያው በኩር ነው፡፡ ሰው ደግሞ ሟች እና ወደ አፈር የሚመለስ ነው፤ ስለዚህ ሰው ለዘለዓለም የቤተ ክርስቲያን ራስ ለመሆን አይቻለውም በጊዜ ገደብ የተወሰነ ነው፡፡

የተቀበልነውን ሥልጣነ ክህነት ምእመናንን እና ምእመናትን በመንፈሳዊ አባትነት ለማስተዳደር ከክርስቶስ ያገኘነውን ሥልጣን ነው፡፡ (1ጴጥ. 5÷14)፡፡ ይህን ሥልጣን ከታሰበለት ዓላማ በተለየ መልኩ ለዓለማዊ ጥቅም ካዋልነው ክርስቶስ በመሠረታት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ እና ቀኖና መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ አልተመራችም ማለት ነው፡፡

የክርስቶስ ትሕትና ለፓትርያርኩም ለሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ መመሪያ ነው፡፡ የክርስቶስ ሕይወት ለሁሉ መመሪያ እንደሆነ ቢታወቅም፤ በተለይ ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ካህናቱና ዲያቆናቱ ይህን ትሕትና በመድገም የክርስቶስን ብርሃን ለጨለማው ዓለም ማብራት ይጠበቅባቸዋል እናንተ የዓለም ብረሃን ናችሁ ተብለናልና፡፡ (ማቴ.20÷26-28)

ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደር ማለት በአንድ ሰው የምትመራ ብቻ ሳይሆን ከቅዱስ ሲኖዶስና ከተሾሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ልጆች ሁሉ ጋር በአንድነት የሚከናወን ሓላፊነት ነው፡፡ ይህንንም ከሐዋርያቱ ሲኖዶስ መገንዘብ ይገባል፡፡ (ማቴ.23÷8፣ 28÷19፣ የሐዋ.14÷23፣ 15÷6-23)፡፡

ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ መንፈሳዊ ዳኝነት የመስጠት የማስታረቅ፣ የመምከር፣ የማስተማር፣ ለሀገር ለወገን የመጸለይ፣ መልካም ዜጋ ሀገሩንና ቤተሰቡን የሚረዳ የሥራ ፍቅርና የሰው ፍቅር ያለው እንዲሆን ግዴታ  ያላት መሆኗንና ይህንም ሥልጣን ተጠቅማ ለሰው ልጆች ድኅነትና መብት መጠበቅ የጐላ ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባታል፡፡

ሐዋርያት በጵጵስና ሥልጣነ ክህነት እና በመንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ጸጋዎች ተሞልተው በየሔዱበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን መሥርተዋል፡፡ ኢ-አማንያንን አስተምረው ከክርስቶስ ጋር አስተዋውቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው የእግዚአብሔርን መንጋዎች አገልግለዋል፡፡ እነርሱ ባሉበት ቦታ አማንያኑ አሉ፡፡ ሐዋርያቱ ያስተማሩትም ሕዝብ ባለበት ደግሞ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ ያለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም አንድ ሁለት እያሉ አስተምረው የሰበሰባት ቤተ ክርስቲያን የአማንያን ስብስብና ጉባኤ በክርስቶስ የሆነ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡  ይቆየን