Archives

All posts for the month October, 2017

ሰውና እውነት የሰው ሙሉ ፈቃደኝነት ለእውነት ተግባር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዲያውቁት ብቻ ሳይሆን እንዲወዱት ይሻል፡፡ ከልብ ሲወዱት ያን ጊዜ ያውቁታል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ማወቅና እንዲወዱትም ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን ለመውደድ ደግሞ ሙሉ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው፣ ልቡን ያልሰጠ ሰው  እግዚአብሔርን አያገኘውም፡፡ እግዚአብሔር እንደተሰወረበት ይቀራል፡፡ የእግዚአብሔር የመጀመሪያው ጥሪ ልብህን ስጠኝ የሚል ነው፡፡ ልቡን ለእግዚአብሔር ያልሰጠ ሰው  እግዚአብሔር ሊያድርበት አይችልም፡፡

የሃይማኖት ፍቅር ወንድምህን እንደራስ አድርገህ ውደድ ብቻ ሳይሆን ጠላትህንም  ወደድ ይላል። ይህ ሃይማኖታዊ ትምህርት ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ሰቦችህን ብቻ ሳይሆን ጠላትህንም ውደድ ይላልና  ሃይማኖት ከሥጋ ፍላጐት ጋር ስለማይደራደር በጣም ከባድ ነው፡፡ ሃይማኖት የሰውን ሁለንተናዊ ተግባሩን ኅሊናውንም ይቆጣጠራል ይህ ደግሞ በሥጋውያን ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ አያደርገውም ሰው ማንም በዚህ ግባ፣ በዚያ ውጣ ብሎ እንዲያስገድደውና እንዲያዘው አይፈልግም ምክንያቱም ይህን እንደ ግል ጉዳዩ አድርጎ ያስባልና ነው፡፡

ስለዚህም ሥጋዊው ሰው ሰነፍ ሰው በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል። ራሱን ለመከላከል ሲል የሃይማኖት ትምህርት ኋላ ቀር የሆነ ጊዜው ያለፈበት ትምህርት አድርጎ በማቅረብና በመተቸት በዚህም ራሱን ለማሳመን ጥረት ያደርጋል፡፡ የሃይማኖት ትምህርት ለትእዛዛቱ ሁሉ መነሻ የሚያደርገው ራሱን  እግዚአብሔርን ስለሆነ የፀያፍ ሥራ ዐመል ያለበት ሰው መጀመሪያ ቁጣውን በራሱ በእግዚአብሔር ላይ ይገልፀዋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር የለም፣ ቢኖር ኑሮ ይታይ ነበር ይላል፡፡

እንዲሁም በሰዎች ላይ የሚታዩ የተለያዩ አሰቃቂ ነገሮችና ችግሮች እግዚአብሔር ቢኖር ኑሮ አይኖሩም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያን ሁሉ ዝም ብሎ አይመለከትም ነበር በማለት መቶ ሃምሳውን ምክንያት ይደረድራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሳይንስ ስም እዚህም እዚያም የሚናፈሱትን የመናፍቃንን ሐሳብ በመጠቃቀስ የሃይማኖትን ትምህርት ውድቅ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ እምነትን ይህን ያህል ጥርጥር ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ከሰው የሥጋ ደካማ ፍላጎት ጋር አብሮ የማይሄድ ሕግና ሥርዓት፣ ትምህርት ስላለው ነው፡፡ ትምህርቱ ከሰው ደካማ የሥጋ ፍላጎት ጋር ስለማይሄድ ሃይማኖት በሰው ዘንድ ተወዳጅነት የለውም፡፡

ወንጭፍ ባልኖረ የማሽላ እሸት ደግ ነበር እንዳለችው ወፍ ሰውም የሚቆጣጠረው የሃይማኖት ሕግና ሥርዐት ባይኖር ኑሮ ይወድ ነበር፡፡ ልጓም የሌለው ፈረስና ሃይማኖት የሌለው ሰው አንድ ናቸው ተብሏል፡፡ ፈረስ ልጓምን የማይፈልገው እንደ ልቡ ለመሆን ነው ሰውም የልቡን ለመፈጸም ሃይማኖትን አይፈልገውም። ፈረስ ልጓም ከሌለው ሩጦ ገደል ሊገባ እንደሚችል ሁሉ ሰውም የሚቆጣጠረው የሃይማኖት ሕግና ሥርዐት ከሌለ ሞተ ኃጢአት ይጠብቆዋል። እንደ ልብ በመፈንጨትና በመጨፈር በመዝለል በመብላት በመጠጣት በመዳራት ተሰናክሎ እንዳይቀር የሚገታው የሃይማኖት ሕግና ሥርዐት ስለሆነ ሃይማኖት ለሰው ልጅ የግድ ያስፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ያለ አግባብ መበልፀግን ብዙ ሰው እንደሚፈልገው ይታወቃል፡፡ ይሁንና ያለ አግባብ መበልፀግን ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አይሄድም ብሎ ስለሚያስተምር ያለ አግባብ መበልፀግን የሚሻ ሰው የሃይማኖት ትምህርት ያስጠላዋል፣ ያስኮርፈዋልም፡፡ ከሃይማኖት ትምህርት ጋር የማይሄድና በዚህም ሰውን የሚያስኮርፈው ሌላው ዐመል ሴሰኝነት ነው፡፡ የሴሰኝነት ዐመል ያለበት ሰው ራሱን ለዚህ ፀያፍ ሥራ ተገዥ ያደረገ ሰው በመሆኑ ምክንያት ከሃይማኖት ትምህርት ጋር ስምምነት የለውም፡፡ ሃይማኖት ለእንዲህ አይነቱ ዐመል ከኃጢአት ሥር ስለሚመድበውና ጧት ማታ ስለሚያወግዘው ትምህርቱ ያስጠላዋል፡፡ በመሆኑም ሃይማኖትን በተለያዬ መንገድ ለመዋጋት ቆርጦ ይነሳል፡፡ ሃይማኖት የሰውን የሥጋ ድካም ፍላጐት የማይቃወም ቢሆን ኑሮ ግን ሰውም ሃይማኖትን ለመቃወም ምክንያት አይኖረውም ነበር፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ በሐሰት አትመስክር የሰው ገንዘብ አትመኝ፣ ሙስና ኃጢአት ነው፡፡ እምነት በተግባር ሲገለጽ ነው በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመስገድ፣ በመመጽወት፣ ሃይማኖት በሥራ ካልተገለጸ የሞተ ነው፡፡ የሚል ትምህርት ታላቅ ትኩረት አለው ከሃይማኖት የሚርቅ ሰው እንዳሻው በፈለገው መንገድ በማናቸውም ፀያፍ ነገር ሁሉ እንዳይገኝ ከሚከላከለውና በዚህም ነጻነቱን ከሚገድብበት አንድ ትልቅ ከሆነ ቀንበር ነጻ እንደወጣ ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ ሰው እንደ ሰው ሳይሆን ሰይጣናዊ ለመሆን ሲፈልገ ቁጥጥር በሚያደርግበት ከሃይማኖት ሕግና ሥርዓት ራሱን ያገላል፡፡ ራሱን ከሃይማኖት ካገለለና የሃይማኖት በእሱ ላይ ቁጥጥር ማድረግን ከተወ እንደፈለገው ሆነ ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት ሕግና ሥርዓት ሰውን ስለሚቆጣጠረው ሰው ሃይማኖትን ለመቀበልና ተግባራዊ ለማድረግ ይቸገራል። ሃይማኖትን ለመቀበል ስለ ማይወድም የልቡን ቀና ሳሊና ይዘጋበታል፡፡ መንፈሳዊና መልአካዊ ልቡናው ስለሚዘጋበትም ትምህርቱን ለማስተዋልና ለመቀበል አይችልም፡፡

ፈረንሳዊው ፈላስፋና የሒሳብ ሊቅ ፓስካልም ሲናገር እንዲህ ብሏል “ልብ አእምሮ ሊያስተውላቸው የማይችሉት የራሷ ምክንያቶች አሏት ማለት ነው፡፡ ይህ አገላለጽ የአእምሮና የልብ መንገድ የተለያየ ነው ጥሩ ማስረጃ ያለው፣ ለአእምሮ አሳማኘ የሆነ ሐሳብ ይዛችሁ አንድን ሰው ልታሳምኑት ካልቻላችሁ ችግሩ ያለው ከሐሳባችሁ ላይ ሳይሆን ሰውየው ሐሳቡን ለመቀበል ካለው አለመፈለግ ምክንያት ላይ በመነሣት ለችግሩ መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡

ለምሳሌ ሌብነትን ስርቆትን በቀጥታ ሌብነት፣ ስርቆት አይለየውም ለመዋሸትም እንዲሁ ነው። እገሌ ቀጣፊ ነው፣ አታላይ ነው፣ አጭበርባሪ ነው ለማለት ተፈልጎ ነገሩን አድበስብሶ ሲያልፍ ብልጥ ነው፣ ጮሌ ነው ብሎ ያልፈዋል፡፡ በአንጻሩ እገሊት ቀጥተኛ ሰው ናት፣ ሐሳቧን ሳትደብቅ እውነቱን፣ ሐቁን ትናገራለች ለማለት እርሷ ሞኝ ናት ጅል ናት፣ ገጠሬ ናት፣ ጥሬ ናት ትባላለች። ይሁንና እውነት መናገር ሞኝነት ጅልነት አይደለም። ገጠሬነትም አይደለም፣ ጥሬ ነው የሚያሰኝም አይደለም እንደዚሁ ሁሉ ማታለልም፣ ማጭበርበርም ብልጥነት አይደለም፣ ጮሌነትም አይደለም፡፡

ሰው ልቡን ካደነደነ አንድን ሐሳብ ላለመቀበል ከወሰነ ምንም ነገር እንደማይመልሰው በአየሁድ ታይቷል፡፡ የአይሁድ አለቆችንና መምህራንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት አላሳመናቸውም። የተአምር ሥራዎች አላስደነቃቸውም በትምህርቱና በሥራዎቹ አልተመለሱም፤ ክርስቶስን ይጠሉት ስለነበርና ሥራውን ላለመቀበል ወስነው ስለነበር የክርስቶስ ትምህርትና ሥራ በእነርሱ ዘንድ ሽንፈት ደርሶባቸዋል። እንግዲያውስ ትምህርቱ  እጅግ በጣም ግሩም ነበር፡፡ እፁብ ድንቅ ነበር፣ ምንም እንካን የማይዋጥላቸው ቢሆንም የተደረጉትና የተፈፀሙት ተአምራትም በደነቅ ግንባብ ላይ ዐይንን ማብራት ሕሙማን መፈወስ፣ ሙታንን ማንሣት ይፈጽም ነበር፡፡ ነገር ግን ያን ሁሉ አልተቀበሉት አላመኑትም ለምን ቢባል ይዘልፋቸው ስለነበር አስመሳዮች ናችሁ ውሸታሞች ናችሁ እያለ በአደባባይ ይናገራቸው ስለነበር በእርሱ ላይ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ተቋውሞና ጥላቻ ነበራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚያደርገውና የሚናገረው ነገር ሁሉ ከልባቸው ጠብ አይልም። ዛሬም ቢሆን ጥሩ ማስረጃ ያለው አሳማኝ የሆነ ሐሳብ ይዛችሁ አንድን ሰው ልታሳምኑት ካልቻላችሁ ችግሩ ያለው ከሐሳባችሁ ላይ ሳይሆን ሰውየው ሐሳቡን ለመቀበል ካለመፈለጉ ላይ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ሐሳባችሁ በቂ ማስረጃ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት ሊሆን ይችላል ይሁንና ሐሳባችሁ ከልቡ አይደርስም ከልቡ ስለማይደርስም ሳይቀበላችሁ ይቀራል፡፡

ሰው የሚያስብ ፍጡር ብቻ አይደለም። ያሰበው ሐሳብ ጉዳት የሚያመጣበት ከሆነ ወይም እንደዚያ መስሎ ከታየው ሐሳቡን እንደገና ያወጣል ያወርዳል። ስለዚህም አንድን ሐሳብ መቀበልና አለመቀበል ማስረጃ የማግኘትና ያለማግኘት ጥያቄ ብቻ አይደለም። ሐሳቡን ለመቀበል ፈቃደኛ የመሆንና ያለመሆን ጥያቄም ጭምር ነው። የፈረንሳዩ ሊቅ የፓስካል ንግግርም አእምሮ የሚያውቃቸው የራስ ምክንያቶች አሏዋት ሲል የተናገረው ቃል በዚህ መንፈስ የሚታይ ሐሳብ ነው። ክርስቶስ ሲያስተምረው የነበረው ትምህርትና ሲፈጽመው የነበረው ተአምራት በአይሁድ ዘንድ ተቀባይነት ያጣው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ካላሰብን ሌላ ምክንያት አይገኝለትም። አይሁድ ክርስቶስን በጣም ይጠሉት ስለነበር የእርሱን ወገኖች ይመለከቱዋቸው የነበሩት እርሱን በሚያዩበት ዓይን ነበር፡፡ ስለ ራሱ ስለ ክርስቶስና ስለ መንገድ ጠራጊው ስለ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የተናገሩትን አስደናቂና ተአምራት መጥቀስ ይበቃል፡፡

መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስን ለማውገዝ ያሰቡበት ምንም በቂ ምክንያት አልነበራቸውም ምክንያቱም ቅዱስ ዮሐንስ የሚመገበው  የበረሀ የጋጃሚርልብስ የማይለብስ ባሕታዊ እህል የማይበላ መናኛ (ማቴ. 3÷4) ገና ሳይወለድ ለአባቱ ለዘካርያስ መልአከ እግዚአብሔር የገለጠለት የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ የማይጠጣ መሆኑን ነው፡፡

ሌላው ሰው የሚበላውንና የሚጠጣውን ስላልበላና ስላልጠጣ አለመብላቱንና አለመጠጣቱን እንደ ኃጢአት ቆጥረውበት ጋኔን አለበት አሉት፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሚበላውን የሚጠጣውን ሲበላና ሲጠጣ ሲያዩት ደግሞ በላተኛና ጠጪ ነው ብለው አወገዙት እንግዲህ መመልከት ነው። አንደኛ መብላትም ሆነ አለመብላት፣ መጠጣትም ሆነ አለመጠጣት ኃጢአት አልነበረም። ኃጢአት ነው ቢባል እንኳ ከሁለቱ አንደኛቸው እንጂ ሁለቱም ጥፋተኞቹ ሊሆኑ እንደማይችሉ መፍረድ ይቻላል፡፡ ይሁንና የአይሁድ አለቆችና መምህራን በክርስቶስና በወገኖቹ ላይ ምንም ይሁን ምን ምክንያት ይፈልጉ ስለነበር መብላትንም ይሁን መጠጣትን እንዲሁም አለመብላትንም አለመጠጣትንም ሁለቱንም እኩል ኃጢአት አድርገው ተመልክተውታል፡፡ መጥምቁ  ቅዱስ ዮሐንስን ባለመብላቱና ባለመጠጣቱ ምክንያት ጋኔን አለበት ሲሉት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ ሲበላና ሲጠጣ ሲያዩት በዚሁ በመብላቱና በመጠጣቱ ምክንያት በላተኛና ጠጪ ነው አሉት፡፡ ከኃጢአተኞች ጋር ስላዩትም የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ነው አሉት፡፡ ከኃጢአተኞችና ከቀራጮች ጋር ባያዩት ኑሮም ነቀፋቸው አይቀርለትም ነበር፡፡ ከኃጢአተኞች ጋር የማይውለው እኮ፣ ተፀይፎአቸው ነው፣ ትዕቢተኛ ነው፡፡ ሰው ይለያል ያዳላል ይሉት ነበር እነሆ ክርስቶስ በዚህ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡

ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፡፡ እነርሱም ጋኔን አለበት አሉት፡፡ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፡፡ እነርሱም እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ነው ይሉት ነበር፡፡ ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች (ማቴ. 11÷18-19)

በጌታችን ኢየሱስ  በክርስቶስም ሆነ በመጥምቁ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ላይ የአይሁድ አለቆችና ጸሐፍት ፈረሳውያን ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበራቸው የተናገሩት ቃል በጣም የተምታታና ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ሊረዱት አልቻሉም። አለመብላትንና አለመጠጣትን እንደ ኃጢአት መቁጠር በአንፃሩም መብላትንና መጠጣትን እንደዚሁ በቁጥር መጃጃል መሆኑን ማንም ሰው ሊያስተውለው ይችላል፡፡ አይሁድ ብቻ አላስተዋሉትም ምክንያቱም ጥላቻቸው የማስተዋል ልባቸውን ሰይጣን አጨልሞት ነበርና ነው። አንድን የተወሰነ ድርጊት ኃጢአት ነው፣ ጸያፍ ነው ብሎ መልስ መመለስ የእሱንም ተቃራኒ እንደዚያው መንቀፍ አያስኬድም አይሁድ ግን አስኪዷቸው ተናግረውታል፡፡ ይህም በጣም አስገራሚ ነው በትክክል የሚያስቡና ለእውነት የቆሙ ቢሆኑ ኑሮ ከሁለቱ አንደኛውን ክርስቶስን ወይም ዮሐንስን ትክክለኛ ብለው መምረጥ ነበረባቸው መብላትን መጠጣትን ካወገዙ ላለመብላትና ላለመጠጣት ድጋፋቸውን መስጠት ነበረባቸው፡፡ ወኃም አለመብላትና አለመጠጣት ትክክለኛ ነው ካሉ ለመብላትና ለመጠጣት ትክክለኛነት መመስከር ነበረባቸው። ነገር ግን ማንኛቸውንም ላለመምረጥ ሲሉ በውስጡ አንዳች የሎጂክ (የእውነት) አካሄድ የሌለበትን ሐሳብ ገልጸዋል። እንግዲያውስ ከመብላትና ከመጠጣት ወይም ካለመብላትና ካለመጠጣት የወጣ ነገር አልነበረም። የአይሁድ አለቆችና መምህራን እንዲህ ዓይነቱን ለዛቢስ ሐሳብ ቢገልጹም እንዲያውም ለጊዜው ያላስተዋሉት አንድ ነገር አለ።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                           ክርስቶስን ስለበላና ስለጠጣ በላተኛና ጠጪ ነው ብለው ሲሰድቡት ራሳቸውንም ጭምር እንደሰደቡ አላስተዋሉም፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ራሳቸው ይበሉና ይጠጡ ነበርና ነው፡፡ አባባላቸው ወደ እነርሱ ወደ ራሳቸውም ሊዞር እንደሚችል ሐሳቡ አልመጣላቸውም፡፡

ይህንን የመሰለ የተምታታ ሐሳብ ከሌላም ቦታ በክርስቶስ ላይ የአይሁድ አለቆችንና መምህራን ተናግረውታል። በአንድ በኩል ክርስቶስ ተአምራት ሠርቶ እንዲያሳያቸው ይሹ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ሊያውቁ እንዲችሉ ተአምራት ሠርቶ ያሳየን ይሉ ነበር፡፡

በመሠረቱ በአይሁድ ኅብረተሰብ ዘንድ ተአምር መፈጸም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር እንደተላከ፣ የእግዚአብሔር ኃይል እንዳደረበት ሆኖ ይታመንበታል፡፡ አይሁድ ከእግዚአብሔር የተላከውን፣ የእግዚአብሔር ኃይል ያደረበትን ሰው የሚያውቁት አንደኛው ዋንኛው መንገድ የተአምር ሥራ መፈጸምን ነበር። ይህም እምነት ኒቆዲሞስ ከሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፣ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውና የምታጸናቸው እነዚህን ተአምራቶች ሊያደርግ የሚችል ማንም የለምና መምህር ሆይ ከእግዚአብሔር እንደመጣህ እናውቃለን አለው (ዮሐ. 3÷1-2) ቅዱስ ጳውሎስም ተአምራት ማሳየት በአይሁድ ኅብረተሰብ ዘንድ ታላቅ ቦታ እንዳለው እንዲያውም አይሁድ ከሌሎች ሕዝቦች ግሪኮችም ጭምር የሚለዩበት ነገር ቢኖር በተአምር ሥራ የሚያምኑና ተአምር ይፈጸምልን የሚሉ መሆናቸውን አስተምሮናል፡፡

መቼም አይሁድ ፍጹም ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ (ቆሮ. 1÷22) ሲል ተናግሯል፡፡ የአይሁድ አለቆችና መምህራን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመፈታተን ሲፈልጉ ተአምር ሠርቶ በእነርሱ ቋንቋ ምልክት እንደሚያሳያቸው ይጠይቁት ነበር፡፡ የጠየቁትን ሲፈጽምላቸው ዘግይተዋል እንዴው ባይሆንለት ነው፣ ቢችል ኑሮ ያደርገው ነበር ሲሉ ይሳለቁበት ነበር፡፡ ተአምር ሲፈጽም ሲያዩ ደግሞ ይህንማ የሚያደርገው በሰይጣንም ኃይል ነው ይሉት ነበር። ከዚህም ላይ የተምታታ እና የተዘበራረቀ ሐሳብ ይታይባቸው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተአምራት መፈጸም በእግዚአብሔር ኃይል በእግዚአብሔር ድጋፍ የሚፈጸም ነው ማለታቸውና በሌላ በኩል ደግሞ በሰይጣን ኃይል በሰይጣን ድጋፍ የሚፈጸም ነው ሲሉ ፍጹም ሊታረቁ የማይችሉ የተምታቱ ሐሳቦች መሆናቸውን ማንም ትንሽ ትምህርት የወሰደ ሰው እንኳ ሊያስተውለው ይችላል። ይህንም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመለከት፡፡

ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ዕውሩም ዱዳውም እስኪያይና እስከሚናገር ድረስ ፈወሰው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን አሉ ፈሪሳውያን ግን ሰምተው ይህ በብኤልዜቡል የአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ፡፡ (12÷22-25)

የልብ መጥመም ትልቅ እርግማን ነው። ልቡን ላጠመመ ሰው መድኃኒት የለውም፤ ስለዚህ ከዚህ ርግማን ይሰውረን አሜን፡፡

 

ከአባ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

       የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

አዲስ አበባ

 

 

ሰዎች የራሳቸውን ማንነት በማስመሰል ጉዞ መቀጠል የለባቸውም። የዚህ ዓይነቱ ጉዞ በደንብ ከተከታተልከውና ካስተዋልከው አንተን ለሁሉም ዓይነት ተሞክሮዎች የተጋለጥክ ያደርግሃል፡፡ በአጋጣሚዎች የተሞላ የአልታወቁ ሰዎችና ቦታዎች አዳዲስ ነገሮችና ፈተናዎች ሕይወትህን ሊፈትኑ የሚችሉ አዳዲስ እይታዎችን፣ አዳዲስ ሀሳቦችን፣ አዳዲስ የጠባይ መንገዶችን ጉዞው ቀስ በቀስ ያመጣብሃል፡፡

ስለዚህ ሰዎች ሆይ የራሳችሁን እውነተኛ ሕይወትና ጉዞ ታገኙ ዘንድ የእናንተን ቀና መንገድ የሚያዘጋጁ በእውነት ላይ የተመሠረቱ አስተሳሰቦች ሊኖራችሁ ይገባል፡፡

ራእያችሁና ጉዟችሁን ቀላል የሚያደርገው በእምነት ላይ የተመሠረቶ  እንቅስቃሴ ሲሆን ነው፡፡ እናንተ በእቅዳችሁ በየቀኑ በመደባችሁት የጊዜ ብዛት አይደለም፤ ጉዳዩን በእቅድ ይዛችሁ ለብዙ ጊዜ በቋሚነት የምታነቡት ረጅም ልብ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ በዐይን የቅኝት ምልከታ እንደ ሚነበብ የረጅም ታሪክ ክፍልም አይደለም፡፡ እየተጓዛችሁ ያላችሁት በእምነት የውስጣዊ ማንነትን በማግኘት ሃይማኖት ላይ ተመሥርታችሁ ነው። ሕይወታችሁን መምራት ያለባችሁ ስለዚህ እናንተ ዛሬ ነው ያላችሁ ለነገ የተስተካከለ ካለ ለማድርግ  ጉዟችሁን ተጠቀሙበት፡፡

“የተጠራቀመ  እምነትና የራስ ማንነት” የራስን ማንነት በማግኘት ጉዞ በጀመራችሁ ጊዜ፣ በመቀጠል ጉዞው ረጅም በመሆኑ በጸሎት ጀምሩት እግዚአብሔር አምላክ የልቡናችሁን መሻት እንዲ ፈጽምላ ችሁ፡፡ የሱ ፈቃድ ነውና  ከዚህ በኋላ በድል የተሞላ፣ በእውቀት የጐላ ጉዞ ይሆንላችኋል፡፡

ለሕይወት መሰናክል የሆኑ ድርጊቶች በኑሮ እንኳን በመንገዳችሁ ፈጽሞ አያጋጥሟችሁም፡፡ ይህም የሚሆነው ሀሳባችሁንና ራስን ዝቅ በማድረግ ከሆነና መልካም ስሜት ሰውነታችሁንና መንፈሳችሁን ሊሰማችሁ ይችላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን በእቅዳችሁ ያልተሸከማችኋቸውን ከሆነ በበሰለ ሁኔታ በእምነት ማየትን ይጠይቃል፡፡ በመቀጠልም የሕይወት ጉዞው ረጅም በመሆኑ አሁንም ጸልዩ፡፡ የክረምቱ እና የበጋው ጊዜ ሲመላለስ በጣም ረጅም ነው፡፡ ይህም እናንተ ወደ ጣፋጭ ፍሬ የምትገቡበት፣ የምታገኙበት ወቅት ስለ ሆነ። እነዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ የትዕግስታችሁና የጽናታችሁ ምክንያት የሚታዩበት ነው፡፡ ሁልጊዜም የተጠራቀመ የራሳችሁን ታሪክ፣ እምነት ማንነት በማይለዋወጥ የጠባይ ሁኔታ ጠብቁት፡፡  በሕወታችን ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ  ነው፡፡ ነገር ግን ወቅቱ አሁን ነው ብላችሁ አትቸኩሉ ይህ ለረጅም ዓመታት በእቅድ የተያዘ እምነትንም የሚጠይቅ መልካም ጉዳይ ነው፣ ይህንን በብቸኝነት እንደ እሴት ከትውልድ ጋር ማያያዝ ይገባል። ይህ መልካም ነውና፡፡ በመንገዳችሁ ባገኛችሁት በሁሉም ድረሱበት ይህም ሲባል የተጠራቀመ የራስ ማንነታችሁ ግድ የለም ይደርስበታል ብላችሁ አለመጠበቅ ነው ጊዜውን ዋጁት፡፡

የተጠራቀመ የራስ ማንነታችሁ ጥሩ የሆነ የሕይወት ጉዞ አላት፡፡ ያለሷ ጉዞውን በፍፁጹም አታገኙትም ጥበብ ናትና፡፡ የተጠራቀመ የራስ ማንነት የጥፋተኝነትና የወንጀለኝነት ስሜት እንዲሰማችሁ አታደርግም፡፡ አሁንም ከእግዚአብሔር ባገኛችሁት ታላቅ ጥበብ በብዙ ተሞክሮ በእርግጠኝነት እንደተረዳችሁት የተጠራቀመ ማንነታችሁ ማለት ማንኛውም ፈተና በትእግሥት ማሸነፍ ስትችሉ ይህች ናት፡፡ “ጸልዩ ጉዞው ረጅም ነውና” የናንተን ዕድል ፋንታ መዳረሻ ለመድረስና መቸኮል ምንም ምክንያት የለም፡፡ ችኮላ ታደናቅፋለችና በዝግታ ጀምሩ፤ ስለዚህ በመንገዳችሁ ላይ በምታገኙት ገጠመኞች ትደሰቱ ይሆናል፡፡ የእናንተን የስብዕና ረገድ በማጥናት እንዲህም ሲባል ሂደቶችን፣ ልምዶችን፣ ደስተኛ ያለመሆን ምንጮችን፣ ረባሽ የሆኑ ሁኔታዎችን ጀብዱ በዕውቀትና በትሕትና የተሞላ እንዲሁም የጥንካሬ እና የጥበብ ግኝትም ጭምር ነው፡፡ ይህም ሲባል ‘Lestrigonians’ or cannibals እነዚህም የናንተን ጉዞ የሚፈትኗችሁ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ሕይወትን የሚያበላሹና የሚያሰናክሉ ክፉ ጥርጥርና ዕድሌ ይህ ብቻ ነው ብሎ አስቀድሞ ለመወሰን ወደ መጥፎ መንገድ የሚገፈትሩ ናቸው፡፡

የእናንተን ሕይወት እና ኑሮ ለሃይማኖት ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግም ድርሻ አለው፡፡ ሁሌም የተጠራቀመ የራስ ማንነታችሁን በህሊናችሁ ያለምንም መለዋወጥ ጠንካራ ነኝ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ማለት ይገባል፡፡ ይህ የራስን በእምነት፣ ባሕል ወግ ለነፍሳችና ለሥጋችን የደኅንነት መንገድ ነው፡፡ ይህም የእናንተ የመጨረሻ ግባችሁ ነው፡፡ አትፍሩ እየተቀያየሩና እየተደጋገሙ የሚመጡ ሀሳቦችንና አስፈሪ ስሜቶችን ፈጽማችሁ አሜን ብላችሁ አትቀበሏቸው፡፡ እነዚህንና መሰል ክስተቶችን፤ ገዳይ ወይም አሳማኝ ሀሳቦችን ወይንም በጭንቀት ጣራ መድረስን ስለዚህ ይህ አላስፈላጊ ነው፡፡ ለሕይወታችሁ መምረጥ ያለባችሁ በራስ የመተማመን ስሜትንና በሌሎች ሀሳብ አለመደናገርን፣ ጥሩ ሰውነት ስሜት እና መንፈስ እንዲሰማችሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ውስጣዊ የራስ ማንነታችሁን የሚያበለፅጉትን ሀሳቦች አስቡ፤ እናም በበለፀገ ሀሳብ እንዲስፋፉ ፍቀዱላቸው፡፡ ያለምንም ፈተና እንድትሆኑ ከፈለጋችሁ፣ አእምሯችሁን ጉዳት በሌላቸው ቅንና እውነትንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ እቅዶችና፣ራእዮችን  ሀሳቦች ሙሉት፡፡ እነዚህም አሳቦች ስቃይ የለሽና የታቀዱ የእግዚአብሔርም ፈቃድ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ዓለምን በራስ መተማመን ተመልከቷት፡፡ ሕይወትን ፊት ለፊታችሁ ተመልከቷት እንጂ በመታከትና በጉዳት መንፈስ አይሁን፡፡ የግድ በማዕበሉ ውስጥ በትክክል በሁለት እግራችሁ መቆም አለባችሁ፡፡

እናንተ በእናንተ የሚሆነውን ነገር የሚደረገውን ሁሉ ፈጽማችሁ አትፍቀዱ፡፡ ወደ ረዳት አልባ ማርሽ ለመግባት ወይም በዘፈቀደ የሚመጣ ጭንቀትን አእምሯችሁን ህሊናችሁን ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጡ፡፡ ስለዚህ ስለ የውስጥ ሰላምን የሚያመጡላችሁን ስሜቶች በተጠራቀመ የራስ ማንነታችሁ በእምነታችሁ ሰላም ሊሰማችሁ የግድ ነው፡፡ ነገር ግን ባመዛኙ የሕይወት ጉዞውን እንዲያድግ አድርጉ፣ ሞክሩ፣ ነገር ግን ጉዞው ዛሬ ነው ብላችሁ ፈጽማችሁ አትቸኩሉ፤ በዝግታ ፍጠኑ እንጂ፡፡ በመኖር ውስጥ የመጨረሻ ጠቃሚ ግብና ለውጥ በሰላም መኖር ነው፡፡ በየጊዜው ክስተቱ ዕውቅናንና ዕድልን በእውነተኛ ደስታ በማፈራረቅ ነው፡፡ ሀብታም መሆን ይቻላል ግን ሀብቱ የሚገኝበትን መንገድ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ሀብታም መሆንና ታዋቂ ሰው መሆን ይቻላል፡፡ የቅድስና ዕውቀትም ለሰው ተሰጥቶታልና፡፡ እንደ ፍላጎታችን ለመሆን ያለንን ጉጉት በመተው ራስን ለእግዚብሔር ማስገዛት ነፃና የተረጋጋን ሰዎች እንሆናለን፡፡ በቀላል መመዘኛዎች ከኖርን ጉዞውን አስደሳችና ረጅም እናደርገዋለን፡፡ ማንም ቢሆን የገጠመኙን ጥቅም በየጊዜው እያንዳንዷ ቀን ውስጥ እና ለእያንዳንዷ ቅፅበት በደስታ መኖርን እያንዳንዱ በእምነት ማግኘት ይችላል፡፡ ሕይወትን ለማስደሰት ቦታው መንፈሳዊነት ብቻ ነው፡፡ ጊዜውም አሁን ነው፡፡ ደስተኛ እና ታማኝ በመሆን አብረዋችሁ የሚጓዙትንም የሰው ዘር ሁሉ በእምነት ጽናት ደስተኛ አድርጓቸው፡፡

እናም ከአባቶች በወረሳችሁትና በራሳችሁ የተጠራቀመች ማንነት ስትደርሱባት ያገኛችሁትን ታላቅ ጥበብ አስቡ፡፡ የተጠራቀመች የራስ ማንነታችሁ ከሁሉም በላይ የሆነውን ጉዞ ሰጥታችኋለች ተቀበሏት፡፡ የተጠራቀመች የራስ ማንነት ነው፡፡ ከተለያየ ፈተና የዳንክበት ትልቁ ሃይማኖት ነው፡፡ የራስም ማንነት ነው፡፡ እውነተኛ የራስ መገለጫ ነው፡፡ የተጠራቀመ ሰብዕና ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የራሳችሁ መገለጫ ሲለካ ሁልጊዜም እንደገና የምታገኙት ሚሥጢር ነው፡፡ የማያልቅ ዘለዓለማዊ ነው፡፡

በሰዎች የሃይማኖትና የዓላማ ፅናት ሲሆን ይህም የሰው ልጆች የሚኖራቸው የራሳቸው የመዳን አቅም ኃይል በሳይኰሎጂና በአካል ደረጃም ጭምር ለሁሉም የተሰጠው በመሆኑ ነው፡፡ ባለሙያ ማለት የሚሠራው ይህንን የማዳን ኃይል በሕክምና ወይም በሳይኰቴራፒ የማገገም ሥራን ወደ ሰዎች አእምሮ ማምጣት ነው፡፡ ነገር ግን ጤና በተፈጥሮ ደረጃ የሚገኝ አካል ነው፡፡ ሰው በራሱ የራሱን ማስመለስ ይችላል፡፡ However, health is the natural state of being a person can restore himself or herself ‘by reframing’ አዲሱ የራስ ገፅታ ሌላ አይደለም፣ ማንነትህን ማወቅ በእቅድ መመራት እንጂ ሌላ ምስጢር አይደለም፡፡ ነገር ግን ሥራን ወይም ተግባርንና በትክክለኛ አረዳድ ተረድቶ ራስን በአግባቡ መምራት ነው፡፡ ይህም የግለሰቦች፤ የቤተሰብ፣ የሀገርም ጭምር ነው፡፡ ሀሳቡ የተለየዩ ዘዴዎች ውጤት ነው፡፡ የተለያዩ የተዘበራረቁ እና በጣም በሰዎች ያልተሰካኩ ስብዕናዎችን ለማየት የሚረዳ ነው፡፡

ማንም ሁኑ፣ ምንም ሁኑ፣ የትም ኑሩ፣ ምንም ሥሩ ነገር ግን የምትኖሩ፣ የምታስቡ የራሳችሁ ፀባይ ያላችሁ ሁሉ፣ የራሳችሁ እምነትና ገፅታ ወይም መገለጫ ተፅዕኖ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራችኋል፡፡ የራስ ገፅታችሁ መልካም ከሆነ ይህ ለእናንተ መልካም ነው፡፡

እንደ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፡፡ ነገር ግን በሃይማኖትና በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ሮሜ 8÷13፡፡

መንፈስ ማለት መንፈሳዊ ሥነ ምግባር ነው፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ምጽዋት፣ ቸርነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ንጽሕና ነው፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኃጢአት ለዩ አሁንም በመንፈስ እንኑር በመንፈስም እንመላለሰ ገላ 5፥22። ኤፌ. 4፥30

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ

ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

 

                                       በርታ ሰውም  ሁን!!

ነቢየ እግዚአብሔር ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የሚሞትበት ቀን በቀረበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፡- በርታ ሰውም ሁን የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ በሙሴ ሕግ እንደተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴም ትሄድ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን አይቋረጥም ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው፡፡

1ኛ ነገሥት 2÷1-4 በነቢዩ ቃል መሠረትነት ላይ ተመርኩዘን ዓለም በተለያዩ ባሕርየት ባላቸው ሰዎች የተሞላች ናትና በመልካም ሥነ ምግባር አስተምሮ ዙሪያ ያለንን ግንዛቤ እንገልጻለን፡፡

በዓለም ላይ አንድ አይነት ባሕሪ ያሏቸው ሰዎች አሉ ለማለት በእጅጉ ያስቸግራል፡፡ ሰዎች በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው የሚሠሩ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብረውን የሚያገለግሉና የሚገለገሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁበት የራሳቸው የሆነ የተለየ ክፉ ጠባይ አላቸው፡፡ ይኸውም ከቁጥጥር ያለፈ ቁጣ፣ ጎጂ የሆነ ምላስ፣ በቀላሉ የመከፋት እና የማዘን ጠባይ የሚታይባቸው፣ አሁን ስቀው እና ተጫውተው እንደሆነ ከልቡናቸው በሚፈልቀው ክፋት ምክንያት ወዲያው የሚያኮርፉ፣ ዛሬ ያመሰገኑትንና ያደነቁትን ሰው በቅጽበት የሚነቅፉና የሚተቹ፣ አሁን በጣም የወደዱትን ትንሽ ቆይተው በእጅጉ የሚጠሉ፣ ስለ ራሳቸው እንጂ ስለ ሌላው ሰው ፍላጎት እና ፈቃድ ፍጹም ግድ የሌላቸው፣ ተጠራጣሪዎች፣ ስጉዎች፣ በየጥቃቅኑ ምክንያት የሚነጫነጩ፣ ስግብግቦች፣ በዚህች ምድር እኛ ብቻ እንኑር የሚሉ ሆዳሞች፣ የሌላው ሰው ጉዳይ የማይሰማቸው እና የማይቆረቁራቸው፣ የተማሩ የሚመስሉ ነገር ግን አንዳች የማያውቁ፣ በተተኪ ትውልድ ላይ ሬት የሚዘሩ ወዘተ ናቸው፡፡

አስቸጋሪ ከሆነባችሁ ሰው ጋር ያላችሁን ግንኙነት ሰላማዊ ለማድረግ፣ በየጊዜው በመካከላችሁ የሚፈጠሩትን ግጭቶች በተለያየ መንገድ ለመፍታት የተቻላችሁን ሁሉ ሞክራችሁ አቅቷችሁ ይሆን? የራሳችሁን ፍላጎት ትታችሁ አስቸጋሪው ወይም ነገረኛው ሰው የጠየቀውን ሁሉ “እሺ!” በማለት ሰላም ለመፍጠር ሳትሞክሩ እንዳልቀራችሁ እንገምታለን፤ “እሺ! አንተ እንዳልክ” በማለት የራሳችሁን ፈቃድ መሥዋዕት ብታደርጉም በመካከላችሁ ያለውን ግጭት ማቃለል እንዳልቻላችሁ ስትረዱ፤ “ሰላም ማምጣት የሚቻለው በደካማነት ሳይሆን በብርቱነት ነው” ብላችሁ በማመን ኮስተር ብላችሁ ጽኑ የሆነ አቋም ለመያዝ ሞክራችሁም፣ የምትፈልጉትን ዓይነት ውጤት ስላላስገኘላችሁ፣ አሁንም አልቻልኩም! አቃተኝ! ብላችሁ ተስፋ ቆርጣችሁ ይሆን? ሁኔታው የበለጠ እየከፋ ሲመጣባችሁ፣ ያ አስቸጋሪ የሆነባችሁ ሰው፣ የእናንተን ሕይወት መራራ በማድረግ እናንተን ለመቅጣት ታስቦ የተፈጠረ፣ እናንተ ደግሞ የእርሱን ሕይወት ለማመቻቸት ብቻ እግዚአብሔር “የመሥዋዕት በግ” አድርጎ የፈጠራችሁ መስሎ ተሰምቷችሁ ያውቅ ይሆን? በቀመሳችሁትስ መራራ ሕይወት ምክንያት ከላይ የጠቀስነውን ዓይነት ስሜት ቢሰማችሁ፣ ከአስቸጋሪው ሰው በስተቀር የሚፈርድባችሁ ሌላ አካል ይኖራል ብላችሁ አትገምቱ ይሆናል፡፡ “አእምሮው ከጡንቻ የተሳለ” እንደተባለ፡፡

አስቸጋሪ ሰዎች እንዴት ዓይነት ናቸው? ተለይተው የሚታወቁበትስ ምልክታቸው ምንድነው? አስቸጋሪ ሰዎች ተለዋዋጭ ባሕሪ ስላላቸው ምን እንደሚወዱ እና ምን እንደሚጠሉ፣ ምን እንደሚያስደስታቸውና እንደማያስደስታቸው ለይቶ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ አስቸጋሪ ሰዎች እውነተኛ ማንነታቸው እንዳይታወቅባቸው በቀልጣፋ ንግግራቸው ራሳቸውን የመደበቅ ልዩ ችሎታ ያላቸው በመሆናቸው ቀረብ ብለው ካላዩአቸው በስተቀር ሰላማዊ ሰው በመምሰል ብዙዎች “አስቸጋሪ” የምንላቸው ሰዎች በባሕሪያቸው እንዲሁም የአስቸጋሪነታቸው መጠን የተለያየ ይሁን እንጂ ሁሉም የሚመሳሰሉበት አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም ከእነርሱ ጋር ተቀራርቦ መኖር፣ አብሮ መሥራትም ሆነ ቤተ ክርስቲያን አብሮ ማገልገል በጣም ከባድ መሆኑ ነው፡፡ አስቸጋሪ ሰዎች ምን ዓይነት አስተሳሰብ እና ጠባይ እንዳላቸው መሠረት ላይ ተመርኩዘን ተጨማሪዎችን ለማሳየት የሚከተሉትን ዘጠኝ ጠባዮች ከዚህ በታች እንመለከታለን፡፡ በማር. 7÷22

ተጠራጣሪነት

ሀ. አስቸጋሪ

አስቸጋሪ ሰዎችን አስቸጋሪ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ በብዙ ነገር ተጠራጣሪ መሆናቸው ነው፡፡ በሃይማኖት፣ በሥልጣን፣ በሥራ፣ በማንኛውም መልካም ግንኙነት ይጠራጠራሉ፡፡ ያዕ. 3÷17

ለ. ቁጡነት

ቁጡነት ብዙዎቻችን ቁጣ በአግባቡ ወይም በሥርዓቱ ሲገለጽ ነው የምናውቀው ነገር ግን እያየንና እየሰማን ያለው ቁጣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲፈታ አላየንም፡፡ ታዲያ “በምንም ምክንያት እንዳትቆጡ” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል መተላለፍ አይሆንምን? 2ኛ ጢሞ. 4÷2-3

ሐ. ነቃፊነት

መንቀፍ ልማዳቸው የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ከሰው ሁሉ የበላይ አድርገው ሌላውን የበታች በማድረግ በየአደባባዩ በነቃፊ ቃል ንግግራቸውን ይከፍታሉ፡፡ እብሬት በተሞላበት ንግግራቸው አያውቁም እንዳይባሉ በማንኛውም ነገር ራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ የሚያሳዩትና የሚያቀርቡት ሁሉን እንደሚያውቁ አድርገው ነው፡፡ መጽ. ምሳሌ 20÷19

መ. ስለ ሌላ ሰው ስሜት ግድ የለሽነት

አስቸጋሪ ሰዎች የሌላውን ሰው ስሜት ምን ያህል እንደሚጎዱ እያወቁ በግድ የለሽነት የመጣላቸውን ቃል ከአፋቸው አውጥተው ይወረውራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቤት ራስ ያለው እኮ ግድ የለሹን ሳይሆን ለዚች ቤት የሚያስበውን ነው፡፡ ዘሌ. 19÷17፣ ማቴ. 18÷19፣ ፊልጵስ. 3÷4

ሠ. አኩራፊነት

ፊት ለፊት እንዲህ ዓይነት ቃላት ተናግረኸ ለምን ትጐዳኛለኸ በማለት ፈንታ ማኩረፍ የሚቀናቸው ሰዎች አሉ፡፡ ባኮረፈኝ ቁጥር ሁል ጊዜ እርሱን መለማመጡ አሁንስ ሰለቸኝ የምንል ስንቶች እንሆን? በዚሁ ምክንያት እናንተ በጸሎታችሁ ደግፉን የምንል ብዙዎች ነን፡፡ 2ኛ ቆሮ.1÷11
ረ. ለእኔ ብቻ ይደረግልኝ ባይነት
  ፊት ለፊት እንዲህ ዓይነት ቃላት ተናግረኸ ለምን ትጐዳኛለኸ በማለት ፈንታ ማኩረፍ የሚቀናቸው ሰዎች አሉ፡፡ ባኮረፈኝ ቁጥር ሁል ጊዜ እርሱን መለማመጡ አሁንስ ሰለቸኝ የምንል ስንቶች እንሆን? በዚሁ ምክንያት እናንተ በጸሎታችሁ ደግፉን የምንል ብዙዎች ነን፡፡ 2ኛ ቆሮ.1÷11

ስለ ሌላው ሰው ግድ የሌላቸው ለራሳቸው ብቻ የሚያስቡ የዚህ ዓይነቱ ፀባያቸው ምክንያቱ ምን ይሆን? “ ምክንያቱማ ፈረሱ የታሰረበት ቦታ መጋጥ ብቻ ነው፡፡” እንደተባለ፡፡ ማቴ. 23÷25

ሰ. ተለዋዋጭነት

ተለዋዋጭ የሆነ ጠባይ ያላቸው አሁን ጥሩ ሰው መስለው እንደሆነ ጥቂት ቆይተው መጥፎ ይሆናሉ፡፡ ለአንድ ሳምንት ያህል ሰላማዊ ሰው መስለው እንደሆነ ድንገት ባልታወቀ ምክንያት ፍጹም ተለውጠው ሌላ ሰው ይሆናሉ፡፡

ሸ. አምባገነናዊነት

ሁልጊዜ ሌላውን በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ስለሚፈልጉ ከሰዎች ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት መፍጠር አይችሉም፡፡ ሁሉን በእጃቸው ጭብጥ በእግራቸው እርግጥ አድርገው መያዝ ስለሚፈልጉ የሌላውን ሐሳብ ምንም ያህል ጥሩና ትክክል ቢሆንም መቀበል አይፈልጉም፡፡ እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውን እንጂ ራሳችሁን የሚጠቅመውን አትመልከቱ፡፡ ሮሜ 12÷3

ቀ. ተበቃይነት

በተበቃይነት አስቸጋሪ የሆኑ ሰዎች በፀባያቸው ማንኛውም በጐ ነገር ጥሩ ሆኖ አይታያቸውም፡፡ ሌላውን ሰው ደስ የሚያሰኝ ነገር እነርሱን ደስ አያሰኛቸውም፡፡ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ከመበቀል ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በእነርሱ ዘንድ ፈሪሃ እግዚአብሔር እና ሃይማኖት ቦታ የለውም፡፡ ሮሜ 12÷19

ከእንዲህ ዓይነቱ እጅግ አስቸጋሪ ሰው ጋር የሚኖር ወይም የሚሠራ ማንኛውም ሰው በቅድሚያ ማወቅ ያለበት፣ ከላይ የገለጽናቸውንና ሌሎችንም የአስቸጋሪነት ጠባይና እንዲሁም ከአስቸጋሪው ሰው ጋር አብሮ ሲኖር ሁልጊዜ ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑን ነው፡፡ ይኸውም አስቸጋሪ ሰዎችን ለመምከር ወይም የአስቸጋሪ ሰዎችን ጠባይ ለመለወጥ ሳይሆን አስቸጋሪ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁበትን ምልክቶች ለመጠቆምና እንዲሁም አብሮአቸው የሚኖረው ሰው፣ በአስቸጋሪ ሰዎች ጠባይና ድርጊት እንዳይጎዳ ራሱን መጠበቅ የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶችን ለመጠቆም ነው፡፡ አስቸጋሪ የሆኑ ሰዎችንና ጎጂነት ያለውን ጠባያቸውን ለይተን እንድናውቅና እንዲሁም አብረን እንዴት መኖርና መሥራት እንደምንችል ጠቃሚ የሆነ ምክር ያስፈልገናል፡፡ ያለአግባብም ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ በተረጋጋ መንፈስ መምራት እንድንችል፣ ዓላማችንን እንዳንሥት፣ እግዚአብሔር የሰጠንን የመምረጥና የመወሰን ነጻነቱን እንዳንለቅ፣ እንዲሁም በአስቸጋሪ ሰዎች እንዳንጎዳ አስፈላጊውን ድንበር ማበጀት እና ድንበሩን እንዴት ማስጠበቅ እንደምንችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ይህን ካደረግን ድንበር ምን እንደሆነ፣ እንዲሁም ድንበር የሌለው ሕይወት ምን ያህል ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ሰው ከሰው ሁሉ ጋር ሁልጊዜ በሰላም አብሮ መኖር የሚችል ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከልምዳችን እንደተረዳነው ከሰው ሁሉ ጋር ሁልጊዜ በሰላም መኖር አይቻልም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የሚቻላችሁ ቢሆን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የሚያስፈልገውን ሁሉ አድርጉ” ሮሜ. 12÷18 ብሎ ባልጻፈም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለብቻችን እንድንኖር ስላልፈጠረን፣ ከሰው ሁሉ ጋር ያለን ግንኙነት አስቸጋሪ ሲሆነብን፣ ከሰው ሁሉ ሸሽተን ለብቻችን ለመኖር ከማሰብ ይልቅ ተቻችለን መኖር የምንችልበትን መንገድ መፈለግ አለብን፡፡ ከምንጊዜውም የበለጠ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እርስ በእርስ ወዳጆች የነበሩ ጠላቶች ለምን ይሆናሉ? በሥልጣን፣ በገንዘብ ወዘተ ምክንያት ሰው የሰው ጠላት ለምን ይሆናል? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ ችግሩን ብቻ ማውራት የማይጠቅም መሆኑን ነው የተረዳነው ነገር ግን መፍትሔው ምን ይሆን? ከሁሉም በላይ ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነትና እንደዚሁም እውነተኛ የማኅበረሰብ እኩልነት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ገላ. 5÷22 ሆኖም ሰላም፣ ሁለት ተቃራኒ ወገኖች የሚያገኙት ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ሰላም በየትኛውም አቅጣጫ የሕይወት ሁለንተናዊ ፍጹምነትን የሚያመለክት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን እና የሀገርን ዕድገት ብልጽግና፣ ትምህርትና ጤናን፣ እንዲሁም ሕይወት በጠባይዓዊ ሞት ኅልፈት እስኪፈጸም ድረስ ያለውን ረዥም ሕይወት ይገልጣል፡፡ ግላዊና ማኅበራዊ ደኅንነትን ፀጥታና መረጋጋትንም ያሳያል፡፡ ዮሐ. 20÷19፡፡ ሰላም በምድር ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ እጅግ የከበሩና የተወደዱ ከሁሉም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ሁሉ በላይ ነው፡፡ ሮሜ 13÷10 ቅዱስ ጳውሎስ “ያለ ሰላም እግዚአብሔርን ማየት የሚችል የለም” እንዳለ ዕብ. 12÷14 ሰው ያለ ሰላም ማየት የማይችለው እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን ባልንጀራውንም ጭምር ማየት አይችልም፡፡ ሰላም የሌላቸው ወገኖች ሊተያዩ እና ሊነጋገሩ አይችሉም፡፡ መልካም ሥራ የሚገለጸው ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም እና የእግዚአብሔርን ሥራ በመሥራት ነው፡፡ ማቴ. 5÷16፣ ዮሐ. 4÷34፡፡ ሰው ያለእምነት እግዚአብሔርን ሊያስደስት አይችልም ዕብ.11÷6፡፡ ይልቁንም ሰው በክርስቶስ ሲያምን የተለወጠ ልብ ስለሚኖረው መልካም ሥራ ይሠራል፡፡ በዚህም በጐ ሥራው ይመሰገናል ዋጋውንም በመንግሥተ ሰማያት ይቀበላል፡፡ ማቴ. 25÷21፣ 2ኛ ቆሮ. 5÷10፡፡

“ዓለም በሦስት ነገሮች ማለትም በፍትሕ፣ በእውነትና በሰላም ትጸናለች” እንዲሉ ቤት ያለ ምሰሶ ሰላምም ያለ ፍትሕ አይጸናም፡፡ በኅብረተሰብ ውስጥ ፍትሕ ካለ አንዱ የሌላውን ሀብት አይመለከትም፡፡ የራሱን ትቶ በሌላው እጅ ያለውን በቅንዐት አያይም ደግሞም ፍትሕ እና ሰላም በሰፈነበት ኅብረተሰብ ውስጥ አስቸጋሪ ሰዎች ብዙም አይኖሩም፡፡ ቢኖሩም እንኳ በሚፈጥሯቸው እኩይ ተግባራት በእጅጉ ስለሚታወቁ የሌላውን ሰላምና መልካም ሥራ ሲያናጉ ይለያሉ ሁሉም ከተገነዘባቸው ደግሞ ብዙም ሕይወት አይኖራቸውም፤ ክፉ ሥራቸውንም ሥር ሳይሰድ መቁረጥ መለየት ይቻላል፡፡

 

አባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ

ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ