ዐቢይ ጾም
ዘወረደ
ዘወረደ ማለት ፦ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደገለጸው ‹‹ ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ (ከሰማየ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤ ሁን ብሎ የማዳነ ሥልጣን ያልው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም) በማለት ከሰማየ ሰማያት ወረዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለሙን ያዳነበት ምስጢር የሚነገርበት ሳምንት ማለት ነው (ድጔ ዘአስተምህሮ)
፩ መዝሙር፦ተቀነዩ ለእግዚአብሔር
ምስባክ፦ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤
ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ፤ አጽንዕዋ
ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር (መዝ 2፥11-12)።
ምንባብ፦ ዮሐ.3፥10-20
ይህ የዛሬው እሑድ ዐቢይ ጾምን የምንቀበልበት እሑድ ነው። ቅበላ ይባላል። ከነገ ሰኞ ጀምሮ የምንጾመውን ጾም የምንቀበልበት እሑድ ነው። ይህ ነገ የምንቀበለው ጾም በልዩ ልዩ ስሞች ይታወቃል፦ዐቢይ ጾም ይባላል፤ ዐቢይ ጾም ማለት ትልቁ ጾም ማለት ሲሆን ዐቢይ የተባለበትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ስለሆነ ነው (አርባ) ጾም ይባላል፤ ‹‹ከዚህም በኋላ ጌታ ወደ ምድረ በዳ (ቆሮንቶስ ገዳም) ሄዶ አርባ ቀንና አረባ ሌሊት ጾመ፤ (ማቴ 4፥1 )
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዓብይ ጾም የምትሠጠው ክብር በማንም አገር ጥንትም ሆነ ዛሬ አልታየም። በጾሙ ስምንት እሁዶች አሉ። ለስምንቱ ሁሉ የተለያየ ስያሜ አላቸው። ስያሜውም ሐዲስ ኪዳንንና ማሕሌተ ያሬድን መሠረት ያደረገ ነው። የመጀመሪያው እሁድ ዘወረደ ይባላል። ጾሙ ሰኞ ሊጀመር መንፈሳዊ አገልግልቱ በጾም ሥርዓት ከወደዚህ ባለው ቅዳሜ ይጀመራል። “ዘወረደ እምላእሉ አይሁድ ስቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ” ትርጉሙ “ከለይ ወርዶ ሥጋ የለበሰውን አካላዊ ቃል አይሁድ ሰቀሉ፣ ሁሉን የሚያድን ሁሉን የሚያኖር መሆኑን ግን አላውቁም” የሚለው መሐትው በዓቢይ ጾም ዋዜማ ቅዳሜ ጧት ከቅዳሴ በኋላ ይቆማል መሐትው የሚለው ቃል ዋዜማ ድራር ከሚለው ቃል ጋር ይመሳሰላል። ድራር ማለት “ራት” ማለት ሲሆን ከሌላ ቃል ጋር ከተናበበ ግን እንደ ዋዜማ ያገለግላል፣ ዋዜማና መሐትው የአቀራረብ ጊዜአቸው ይለያያል። ዋዜማ ለሚቀጥለው ቀን ክብረ በዓል በሠርክ የሚካሄደው መንፈሳዊ አግለገልት ነው። መሐትው ደግሞ ለምሳሌ ሰኞ አንድ ክብረ በዓል ቢኖር እሁድ ጧት ከቅዳሴው ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ምንፈሳዊ አገልግልት ነው። “ሐተወበራ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ ማሕቶት ይወጣል፣ ማሕቶት ሲበዛ መሐትው ይባላል። በጥንት ዘመን በክብረ በዓሉ ዋዜማ በዓሉን ለማብሠር መብራትብ የማብራት ልምድ ነበር። በዚሁ ነው መሐትው የተባለው።
መሐትው ፍሲካ መሐትው ዮሐንስ። … ከተባለ በዋዜማው የሚዘመረውን መዝሙር መግለጹ ነው።
ከዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት እስከሚቀጥለው ሳምንት ዘወረደ ይባላል። ቅዱ ያሬድ ምሥጢረ ትስብእትንና ሥነ ስቅለትን እያገናዘበ የዘመረው መዝምር ለስያሜው ዋና መነሻ ነው። በአንዳንዱ የዜማ ሊቃውንት ይህ ስሙን መዋዕለ ሙሴኒ ይሉታል። ከዘወረደ ሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ያምስቱ ቀን የጾምድጔው ዕዝልም ሆነ እስመለአለም አብዛኞቹ በዘፀአት 24፥5 እስከ መጨረሻው እንድተገለጸው ሙሴ በደብረ ሲና ስድስት ቀን ከቆየ በኋላ እግዚብሔር እንዳነጋገረው በሚተርከው መሠረት የተሰጠ ስያሜ ነው። ባንድንድ የፍትሓ ነገሥት በዚህ ሰሞን እስከ 12 ሰዓት ድረስ መጾም እንዳለበትና በተቀሩት ሌሎች ሳምንታት ከሕማማት በቀር እስከ 11 ሰዓት ብቻ መጾም እንዳለበት ተመዝግቧል።
ከነገ ሰኞ ጀምሮ ዐቢይ ጾምን እንጀምራለን። ዛሬ መነጋገር ያለብን ይህን ዐቢይ ጾም እንዴት አድርገን እንደምንጾመው ነው። ስለ አራት ነገረሮች ማሰብ አለብን፦
- ጾም በምንጾምበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል እንደሚያስጠነቅቀን ጾም ስንጾም ጾማችን ለተርእዮ፣ ሰው እንዲያመሰግነን ማድረግ የለብንም። ከልዑል እግዚአብሔር ዋጋ እንድናገኝበት መሆን አለበት እንጂ። አንዳንድ ሰዎች እስከ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚጾሙ ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ በጥሬ ብቻ እንደሚጾሙ ይናገራሉ። ይህ ሁሉ ጥሩ ነው። ነገር ግን ይህ ለውዳሴ ከንቱና ለተርእዮ እንዳይሆንብን መጠንቀቅ አለብን። እንደዚህ መጾማችንንም ለሰው መንገር የለብንም። ለተርእዮ ወይም ሰዎች እንዲያውቁን የምናደርገው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ አያሰጥም (ማቴ 6፥16-18)
- ጾም በምንጾመበት ጊዜ ከምግብ ብቻ መከልከል የለብንም። የምንጾማቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች አሉ የአልክሆል መጠጦችንም መጾም አለብን። እንዲያውም የተለያዩ ኃጢአቶችን እንዳንሠራ ያለመጠን ከመጣጣት መቆጠብ አለብን። በመሆኑም ከሚያሰክሩ መጠጦች መከልከል ያለብን በጾም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ከአልኮሆል መጠጦች አዘውትሮና አብዝቶ ከመጠጣት መከልከል አለብን። 2. በተጨማሪ ክፉ ነገር ከማየት፣ ክፉ ነገር ከመናገር፣ መጥፎ ነገር ከመስማት ወደ መጥፎ ቦታም ከመሄድ መከልከል አለብን። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለ ጾመ ሲዘምር ‹‹ይጹም ዓይን ይጹም ልሳን፣ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሱም እምተናግሮ፤›› (ዓይን ይጹም፤ አንደበትም ይጹም፤ ጆሮም ክፉ ነገር ከመስናት ይጹም) ይላል።
- ጾም በምንጾምበት ጊዜ የምንጾመውን ምግብ ማለት ቊርሳችንን ወይም ምሳብ የምንበላው ማታ ከሆነ ምሳችንን ጭምር አጠራቅመን ወይንም በቊርሳችን በምሳችን ጊዜ የምንመገበውን በገንዝብ ተምነን ለእግዚብሔር (ለቤቱ ክርስቲያን) ወይንም ለበጎ አድራጎት ድርጅት ወይንም ለነዳያን መስጠት አለብን። የምንጾመውን ምግብ በገንዘብ ለውጠን ለቤተ ክርስቲያንና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ እንዲሁም ለነዳያን እንዲውል ከአደረግን በውኑ ጾማችን እውነተኛ ጾም ይሆናል። ይህን ያደረግን እንደሆነ ነው ጾም ጾምን ማለት የምንችለው።
- የጾም ጊዜ የንስሓ ጊዜ ነው። ስለዚህ በጾም ጊዜ በፊት የሠራነውን የስሕተት ሥራዎችን እያስታወስን በመጸጸት ንስሓ መግባት 2. ከመጥፎ መንገድ ወይም ከክፉ ሥራ ሁሉ ከልብ መመለስ፤ 3. ጠባያችንን ማረም እና መ. ኃጢአታችን በደላችን የእግዚአብሔር ሕግ በመተላለፋችን እያስብን ማዘንና ማልቀስ እንዲሁም ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን አጥብቆ መጸለይ ያስፈልጋል።
እንግዲህ ልዑል እግዚአብሔር መዋዕለ ጾሙን በሰላመ ያስጀመረ በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃን ትንሣኤው በሰላምና በጤና ያድርሰን። አሜን!