Archives

All posts for the month July, 2017

ማንነት ማለት መታወቂያ፣ መለያ ማለት ነው። በመሆኑም ማናቸውም ነገር የራሱ የሆነ ማንነት አለው። ከዚህም የተነሣ በማንነቱ እየተለየና እየታወቀ እገሌ ነው ይባላል። ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን‹‹እርስ በርሳችሁ ፍቅሩ ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያወቃሉ።››ሲል የገለጠላቸው ፍቅር   የማንነታቸው መታወቂያ መሆኑን ሲነግራቸው ነበር። ዮሐ.፲፫፥፲፭። ይህችም ፍቅር ጠላትን እስከመውደድ ድረስ የምትዘልቅ ናት። ማቴ ፭-፥፵፬ በብሉይ ኪዳንም ስለማንነት ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› ተብሎ ተገልጧል። ኤር.፲፫፥፳፫።

የማንነት ጥያቄ ቀላል አይደለም ምክንያቱም የማንነት ምልክት የጠፋበት ሰው ‹‹እገሌ ነኝ›› ማት አይችልምና። ለምሳሌ ኦርቶዶክሳዊ ማንነታቸውን ከጠሉ በኋላ ኦርቶዶክስ ነኝ የሚሉ አሉ። ይሁን እንጂ የማንነታቸው መግለጫ የሆነውን ኦርቶዶክሳዊ ማንነታቸውን ይዘው እስካልተገኙ ድረስ እነርሱ ኦርቶዶክስ አይደሉም።ስለሆነም ‹‹እገሌ የምንባልበትበትን እና ሕይወታችንም ጭምር የሆነውን ማንነታችንን ከነምሥጢሩ ከትርጓሜው፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችንን ከነምሥጢሩ ከነትርጓሜው ከነጸጋው ቅርሳችንን ከቅድስናው፣ ከነበረከቱ፣ ታሪካችንን ከነገድሉ በእምነት ልንጠብቀው ይገባል።

ሃይማኖት ከጥንት ከመጀመሪያው የሰውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እና በምሳሌው የፈጠረው ስሙን እንዲቀድስ ክብሩን እንዲወርስ ነውና። ዳግመኛም የሰው ልጅ እምነት አጉደሎ፣ በኃጢአት ወድቆ በተደበቀበት ጊዜም እግዚአብሔር ‹‹አዳም አዳም ወዴት ነህ›› ብሎ ያሰማው ድምጽና እርሱን ለመፈለግ ወደ እርሱ ያደረገው ጉዞ ሃይማኖት ነው። ከዚህም የተነሣ ሃይማኖት ፍኖተ እግዚአብሔር ይባላል። በተለይም የክርስትና ሃይማኖት የአምላክ መገለጥ ነው። ምክንያቱም ጌታ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የተገለጠውና የጠፋውን ሰው ለመፈለግ ነውና። በመሆኑም ይህ የሰውን ልጅ ለመፈለግ የተደረገ አምላካዊ ጉዞ የተፈጸመበት እና የታተመበት ሃይማኖት ፍኖተ እግዚአብሔር መባሉ የሚገባ ነው።

ሃይማኖት ከመጀመሪያው ጀምሮ የመጣ አንድ ጊዜም ለቅዱሳን የተሰጠ ነው። ይኸንንም በተመለከተ ሐዋርያው ይሁዳ በመልእክቱ ‹‹ወዳጆች ሆይ ስለመዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድታገደሉ እየመክርኋቸው እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።›› ሲል ተናግሯል። ይሁ.፩፥፫ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ አንድ ሃይማኖት›› ሆነዋል። ኤፌ.4፥4። ቅዱስ ዮሐንስ የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን›› ብሎአል። ፩ኛ. ዮሐ. ፩፥፩።

ይህ ነው ሃይማኖት ለሰው ልጆች የተሰጠ፣ በቅዱሳንም አንደበት የተሰበከ ብቻ ሳይሆን በኋላም ጌታ ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው ባስተማረው ትምህርት እና በፈጸመወ ቤዛነት ያጸናው ነው። ቀጥሎም ከእርሱ የተማሩ ሐዋርያት በዓለሙ በሙሉ አስፋፍተውታል ቅዱስ ፪ጳውሎስ ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁ›› ያለው ለዚህ ነው ፩ኛ. ቆሮ. ፲፩፩፥ ፳፫። በገላትያ መልእክቱም ወንድሞች ሆይ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደሰው እንዳይደለ አስታወቃችኋለሁ። ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው  አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም›› ብሏል። ገላ. ፩፥፲፩-፲፪።

                                                                                        ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ

 

 

መግቢያ

የሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ውርስ

      ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ውርስ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው፡፡ የእነኚህ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ተቀዳሚ አበው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ከሆኑት እነርሱም የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ፡፡

ቤተ ክርስቲያንን እና (መንጋውን) ይጠብቁ ዘንድ ጌታ ለሐዋርያቱ እኩል ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል፡፡ በሐዋርያት መካከል የሥልጣን የበላይነት ጥያቄ በተነሣ ጊዜ እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እና በእነርሱም መካከል መበላለጥ እንደሌለ አስረድቷቸዋል፡፡ በበላይነት የመምራቱን ሓላፊነት በኩረ ትንሣኤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን የመንጋው ጠባቂ አድርጐ በተለያየ አቅጣጫ ወደ ዓለም አሰማርቶአቸዋል፡፡ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡” ማቴ. 28÷19-20፡፡ ሐዋርያቱ የሚጠብቁት የራሳቸውን መንጋ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስም የተሰየመውንና የእግዚአብሔር የሆነውን መንጋ ነው፡፡ ስለዚህ ነው በታላቅ አደራ በመንጋው ላይ የተሾሙት፡፡     በተመሳሳይ መልኩ በሐዋርያቱ ተከታይ እና ወራሽ በሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት መካከልም የሥልጣን መበላለጥ የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊት መንግሥት ስትሆን መሥራቿ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያኗ ራስ እና አካሏ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የእርሱ አካሉ ናት፡፡ (ኤፌ.1÷23)

ሊታወሱ የሚገባቸው ዋና ዋና ነገሮች

ሀ.  የተቀበሉት ሥልጣነ ክህነት ምእመናንን እና ምእመናትን በመንፈሳዊ አባትነት ለመምራትና ለማስተዳደር ከክርስቶስ ያገኙት ሥልጣን ነው፡፡ (1ጴጥ. 5÷14)፡፡ ይህን ሥልጣን ከታሰበለት ዓላማ በተለየ መልኩ ለዓለማዊ ጥቅም ካዋልነው ክርስቶስ በደሙ በመሠረታት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ እና ቀኖና መሠረት ያስጠይቃል፡፡

ለ. የክርስቶስ ትሕትና ለሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ መመሪያ ነው (በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ)፡፡ የክርስቶስ ሕይወት ለሁሉም መመሪያ እንደሆነ ቢታወቅም፤ በተለይ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህን ትሕትና በመድገም የክርስቶስን ብርሃን ለጨለማው ዓለም ማብራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ “ወለክሙሰ አኮ ከማሁ ወባሕቱ ዘይፈቅድ እሞኔከሙ ይኩን ዐቢየ ይኩንክሙ ላእከ፡- ወዘሂ ይፈቅድ እምኔክሙ ይኩን ሊቀ ይኩንክሙ ገብረ፡፡ እስመ ኢመጽአ ወልደ እጓለ እመሕያው ከመ ይትለአክዎ ዘእንበለ ዳእሙ ከመ ይትለአክ ወየብ ነፍሶ ቤዛ ብዙኃን” በእናንተስ እንዲህ አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም፡፡ (ማቴ.20÷26-28)

ሐ. ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደር ማለት በአንድ ሰው የምትመራ ብቻ ሳይሆን ከተሾሙት የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ጋር በአንድነት የሚከናወን ሓላፊነት ነው፡፡ ይህንንም ከሐዋርያቱ ሲኖዶስ መገንዘብ ይገባል፡፡ (ማቴ.23÷8፣ የሐዋ.14÷23፣ 15÷6-23)፡፡

መ. ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደርና ምእመናንን ማስተማር እንዲሁም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የተያያዙ ናቸው፡፡ (1.ተሰ 5÷12፤ 1ጢሞ.3÷2-7)፡፡

ሠ. የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከጌታ ትምህርት እና ከሐዋርያት ስብከት እንዲሁም ከዚሁ ጋር ከማይጣረሰው ቅዱስ ትውፊት የወጣ አይደለም፡፡ (ገላ.1÷8-9)

ረ. ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን ያላት መሆኗንና ይህንም ሥልጣን ተጠቅመው ለሰው ልጆች መብት መጠበቅ የጐላ ድርሻ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሐዋርያት በጵጵስና ሥልጣነ ክህነት እና በመንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ጸጋዎች ተሞልተው በየሔዱበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን መሥርተዋል፡፡ ኢ-አማንያንን አስተምረው አሳምነው አጥምቀው ከክርስቶስ ጋር አስተዋውቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው የእግዚአብሔርን መንጋዎች አገልግለዋል፡፡ እነርሱ ባሉበት ቦታ አማንያኑ አሉ፡፡ ሐዋርያቱ ያስተማሩትም ሕዝብ ባለበት ደግሞ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ ያለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም አንድ ሁለት እያሉ አስተምረው የሰበሰባት አንዲት ቤተ ክርስቲያን የአማንያን ስብስብና ጉባኤ በክርስቶስ የሆነ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡

ስለዚህም አግናጥዮስ የተባለ የመጀመሪያ የክርስትና ዘመን አባት በመልእክቱ እንዲህ ብሏል፡-

  • ሊቀ ጳጳሱ ባለበት ቦታ መንጋው ደግሞ አለ፡፡ ልክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባለበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳለች ማለት ነው ይላል፡፡
  • ስለዚህም አንድ ሊቀ ጳጳስ እንደተቋም ይታያል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ የሕዝብ አገልጋይ ታማኝ መንፈሳዊ አባት ሕዝቡን በፍቅር ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚመራ፤ ታማኝ ጠባቂ፣ ለመንጋው የሚገደው፤ እርሱ በጾም በጸሎት በስግደት በማስተማር በመምከር በማስተዳደር ዕረፍት አጥቶ ለሌሎች ዕረፍትን የሚያሰጥ፣ በስሙና በማዕረጉ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ በቅድስና የሚታወቅ መሆን ይገባዋል፡፡
  • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ረዐይኬ አባግዕየ” “በጐቼን ጠብቅ” አለው ምን ዓይነት አጠባበቅ? ዮሐ. 21÷15
  • መንጋዎቻቸውን ከእነዚህ ዓይነቶች የገሃነም ደጆች ተከላክለው በትጋት እንዲጠብቁ የተመረጡት ደግሞ 12ቱ ሐዋርያትና በእነርሱ እግር የተተኩ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው፡፡ (ሮሜ.1÷5፣ 1ቆሮ 9÷1)፡፡
  • ሊቃነ ጳጳሳቱ ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎችን በሓላፊነት ተቀብለዋል፡፡ በበላይነት የእግዚአብሔር መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ እየተቆጣጠራቸው በእርሱ አጋዥነት በክርስቶስ ያመኑትን በትምህርታቸው በምክራቸውና በጸሎታቸው እገዛ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲያደርሱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
  • ይህንንም በታማኝነት ሲፈጽሙ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የተመሰገኑ (ብፁዓን) ተብለዋል፡፡ ስለዚህ አገልግሎታቸው በምድር ይሁን እንጂ የአገልግሎታቸው ፍሬ መንግሥተ ሰማያት እንደሆነ ይህ የጌታችን ቃል ያረጋግጥልናል፡፡
  • የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻውን በአንዱ በቅዱስ ጴጥሮስ እጅ ብቻ አላስቀመጠውም፡፡ ለአንዱ ጴጥሮስ የተሰጠው በሌሎች አገልጋዮቹ ሐዋርያት ላይም እንዳለ እሙን ነው፡፡ በመሆኑም ለሐዋርያቱ ሁሉ እኩል ሥልጣን ሰጣቸው፡፡
  • እየተመካከሩ በተሻለ መልኩ አገልግሎታቸውን በታማኝነት እንዲወጡ በጋራ መክረው የተሻለውን እንዲወስኑ ብዙ የሆነውን የመንጋውን ደኀንነት የመንጋው እረኞች ተቀራርበውና ተመካክረው እንዲጠብቁ ለእያንዳንዱ እኩል ሓላፊነትን ሰጣቸው በመንጋው ላይ (በቤተ ክርስቲያኑ ላይ) በእውነት በቅንነት የሚያስተላልፉት ውሳኔ ሁሉ በሰማያት የሚጸና ውሳኔ አድርጎ እንደሚቆጥርላቸው አረጋገጠላቸው፡፡ (የሐ.ሥራ 13÷4-12)፡፡
  • መንጋውን በሙሉ ግልገሎቹንም ጠቦቶቹንም በጎቹንም በእኩል እንዲጠብቁ አዘዛቸው መንጋውን በዕድሜ ልዩነት፣ በሀብት ልዩነት፣ በቦታ ልዩነት፣ በሥጋ ዝምድና፣ ሳያበላልጡ በተመሳሳይ ሕግና ሥርዓት በእኩልነት እንዲያስተዳድሩ አደራ ተጣለባቸው፡፡ (ማቴ.11÷25፣ ሉቃስ 16÷15)፡፡
  • አደራውን በአግባቡ እስከፈጸሙ ድረስ በመንጋው የክርስቶስ ሕዝብ ላይ ያላቸው ሥልጣን በሰማያትም የሚያስከብራቸው እንደሚሆን ጽኑዕ ተስፋ ተሰጣቸው፡፡ (ማቴ.13÷11፣ 18÷18፣ 20÷19-28፣ ማር.6÷7-13፣ ሉቃስ 9÷1-6፣ 10÷1-12)፡፡

ይቀጥላል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

አዲስአበባ