Archives

All posts for the month March, 2018

፩. ቅዱስ ኤራቅሊስ “እምፅቡር ጽሩይ ገብራ ለድንግል፤ ከንጹሕ ዘርዕ ድንግልን ፈጠራት” ይላል፡፡ ይህም የሚያመለክተው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

ንጽሐ   ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ያላደፈባት ንጽሕት ዘር መሆንዋን ነው፡፡

(ሃይ. አበው ም.፵፰ ክፍ. ፰ ቊ. ፴፩)

፪. ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ወሶበ ረከበ ሥጋሃ ቅዱሰ ወነፍሳ ንጽሕተ ፈጠረ ሎቱ ሕያወ መቅደሰ:- ሥጋዋን ቅዱስ ሆኖ ነፍስዋንም ንጽሕት ሆና ባገኘ ጊዜ ለራሱ ሕያው ማደሪያን ፈጠረ” ይላል፡፡

(ሃይ.አበው ም. ፷፮ ክፍ. ፱ ቊ. ፲፬)

፫. መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ቡሩክት አንቲ እምአንስት” ሲል የተነገረላትንም የምስጋና ቃል  የቤተ ክረስቲያን ሊቃውንት ሲተረጉሙ  “ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለብሽ ነሽ” በማለት ያብራሩታል፡፡

( የሉቃስ ወንጌል ም.፩ ቊ. ፳፰ )

፬. ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “አንጺሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ” ያለውንም ሲተረጒሙ ጥንቱን ጥንተ አብሶ ኑሮባት አነጻት ማለት ሳይሆን ጥንቱንም እንዳይኖርባት አደረገ ማለት ነው ሲሉ ያትታሉ፡፡

፭. ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ  ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ “ማርያምሰ ተሐቱ እምትካት ውስተ ከርሡ ለአዳም ከመ ባሕርይ ፀዐዳ” ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ውስጥ እንደ እንቊ ታበራ ነበር በማለት ከጥንት ጀምሮ  ንጽሐ ሥጋ፤ ንጽሐ ነፍስ፤ ንጽሐ ልቡና ያላደፈባት መሆንዋን መስክሯል፡፡

(ድጓ ዘኅዳር ማርያም ቅንዋቱን ተመልከት)

፮. ኦርቶዶክሳዊው ሊቅ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን የቅዱስ ያሬድን ቃል  “ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም አዝማንየ አዝማንኪ፤ አምጣንየ አምጣንኪ፤ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድክዎ፤ እግዚአብሔር አብ ማርያምን አላት፡- ዘመኔ ዘመንሽ፤መጠኔም  መጠንሽ ነው፤አንች ታቀፍሽው እኔ ዛሬ ወለድኩት፡፡” ምሥጢራዊ ዘይቤ፡- “ዘመኔ ዘመንሽ ነው” የሚለው ቃል የሚያመለክተው እሱ (እግዚአብሔር አብ) በአካል ቅድመ ዓለም በኖበረበት ጥንት ሁሉ እሷም በእሱ ኅሊና የዚያኑ ያህል ዘመን ያላት መሆኑን ሲሆን “መጠኔ መጠንሽ ነው” የሚለው ደግሞ ወልድ  ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት እንደተወለደ ፤ ድኅረ ዓለምም ከድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን ለማመልከት የተነገረ ቃል ነው፡፡ “እኔ ዛሬ ወለድኩት፤አንች ታቀፍሽው” የሚለው ቃል የሚያመለክተውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ አንድም “እኔ ዛሬ ወለድኩት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ያን ጥንተ-ልደት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ጊዜዬ ነውና በማለት ተርጒመውታል፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች ፤ከጥንት ጀምሮ  ንጽሐ ሥጋ፤ ንጽሐ ነፍስ፤ ንጽሐ ልቡና ያላደፈባት ንጽሕት ቅድስት መሆንዋን መስክረዋል፡፡

(መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን, መድበለ ትምህርት ኦርቶዶክሳዊ, ፳፻፮ ዓ.ም)

፯. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም የአበውን አሰረ ፍኖት በመከተል “መሠረተ ሕይወት ማርያም ወጥንተ መድኃኒት ዘእምቀዲሙ” ከጥንት ጀምሮ ንጽሕት ቅድስት መድኃኒት የሕይወት መሠረት እያሉ በማኅሌታቸው፤ በዝማሬያቸው ያመሰግኗታል፡፡

ነግሥ

፰. ቅዱስ ኤፍሬም “የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኵሎሙ ቅዱሳን… ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል ወትፈደፍድ እምሱራፌል” በጽርሐ አርያም ያሉ መንበረ ሥሉስ ቅዱስን የተሸከሙ ንጹሓን መላእክት እንኳ እንደማይስተካከሏት፤ ከቅዱሳን ሁሉ በላይ ክብሯ የበለጠና መትሕተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን፤ ከጥንት ጀምሮ ንጽሕት፤ ቅድስት፤ ድንግል፤ እመ አምላክ፤ ወላዲተ አምላክ፤ ድንግል ወእም  ጥንተ አብሶ የሌለባት መሆኑዋን መስክሯል፡፡

የረቡዕ ውዳሴ ማርያ

፱. ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ  ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ዝማሬ መላእክትን በዘመረበት ቃሉ “ብኪ ድኅነ ዓለም ወበወልድኪ ኮነ ሰላም” ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች፤ የንጹሓን፤ የቅዱሳን መላእክትን ባሕርይ ባሕርይ ሳያደርግ፤ በልሳነ ከይሲ ተሰውሮ የገባውን ሠይጣን በለቢሰ ሥጋ ድል የነሣባት ከጥንት ጀምሮ ንጽሕት ቅድስት መሆኑዋል አመስጥሯል፡፡

መቅድመ ኪዳን

ለዚህም  ነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም የአበውን አሰረ ፍኖት በመከተል መጽሐፍ ቅዱሳዊና ቅዱስ ትውፊታዊ በሆነው ማስረጃነት መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ፤ መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ የሌለባት፤ ንጽሐ ሥጋ፤ ንጽሐ ነፍስ፤ ንጽሐ ልቡና ያላደፈባት ንጽሕት ዘር መሆንዋን ታምናለች፤ ታስተምራለች፡፡

ለዚህም ነው ቅዱስ ያሬድ የነቢያትን ትንቢት፤የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት፤ የሐዋርያትን ስብከት፤ የሊቃውንትን ትርጓሜና ድርሰት፤ የእርሱንም ድርሰት እያስማማ ሲዘምር የቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን ስም በግልጽ  ጠርቶ ወይም በምሳሌም ወይም በምሥጢርም ያላነሳበት አንድም ምስጋና የለውም፡፡ በረከቱ ይደርብን፡፡ አሜን

የአምላክ እናት፤ የፈጣሪ እናት፤ ወላዲተ አምላክ፤ እመ ብርሃን፤ ሰአሊተ ምሕረት፤ አቁራሪተ መዓት፤ ርኅርኅተ ኅሊና ከልጅሽ ከፈጣሪሽ ዘንድ በተገባልሽ ቃል ኪዳን መሠረት አማልደሽ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ለሕዝቧ ምሕረትን፤ ይቅርታን፤ ቸርነትን፤ በረከትን፤ሰላምን አሰጭን፡፡ አሜን!

 

ይቆየን

ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

አዲስ  አበባ