Archives

All posts for the month August, 2018

 

“መኑ ይከልአነ ፍቅሮ ለክርስቶስ„ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?
1. መከራ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሃብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሞት ነው። ሮሜ 8፥35

2. “ኢትፍርህዎሙ ለአለ ይቅትሉ ሥጋክሙ”
“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል
የማይቻላቸውን አትፍሩ ፣ ይልቅስ ነፍስንም
ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ„ ማቴ 10፥28
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ስንኖርና የምንቀበለው መከራ ሁሉ ቢበዛ ከሥጋ ያለፈ እንዳልሆነ ነገር ግን በነፍሳችን ላይ ጠላታችንን አንዳች ማድረግ እንደማይችል አረጋግጦልና።
3. ቅዱስ ጴጥሮስም “ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳን መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም ብሏል። 1ጴጥ. 3-14 ከዚም የተነሣ ሰማዕታት ለሥጋቸው ሳይሳሱ “እስም በእንቲ አሁ ይቅትሉነ ኩሎ አሚረ ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሁ።„ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን እያሉ ስለ ክርስቶስ ፍቅር እራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል። ሮሜ 8፥35
ሐዋርያትና አብዛኛው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት ጳጳሳት ሊቃውንት በሰማዕትነት አልፈዋል።
በድንጋይ ተወግረው ተፈተኑ ሞቱ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው በሰማእትነት ሞቱ፣ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፣ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉዳጓድ ተቅበዘበዙ። እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.11፥37
4. ጸርሑ ጻድቃን ወእግዚአብሔር ስምዖሙ። ጢሞ. 3፥11 ጻድቃን ወደ እግዚአብሔር ለመኑ እሱም ልመናቸውን ሰማ ካገኛቸውም መከራ ሁሉ ያድናቸው ዘንድ መልአኩ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ እሳቱን አጠፋው። የሚፍለቀለቀውም ውኃ እንደ በረዶ ቀዘቀዘ። ይህንን ተአምር ከተመለከቱት ብዙዎቹ ኢ አማንያን በክርስቶስ አመኑ። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት
5. “ይትአየነ መልአከ እግዚአብሔር አውዶሙ፤ ለእለ ይፈርህዎ„
ወያድኅኖሙ። የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔር በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል መዝ. 33፥7
6. ቅዱስ ጳውሎስም ሲገልጽው፣ “እነርሱ በእምነት ሁሉንም ድል ነሡ፣
ጽድቅን አደረጉ፣ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ የአናብስትን አፍ ዙጉ የእሳትን ኃይል አጠፉ ከሰይፍ ስልት አመለጡ ከድካማቸው በረቱ
ዕብ.11፥33 ሠለስቱ ደቂቅን፣ ቅዱስ ቂርቆስን፣ እነ ቅዱስ አግናጤዎስ ሐዋርያ ቅዱስ እስጢፋኖስ ማለት መሆኑን ግድ ይላል።
7. “እሰመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአክ„
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስላንተ ያዛቸዋልና እግርህም
በድንጋይ እንዳትሰናክል በእጆቻቸው ያነሡሃል “መዝ. 90፥1
8. “ከመ ይዕቀቡከ በኵሉ ፍናዊክ„
በመንገድ ይጠብቅህ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ
መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም
በርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት። ማቴ.
4፥7
9. “ብዙኅ ሕማሞሙ ለጻድቃን። የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው„ ሐሥ13፥50
የአባቶቻቸውን ርስት አሳልፈን ለባዕድ አንሰጥም በማለት የተገደሉትን መጽሐፍ ቅዱስ ክብር ሰጥቶ መዝግቧቸዋል። እስራኤላዊው ናቡቴ 1ኛ ነገ. 20፥1-15 ስለዚህ ቅዱስት ቤተ ክርስቲያን በሰማያት ያለውን ርስት በሚያሰጥ እምነትን መስክረው መሥዋዕት ለሆኑ ተከታዮቿ የቅዱስት ቤተ ክርስቲያን ሰማእታት ናቸው።
1.0 “ወእምኵሉ ያድኅኖሙ„ እግዚአብሔር እግዚአብሔር ግን ካገኛቸው
መከራ ሁሉ ያድናቸዋል። 2ቆሮ. 1፥5
በዘመነ ሰማዕታት እንደ ወርቅ በእሳት፣ በመከራ ተፈትነው በሃይማኖት ነጥረው ከወጡ ሰማዕታት አንዱ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። የዚህን ሰማዕት ገድልና ታሪክ ከሌሎች ለየት አድርጎ በአስደናቂ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠው የዕድሜው ሁኔታ ነው። ቅዱስ ቂርቆስ የሦስት ዓመት ሕፃን ነበር። ለነገሩ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስም ስማቸውን ከፍ ከፍ አድርጎ የሚያስተጋባው ገድላቸውና የሰማዕትነት ታሪካቸው እንደሚገልጸው ተጋድሎውን የፈጸሙት በሃያ ዓመት የወጣትነት ዕድሜአቸው ነው።
ከእነ ቅዱስ ቂርቆስ ባነስ የዕድሜ ደረጃ ባሉ ሕፃናትም የተፈጸመ ብዙ የምስክርነትና የምስጋና ታሪክ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎዋል።
11. መጥምቁ ዮሐንስ ለልዑል እግዚአብሔር አምልኮትና ስግደት ያቀረበው ገና በእናቱ ማህፀን ሳለ ነው (ሉቃ.1፥40)። እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ ዝማሬና ምስጋና ያቀረቡለት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩት ሕፃናት ነበር። ሆሣእና ለወልደ ዳዊት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመንግሥተ ሰማያት ወራሽነት ምሳሌ አድርጎ ያስተማረባቸው ሕፃናትን ነበር (መዝ. 60፥61-2 ማቴ. 19፥14) እንደ ሕፃና ካልሆናች
12. “ቅሩብ እግዚአብሔር ለየዋሃነ ልብ„ እግዚአብሔር አምላክ ቅን ልቡና እና ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ቅርብ ነው ልመናቸውን፣ ጸሎታቸውን፣ ስዕለታቸውን፣ ፈጥኖ ያሰማል።

ይቆየን

ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ

 

 

 

መግቢያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሺህ ዘመናት ያስቆጠረች ሐዋርያዊትና ጥንታዊት የሃይማሃት ተቋም ናት፡፡ በዚህም መሠረት የክርስትና እምነት እንዲስፋፋ፣ የሕዝቡን ሥነ ምግባር፣ አንድነትና ማንነት በመጠበቅ እንዲሁም ሥልጣኔን በመምራት ጉልህ ስፍራ ነበራት፡፡ ሆኖም ግን ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ጀምሮ ከውስጥም ከውጭም ከባድ ፈተና ደርሶባታል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ዘመናትን ያስቆጠሩ ቢሆኑም አሁን ካለው የዓለማችን ፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ አንጻር ሲታይ ችግሮቹ በጣም የተንሰራፉና የከፉ ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለችግሮቹ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ በበቂ ሁኔታ እየተጠናከረች ነው የሚለው አመለካከት እና መዘናጋት ችግሮች፡ ተባብሰው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለውድቀት እየዳረጓት ይገኛሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በታሪክ፣ በትውልድና በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚያስጠይቀው ውድቀት ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዳን፣ በመቀጠልም ተገቢውን እስትራቴጂና የማስፈጸሚያ ስልት በመንደፍ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን እምቅ ሀብት በመጠቀም ለሀገሪቱና ለዜጎቿ ተጨባጭ መንፈሳዊ እድገትን ማጎናጸፍና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት አስተዋጽኦዎችን በብቃት እንድታበረክት ማድረግ ወቅቱ አበክሮ የሚጠይቀው እጅግ ወሳኝና መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕልውና እየተፈታተነ ያለውን ችግር ለመፍታት ተቀዳሚው ተግባር ችግሩንና የችግሩን ምንጭ በማወቅ መለየት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ጽሑፍ በአሁኑ ሰዓት የሚታዩትን የቤተ ክርስቲያናችንን ዐበይት ችግሮችና መፍትሔውን በአጭሩ ይቃኛል፡፡
1. የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር ዐበይት ችግሮች
ቅዱስ ሲኖዶስ ቁልፍ ተግባራትን በማቀድ የማይመራበት፤ የወሰነውን ውሣኔ ማስፈፀም ያልቻለበትና ክትትልና ግምገማ የማድረግ ልምዱ ዝቅተኛ የሆነበት ነው፡፡
2. በቅዱስ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት በእቅድና ፕሮግራም መሥራት ፈጽሞ የማይታወቅበት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ዓላማ ማስፈጸሚያ ሳይሆን ውጤት ለሌላቸው ተግባራት የሚባክንበት፣ በሙያቸውና በችሎታቸው የተመረጡ አማካሪ ቡድኖች የሌሉበት፤ በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማያውቁ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ግድ የሌላቸው ሰዎች በወሳኝነት የሚንቀሳቀሱበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንን ስልታዊና ዘለቄታዊነት ባለው መልኩ ለመምራት የተዘጋጀ መሠረታዊ የአመራር ስልት የሌለና አካሄዱ በሙሉ በዘፈቀደ ግብታዊና ልማዳዊ የሆነበት ነው፡፡
3. የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ተልዕኮ የክርስቶስን ወንጌል በማስፋፋት የምዕመናንን ክርስቲያናዊ ሕይወት ማጽናትና ያላመኑትን በማሳመን ምዕመናንን ማብዛት መሆኑ እየታወቀ ይህን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያስችል እቅድና ግብ እየተቀመጠ፤ ለዚሁ ተግባር ማስፈጸሚያ ተገቢው በጀት እየተመደበ የሚሠራበት ሁኔታ ባለመኖሩ ምዕመናን ለሌሎች ባዕድ ሃይማኖቶች ቅሰጣ ተጋልጠዋል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ ማስፈጸም በእጅጉ ተዘንግቷል፡፡
4. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የኃላፊዎች ምደባ በሞያ፣ በችሎታ ወይም በብቃት ሳይሆን በዝምድና፣ በሀገር ልጅነት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ሳይሆን ለግለሰቦች ባለው ታማኝነት በመሆኑ፣ ለከፍተኛ የአመራር ችግር፤ ለሀብትና ንብረት ብክነትና ዝርፊያ፤ ለውዝግብና ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ለብልሹ አመራርና አስተዳደር እንደ ጥሩ ማሳያ እየጠቀሰው ይገኛል፡፡
5. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለሁለት የተከፈለበት፤ በአንድነትና በሰላም ከመፈጸም ይልቅ የተከፋፈሉበት፣ ያልተረጋጉበት፣ ብሎም በሁከትና በግጭት ሰላማቸውን ያጡበት ሆኖ ይገኛል፡፡
6. የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ አወቃቀርና አደረጃጀት አሁን ካለንበት ሁኔታ፣ ከአገልግሎቱ ስፋትና ከልማትና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ጋር አብሮ የሚጓዝ ባለመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ወቅቱን በመዋጀት ከጊዜው ጋር እንዳትራመድና ተከታዮቿን በአግባቡ እንዳትጠብቅ አድርጓታል፡፡
7. የወደፊቷ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች የሆኑ አገልጋዮችን የሚያፈሩት የአብነት ት/ቤቶችና የሰንበት ት/ቤቶች አደረጃጀት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት በበቂ በጀትና ብቃት ባለው አመራር የተደራጀና የተደገፈ ባለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚረከቡ አገልጋዮች ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይታይበታል፡፡
8. የረጅም ጊዜ ግባችንንና ራዕያችንን የሚያመለክት ስትራቴጂክ ዕቅድ ባለመኖሩ አሠራሩ ሁሉ በእለት ተእለት ጉዳዮች እንዲሁም ጥቃቅንና ረብ የሌላቸው ተግባራት ላይ ብቻ በማተኮሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ራእይ የሌላት አስመስሏታል፡፡
9. በየዓመቱ ከሚደረገው የሥራ ፕሮግራም ጋር ተገናዝቦ የደመወዝ፣ የሥራ ማስኬጃና የካፒታል (የፕሮጀክቶች) በጀቶች የአዘገጃጀትና የአመዳደብ ሥርዓት ባለመኖሩ በተለይ የካፒታል በጀት የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ያለበቂ ጥናትና ዕቅድ እየተጀመሩ ለከፍተኛ የበጀት እጥረት፣ ለምዝበራና ለውዝግብ ምክንያት ሆነዋል፡፡
10. ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ድርጅቶችና በሐዋርያዊ ተልዕኮ ስም በየደረጃው የሚሰበሰበው ሀብት ያለአግባብ ከዕቅድና ከፕሮግራም ውጭ ጥቅም ለማይሰጡ ተግባራት ይባክናል፡፡ በዚህም የተነሳ ለብዙ አብያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ለካህናት መሰደድ፣ ለምዕመናን መፍለስ ምክንያት ሆኗል፡፡
11. ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶች በማጥናት ተግባራዊ ለማድረግ ያለው አመለካከት እና ፍላጎት ዝቅተኛ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን የችግር ጊዜ መውጫ ጥሪት ከማባከን ውጪ ሌሎች አማራጭ የገቢ ምንጮችን አስፍቶ ማየት አልተቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ በየጊዜው ለሚያጋጥመው የበጀት እጥረት ምላሽ መስጠት እጅግ ፈታኝ ሆኗል፡፡
12. ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት ጠብቃ ያቆየቻቸው ቅርሶችና ንዋያተ ቅድሳት በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘረፉና እየተመዘበሩ ያሉበት ወቅት ሲሆን ለችግሩም የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ተገቢ ትኩረት አልሰጠውም፡፡
13. በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ የሆነ የሀብት አስተዳደር ባለመኖሩ አገልጋዮቿ ገጠሩን እየተው ገቢ ይገኝበታል በሚል ወደ ከተማ እንዲጎርፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም በገጠር የሚገኙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያለአገልጋይና ያለንዋያተ ቅድሳት በማስቀረቱ አብያተ ክርስቲያኗት እንዲዘጉ ሆነዋል፡፡
14. በደቡብ፣ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብና በመሳሰሉት የሀገሪቱ ክፍሎች ቤተ ክርስቲያን ወደ ሕዝቡ አልደረሰችባቸው ቦታዎች ትኩረት በመስጠት ልዩ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መርሐግብር በተጠና ሁኔታ በማካሔድ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የየቦታውን ተወላጆች ከመነሻው ጀምሮ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በማስተማርና በማሰልጠን ለአገልግሎቱ ብቁ የሚያደርግ መሠረታዊ ሥራ አልተሠራም፡፡
15. ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያናችን ረጅም እድሜን ያስቆጠረችና እምቅ አቅም ያላት ቢሆንም በዋናነት በአስተዳደር ችግር ምክንያት በማኅበራዊ አገልግሎትና በኢኮኖሚያዊ ልማት ዘርፍ ያላት አስተዋጽዖ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገሪቱ ካለው አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ አንጻር እጅግ ውሱን ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር ሠራተኛን፣ ገንዘብንና ንብረትን በአግባቡና ዘመኑ በሚጠይቀው የአሠራር ዘይቤ በማቀናጀት የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ዓላማ የሆነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ የሚያስችል ችሎታ ዕውቀትና ልምድ የሚጠይቅ፣ ከፍተኛ አደራና ኃላፊነት ያለባት ቢሆንም ያለው ተጨባጭ እውነታ ግን በዚህ መንገድ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየተሠራ እንዳልሆነ የሚታይ እውነት ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልዕኮ የተደናቀፈበት፤ በማኅበራዊ አገልግሎትና በኢኮኖሚያዊ ልማት አስተዋጽዖ ማድረግ ይቅርና የራሷን አገልጋዮች በአመዛኙ ከችግር ማላቀቅ ያልቻለችበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያናችን በምዕመናን፣ በመንግሥትና በተለያዩ አካላት ያላትን አመኔታና ከበሬታ እያሳጣት ይገኛል፡፡
በመሆኑም በአደጋ ላይ ያለውን አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ወደ መልካም ሁኔታ ለመመለስ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጧን በአስቸኳይ በመፈተሽ ተገቢውን ወቅታዊ የማስተካከያ ሥራ በመሥራት ዘለቄታ ያለው መፍትሔ ለመስጠት መሠረታዊ የሆነ አስተዳደሩን የማስተካከል ውሣኔ በመስጠት በአስቸኳይ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡
ይህንን ውሣኔ ተግባራዊ በማድረግና እምቅ ሀብቷን በመጠቀም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነቷንና ሥርዓቷን፣ ታሪኳንና ቅርሷን መጠበቅና ማስጠበቅ ግዴታ አለብን።
2. ጠቅላይ ጽ/ቤቱን በተመለከተ
ቤተ ክርስቲያኒቱ የቤተ ክህነቱን ጠቅላይ ጽ/ቤት ያደራጀችበት ራሱን የቻለ መዋቅር ቢኖርም መዋቅሩን ሊያሠራ የሚችል እና ቤተ ክርስቲያኒቱንም የሚጠበቅባትን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችል የሰው ኃይል አሰላለፍ እና አሠራር የውለም፡፡
1. በጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃ አብዛኛው የሰው ኃይል፣ ሙያን እና ችሎታን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በዝምድና ወይም በቅርበት የተደረገ ምደባ ነው፡፡ ይህም የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎች ስም ብቻ ተሸክመው ከዓመት ዓመት ከመሸጋገር ውጭ ስያሜያቸውን የሚገልጽም ይሁን የሥራ ዝርዝራቸውን በተግባር እንዳይተገብሩ ደካማ አድርጎ አስቀምጧቸዋል፡፡
2. የተማሩና ቤተ ክርስቲያኒቱን ከጊዜው ጋር እንድትራመድ ሊያግዙ የሚችሉ ባለሙያዎች አለማሳተፍና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ገፍተው ሲመጡ በተለያዩ መንገዶች አማሮ ማባረር ደግሞ ሌላው በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡
3. መምሪያዎች በየዓመቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገት እና ጉድለት ለመገምገም የሚያስችል በዕቅድ እና ሪፖርት ላይ ያተኮረ አሠራር ስለሌላቸው ሥራቸው ሁሉ በልማድና በግብታዊነት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት ከማዳከሙ በተጨማሪ የወደፊት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ለመተለም አስቸጋሪ አድርጎታል፣
4. በስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ክርስትናን ያላወቀውን ሕዝብ ቀርቶ የተጠመቀውን ሕዝብ እንኳን በወንጌል ኮትኩቶ ማሳደግ የሚችል ተግባር አለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን የወላድ መካን እያደረጋት ያለ ጉዳይ ነው፣
5. በማዕከል ደረጃ የሚዘጋጁ በሕዝቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው ወቅታዊ መረጃዎችን የሚያቀርቡ እና የምዕመናንን ጥያቄዎች የሚመልሱ ጠንካራ ሚዲያዎች አለመኖራቸው ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን በሚገባ እንዳያውቋት ሆነዋ፣
6. ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋም በማቋቋም መሪ ብትሆንም የከፈተቻቸው ተቋማት በበቂ የማስፋፋት ሥራ አልተሠራባቸውም፡፡ እንደ ተከታዮቿ ብዛት እና በሀገሪቱ እንዳለ ድህነት ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ረገድ መሪ ፊት አውራሪ መሆን የሚገባት የኛ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ያሏት ከጣት ቁጥር ያነሱ ተቋማት እንኳን የሚሰጡት አገልግሎት በራሱ የማያረካና አሠራሩም ብዙ ሳንካ ያለበት ነው፡፡
7. የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በሰፊው ለችግር መጋለጣቸው በየመንገዱ ሥዕል እና ጃንጥላ ዘርግተው ሳንቲም የሚለምኑ ካህናትን አብዝቶአል፡፡ በዚህም ከለላ በርካታ ሕገወጦች ተግባሩን ገንዘብ እንደመሰብሰቢያ መንገድ እየተጠቀሙበት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ የማታለል ወንጀል እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
8. ወጥ የሆነ የገንዘብ አስተዳደር አለመኖሩ የደመወዝ ክፍያ እንደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ አቅም እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሳ በከተማ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አንጻራዊ ገቢ ከፍተኛ ስለሆነ ድሀ በሆኑ አበብያተ ክርስቲያናት የሚኖሩ አገልጋዮች ገጠሩን እየተው ወደ ከተማ እንዲጎርፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ሁኔታ እያራቆታት ብሎም አገልጋዮቿ ለፍልሰት ዳርጓል፡፡
9. በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባሉ መምሪያዎች በተለይም በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ አስተባባሪነት በየጊዜው ጉባኤዎች ይካሄዳሉ፡፡ በጉባኤዎቹም ላይ ተግባራዊነታቸውን ለማየት የሚያጓጉ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ያላቸው በርካታ ጠቃሚ ውሣኔዎች ይተላለፋሉ፡፡ ሆኖም ውሣኔዎቹ ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊ ሲደረጉ አይታይም፡፡
በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር ከተለያዩ ፈተናዎችና ጥገኝነት ነጻ በማድረግ በገቢዋ ረገድ ራሷን ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ አባቶችም ባለባቸው ኋላፊነት መጠን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራትና ለማስተዳደር ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ አሁነ ያለውን በችግር የተተበተበ አስተዳደር፣ የዘፈቀደ አሠራር እንዲሁም አንድ በአንድ ችግሮችን በመፈተሽ ለማስተካከል ወቅቱ የሚጠይቀውን መፍትሔ ለማምጣት ጊዜው አሁን ነው፡፡
የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ልዑል እግዚአብሔር ኃላፊነቱን በእኛ በአባቶች ትከሻ ላይ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ትውፊቷንና ሃይማኖቷን በጠበቀ መልኩ በአስተዳደሯ ላይ መሠረታዊ የአሠራር ሒደት ለውጥ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለተሻለ ተልዕኮ ማብቃት እግዚአብሔርና ሕዝበ ክርስቲያኑ ከእኛ የሚጠብቁት አስቸኳይ ተግባር ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታት በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት ሁሉ የበኩላቸው ሚና ቢኖራቸውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ወሳኝ አካል ሆኖ ሳለ ይህ ሁሉ ችግር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያለማቋረጥ እንደ ሐምሌ በረዶ ሲወርድባት በቂ የሆነ ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ የመፍትሔ እርምጃ አልወሰደም፡፡ አልፎ አልፎ ለችግሮቹ መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ውሣኔዎችን በተለያዩ ጊዜያት ቢያስተላልፍም የተላለፉ ውሣኔዎችን ተግባራዊነት ተከታትሎ ማስፈጸም አልቻለም፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለምንም ማቋረጥ በችግር ቀጠና ውስጥ እንድትጓዝ ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለሆነም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሁሉ በአንድ መንፈስ ሆነው ቤተ ክርስቲያኒቱን ከወደቀችበት አዘቅት ለማውጣት ጠንክረው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
በተለይም ችግሩ ጣሪያ በነካበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ ነገሮችን በቸልታ መመልከቱን ትቶ አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለውጥና መልካም አስተዳደር ለማምጣት ጉዳዩን በጸሎት ከማሰብ ጋር በትኩረት መከታተል መሥራት ያስፈልጋል፡፡
የአጭር እና መካከለኛ ጊዜ የመፍትሔ ሐሳቦች
ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ባለችበት የአስተዳደር ሁኔታ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፍተኛውን የተጠያቂነት እና ኃላፊነት ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የወደቀው ሸክም የተወሳሰበ እና ጠንካራ አመራር የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሆኖም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በተፈጠረ ክፍተት ምክንያት ችግሮቹን መፍታት ስላልቻሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወርቃማ የሥራ ጊዜ እያመለጣት ነው፡፡ ጉዞዋም ወደ ኋላ ሆኖአል፡፡ አንገብጋቢ እና ፋታ የማይሰጡ ችግሮች በአደባባይ የተገለጡ ሆነው ሳለ ትኩረት እየተሰጣቸው ያሉት ጊዜያዊ በሆኑ መሠረታዊ ችግር የማይፈቱ በግርግር የታጀቡ ተግባሮች ናቸው፡፡ እንዲሁም እንደ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈጻሚ አካል የቤተ ክህነቱ ጠቅላይ ጽ/ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ አልሆነም፡፡ ይህንንም ግልጽ የሚያደርጉ መገለጫዎችን ቀደም ሲል አይተናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትሪቴጂያዊ ፖሊሲና ስልት እየተከተለች መሥራት እንዳልቻለች ነው፡፡ ስለሆነም ይህን የችግር ጅረት ገድቦ ለማቆም ብሎም ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትፈልገውንና የሚጠበቅባትን አገልግሎት ለማበርከት እንድንችል ቀጥሎ ያሉት የመፍትሔ ሀሳቦች ተገቢ ናቸው ብዩ እናምናለን፡፡
የአጭር ጊዜ አስተዳደራዊ መፍትሔዎች
እነዚህ ተግባራት በከፍተኛ ርብርብ ወጥና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ተግባር ላይ ሊውሉ የሚገባቸው ተግባራት ናቸው፡፡ የእነዚህን ተግባራት ዋና ዓላማና ግብ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣንና ኃላፊነት ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት ተፈጻሚ ማድረግ፣
2. ስለዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደሩንና አሠራሩን አሻሽሎ አመራር በመስጠት በኩል መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መንገድ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከችግር ቀጠና ማውጣት ወቅቱ የሚጠይቀው ተልእኮ ነው፡፡
3. ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በአህጉረ ስብከቶች ያሉ አካላት ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ትክክለኛ ስዕልት ማየት እንዲችሉ ማድረግና የሀሳብ ልውውጥና ምክክር አድርገው ሊሠሩ ስለሚገባቸው ሥራዎች ተወያይተው አቅጣጫ እንዲተልሙና በቀጥታ ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ በመቀየስ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ፣
4. በየአጥቢያው ላሉ ካህናት አንደኛ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ፤ ሁለተኛ እስከዛሬ በመደበኛ ሁኔታ እንደትምህርት የማይሰጡ የሕግ፣ የአስተዳደር እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በአጠቃላይ ሊሠሩና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ስልታዊና ዘለቄታዊ ሥራዎች ተከታታይና ጥልቀት ያላቸው ሥልጠናዎችን መስጠት፣
5. በቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊውን መሠረታዊ የአሠራር ሂደት ለውጥ በማድረግ የአስተዳደር ብቃት ያላቸውና የተማሩ ኃላፊዎችን፣ ሥራና ሠራተኞች ለማገናኘት በየዘርፉ መመደብ፣
6. በዘመድና በሙስና የሚፈጸሙ ቅጥሮችንና የተለየዩ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣
7. በቅዱስ ሲኖዶስ የሚያዙ አጀንዳዎችና ውሣኔዎች ላይ ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት እኩል ሥልጣን እንዲኖራቸው እና የውሣኔዎቹን ተግባራዊነት የሚከታተሉበትን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት፣
8. የሕትመት ውጤቶቹ ለምእመናን ተገቢውን ትምህርት የሚያስተላልፉና ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊውን መረጃ የሚሰጡ እንዲሆኑ በመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተዳደር ሥር ማደራጀት፤ እንዲሁም የተጠናከረ የኦዲቶሪያል ሂደቶችን እንዲያልፉ ማድረግ፡፡
9. የንብረት፣ የቤትና የገንዘብ አስተዳደር ሂደቱ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲከናወን ማስቻል፣
10. ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዕከል ያላደረገ አስተዳደር እንዳይኖር አደረጃጀቱን ማስተካከል፡፡
4. በአጭር ጊዜ መተግበር ያለባቸው ሐዋርያዊ አገልግሎትን የሚያጠናክሩ መፍትሔዎች
1. የራሳቸውን እምነት ከማስተማር ይልቅ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በማጥፋትና በማጥላላት በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ የተሰማሩትን ወገኖች ስህተታቸውና ማንነት ታቸውን በመግለጥና በማሳወቅ ምእመናን በሃይማኖታቸው ልበሙሉነት እንዲሰማቸው ማስቻል፣
2. ቤተ ክርስቲያኒቱ እያንዳንዱ ምእመን ዘንድ የሚደርስ መዋቅር ያላት በመሆኑ ካህናት ይህንን መልካም ሁኔታ በመጠቀም የንስሐ ልጆቻቸውን ተግተውና ነቅተው እንዲያስተምሩና እንዲጠብቁ ኃላፊነታቸውን ማሳሰብና ይህንን ለማድረግ እንዲችሉ አቅማቸውን ማሳደግና ማገዝ፣ ለዚህም መጠነ ሰፊ የሆነ የካህናት ሥልጠናዎች በየሀገረ ስብከቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተተለመና ስልታዊ በሆነ መንገድ በማዘጋጀት ስልጠና መስጠት፡፡
3. መሠረታዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችንና በየጊዜው የሚነሱ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ለእያንዳንዱ ምእመን ዘንድ ሊደርስ በሚችል መልኩ በራሪ ጽሑፎችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣
4. የበራሪ ጽሑፎች ዝግጅትና ስርጭት ማዕከል (Tract Centre) በማቋቋም፣ የሚዘጋጁ ጽሑፎችም እያንዳንዱ ምእመን እጅ እንዲደርሱ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፣
5. የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ከጽሑፍ በተጨማሪ በተለያዩ መንገዶች በተለይም በEOTC TV ፕሮግራም በምስልና በድምፅ ለማሰራጨት እንዲቻል ይህንኑ ለመፈጸም የሚያስችል ከዝግጅቱ እስከ ስርጭቱ ያለውን ሥራ የሚሠራና ኃላፊነቱን የሚወስድ አንድ ማዕከል ወይም ክፍል ማቋቋም፣
6. በዚህ ላይ አስቀድሞ የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠትና ከዚህም ቀጥሎ በየአጥቢያው ላሉ ካህናት የመሠረታዊ ትምህርት ኮርስ መስጠት፣ እነዚህ ካህናትም ልጆቻቸውን የማስተማርና የመጠበቅ ተግባራቸውን በተጠናከረና ጥበባዊ በሆነ መንገድ በርትተው እንዲፈጽሙ ማድረግ፣
7. በየሀገረ ስብከቱ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ምእመናን ሃይማኖታቸውን በሚገባ ማወቅ የሚያስችላቸው መሠረታዊ ትምህርቶችን የሚማሩባቸው ተከታታይነት ያላቸው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን ማካሄድ፣
8. በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ላይ ተጽዕኖዎችና ፈተናዎች የበለጠም ጠንከር ያሉባቸውን ቦታዎች ለይቶ በማወቅ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሰፊና ተከታታይነት ያለው ጠንካራ ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረግ፣ በቦታው ላይ በቋንቋቸው ሰባክያነ ወንጌል እንዲኖሩ የሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ፣
9. ከጠረፋማ ቦታዎችና የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ በአካባቢ ቋንቋ የሚሰብኩ መምህራን በጣም ጥቂት በሆኑበት ወይም በሌሉበት ቦታዎች መጠነኛ መነሻ ዕውቀት ያላቸውንና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑትን አሰባስቦ በአዲስ አበባ ወይም በሚያመች አቅራቢያ ለተወሰኑ ወራት ያህል ጥሩ መረዳት ሊፈጥርላቸውና ለማስተማር የሚያስችላቸውን ትምህርት መስጠት፣
10. ለገዳማት አባቶች ግንዛቤ በማስጨበጥና በማወያየት በየአካባቢያቸው ያሉ ምእመናን በማስተማርና በመጠበቅ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ፡፡
5. የመካከለኛ ጊዜ ተግባራት
እነዚህ ተግባራት በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት (ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም) ድረስ የሚፈጸሙ ተግባራት ናቸው፡፡ የእነዚህ ተግባራት ዓላማዎች (ግቦች) የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ምእመናን እምነታቸውን በሚገባ ከማወቃቸው በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ሙሉ ተሳትፎ ያላቸው እንዲሁም ለሌሎች መዳን የሚያስቡና የሚሠሩ እንዲሆኑ ማድረግ፡፡
2. ካህናት ራሳቸውን በዕውቀት ያበለጸጉ፣ በዘመኑ ካለው ሁኔታ አንጻር ምእመናንን እንዴት መጠበቅና መምራት እንዳለባቸው የሚያውቁና በተግባር የሚያውሉ እንዲሆኑ ማድረግ፣
3. ቤተ ክርስቲያን በዘለቄታዊነት ልትደርስባቸው ወደሚገቡ ግቦች ለመጓዝ ልጆቿ በተቀናጀ ሁኔታ የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣
4. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኢኮኖሚያዊ ልማት በኩል ጠንካራ መሠረት ያላቸው አሠራሮችና ተቋማት እንዲኖሯት ማስቻል፡፡ እነዚህን ግቦች ከዳር ለማድረስ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የመፈጸሚያ ስልቶች (ተግባራት) ማከናወን አስፈላጊ ነው፡፡
6. ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎትን በተመለከተ
1. የአብነት ት/ቤቶችን ሥርዓተ ትምህርት ለቤተ ክርስቲያኒቷ ስብከተወንጌል መሠረታዊ በቁዔት ያላቸውን ሰዎች ሊያፈራ በሚችል መልኩ መቅረጽና ተግባራዊ ማድረግ፣
2. የዕጩ ካህናት፣ የካህናትና የሰባክያነ ወንጌል ማሰልጠኛዎችን በየአህጉረ ስብከቱ በአግባቡ በማደራጀት አሁን ላሉትም ሆነ ወደፊት ለሚመጡት አገልጋዮች መሠረታዊና ጠንከር ያለ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ፣
3. በሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ትምህርቶች ወጥና ተከታታይነት ያላቸው እንዲሆኑ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ፣ የማስተማርያ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ፣
4. በየዓመቱ ባሉት የሁለት የክረምት ወራት የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን ሆነው ሊያገለግሉ ለሚችሉ መሠረታዊና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና በማዕከል መስጠት፣
5. ምእመናንን በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለዚህም እርስበራሳቸው የመደጋገፍና የመረዳዳትን ባህል እንዲያዳበሩ ማስገንዘብና ማበረታታት፣ ይህም ለቤተ ክርስቲያንም ጠቃሚና አንድ የአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ማመልከት፣
6. በሀገራችን ቤተ ክርስቲያናችን ሕዝቡን ወዳልደረሰችባቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት ልዩ የስብከተ ወንጌልና የሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት በተጠና ሁኔታ በማካሄድ ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው የየቦታውን ተወላጆች ከመነሻው ጀምሮ ማስተማርና ማሰልጠን፣
7. ቢያንስ በከተማ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት በንግሥ ቀናትና በመሳሰሉት በዓላት ጥላ እያዞሩ መለመንን ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ማድረግ፣
8. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የአገልጋይ ብዛትና ዓይነት በጥናት ላይ ተመስርቶ ወጥ በሆነ ሁኔታ በመወሰን መገደብ፣
9. የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ወደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን በማድረግ ሕዝቡን ማስተማርና ማጥመቅ፣
10. በካሪቢያን አካባቢ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖችን ቢያንስ አንድ ጊዜ በተቀናጀ መርሐ ግብር መጠየቅ፣
11. በአጠቃላይ በሕዝቡ ክርስቲያናዊ የሕይወት ጉዞ ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ቀኖናዊ ጉዳዮችን አስቀድሞ በመለየት አግባብነት ባለው አንድነትን በሚጠብቅ መንገድ መፍትሔ መስጠትና ሕዝቡ የክርስቶስ የማዳን ጥሪ ለሚሰጠው አወንታዊ ምላሽ እንቅፋት እንዳይገጥመውና ሸክም ከብዶት እንዳይቸገር መርዳት ናቸው፡፡

7. የገንዘብ አስተዳደር እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በተመለከተ
ቤተ ክርስቲያኒቱ በገንዘብ አስተዳደር ከመቸውም ጊዜ በከፋ መልኩ የገንዘብ ብክነት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይኸም የሆነበት ምክንያት በዋናነት ቤተ ክርስቲያኒቱ በእቅድና በህግ የማትመራ መሆኑን ያሳያል በዕቅድና በጥናት ያልተመሠረተ ከፍተኛ ምዝበራዎች እየተፈጸሙ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን አስተዳደሯም በቤተ ዘመዳዊ በአካባቢ በጥቅም ስለለትን በመዘርጋት በሚፈጸም አድሎ ለሙስና መጋለጡ እንዲሁም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው ፍላጎት ደካማ በመሆኑ እና ሁል ጊዜም የሚጠበቀው ከታወቁት (ቋሚ ከሆኑት) የገቢ ምንጮች ብቻ በመሆኑ ነው፡፡
ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች ዛሬ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለከፍተኛ የገንዘብ ችግር በመጋለጡዋ በተለያዩ ጊዜያት በስጦታና በስዕለት የገቡ ወርቆች እየተሸጡ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ መፍትሔ ሳይሰጠው ከቀጠለ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሬት ሕንጻዎች ንብረቶች መሸጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ በዚህ እንዲያበቃ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ፤ ብሎም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በመሳተፍ ለሀገሪቱ ልማት አስተዋጽኦ እንዲኖራት የሚከተሉት መፍትሔዎች በአስቸኳይ መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
ሀ. የንዋያተ ቅድሳት ኢንዱስትሪ
ቤተ ክርስቲያ የምትገለገልባቸው ንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ፋብሪካ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መክፈት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ ልብሰ ተክህኖ፣ ጧፍ፣ ሻማ፣ እጣን፣ ወይን (ዘቢብ)፣ መስቀሎች (አርዌ፣ ብርት፣ ጽንሐ) እና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት እንዲመራት ማድረግ ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሱዋን አስተምህሮ የሚያስረዱና ትውፊትዋን የጠበቁ ንዋያተ ቅድሳትን ማምረት ከማስቻሉም በላይ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትዋ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡
ለ. ማተሚያ ቤት
ቤተ ክርስቲያኒቱ በሕትመቱ ኢንዱስትሪ ተሳትፎዋ በዕድሜ ቀዳሚ ብትሆንም ኢንዱስትሪውን አሳድጋ እና አስፋፍታ ጊዜያችን የሚጠይቀው ደረጃ ላይ ማድረስ አልቻለችም፡፡ ስለሆነም በዘመናዊ መልኩ የተቀናጀና በባለሙያ የሚመራ ማተሚያ ቤት ቢኖራት በዚህም ውስጥ ጋዜጦችን፣ መጻሕፍትን፣ የተለያዩ ሰነዶችን፣ የተለያዩ ፖስተሮችን፣ ወዘተ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ከሌላውም ጋር ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚያስችል በጥራት የሚያትም እንዲሆንና ገቢ ሊያስገባ እንዲችል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ በኩል የሚታተሙ ሕትመቶችን በፍጥነት እና በጥራት ማተም ከማስቻሉም በላይ በሀገሪቱ ያለውን የማተሚያ ቤት እጥረት በማቃለል በኩል ቤተ ክርስቲያን የበኩልዋን እንድትወጣ ያደርጋታል፡፡
ሐ. ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት
ዛሬ በሰለጠነው ዓለም ላሉ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች መሠረታቸው የሃይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ በኛ ሀገር ግን በዚህ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዋጽዖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን ከተሠራ በቂ ጊዜ እና ሀብት አለ፡፡ ስለሆነም በነገረ እግዚአብሐር፣ በቀለምና በቴክኒክ ሙያ ሚያሰለጥኑ በተመጣጣኝ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ደረጃቸውን የጠበቁ ኮሌጆችን በመክፈት በሥነ ምግባርና በሙያ የታነጹ ዜጎችን ማፍራት ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጠበቅ ወቅታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እንድትወጣ የሚያደርጋት ተግባር ነው፡፡ በሁሉም አህጉረ ስብከት ያሉ አድባራትና ገዳማትን እንደ ቦታው ሁኔታና ኢኮኖሚ በማጥናት የአደኛ ደረጃ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች መሥራት ግድ ይላል በአለንበት ክፍል ዘመን ትውልዱን የምናገኝበትና የምንቀርጽበት ብቻ አማራጭ ነው።
መ. የጤና ተቋማት
በጤናው ረገድ ከከፍተኛ ሪፈራል ሆስፒታሎች እስከ ክሊኒክ በመክፈት ኅብረተሰቡን ከማገልገል በተጨማሪ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ በተያዥነትም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና አቅም የሌላቸውም በነጻ ሕክምና እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

ሠ. የሕትመት ውጤቶች
ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷን ፍልስፍናና የሊቃውንቶቿ ውጤት የሆኑ ትምህርቶቿን በማሳተም ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ግለሰቦች ከቁጥር በላይ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በዘረፈ በኪሣራ እየተንቀሰች ትገኛለች፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ አሳታሚ ድርጅት ቢኖርም በሚፈለገው መጠንና ጥራት ማሳተም ባለመቻሉ ለሊቃውንትና የምእመናንን ፍላጎት ማርካት አልቻለም፡፡ የሕትመት ሚዲያዎቹም ቢሆኑ ማስተማሪያ ሳይሆኑ መሳደቢያና የግለ ሰዎችን ዝና ብቻ የሚያወሩ በመሆናቸው በአንባቢውና በኅትመት ዓለም ተቀባይነታቸው ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ በገበያም አይፈለጉም፡፡ ይህም የሆነው የተቀላጠፈና ማዕከላዊነቱን የጠበቀ አፈጻጸም ባለመኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱንና አሠራሩን አስተካክሎ የተለያዩ የሕትመት ውጤቶችን በጥንቃቄ ለሕጻናት፣ ለወጣቶች፣ ለአረጋውያን በተለያዩ ቋንቋዎች ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ቢታተሙ የስብከተ ወንጌል አድማስ ይሰፋል፡፡ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገቢ በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ይቻላል፡፡
ረ. ግብርና እና መሬት አስተዳደር
የሀገራችን የገቢ ምንጭ በከፍተኛ ደረጃ የተመሠረተው በግብርና ነው፡፡ ይኸውም 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝባችን የሚተዳደርው በግብርና ስለሆነ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን በግብርና ላይ የተመሠረተ መጠነ ሰፊ የልማት ዘመቻ ሥራ ለማጠናከር ቤተ ክርስቲያኒቱ በየአህጉረ ስብከቱ ባሏት መሬቶች ላይ ወይም ለዚሁ ሥራ መሬት በመቀበል የግብርና ሥራ መሥራት አለባት፡፡ የግብርና ምርት ሽያጩንም ለሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በገበያ ላይ ማቅረብ ይጠበቅባታል፡፡ ይህም የካህናቷን ገቢ ማሳደግና ለሀገሪቱ ትርጉም ያለው የልማት አስተዋጽዖ ከማበርከተ አንጻር ትክክለኛ አቅጣጫን መንደፍ ያስችላታል፡፡

ሰ. የቤቶች አስተዳደር
ቤተ ክርስቲያናችን ከቁጥር በላይ የሆኑ የኪራይ ቤቶች አሏት፡፡ ነገር ግን ቤቶቹ በብልሹ አሠራር የተነሳ የተፈለገውን ያህል ገቢ እያስገኙ አይደለም፡፡ እንዲሁም ሆኖ የሚሰበሰበው ገቢ ዝቅተኛ አይደለም፡፡ ይህን የበለጠ ለማጠናከር፡-
1. ወቅቱን ያማከለ የኪራይ አከፋፈል እንዲኖረው በማድረግ ገቢውን ማሳደግ፣
2. አዳዲስ ቤቶችን ባሉን የከተማ መሬቶች ላይ እንደየቦታዎቹ አቀማመጥና ሁኔታ የተለያዩ ሕንጻዎችን በማስገንባት ማከራየትና በሪል እስቴት ኢንዱስትሪ ተሳታፊ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡
ሸ. ቱሪዝም
ቤተ ክርስቲያኒቱ የዘረፋ ብዙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ባለሀብት ስትሆን በዘርፉ ያላት ጥቅም ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘርፍ አስጎብኚ ተቋማት በመክፈት እና በማስጎብኘት ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ እንዲሁም በቱሪዝም ቦታዎች ላይ ለጎብኚዎች አስፈላጊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመክፈት በሀገሪቱ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አወንታዊ ሚና መጫወት አላስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያኒቱ ስር እንደመሆናቸው ከዘርፉ መንግሥት ከሚያገኘው ገቢ የባለቤትነት ገቢ እንድታገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ
አዲስ አበባ