Archives

All posts for the month November, 2017

“ወኲሉ መጽሐፍ ዘበመንፈሰ እግዚአብሔር ተጽሕፈ ይበቊዕ ለኲሉ ትምህርት ወተግሣጽ ወአርትዖ ወጥበብ ወጽድቅ ከመ ይትገሠጽ ብእሴ እግዚአብሔር ውስተ ኲሉ ምግባረ ሠናይ”

የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም እና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርት ለተግሣጽ ልብን ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ.ጢሞ 3፥16-17 በማለት በታዘዝነው መሠረት የኅዳር ሚካኤልን የምናከብርበትን ምክንያት ከዚህ ቀጥለን እናቀርባለን። 

ዘምስለ ዮሴፍ ተሰይጠ ከመ ይስፍር ሲሣዮ ለሕዝብ፡፡

ለሕዝበ እስራኤል ምግባቸውን ያዘጋጅ ዘንድ ከዮሴፍ ጋር ተሸጠ

( አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ሰዓታት)

የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን ለእስማኤላውያን  ሽጠውት ሳለ  እስማኤላውያን ለጲጥፋራ ሸጡት፡፡ ከጲጥፋራ ቤት ገብቶ ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን የጲጥፋራ ሚስት ሩካቤ ሥጋ እናድርግ አለችው፡፡ እሱም ጌታየ በሁሉ ቢያሰለጥነኝ በዚህ በአንች ላይ አላሰለጠነኝም አይሆንም አላት፡፡ እሷም አውቃ ልብሷን ከፊቷ ቀዳ አውልቃ ሰው ባርያ ሲገዛ መልከ ክፉውን ፀጉረ ከርዳዳውን ይገዛል እንጂ መልከ መልካሙን ገዝቶ ልድፈርሽ አለኝ አለች፡፡ አሕዛብም ዮሴፍን ወህኒ ቤት አገቡት፡፡ ዮሴፍም ከወህኒ ቤት ገብቶ ሳለ የፈርዖን ጠጅ አሳላፊውና እንጀራ አሳላፊው ተጣልተው ወህኒ ቤት ገብተው ሲኖሩ ከዕለታት አንድ ቀን እየራሳቸው ሕልም አይተው ነበርና ሕልማቸውን ለዮሴፍ ነግረውት ዮሴፍም እንደሕልማቸው ፈታላቸው፡፡ የጠጅ አሳላፊውን እንደነበርክ ትሆናለህ አለው፡፡ የእንጀራ አሳለፊው ዮሴፍ እንደነገረው ተሰቀለ፡፡ ዮሴፍም የጠጅ አሳላፊውን እንዳትረሳኝ አለው፡፡ከዕለታት አንድ ቀን ፈርዖን ሕልም ያያል፡፡ ሕልሙም ትርጓሜውም ይጠፋዋል፡፡ ሕልሙም እንዲህ ነው፡፡

ከወንዝ ውኃ ሲጠጡ ሰባት የከሱ ላሞች ሰባቱን ያልከሱትን የወፈሩትን  ላሞች ሲውጧቸው አየ፡፡ ሕልሙንም የሚፈታለት አላገኘም፡፡ የጠጅ አሳላፊውም የሴፍ ያነን አትርሳኝ ያለው ነውና ዮሴፍም የሚባል ሕልም የሚፈታ አለ ብሎ  ለንጉሡ ነገረው፡፡ ፈርዖንም ዮሴፍን ከወህኒ ቤት አስመጣው፡፡ ሕልሙንም  ሰባት ዓመት ረኃብ ችግር ይሆናል አለው፡፡ ታዲያ ምን ላድርግ አለው፡፡ ለሰባት ዓመት የሚበቃ እህል አሰብስብ አለው፡፡ ያን ጊዜ ዮሴፍን ሾመው፡፡ ዮሴፍም ለሕዝቡ የሚበቃ እህል ሰበሰበ፡፡

በእየሀገሩ ረኃብ ጸና፡፡ ረኃብ ኮነ በበብሔሩ ወፈድፋደሰ በከነዓን ጸና ይላል፡፡ እህልም በከነዓን ጠፋ፡፡ የእየሩሳሌም ሰዎች እስራኤል ከግብጽ ሰዎች ውስጥ ዮሴፍ የሚባል የሰበሰበውን እህል ያቀና ነበርና  ሸምቶ ለመብላት ወደግብጽ ተሰደዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ዮሴፍን የሾመው ሞቶ ሌላ ፈርዖን የሚባል ክፉ ንጉሥ ነገሠ፡፡ የእስራኤልን ብልሀትና ብዛት አይቶ ከእስራኤል ወገን ወንድ ልጅ ሲወለድ በሰይፍ ይቆረጥ ብሎ አዋጅ ነገረ፡፡ ሙሴ በዚያን ጊዜ ሲወለድ ከግንባሩ ላያ ብርሃን ተስሎበት፤ ተጽፎበት ተወለደ፡፡ እኅቱና እናቱ ፈርዖንን በመፍራት ከወንዝ ዳር በሳጥን ውስጥ አርገው ጥለውት እኅቱ ማርያም በጎዳና ሆና ትጠባበቀውና ታየው ነበር፡፡ አንዲት ሴት ልብስ ልታጥብ ወደ ወንዝ ስትሄድ ሳጥን አግኝታ ብትከፍተው ሙሴን አገኘችው፡፡ የንጉሡ ልጅ ሰውነቷን ልትታጠብ ሂዳ አገኘችውም ይላሉ፡፡ እኅቱ ማርያምም አውቃ ከእስራኤል ወገን ልጅ የሞተባት አንዲት ሴት አለችና ታሳድገው አለቻት፡፡ አምጫት አለቻት፡፡ ለእንበረም ሚስት ለዮካብድ ሰጠቻት፡፡ ዮካብድም ከቤት ወስዳ ሙሴን ሦስት ዓመት አሳደገችው፡፡ ከዚህ በኋላ ሙሴ ከፈርዖን ቤት አደገ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ፈርዖን በእስራኤል ላይ ፍርድ ሲያጣምም አየው፡ ከአየው በኋላ ሙሴ ፈርዖንን በጥፊ መታው፡፡ ፈርዖንም ተናዶ ሊገድለው ሲል መካሮቹ/አማካሪዎቹ ንጉሥ ሆይ ሕፃን ምን ያውቃል እሳትና ፍትፍት ቢያቀርቡለት ፍትፍቱን ትቶ እሳቱን ይጎርሳል አሉት፡፡ እስኪ አቅርቡለት አላቸው፡፡ ቢያአቀርቡለት ሙሴ ወደ ፍትፍቱ እጁን ሊሰድ ሲል መልአኩ  በረቂቅ ነገር ወደ እሳቱ መለሰው፡፡ ሙሴ ልቱት (ኮልታፋ) የሆነበት ምክንያት ይህ ነው። ስለዚህ ፈርዖን ከመግደል ተወው፡፡ እንዲህ እያለ ከአደገ በኋላ ከዕለታት አንድ ቀን ግብጻዊና ዕብራዊ በልብስ ማጠቢያ ተጣልተው ሳለ ለዕብራዊው አድልቶና ተረድቶ ግብጻዊውን ገድሎ አሸዋ አለበሰው፡፡ ይህ ነገር በፈርዖን ዘንድ አልተሰማም ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ ግብጻዊና ዕብራዊ ተጣልተው ሙሴ ሊገድል ቀርቦ ሳለ ግብጻዊው አንስቶ ከዚህ ቀደም ቢጣሉ ግብጻዊውን ገደልክ ሳይሰማብህ ቀረ ቢለው ያን ጊዜ ሙሴ ፈርቶ ወደምድረ ምድያም ተሰደደ፡፡ ከዚህ በኋላ የዮቶር ልጆች በጎቻቸውን ሲያጠጡ የሀገራቸው ውኃ ለሀምሳ ሰው የሚፈነቀል ድንጋይ ተገጥሞ ነበር፡፡ ሙሴን ከዚያ አግኝተው ፈንቅልልን አሉት፡፡ መጥቶ ለሀምሳ የሚፈነቀለውን ድንጋይ ብቻውን ፈንቅሎ በጎቻቸውን አጠጥቶላቸዋል፡፡ ፈጥነውም ወደቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ አባታቸውም ዮቶር ፈጥናችሁ መጣችሁ አላቸው፡፡ እነሱም አንድ ሰው አግኝተን ብቻውን ፈንቅሎ አጠጥቶልን ፈጥነን መጣን አሉት፡፡ ዮቶርም እንዲህ ያለውን ሰው ለምን ትታችሁት መጣችሁ አሁንም ሂዱና አምጡት አላቸው፡፡ እነሱም ሂደው አመጡት፡፡ ሙሴም ከዮቶር ቤት አደረ፡፡ ዮቶርም ልጁን አጋባው፡፡ ሙሴም ከዮቶር ቤት በግ ሲጠብቅ ኖረ፡፡

ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል/ የእስራኤል አምላክ በዚህ ሰማይ የለምን?

እስራኤል ከግብጽ ውስጥ ሲኖሩ ንጉሡ ፈርዖን በጣም ያሰቃያቸው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን  ራሄል የምትባል ርጉዝ ሴት ባሏ ሞቶ በባሏ ምትክ ኖራ እርገጭ ተብላ ኖራ የምትረግጥ ነበረች፡፡ ፈርዖን ለሕንጻ ጭቃ ሲያስቦካት ከዚያ ገብታ ጭቃ ስታቦካ ምጥ መጣባት፡፡ በዚያን ጊዜ ለፈርዖን ብታመለክት ከዚያው አብረሽ ርገጭው የሰው ደም ሕንፃ  ያጠብቃል፤ያጸናል አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ራሄል ከዚያው መንታ ልጆች ወልዳ ከጭቃው ላይ አብራ ረግጣቸዋለች፡፡ በዚያን ጊዜ ምርር ብላ ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል/ የእስራኤል አምላክ በዚህ ሰማይ የለምን? ብላ ብታለቅስና እንባዋንም ወደ ላይ ብትረጨው ቅድመ እግዚአብሔር ከመንበረ ጸባዖት ደርሷል፡፡

ሰማዕኩ ገዓሮሙ ለሕዝብየ ወወረድኩ ከመ አድኅኖሙ/ የሕዝቤን ጩኸት ሰምቻለሁና አድናቸው ዘንድ ወረድኩ !

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የራሄልን ጩኸቷንና ግፏን በመመልከት ከዕለታት አንድ ቀን በደብረ ሲና ዕፀ ጳጦስ ከምትባል እንጨት ሥር ጌታ ለሙሴ ተገልጾ የሕዝቤን ጩኸት ሰምቻለሁና ሂደህ ፈርዖንን ሕዝቤን ልቀቅ በለው አለው፡፡ ሙሴም ምን ምልክት አለኝ አለው፡፡

1ኛ. በትርህን ከመሬት ጣላት አለው ቢጥላት እባብ ሁናለች፡፡ ፈርቶ ሸሸ፡፡ ጅራቷን ይዘህ አንሳት አለው፡፡ ቢያነሳት ደህና ሁናለች፡፡

2ኛ. እጅህን ከብብትህ አግብተህ አውጣው አለው፡፡ አግብቶ ቢያወጣው ለምጽ ሆነ፡፡ ደግመህ አግብተህ አውጣው አለው ደግሞ አግብቶ ቢያወጣው ደህና ሁኗል፡፡

ሙሴም ይህን ነገር ለፈርዖን አሳይቶ እስራኤልን ስደዳቸው ቢለው እምቢ አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ፈርዖን እስራኤልን አለቅም እግዚአብሔርንም አላውቅም በማለቱ ምክንያትና ልቡን በማደንደኑ ፈጣሪ ብዙ መቅሰፍት አወረደ፡፡ በዚያን ጊዜ መቅሰፍት ሲወርድ የእስራኤል ሕዝብ በሚኖርበት በጌሤም መቅሰፍት አልነበረም፡፡ ሙሴን አሮንን ጸልዩልን እያሉ መቅሰፍቱ ይቆም ነበር፡፡ ሙሴም እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘርግቶ በመጸለይ ያማልድ ነበር፡፡ ሎቱ ስብሐት

ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፡፡ ዘፀ. 9፡- 1 8፡- 2

በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ፦ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳላሁ። በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት። አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ ዘፀ. 23፥20-22

እግዚአብሔር አምላክ ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ እያለ በተደጋጋሚ ፈርዖንን  በሙሴ አማካኝነት ቢያዘው ፈርዖን እምቢ በማለቱ ምክንያት ከፈጣሪ የታዘዙ መቅሰፍታት እኒህ ናቸው፡፡

1ኛ. ጓጉንቸር 2ኛ. ቅማል 3ኛ. የዝንብ መንጋ  4ኛ. ቸነፈር 5ኛ. ቁስል 6ኛ. ሻኝህ 7ኛ. በረዶ  8ኛ. አንበጣ 9ኛ. ሰው የሚዳስሰው ጽኑ ጨለማ 10ኛ. ሞተ በኲር 11ኛ. ስጥመት ናቸው፡፡

ወፈነወ መልአኮ ወአድኀኖሙ/ መልአኩን ልኮ አዳናቸው

ከዚህ በኋላ ፈርዖን እስራኤልን ወደሀገራቸው ሰደዳቸው፡፡ እሱም ከዋለበት ቢመጣ ከተማይቱ ጭልል ብላ አገኛት፡ ፈርዖንም ለካስ ከተማይቱን ያስከበሯት እስራኤሎች ናቸው ብሎ እነሱን ለመመለስ አንድ የወይራ ፍልጥ የሚበላ ፈረስ ነበረው፡፡ ሠራዊቶቹንና እያኔስን እያንበሬስን ባሬስን አስከትሎ እሱ በፈረስ ሆኖ ገስግሶ ከእስራኤል ደረሰባቸው፡፡ እስራኤልም ከባሕረ ኤርትራ ደርሰው ባሕረ ኤርትራ ሞልታ ነበርና ሙሴ በበትሩ ቢመታት እንደ ግድግዳ ወደታች ወደ ላይ ከሦስት ተከፍላ አሳልፋቸዋለች፡፡ ያን ጊዜ እስራኤልን ቅዱስ ሚካኤል እየመራ አሻገራቸው፡፡ ፈርዖንም እነሱን አይቶ እሻገራለሁ ብሎ ባሕረ ኤርትራ ገብቶ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ ቁጣውን ቢያሳየው ከነፈረሱና ከነሰራዊቱ ሰጥሞ ቀርቷል፡፡ እስራኤልም ሰባት ደመና ታዞላቸው አንዱ በፊት፤ አንዱ በኋላ፤ አንዱ በቀኝ፤ አንዱ በግራ፤ አንዱ ለእግራቸው ምንጣፍ፤ አንዱ ከላይ ለእራሳው ጥላ ከለላ፤ አንዱ መንገድ ጠራጊ ሆኖ እየመራቸው ከስደት ወደ ምድረ ርስት ተመልሰዋል፡፡ የእስራኤልም ልጆች በግብጽ የኖሩበት ዘመን ዐራት መቶ ሰላሣ ዓመት ነው፡፡ ዘፀ. 12፡-40

ይህ ሁሉ የሆነው ከፈጣሪያችን ታዞ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና ረዳትነት ሕዝበ እስራኤል/እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን በማሰብ ስለሆነ እኛን እስራኤል ዘነፍስንም ከሲኦል፤ ከገሃነም እንዲያወጣን፤ በነፍስ በሥጋ እንዲታደገን፤ከፈጣሪያችን እንዲያማልደን በእየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን የቅዱስ ሚካኤልን በዓል የምናከብርበት ምክንያት ይህ ነው፡፡

 

ስብሐት ለእግዚአብሔር

 

   ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

          አዲስ አበባ

 

 

ዘመነ ጽጌ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ያሉት 40 ዕለታት ሲሆኑ ትርጓሜው የአበባ ጊዜ ማለት ነው። “ወይቤሎ ለአዳም ወሀብኩከ ርስተ ገነት ትፍስሕት በፅጌ ሥርጉተ ወበፍሬ ክልልተ ዘፍ.2፥8 ” እግዚአብሔር ጠፈርን በአድማስ ደግፎና በደመና ከፍክፎ መባርቅትንና ዝናማትን በደመና ጭኖ ደመናውን በነፋስ አሽክሞ ዓለምን በፀሐይና በጨረቃ አብርቶ በፅጌያት አስጊጦ ገነትን በአዝርዕትና በአትክልት አዘጋጅቶ መንግሥተ ሰማያትን ሠርቶ የሰውን ልጅ ፈጠረው።
አምሳላተ ጽጌ (የጽጌ ምሳሌዎች)
1. ጽጌ የጌታ ምሳሌ ነው
“ትወፅዕ  በትር  እምሥርወ  እሴይ  ወየዐርግ  ጽጌ  (ኢሳ. 11፥1 ) ትርጓሜ  ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም  ቅድስት  ይእቲ  ወፅጌ  ዘወጽአ  እምኔሃ  አምሳሉ  ለወልድ ( ዮሐ. 1፥1- 14 ድጓ ዘጽጌ)ʼʼ

ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች። ከእርሷም አበባ ይወጣል፤ ይህችውም በትር የማርያም አምሳል ናት። ከእርሷ የተገኘው አበባም የወልድ አምሳል ነው። በመሆኑም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እውነተኛ መብልና እውነተኛ መጠጥ አድርጐ በመስጠቱ የፍሬ መገኛ በሆነው አበባ ተመስሏል። ቅዱስ ያሬድ ቡሩክ ዕፅ ዘሠናየ ይፈሪ ወኃጢአተ ይሰሪ ( ድጔ ዘጽጌ ) የኃጢአት ማስተሥሪያ የሚሆን መልካም ፍሬን ያፈራ የበረከት እንጨት ክርስቶስ ነው። ለሕያዋን ፍጥረታት የሕይወት ምግብነት ከሕቱም ምድር በቅሎ አብቦና አፍርቶ የተገኘው ክርስቶስ ከፍሬው የበሉትን ደቂቀ አዳም በሙሉ አድኗል።
2. ፅጌ የቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ምሳሌ
እመቤታችን የእውነተኛው ፍሬ ክርስቶስ መገኛ በመሆኗ በአበባ ትመሰላለች፤ እመቤታችን የኃጢአታችን ክብደት ሳይሆን የግፋችን ብዛት የታየባት እውነተኛ ችሎት (ፍትሐ አምላክ) የተገኘባት ናትና። ትውልድ ሁሉ ለዘላዓለም ያመሰግኗታል። “እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ (ሉቃ. 1፥481) መዝገቡ ለቃል ፅጌ እንተ ኢትትነገፍ መድኃኒተ ሕዝብ (ድጔ ዘጽጌ) ያገልጋዩን መዋረድ አይቷልና በክንዱ ታላቅ ሥራን አድረገ። የቃል ማደሪያ ( የፍሬ ሙዳይ ) የሆነችው አበባ ለዘለዓለም አትረግፍም። ስለዚህ በፍሬዋ የሕዝብ መድኃኒት በመዓዛዋ የቅዱሳን የሕሊና እረፍት ናት።
‹‹ ዕፀ ጳጣስ እንተ በአማን ፅጌ ደንጐላት ሐረገ ወይን ዘእምነገደ ይሁዳ እንተ ሠረጸት ለሕይወት (ዘፍ. 49፥1 ድጓ ዘጥቅምት ማርያም) እመቤታችን ከይሁዳ ነገድ ለዘለዓለም መንግሥት የወጣች የወይን ሐረግ በደብረ ሲና በጳጦስ እንጨት ላይ የታየውን ምሳሌ በእውነት ያሳያች ናት።››
3. ጽጌ የመስቀል ምሳሌ
በማር ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኛ ንቦች አንድ ሆነው በአበባ ላይ እንደሚሠፍሩ ሁሉ ሕዝብና አሕዛብ በአንድነት የተሰበሰቡበት አበባ የዕለተ ዐርቡ የክርስቶስ መስቀል በመሆኑ መስቀል አበባ ይባላል። በከመ ይቤ ሰሎሞን በእንተ ማርያም ንዑ ንትፈጋዕ ወኢይኅልፈነ ፅጌ ደመና መስቀል ዘዮም አብርሃ በስነ ማርያም። (ድጓ ዘጽጌ ) ሰሎሞን ስለ ማርያም ሲናገር እነሆ ክረሞቱ፣ (ውርጩ፣ ውችንፍሩ፣ ጭቃው፣ ቁሩ ) አልፎ በረከት ተተካ እንዳለ። የክርስቶ መስቀል በማርያም ባሕርይ ዛሬ አብቧልና የበረከት አበባ ሳያልፈን ኑ እንደሰት እንዲል።
በባሕርዩ መወሰን የማይስማማውን አምላክ ማርያም በባሕርይዋ ስለወሰነችው (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ስለሆነ) በተመረጠችው የማዳን ሰዓት / ዕለተ ዐርብ / መስቀል ያለባሕርዩ በማርያም ባሕርይ ተሸከመው።
4. ጽጌ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ
የክርስቶስ ሥጋ የሚያፈራባት የአበባ እንጨት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አበባ ትባላለች። ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው “ወልድ እኁየ ጸዓዳ ወቀይህ ፀዓዳ ትቤሎ በእንተ ሥጋሁ ለክርስቶስ” ልጅ ወንድሜ መልከ መልካም ደመ ግቡ ቀይ ነው። ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ስለለበሰው ሥጋ ቀይ ጐልማሳ አለችው ይላል። ቤተ ክርስቲያን ምድራዊት ስትሆን ሰማያዊት ናት። ለምድራዉያን ሰዎች የምትሰጠው ልጅነት የምታድለው ሰማያዊ ፀጋና ሀብት ነው።
‹‹ ሐረገ ወይን እንተ በሞድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ›› ሥሯ በምድር ቅርንጫፚ በሰማይ የሆነች የወይን ሐረግ በፈቃደ ሥላሴ ዛላዋ የምትቆረጥ ፍሬዋ የምትለቀም የበረከትም ፍሬ የምታፈራልን የወይን ሐረግ ቅዱስት ቤተ ክርስቲያን ናት።
‹‹ቅዱስ ያሬድ “ጽጌ ብሂል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን›› ጽጌ ማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት ይላታል (ድጓ ዘጽጌ)
በጽጌ የተመሰሉ የጌታችንና የእመቤታችን ስደት (ማቴ. 2፥13 -ፍ)
“እምግብፅ ጸዋዕክዎ ለወልድየ ” (ሆሴዕ. 11 ፥ 1) ልጄን ከግብጽ ጠራሁት ለጊዜው የተነገረው ለያዕቆብ ሲሆን ፍጻሜው ግን ለጌታ ነው። መልከ ጼዴቅም ዘመዶቹን ማርልኝ ቢለው ልጄን በሥጋ ሰድጄ እምርልሀለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት ነበርና ኪዳነ መልከ ጼዴቅን ለመፈጸም ጌታ ወደ ግብጽ ተሰደደ።
“መልአከ እግዚአብሔር አስተርአዮ በሕልም ለዮሴፍ” ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው። “እንዘ ይብል ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጐየይ ውስተ ሞድረ ግብፅ” ተነሥተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ ብሎ ነገረው። እስመ ሀለዎ ለሄሮድስ ይኅሥሦ ለሕፃን ከመ ይቅትሎ ” ሄሮድስ ብላቴናውን ሊገድለው ይሻው ዘንድ አለውና።
• ወተንሥኦ ነሥአ ሕፃነ ወእሞ በሌሊት ወሖረ ውስተ ብሔረ ግብጽ” ተነሥቶ ብላቴናውን እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሂደ። ከላይ በመግቢያው እንደተገለጸው
• ከመ ይትፈጸም ዘተብህለ እም ኃበ እግዚአብሔር በነቢይ እንዘ ይብል እምግብፅ ጸዋዕክዎ ለወልድየ” እግዚብሔር በነቢይ አድሮ ነቢይ ከእግዚብሔር ተገልጾለት በነቢዩ
ቃል ልጄን ከግብጽ ጠራሁት ተብሎ የተነገረው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ፤ ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብጽ ዲበ ደመና ቀሊል” በደመና ተላይ ሆኖ ወደ ግብጽ ይወርዳል ተብሎ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ።
• “ወነበረ ህየ እስከ አመ ሞቱ” ለሄሮድስ” የተነገረው ይፈፀም ዘንድ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በግብጽ ኖረ።
ጌታ ለምን ተሰደደ?
1. ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ፤ 2. ስደትን ለመባረክ 3. በፈቃዱ የሚሞትበት ጊዜ አልደረሰምና። 4. አዳሞ ከዚህ ዓለም አፍአ ከምትሆን ከገነት ተሰዶ ነበር። 5. ሰማዕትነት በእሳት በስለት ብቻ አይደለምና እኛን ለማስተማር ተሰደደ ብለው ሊቃውንት ይተርጉማሉ። ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሳለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሁለት ዓመት ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናትን ሁሉ ግደሉ አለ። ቄሣር ሕፃናትን ሰብስበሕ ልብስ ምግብ እየሰጠህ በማር በወተት አሳድገህ ለእናት ለአባታቸው ርስት ጉልት እያሰጠህ ጭፍራ ስራልኝ ብሎኛል ብሎ አዋጅ ነገረ። በዚያ ጌዜ ያላት ልጅዋን የሌላት ልብስ ምግብ ልቀበልበት ብላ እየተዋሰች ይዛ ሂደላች። በዚያን ጌዜ 144.00 (አሥራ አራት እልፍ ከአራት ሺህ )ሕፃናት ታርደዋል።
በባሕርየ መለኮቱ ስደት የማይስማማው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል እንደ አስተማረው ሥጋዊ ስደቱ ፤
1. ስደትን ለተከታዮቹ ለማስተማር በአንዲቱ ከተማ መከራ ቢያደርሱባችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ (ማቴ. 10፥23 )
2. ሰው መሆኑን ለመግለጽ ከአዳም አካል አንድም ያልጐደለው ሙሉ ዳግማዊ አዳም መሆኑንና የለበሰው ሥጋ የሚደማ የሚቆስል በሰይፍም ሆነ በጦር ቢወጋ ጉዳት የሚደርስበት ሰብአዊ ባሕርይ ያለው መሆኑን ለማስረዳት
3. ዲያብሎስን ለማሰደድ የጌታ ስደት በተዛዋሪ የዲያብሎስ ስደት ሆነ፤ ጌታ የሚቀበለው መከራ ሁሉ ዲያብሎስን በርቀት የሚመታ መሣሪያ ነው። በመጨረሻም በመስቀሉ ላይ የሆነው የጌታ ሞት የዲያብሎስ ሞት ሆነ። የኢትዮጵያ ኦቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህን አጽንተው ያስተምራሉ ያምናሉ።
የጌታንና የእመቤታችን ጉዞ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ
እመቤታችን ቅዱስት ድንግል ማርያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜ በብሩህ ደመና ላይ ሆነው ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ናግራን ከተባለ ሀገር ደረሱ። በናግራን ሳሉ ጌታ እንዲህ አለ። ከቀኝ ጐኔ የሚፈሰው ደሜ በብርሃናት አለቃ በቅዱስ ዑራኤል እጅ ተቀድቶ  በቅድሚያ በዚች ሀገር ይፈሳል፣ ይረጫል ። እመ ብዙኃን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲህ አላት፤ አንች በድንግልና ፀንሰሽ በድንግልና እንደወለድሽኝ አምነው የሚያከብሩሽ በእኔም የሚያምኑ ብዙ የተቀደሱ ሰዎች በዚህች ሀገር ይወለዳሉ። ከናግራን ተነሥተው ለትግራይ ትዩዩ ከሚሆን ሐማሴን ከሚባለው ሀገር ሲደርሱ በምሥራቅ በኩል ከፍተኛ ተራራ ተመለከቱና ወደ ተራራው ሄዱ። ጌታም በተራራው ላይ ሳሉ እመ ብዙኃንን እንዲህ አላት። ይህች ተራራ ምስጋናሽ የሚነገርባት ቦታ ትሆናለች። የተራራዋም ስም ደብረ ሃሌ ሉያ ወይም ደብረ ዳሞ ይባላል። ትርጓሜውም የአምላክ ልጅ፣ የመስቀሉ፣ ቦታና የስሙ መገኛ ወይም አደባባይ ማለት ነው።
ከዚያም በኋላ ታቦተ ጽዮን ወደሞትኖርበት ወደ አክሱም ደረሱ። ታቦተ ጽዮን ባለቸበት ቦታ ሳሉ ባዚን የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ታቦተ ጽዮንን ለመሳለም መጣ። የካህናቱ አለቃ አኪን የኢሳይያስን መጽሐፍ ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች የሚለውን አነበበ (ኢሳ 7 ፥ 14)
ስደተኞች ግን ለንጉሡም ሆነ ለካህናቱ ሳይገለጡ የመጽሐፋን ቃል ከሰሙ በኃላ በብሩህ ደመና ላይ ሆነው ወደ ደብረ ዐባይ ሄዱ። ጌታም እናቱን እንዲህ አላት። ይህች ሀገር እንደ አክሱም ለስምሽ መጠሪያ ርስት ትሁን፣ በኋላ ዘመን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ሕጌን የሚያስተምሩ አንችን የሚወዱ ሰዎች ይኖሩባታል አላት።
ከዚያም ደብረ ዐባይ ተነሥተው ዋሊ ወደሚባለው ገዳም ወደ ዋልድባ ሄዱ። በዋልድባ በረሃም ሳሉ በራባቸው ጊዜ ጌታ በዮሴፍ በትር የአንድን ዕንጨት ስር አወጣና ለእናቱ ብይ ብሎ ሰጣት። እናቱም ይህን የሚመር እንጨት አልበለም አላችው። ጌታም በኋላ ዘመን ስምሽን የሚጠሩ አንችን የሚያከብሩ ብዙ መናንያን ይህን እየበሉ በዚህ ቦታ ይኖራሉ አላት።
እንጨቱም የሚጣፍጥእስራኤል ነገር ሂድ አለው (ማቴ. 2፥19-21 )
ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ከስደት በሚመለሱ ጊዜ ወደ ደብረ ቁስቋም የገቡበት ዕለት በየዓመቱ ኀዳር 6 ቀን ይከበራል።
በዚህ መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶና እናቱ የእኛም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሊቀበሉት የማይገባውን ሥጋዊ መከራ ለእኛ ሲሉ በመቀበላቸው ምክንያት ለእኛ እመቤታችንና አምላክን የምናመሰግንበት ክፍለ ዘመን ዘመነ ጽጌ ስለተባለ ኢትየጵያውያን ሌቃውንት አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም የተባሉ አበው መነኮሳት ማሕሌተ ጽጌን ደርሰውልናል። ይቆየን —

ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

    አዲስ አበባ

“ሤመክሙ  እግዚአብሔር  ጳጳሳተ፣ ቀሳውስተ  ወዲያቆናተ  ከመ  ትርዐዩ  ቤተ  ክርስቲያኑ  ለክርስቶስ  እንተ አጥረያ በደሙ ወአተባ  በዕፀ  መስቀሉ”

በገዛ  ደሙ  የዋጃትንና  በዕፀ  መስቀሉየባረካትን  የእግዚብሔርን ቤተ ክርስቲያን  ትጠብቁአት  ዘንድ  መንፈስ  ቅዱስ  እናንተን ጳጳሳት ቀሳውስትና ዲያቆናት አድርጎ ለሾመባት፤  ለመንጋው  ሁሉና  ለእራሳችሁ  ተጠንቀቁ (የሐዋ ሥራ 20፥28) በማለት ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ገልጾልናል። በመሆኑም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከመሾሙም በተጨማሪ ይህን ቃል  ኢትዮጵያዊ  ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ዘምሮታል።  ድጓ ዘሐዋርያት

“ይቤሎሙ  ኢየሱስ  ክርስቶስ ለአርዳሁ  ኢይብለክሙ  አግብርትየ  አላ  አእርክትየ  አንትሙ” ( ኢየሱስ ክርስቶስ ) ሐዋርያቱን ከእንግዲህ  ወንድሞቸ እንጂ አገልጋዮቼ  አልላችሁም  በማለት ፍቅሩን ገልጾላቸዋለ። ዮሐ. 15፥15 አማን አማን እብለክሙ ዘየአምን ብየ ግብረ ዘአነ እገብር ውእቱኒ ይገብር ወዘየዓቢ  እመኔሁ ይገብር” እውነት እውነት እላችኋላሁ በእኔ የሚያምን  እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል። ከዚህ የሚበልጥ ያደርጋል። ዮሐ. 14፥12   በማለት ሙሉ ስልጣኑነ ሰጥቷል።

እኒህ  ቅዱሳን  “ጸሎትክሙ  ጽንዕት  ሃይማኖትክሙ  ርትዕት  እንተ በኵሉ ትረድዕ” የጸናች ጸሎታችሁ የቀናች ሃይማኖታችሁ በሁሉም መልካም ነገር ትረዳለች ተብሎ ተነግሮላቸዋል። በመሆኑም  ቅዱሳን  ሐዋርያት  ቅዱሳን  ሊቃውንት እና ቅድሳን ካህናት  በየዘመኑ  የሚነሳውን  የጥርጥር እና የምንፍቅና ትምህርት የነገሥታቱ ቁጣ ግልምጫ፣ ፍጥጫ፣ ዛቻ፣ ሳይበግራቸው  እሳቱ ስለቱ  ሣያስፈራቸው  እንደ ዱባ  እየታረዱ፣  እንደ  ጐመን   እየተቀረደዱ አጥንታቸው ተከስክሶ ደማቸው እንደውኃ ፈሶ ለእውነተኛዋ ርትዕት ሃይማኖት በሰማዕትነት ያለፉ አበው ቅዱሳን   እግዚአብሔር  በገባላቸው  ቃል  ኪዳን  መሠረት  ዓለሙን  ሲያማልዱና  በሠሩልን ሕግና ቀኖና ስንጠቀም የሞንገኝ ብዙዎች ነን።

ወእሙንቱ  ሠርዑ  ሕገ  ወቀኖና  ወኮነ  እግዚእነ  ኢየሱስ  ክርስቶስ  ሎቱ  ስብሐት ይነብር ማዕከሌሆሙ  እስመ  ብዙኃን  እለ  ኮና  አልባቢሆሙ  ብርሃነ በመንፈስ ቅድስ (ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሀላቸው ሆኖ  የሚገኝ እና በመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ብሩሃን የሆኑ። ሐዋርያት ሕግንና ቀኖናን ሠርተውልናል።

ጌታችን መድኃኒታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ  “አማን እብለክሙ ዘአሰርክሙ በምድር ይከውን እሱረ በሰማያት ወዘፈታሕክሙ  በምድር ይከውን ፍቱሐ በሰማያት”  እውነት እላችኋላሁ በምድር  የምታስሩት ሁለ  በሰማይ የተሳረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል  ብሎ ሙሉ  ስለጣኑን ሰጥቷቸዋል ማቴ.18፥ 18

“ መሀሩ  ሃይማኖተ  ርትዕተ  እንዘ  ያጤይቁ  ከመ  ወልድ  ዕሩይ  በመለኮቱ  ምስለ  አብ” (አካላዊ  ቃል   ቃለ እግዚብሔር  ወልድ  በመለኮቱ  ከአብ ጋር ትክክል መሆኑን  ለማስረዳት  የቀናች   ሃይማኖትን አስተማሩን ) ሎቱ ስብሐት።

ዓለም አቀፍ ጉባኤ ኒቂያ

 ለሠለስቱ  ምዕት  መሰባሰብ  ዋናው  ምክንያት  የሆነው  የአርዮስ   የክህደት  ትምህርት  ነው።  ስሑት  ኢርዮስ  ወልድ  የባሕርይ  አምላክ  አይደለም  ፈጡር ነው። በማለት  በሚያሰራጨው የክህደት  ትምህርት  የተነሣ  ከስሕተት  ትምህርቱ  እንዲመለስ  እና  እንዲታረም  ቢመከረም  አሻፈረኝ ብሎ  እምቢ  በማለቱ አበው ሊቃውንት  በኒቂያ  ተሰበሰቡ።

በጉባኤው  ከምዕራብ  አውሮፓ  እና  ምሥራቃውያን  ተገኝተውበታል።   ከምሥራቅ  የእስክንድርያው  ሊቀ ጳጳስ እለ እስክንድሮሲ ሊቀ  ዲያቆኑ አትናቴዎስና  የንቢጽኑ  ያዕቆብ  ይገኙበታል።

አበው  ከመስከረም  ማርያም  (የብዙኃን ማርያም) እስከ ኀዳር ዘጠኝ ሱባኤ ገቡ። ወዲያው  በኀዳር ዘጠኝ ክርክሩ ተጀምሮ አርዮስ ተወገ። ሠለስቱ ምዕት አንደ አንድ ልብ መካሪ  እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው “ወልድ ዋሕድ”  ብለው  አምነዋል። “ዋሕደ  ባሕርይ ምስለ አብ” ከባሕርይ አባቱ  ከአብ ጋር በባሕርይ  አንድ  የሆነ አምላክ  በማለት  የመለኮትን  አንድነት  የአካላትን  ሦስትነት የወልድን  አምላክነት  በመጽሐፍ  ቅዱሳዊ  ትምህርት  አንቀጸ   ሃይማኖት  አጽድቀዋል። የርጉም አርዮስ የረከሰች ትምህርትንም አውግዘዋል። ከቤተ ክርስቲያን ማንኛውንም አገልግልት እንዳይከፋል ለይተው አውግዘውታል።

በኒቂያ ጉባኤ የተነሱ ዋና ዋና መከራከሪያዎች

  1. ርጉም ውጉዝ አርዮስ አካል ዘእምአካል ወለደኝ የሚለውን ትክክለኛ ትርጓሜ ሳይረዳ በምሳሌ ሰሎሞን ምዕራፍ 8 ቁጥር 22 “እግዚአብሔር ፈጠረኒ ቀዳሜ ኩሉ ተግባሩ” እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ በቀድም ሥራው መጀመሪያ የሚለውን (ፈጥሮ ፈጠረብኝ )በማለትና“ ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ”የሚለውን ሐረግ (ጥበብ ፈጠረኝ) ይላል ብሎ የአካላዊ ቃል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን በለበሰው ሥጋ የባሕርይ አምላነቱን በመካድ ክርክር ተደርጐ፤

1ኛ.  ቃል ፍጡር ግቡር ከተባለ ፍጡር ፍጡራንን እንዴት ማዳን ይችላል ?

2ኛ. ሥጋዬና የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው እኔም እኔም ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር

እኖራለሁ ይላል። ታዲያ ሰው የሰው ሥጋ በልቶ እንዴት ዘለዓለማዊ ሕይወት ያገኛል ይድናል?

3ኛ. በእግዚአብሔር  ወልድ  መዳናችን  ካመን ያዳነን  አምላክ  መሆኑን ማመንና  ማወቅ

አለብን  ይህ  ካልሆን አልዳንም  ማለት ነው  የሚሉ  ጥያቄዎችን ቢጠየቅ አይኑ ፈጠጠ

ጥርሱ ገጠጠ የሚመልሰው ቃል አጣ። በዚህ ጊዜ በእነ ሊቁ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ አትናቴዎስ

እውነተኛ  ርትዕት ኦርቶዶክሳዊ ክርክር ተረትቶ ተወግዞ ተለየ።

አንቀጸ ሃይማኖት

ጸሎተ  ሃይማኖት 12  አንቀጽ  አለው  ከዚህም  ውስጥ  ሰባቱ  በሠለስቱ  ምዕት  የተረቀቁ  ሲሆን  አምስቱ  ደግሞ  በሁለተኛው  ጉባኤ  በቁስጥንጥንያ  ጉባኤ  የተወሰኑ  ናቸው።

  1. ነአምን በአሕዱ  አምላክ  ( በአንድ  አምላክ  እናምናለን ) ከሚለው ጀምሮ   እስከ  ይኴንን  ሕያዋነ ወሙታነ  ( በሕያዋንና  በሙታን  ላይ ) ይፈርዳል እስከሚለው   ድረስ  7ቱ  አንቀጽ  በጉባኤ ኒቂያ በሠለስቱ  ምዕት  ተወሰነ።
  2. ወነአምን በመንፈስ  ቅዱስ  (በመንፈስ  ቅዱስ  እናምናለን) ከሚለው ጀምሮ እስከ ወሕይወተ ዘይመጽእ ለዓለመ ዓለም  ( ለዘለዓለማዊ  ሕይወትን  ለመስጠት ይመጣል) እስከሚለው ድረስ  5ቱ  አንቀጽ  በቁስጥንጥንያ ጉባኤ ተወሰኗል። ስለዚህ  አበው በኒቂያ ጉባኤ  “ወልድ  ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ”  (ወልደ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ መሆን አረጋግጠው ወስነዋል።

ቤተ ክርስቲያን

  ቤተ ክርስቲያን  ከጥንት  ጀምሮ  ከውጭ  በአለውያን   ነገሥታት  ከውስጥ  በልጆቿ  ስትፈተንና

ስትቸገር  የነበራች፤  በየዘመናቱ  የሚያጋጥሟትን  የመከራ ዘመናት  ሁሉ ተቋቁማ አሁን ካለንበት

ዘመን ደርስላች።  አሁንም ተረፈ  አርዮሳውያን  እየተዋግዋት  ያለች  ምድራዊት ስትሆን ሰማያዊት በደሙ የዋጃት የእግዚአብሔር ቤት ናት።

 

 ይቆየን

ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ አበባ

የሚመስሉ የእንግሊዝኛ ቃለት ትክክልኛ የአማርኛ ናቸው
1. ኮሌጅ —————————— መካነ ትምህርት (የእውቅት ቦታ)
2. ዩኒቨርስቲ ————————– መካነ አእምሮ (ከፍተኛ የእውቀት ቦታ)
3. ሌክቸር——————————- ትምህረተ ጉባኤ (ትምርት መስጠት)
4. ሌክቸረር ————————— መምህረ ጉባኤ (ትምርት ሰጪ)
5. ዲን ——————————— ሊቀ ጉባኤ
6. ቢሮ ——————————– መስሪያ ቤት
7. ባንክ ———————————– ቤተ ንዋይ (ገንዘብ ቤት )
8. ሲቪል ሰርቪስ ———————— ሰላማዊ( ሰበአዊ አገልግሎት) የሕዝብ አገልግሎት
9. Custom ————————- — ባህል ልማድ (ወግ)
10. ኮምፒዩተር —————————– መቀመሪያ (መዝገበ ቀመር)
11. ድግሪ ———————————- ማዕረግ (ልዕልና )በትምህርት የሚገኝ
12. ሚኒስተር ————————–ምሉክ ወኪል ተወክሎ የሚሠራ (መልአከ ምኩናን)ልዑካ
13. Mass media————————– ምሕዋረ ዜና (ማሰራጫ)
14. ፎቶ ግራፍ—————————— ብራናዊ ስዕል (አካለ ምስል)
15. ራዲዮ ———————————-ንፋሰ ድምፅ (ምስምአ ድምፅ) በነፋስ ሐይል የሚሰማ ጽምፅ
16. ፖሊስ ——————————– የሕግ ዘበኛ ሕግ (አስጠባቂ) አቃቢ
17. ኢንተርኔት —————————– መልዕክት /ነገር/ አየራት የመልእክት መረብ
18. ሎሬት ——————————— በዓለ አእምሮ አምበል፣ ተሸላሚ የእውቀተ የልምድ ( ሊቀ አእምሮ)
19. ዶክተር ——————————– ሊቀ ምሁራን
20. ኢምባሲ —————————— የእንደራሴ ጽ/ቤት (የመንግሥት ወኪል)
21. ዲፕሎማት————————— — የመንግሥት መልእክተኞች
22. ኢኮኖሚክስ —————————– ስነ ብዕል (ሊቀ ሀብታት) ስለ ገንዘብ አጠቃቀም ያጠና
23. ሀዋላ ———————————- ምሕዋረ ንዋይ( ገንዘብ ማስተላለፋ)
24. ሳሎን ————————————እንግዳ መቀበያ ( ምዕራፈ ነግድ)
25. ቱሪዝም ——————————– ስነ ሕዋፄ (ሑረት /ጉብኝት)
26. ፕሬዝዳንት————————- ሊቀ ሀገር /ሙሴ/መራሄ ሀገር/ ገር መሪ/
27. ቴሌኮሚኒኬሽን —————————-ምሕዋረ ቃል ( በነፋስ ሐይል ቃላትን መለዋወጥ)
28. ቪዛ ————————————— የይለፍ ፍቃድ
29. ፓስፓርት ———————————የኬላ ማለፊያ ፈቃድ (መታወቂያ)
30. ሳተላይት——————————— የሕዋ አውታር

ከአባ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

               የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

አዲስ አበባ