Archives

All posts for the month May, 2018

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የልዩ ልዩ ሃይማኖት መሪዎችና ተወካዮች፤ የተከበራችሁ አምባሳደሮች፤

የተከበራችሁ የዓለም አቀፍ የዕርዳታ ሰጪ ተወካዮች እንዲሁም የዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች፤

ከሁሉ አስቀድሜ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለአሉ ሰብአዊ ዕርዳታዎችና አገልግሎቶች እንድንወያይ ይህንን የተቀደሰ መድረክ ለአደራጁ አካላት እግዚአብሔር በጎ አመለካከትን ስለሰጣቸው ለኃያሉ አምላክ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡

ይህ የበጎ አድራጎት ስሜት በተለይ ከውጭ የሚመጣ ዕርዳታና ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ ባለመሰጠቱ በሚሰጡ መግለጫዎችና በሚዘጋጁ ሰነዶች በውጤትም ሆነ በአሐዝ ተዘጋጅተው ለሕዝብ ባለመቅረባቸው ለሕዝቡም ሆነ ለለጋሽ ድርጅቶች ጥንካሬአቸውንና ከሕዝብ ጋር ያላቸውን የድጋፍ ቁርኝት ለማረጋገጥ እንዲችሉ ግልጽ የሆነ አገር አቀፍ እና ኅብረተሰብ ተኮር መስመርና ሥርዓት እንዲዘረጋ ያስፈልጋል፡፡

ይህም ጉባኤ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውና የድጋፍ መዋቅር በየደረጃው የሚታይበት ስልት እንዲጠቁም ተፈልጎ እንደተዘጋጀ ግልጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዋናው መሥሪያ ቤት ጀምሮ እስከ መንደርና ቤተሰብ ድረስ ቁርኝት ያላት ስለሆነ በየደረጃው ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሠራሽ ችግሮች አቅሟ በፈቀደው መሠረት ፈጥና ትደርሳለች፡፡

በዚህ ረገድ ልዩ ልዩ መዋቅሮች ባልተዘረጉበት ዘመን ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለተፈናቃዮች፣ ለአረጋዊያን፣ ለነዳያን፣ ለአእምሮ ሕመምተኞችና ለአካል ጉዳተኞች፣ ለወጣቶችና ለሴቶች የሚረዱ አገልግሎቶችንና ቱሩፋቶችን በአጋርነት ስትሰጥ ቆይታለች አሁንም ይህንን ሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት ትቀጥላለች፡፡

እንደሚታወቀው እ.ኤ.አ. በበ1970 በጋራና በአጋርነት የሰብአዊ እርዳታ አገልግሎት የሚሰጥ መርኃ ግብር (Joint Relief Program) ተቋቁሞ ከዚያን ጊዜ ወዲህ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ድርጅቶች በመረባረብ በድርቅና በአደጋ ምክንያት የደረሰ ችግርን ለመቋቋም ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን የዕርዳታ ድርጅት በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም ልዩ ልዩ ግብረ ኃይሎችን አቋቁሞ የሰብአዊ ድጋፍ በኢትዮጵያ በተሻለ መንገድ እንዲሰጥ ጥናት አዘጋጅተዋል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡

የተከበራችሁ የጉባአው ተሳታፊዎች፤

ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነትና እንደዚሁም እውነተኛ የማኅበረሰብ እኩልነት ነው፡፡ ሰላም ሁለት ተቃራኒ ወገኖች የሚያገኙት እኩል ሚዛናዊ ፍትሕ ነው፡፡ ሰላም የጦር መሣሪያን መቀነስና ጦርነትን ማቆም ከሰዎችም መካከል የጥላቻ መወገድ ብቻ እንዳይደለ ይታወቃል፡፡

ዛሬ ዓለማችን ከምን ጊዜውም ይበልጥ እርስ በእርስ በሚቃረኑ ሁኔታዎች ውስጥ ትገኛለች፡፡

ዓለማችን ከባድና አነስተኛ ድንበር ዘለልና አካባቢያዊ ግጭቶች በመስፋፋታቸው ምክንያት እነዚህ ሁኔታዎችምደግሞ በድሀና በአዳጊ ሀገራት ዘላቂ ልማት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ምክንያት ሆኗል፡፡

ሰላም በየትኛውም አቅጣጫ የሕይወትን ሁለንተናዊ ፍጹምነት የሚያመለክት ነው፡፡ እንዲሁም የሀገርን ዕድገት፣ ብልጽግና፣ ትምህርትንና ጤናን እንዲሁም ሕይወት በተፈጥሮአዊ ሞት እስኪፈጸም ድረስ ያለውን ረዥም ሕይወት ይገልጣል፡፡ ግላዊና ማኅበራዊ ደኅንነትን ፀጥታንና መረጋጋትንም ያሳያል፡፡ (ዮሐ. 20÷19) ሰላም በምድር ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ እጅግ የከበሩና የተወደዱ ከሁሉም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ሁሉ በላይ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ያለሰላም እግዚአብሔርን ማየት የሚችል የለም ይላል (ዕብ. 12÷14) ሰው ያለ ሰላም ማየት የማይችለው እግዚአብሔርን ብቻ አይደለም ባልንጀራውንም ያለሰላም ማየት አይችልም፡፡ ሰላም የሌላቸው ወገኖች ሊተያዩና ሊነጋገሩ አይችሉም፡፡

ይሁን እንጂ ሰላም በዓለማችን ላይ የሚናፈቀውን ያህል አይደለም፡፡ ከየአህጉራቱ ዘወትር የጦርነት ዜና ይደመጣል፣ የአንዱ ሀገር ሕዝብ ከሌላው ሀገር ሕዝብ ጋር፣ በዚያው በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል በጎሣ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ሳበያ በሚከፈተው ግጭት ሰላም እየታጣ ነው፡፡

የሰላም መታጣትም ብዙ ማኅበራዊ ችግርን ያስከትላል፡፡ ሰላም ሲጠፋ፣ ሁሉም ወደ ጦርነት ሲያተኩር ለማኅበራዊ ዕድገት መዋል የሚገባው ሀብት ለጦርነት ይውላል፡፡ በዚህ ምክንያት ሀገር ምድረ በዳ ይሆናል፤ ዜጎች ከመንደራቸው ከአገራቸው ከሞቀ ቤታቸው ይፈናቀላሉ ለስደትም፣ ለፍልሰትም ይዳረጋሉ፣ በዚሁም ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ቁጥር ይበረክታል፤ በጥገኝነትና በሌላ ሰው ጉልበት የሚረዳው ሰው ቁጥር ይበዛል፡፡ ሠርቶ ከሚኖረው ይልቅ በሌላ ላብ የሚኖረው ሰው ቁጥር ሲበዛ ማኅብራዊ ኑሮ ይቃወሳል፣ በዓለማችን እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡፡ ላይኛው እንደታችኛው ሆኖ ሁሉም ለድኅነት ይዳረጋሉ ሥራና የሥራ ውጤት ይቀንሳሉ፡፡

ድኅነት፣ የበዛበት ኅብረሰብ መረጋጋትና ፀጥታ ያጣል፤ ብስጭት ያጠቃዋል፣ መልካም ሥነ ምግባር ይጎድለዋል፣ አለመከባበር ይፈጠራል፣ ተስፋ ይቆርጣል፣ የሌላውን የጎረቤት ሀገር ኅብረተሰብ ሰላም ያውካል፣ ችግረኛ ብቻ ሳይሆን ራሱ ችግሩ በሽታ ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርግና የሚያስደርግም የሰላም እጦት ነው፡፡ የሰላም መገኘት ግን ለእነዚህ ማኅበራዊ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ሰላም ካለ በሁሉም ፊት የደስታ ፈገግታ ይነበባል፣ የሁሉም ፊት የደስታ ፈገግታ ይነበባል፣ የሁሉም ሰው የወደፊት ሕይወት ብሩህ ይሆናል፣ ሰላም ካለ ሰው በሰው ላይ ከሚኖረው ጥርጣሬ ይልቅ እርስ በእርስ መቀራረብን፣ መተማመን፣ መረዳዳትና ለድኅነት ምክንያት የሆነው ሁሉ ለማስወገድ እርስ በእርስ መተጋገዝ እየተስፋፋ ይመጣል፡፡ ሰላም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፡፡ (ገላ. 5÷22)

የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት ልማት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ግለሰባዊ፣ ኅብረተሰባዊና አገራዊ ጠባይ ያለው የሚሳተፍ ለዜጎች ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መንገድ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህም ስለሰላም አስፈላጊነት በሚያስገነዝብ በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ “ሰላምን እሻት እስከ መጨረሻም ተከተሏት” Seek Peace and Pursue it አሁንም መቼም ሰላምን መሻት፣ እስከ መጨረሻውም እርሷን መከተል ለሕልውናችን ብቻ ሳይሆን፤ ለምድራዊና ለሰማያዊ ሕይወታችን መቃናትም ይበጃል፡፡ መዝ. 33÷12-16

የዘመኑ ወጣቶችን ችግር እና ፈተናዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ትውልዱን ለመቅረጽ ችግሮቻቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት መሥራትና የመፍትሔ ሓሳቦችን ማሳየት ግድ ይላል፡፡

በመሆኑም እኛ የዚህ ጉባዔ ተሳታፊዎች ከምናከናውናቸው የሰብአዊ ዕርዳታ ጐን ለጐን ሁሉንም ሥራ ለማከናወን ሰላም ወሳኝ መሆኑን በማወቅ በምንሠራባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰላም የሚያሰፍኑና ግጭቶችን የሚያስወግዱ በጎ ተግባራትን በማከናወን ተግተን መሥራት እንዳለብን ማሳሰብን እወዳለሁ፡፡

ስለዚህ የዛሬውን ስብሰባ በዚህ ረገድ ተቀናጅተን የምንሠራበትና ውጤት የምናስመዘግብበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን ውይይታችንም ልዑል እግዚአብሔር እንዲባርክልን ጸሎታችን ነው፡፡

 

                                                               ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይህን !!!

ከአባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ

 

 

ገጽ

ማውጫ

መቅድም………………………………………………………………   1

መግቢያ……………………………………………………………….   4

ምዕራፍ አንድ  ሥነ ፍጥረት…………………………………..   8

ሀ. የሰው ተፈጥሮ………………………………………………. 10

ለ. የሰው ነፍስ ተፈጥሮ………………………………………… 11

ሐ. እግዚአብሔርና ሥነ ፍጥረቱ………………………………. 11

መ. ዴይዝም……………………………………………………… 18

ምዕራፍ ሁለት ስለ ሕዝብ ብዙኅነት የፈላስፋዎች

አስተያየት……………………………………….. 20

ሀ. የሕዝብን ብዛት አስተሳሰብ……………………………….. 21

ለ. ጥንታዊ (Classical) ዘመን……………………………….. 23

ሐ. ጥንታዊ (Early) የሥልጣኔ ዘመን………………………. 25

ምዕራፍ ሦስት የሥነ ሕዝብን መመጠን ተጽዕኖዎች……….. 46

ምዕራፍ ዐራት ሳይንስና ውጤቱ! ……………………………..  56

ምዕራፍ አምስት የሕዝብ ብዝኀነት እድገት…………………… 81

ምዕራፍ ስድስት ሰውና ላብራቶሪ (DNA) ……………………  93

ሀ. ስለ ሕዝብ ብዙኀነት የቤተ ክርስቲያን መልእክት………. 106

ለ. ረሀብና እርዛት በሽታና ሞት……………………………… 107

ሐ. ችግር ፈጣሪ ራሱ ሰው……………………………………. 108

መ. የችግሩስ መፍትሔ……………………………………….. 110

ምዕራፍ ሰባት የሰው ሥነ ምግባር በፈላስፎች አስተያየት……. 116

ሀ. ሂዶኒዝም…………………………………………………….. 120

ለ. ዩቲሊቴሪያኒዝም……………………………………………… 126

ሐ. ፔርፌክሽኒዝም……………………………………………… 130

መ. ኃጢአትና ተንኮል…………………………………………… 135

ሠ.  ሰውና ጤናው……………………………………………… 153

ረ. ጠንካራ ሕዝብና እውነተኛ እምነት…………………………. 159

ሰ. ዘመናዊ ሰው…………………………………………………. 165

ሸ. ዩቲሊቴሪያኒዝም ……………………………………………. 171

ቀ. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር…………………………………… 178

ምዕራፍ ስምንት ፅንስ ማቋረጥ ቤተ ክርስቲያን አይፈቀድም.. 187

ሀ. የሰው ነፍስ እና ሞት……………………………………….. 203

ለ. ሞት ምንድን ነው??………………………………………… 204

ሐ. የሰው ነፍስና ከሥጋ ጋር መዋሐድ………………………. 206

መ. ሳይንስ እና ሥነ ሕዝብ……………………………………. 209

ምዕራፍ ዘጠኝ የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ሥልጣኔ………….. 219

ሀ.  ሳይንስና ሐኪሞቹ………………………………………… 225

ለ. ስለ ሕክምና አገልግሎት የቤተ ክርስቲያን መልእክት….. 232

ሐ. የቤተ ክርስቲያን መልእክት………………………………. 241

ዋቢ መጻሕፍት……………………………………………………… 245

ከአሁን በፊት በአዘጋጁ የታተሙ መጻሕፍት……………………. 247

መቅድም

መቅድም ማለት መጀመሪያ በቅድሚያ የሚገኝ በር ወይም መግቢያ (መቅድም) ማለት ነው፤ ለቤት በር አለው ለመጽሐፍም መግቢያ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ  ይህ የመጽሐፉ በር ነው፡፡

 • ፍጡር ፈጣሪውን ለማወቅ ባሰበ ጊዜ እንደ መላእክት በአእምሮ ጠባይአዊ አብርሃም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ እንደ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ፊቱን አይቶ ቃል በቃል ተነጋግሮ እንደ ቅዱስ ጳውሎስም በተአምራት ተገልጾለት ተመልሶም በመጽሐፍ አእምሮአዊና በተስፋ አረጋግጦ አምላክ እንደአለ የሚያምኑበት ትምህርት ነው እንጂ እንደ ዕቃ የሚገዙት፣ በእጅ የሚጨበጥ የሚዳሰስ እንደ መብልና መጠጥ የሚቀምሱት እንደ ልብስ የሚለብሱት አይደለም፡፡
 • ሃይማኖት እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ማንኛውንም ነገር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ያስገኘ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ያስገኘ፤ ለእርሱ አስገኝ፤ አሳላፊ፤ አምጭ የሌለው በአንድነት፤ በሦስትነት ያለ፤ ሁሉን ቻይ፤ የማይለወጥ አንድ አምላክ መኖሩን ማመን ነው፡፡

“ሃይማኖት የአምልኮትን ሥርዓት ከእምነትም የተነሣ የሰውን አካሔድ ያጠቃልላል፡፡ የክርስትና ሃይማኖት መሠረት የሰው ምርምር ሳይሆን የእግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ መገለጥ ነው፡፡ ለዚህም መገለጥ ሰው የሚሰጠው ተገቢ የሆነ የአጸፋ ምላሽ ማመንና መታዘዝ ነው”፡፡ 2ኛ ጢሞ. 4÷7፣ ይሁዳ 3÷20፣ 1ኛ ቆሮ. 2÷11፡፡

 • ሃይማኖት፡- አርአያ ፈጣሪ አምሳለ ፈጣሪ የሆነ ሰው ፈጣሪው እግዚአብሔርን የሚያውቅበት መሣሪያ ነው፡፡ “ነአምር ከመ ተፈጥረ ዓለም በቃለ እግዚአብሔር ወአስተርአየ ዘኢያስተርኢ ምንትኒ ዘኮነ እምኀበ ኢሀሎ”፡፡ ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፡፡ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ በእምነት እናውቃለን፡፡ ዕብ. 11÷3
 • ሃይማኖት፡- ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት የጽድቅ መንገድ ነው፡፡ “አስመ እንተ ውስጡ ለሰብእ የኀድር ክርስቶስ በሃይማኖት ውስተ ልብክሙ” በልባችሁ ውስጥ በፍቅር ሥር መሠረታችሁ የጸና ሲሆን ክርስቶስ በሃይማኖት በሰው ውስጥ ያድራልና፡፡ ኤፌ. 3÷17፣ ዘሌ. 26÷12፡፡
 • “ወኢትኩኑ ኑፉቃነ ወኢትሑር ውስተ አርዑተ ቅኔ እለ ኢየአምኑ፡ መኑ ዘያስተዔርያ ለጽድቅ ምስለ ኃጢአት፣ ወመኑ ዘየኀብሮ ለብርሃን ምስለ ጽልመት፡፡ ወመኑ ዘየኀብሮ ለክርስቶስ ምስለ ቤልሆር፣ ወመኑ ዘይከፍሎሙ ለመሃይምናን ምስለ ኑፉቃን፡፡” ትርጉም
 • የእግዚአብሔር ታቦትስ በጣዖት ቤት ውስጥ የሚያኖር ማን ነው? የሕያው እግዚአብሔር ማደርያዎች እኛ አይደለምን? እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረ “እኔ በእነርሱ አድራለሁ በመካከላቸውም እኖራለሁ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል፡፡” 2 ቆሮ. 6÷16
 • ሃይማኖት፡- ሰው ተፈጥሮውንና ምንነቱን የሚረዳበት የሕይወት መመሪያ ነው፡፡ ንግበር ሰብአ በአርያነ ወበአምሳሊነ ዘፍ. 1÷26
 • ሃይማኖት፡- አእምሩ ከመ እግዚአብሔር ውእቱ አምላክነ፡፡ ወውእቱ ፈጠረነ ወአኮ ንሕነ፡፡ ንሕነሰ ሕዝቡ ወአባግዐ መርዔቱ፡፡ እግዚአብሔር እርሱ አምላካችን እንደሆነ ዕወቁ፣ እርሱ ፈጠረን እኛም አይደለም እኛስ ሕዝቡ የመሰማርያውም በጎች ነን፡፡ መዝ. 99÷3

መግቢያ

ይህን ስለ ሕዝብ ብዙኅነት የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ሳይንስ የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፍንበት ምክንያት በተለያዩ ሀገሮች የነበሩ የሥነ ሕዝብ ጸሐፊዎችና ፈላስፋዎች ያደረጉትን የሥነ ሕዝብ አወዛጋቢ ጉዳይ በግልጽ ለማሳየት የነበረውን የፍልስፍና ዘይቤ እና ሃይማኖታውያን ሥርዓቶችን፣ ለወጣቱ ትውልድ ለማሳወቅና የፈላስፎችን አስተሳሰብና አስተያየት በሥነ ሕዝብ ጥናት ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ጸሐፊዎች በር ለመክፈት ነው፡፡

በሀገራችን አከራካሪው የሥነ ሕዝብ ጉዳይ አዲስ ነገር መስሎ ይታይ ይሆናል፡፡ በዘመናችን በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው የጻፉ ሰዎች ባይኖሩም ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስና በሌሎችም ቀኖናዊ የሃይማኖት መጻሕፍት ተጽፎ እናገኛለን፡፡

“ፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜ” የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ የነበረውንና ያለውን የጋብቻ ሁኔታ ሲገልጽ በውስጡ እምነትን፣ ሥርዓትን፣ ግብረ ገብነትን፣ ፍርድንና ሕግጋትን በአጠቃላይ የመንፈሳዊንና ሥጋዊውን አስተዳደርና ሥነ ሥርዓት አጠቃሎ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን “ልጅ ለመውለድ ዘር ለመተካት፣ ለቀደምት ፍጥረታት ብዙ ተባዙ ምድርን ሙሏት ያላቸው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እንረዳለን፡፡ ዘፍ.1÷28 በሐዲስ ኪዳንም አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይተባበራል፡፡ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው ሊለየው አይገባም ይላል፡፡ ማቴ.19÷6 ቅዱስ ጳውሎስ ሚስት የሌላቸው ወንዶችና ባል የሌላቸው ሴቶች እንደኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል፡፡ መታገስ ባይችሉ ግን ያግቡ በፍትወት ፃር ከመቃጠል ማግባት ይሻላል” ይላል፡፡

በሕገ ወንጌል ሥርዓት መሠረት ጋብቻ የሚፈቀደው ለአንድ ወንድ አንዲት ሴት፣ ለአንዲት ሴት አንድ ወንድ ብቻ ነው፡፡ በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር መፋታት አይፈቀድም፡፡

በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት ስለ ሥነ ፍጥረት፣ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አስፋፍቶ ጽፏል፡፡ ከርሱም በኋላ የተነሱ ነቢያት የእሱን ፈለግ በመከተል ጽፈዋል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ሊቃውንት ብዙ በሥነ ሕዝብና ክርስትናን በማንሳት ጉዳዮችን ግልጽ በሆነ ሐተታ ያብራራሉ፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ግን ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ያለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ታስተምራለች፡፡ መፍጠር የቻለ አምላክ መመገብ አይሳነውምና፡፡ 318ቱ ሊቃውንት የጻፉት ፍትሐ ነገሥት የተሰኘው መጽሐፍ ስለ ሥርዓተ ጋብቻ በስፋት ያብራራልና  አንቀጽ 24 ላይ መመልከት ይቻላል፡፡

ለመግቢያ ያህል ስለአገራችን ይህን ካልን፣ የውጭውን ዓለም በተመለከተ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በስዊድን፣ በጀርመንና በአሜሪካ ተነስቶ የነበረውን የሥነ ሕዝብ ፅንሰ ሐሳብ አወዛጋቢ ጉዳይ እንደየሀገሩ አመለካከትና አስተሳሰብ በመጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ተጽፏል፡፡ ለአብነት ያህል አንዳንዶቹን እንመልከት፤

 • ማክ አቨሊ፤ “ሕዝብ እንዲጨምር ከተፈለገ፣ በተፈጥሮ በታደለች ሀገር ላይ የተለያዩ ኢኮኖሚ ግንባታ መመሥረት አለብን፡፡ ሁሉም ነገር በተፈጥሮ የተሟላ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ሕዝብ ብቻውን በድህነትና በበሽታ ያልቃል፡፡ ሃብትና የሕዝብ ብዛት ለአንድ ሀገር መሪ የኃይል ምንጭ ነው፣ መሪው ብልህ ከሆነ በሕዝብ ብዛት ምክንያት የፖለቲካ ችግር አይኖርም” ይላል፡፡
 • በአንፃሩ ሰር ቶማስ ሙር የተባለ፣ “የሕዝብ ችግር ሊፈታ የሚችለው ሀገር በዕቅድ ሲመራ ነው በማለት የዜጎችንም ቤተሰብ መወሰንና መመጠን ይደግፋል፡፡ በዛን ጊዜ አንድ ቤተሰብ ከ16 ያልበለጠ፣ ከ10 ያላነሰ መሆን አለበት” ይላል፡፡
 • ቦርኒትዝ፣ “በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የጀርመን ጸሐፊ፣ የሕዝብ ዕድገት አስፈላጊ ነው፣ አንድ ሀገር እንዲያድግ ከተፈለገ፣ ዜጎች መጨመር አለባቸው፡፡ ያላገቡና ልጅ የሌላቸው ሊቀጡ፣ ብዙ ልጆች ያሏቸው ደግሞ ሊሸለሙ” ይገባል በማለት ጽፏል፡፡

ስለዚህ የሕዝብ እድገት አስፈላጊ ነው የሚል አመለካከት እና የሕዝብ እድገት አስፈላጊ አይደለም ለድህነት ትልቁ ምክንያት ይህ ነው የሚሉ አስተሳሰቦች፣ እንዲሁም ከሕገ እግዚአብሔር መሠረት አንጻር ጽንስን ማስወረድ  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቀኖና  ሲታይ  በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነና እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ነጥቦች አካቷልና በተለይ የሰው ልጅ ሥነ ምግባር በባሕላችንና በእምነታችን አንፃር ሲታይ ይህ ይገባል ይህ አይገባም የሚለውን ሁሉ የጣሰውን አዲሱ የሳይንስ ፈጠራ መጽሐፉን በማንበብ ይጠቀሙበት፡፡

 

መልካም ንባብ

ከአባ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ