መነኮሳት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አመ ፲ ለወርኃ መጋቢት ፳፻፱ ዓ.ም በዛቲ ዕለት አዕረፈ አባ ገብረ ሥላሴ ወልዱ ለሳሙኤል ዘዋልድባ

በዚችም ዕለት የዋልድባው ታላቁ አባት መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ (አባነጮ) በእረፍተ ሥጋ ከዚህ ዓለም ተለዩ፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ ከአባታቸው ከአቶ ገብረ ሕይወት ዐባይ ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተ ዮሐንስ በ1915 ዓ.ም በዋግ ሕምራ ልዩ ስሙ ሰላምዬማርያም በተባለ ቦታ ተወለዱ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ጊዜ በተወለዱበት ደብር ከመ/ም መ/ጌታ ኃ/ማርያም ከፊደል እስከ ንባብ ከተማሩ በኋላ ለትምህርት ፍለጋ በተለያዩ ጉባኤ ቤቶች ተዘዋውረው አቋቋም፣ ቅዳሴ፣ መጽሐፈ ሐዲሳት ትርጓሜን  ተምረዋል፡፡

ክህነትን በተመለከተ ዲቁና ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ማጨው ቅስና  ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ጐንደር ተቀብለዋል፡፡

እኒህ አባት ከትምህርት ቤት በኋላ በምናኔ ወደ ታላቁ ዋልድባ ገዳም በ1930 ዓ.ም ገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ  በገዳሙ ማኅበር ምርጫ በረድእነት እንዲያገለግሉ ተመድበው የገዳሙን ሕይወት ምናኔ ሀ ብለው ጀመሩት፡፡ አንድ ሰው ኅሊናውን ለምናኔ አነሣሥቶ ወደ ገዳም በሚገባበት ወቅት የሚያጋጥሙት ፈተናዎች እጅግ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓለማችን እንደ ገዳም ያለ ፈተና የሚበዛበት ቦታ የትም የለም፡፡ ሰብአዊ፤ዓለማዊና ሰይጣናዊ ፈተናዎች በሙሉ ተሰባስበው የሚገኙት በገዳም ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙኅ ሕማሞሙ ለጻድቃን ማለት የጻድቃን መከራቸውና ፈተናቸው ብዙ ነው በተባለው መሠረት፣ በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በምናኔ ወደ ገዳም በገቡ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፈተና የበለጠ ክብደት አለውና፡፡

ገዳማውያን አበው መነኰሳት እና እማት መነኮሳይያት በገዳማዊ ሕይወታቸው የሚዋጉት ከዚህ ዓለም ካለው ከሚታየው፣ ከሚጨበጠው፤ ከሚዳሰሰውና ከሚሰማው ፈተና ብቻ ሳይሆን ከማይታዩ፤ ከማይዳሰሱ፤ ከማይጨበጡ ረቂቃን አጋንንት  ጋርም ከመዋጋት አቋርጠው አያውቁም፡፡ ውጊያውም እስከ ዕለተ እረፍተ ሥጋ ድረስ የሚያቆም ውጊያ አይደለም፡፡ ስለዚህ በገዳም በመናንያን ላይ የሚደርሰው ፈተና ስፍር ቁጥር መጠን የለውም፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በገዳማዊ ሕይወት የሥራን ክቡርነት መረዳት፤ የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙ መታገስን፣ ሲታዘዙ ያለማጉረምረምና ያለመታከት የታዘዙትን መፈጸም፣ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ስግደትን፣ ሕርመትን (ጾምን) መለማመድና ገንዘብ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ገዳም የትጉሃን መናኸሪያ እንጂ የሰነፎች መኖሪያ፣ መጦሪያ ወይም መደበቂያ አይደለምና፡፡

ገዳማዊው መነኩሴ መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ በገዳማቸው ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሲመደቡ ማለትም አትክልትን መትከል፣ መኮትኮትና ውኃ ማጠጣትን፣ እርሻ ማረስን ሌሎችንም አስፈላጊና ተገቢ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን፣ በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መሰሎቻቸው ገዳማውያን መነኮሳት ጋር  በመስማማትና ማንኛውንም ዓለማዊና ሥጋዊ ፈቃድን በማስወገድ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጸንቶ በማገልገል መንፈሳዊና ገዳማዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ይህም ተግባራቸውና አገልግሎታቸው ደግሞ የአንድ ገዳማዊ መናኝ ጠባይ፣ ችሎታ፣ ፍቅረ ቢጽነት የሚመዘንበት የምናኔ መስፈርት ነው፡፡ ልክ እንደ አባ ዮሐንስ ሐፂር ትዕግስትን መላበስ ይጠበቅባቸዋልና፡፡

አባ አሞይ የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማ እስክታፈራ ድረስ ውኃ እንዲያጠጣት ለአባ ዮሐንስ አዘዘው አባ ዮሐንስም ያለማጉረምረም በትሕትና በመቲረ ፈቃድ ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ ተሸክሞ እያመላለሰ ያጠጣ ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመት ያች እንጨት ለምልማ አብባ ያማረ ፍሬ አፈራች፡፡

አባ አሞይም በዮሐንስ ታዛዥነት እጅግ ተደሰተ፡፡ ፍሬውን ለቅሞ ለገዳሙ ማኅበር እንካችሁ ይህ የታዛዥነት ፍሬ ነው እያለ ሰጣቸው፡፡ ዮሐንስም በልቡናው ዘወትር እግዚአብሔርን ያስብ ነበር፡፡ ለአንድ ደቂቃ እንኳን ፈጣሪን ከማሰብ አቋርጦ አያውቅም መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባ ነጮ)

በረድእነት ለረጅም ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በገዳሙ ሕግና ሥርዓት በ1947 ዓ.ም ሥርዓተ ምንኩስናን ከመ/ም አባ ተክለገሪማ ተቀብለዋል፡፡ በመቀጠል ማኅበሩ በመደባቸው ማንኛውም የአገልግሎት ሥራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቀዳማዊ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋ፡፡ በተለይ በመምህርነት ገዳሙን ለማስተዳደር የገዳሙ ማኅበር መርጧቸው የገዳሙ አበምኔት መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ገብረ ማርያም (አባነጮ) የዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ አቡነ ጣዕመ ክርስቶስ ገዳም መምህር በመሆን ለረጅም ዘመናት አገልግለዋል፡፡ መምህርነቱን ከለቀቁ በኋላ ለ35 ዓመታት በአብረንታንት ገዳም ተወስነው (በሕርመት) እህል ሳይበሉ ቋርፍ ብቻ በቀን አንድ ጊዜ በመመገብ በጸሎትና በስግደት በተባሕትዎ ነበሩ፡፡ በጠቅላላ በዋልድባ ገዳም ለ71 ዓመታት ኑረዋል፡፡

ሀ. መምህር ወባሕታዊ አባ ገብረ ሥላሴ (አባ ነጮ) ሁሉንም የመነኑ (የናቁ) መንፈሳዊ አባት!!

የዋልድባ ገዳም ገጸ ምድር በሰሜን በኩል የተከዜን ወንዝ በምሥራቅ በኩል የእንስያን ወንዝ በደቡብ በኩል የወይባ ወንዝ በምዕራብ በኩል የዛሬማን ወንዝ የሚያካልሉት ታላቁ የዋልድባ ገዳም በአራት ወንዞቹም በሚገናኙበት የተከበበ ቦታ ተሻግሮ በግርማ ሞገስ የታጀበው በደን ጥቅጥቅ ያለ ቦታ በብዛት የተለያዩ የበረሃ አራዊትና የተለያዩ አዕዋፍ የሚኖሩበት በተለይ የነብሩ ድምፅ ወደ ማታ አካባቢ ለወጣኒ መናኝ እንቅልፍም አያስተኛ፡፡ ከዚህ ጋር የዝንጀሮ አብሮ እየተቀባበሉ በጉሩፕ መጮሕ ምንድነው በዚህ በረሃ (ገዳም) የተፈጠረው ያስብላል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ርጭና ጸጥ ይልና ትንሽ ቆይቶ በአንጻሩ የአባቶች የባሕታውያን ጸሎትና ስግደት የመቁጠርያ ድምፅ ልክ እንደሚጓዝም ንብ ይሰማል፡፡ ያለህበት ቦታ ምንኛ ቅዱስ መሆኑን ሕሊናህ በሙሉ ይሠበራል እኔ ማነኝ የት ነው ያለሁት ከምድር ወይስ ሀገረ ብፁዓን፣ሀገረ መላእክት ያስብላል፡፡ በተለይ በታላቁ አብረንታንት ገዳም ሥራቸውን ምስጋና ብቻ ያደረጉ የምድራችን መላእክት ከአለባበሳቸው እስከ አነጋገራቸው በተባሕትዎ እስከፍጹምነት የደረሱ የዚህን ዓለም ጣጣ ውጣ ውረድ የማያውቁ ከምድራዊ ምኞት ነፃ የሆኑ የዓለም ኅብረተሰብ በተለያየ ምኞት እርስ በራሱ በሚናቆርበትና በሚጠፋፋበት በተለይ በአሁኑ ጊዜ ግማሹ በሃሣብ ግማሹ በተግባር ታላላቅ ምድሪዊ ተስፋዎች አሉን በሚል ምኞት እነኝህ ሐሳቦች ፍላጐቶች ሁሉ ለማግኘት በውኑም በሕልሙም በሚለይበት በአሁኑ ዘመን፡፡

ነገር ግን እንዲህ ያለ ከንቱ ምኞት ዓለም በአንተ እንጂ አንተ በዓለም እየኖርክ አይደለህም እነዚህ ሥጋዊ ተስፋዎችና ፍላጎቶች ስኬታማ ስለማይሆኑ ግራ ትጋባለህ በስሜት ህዋሳትህ ለብዙ ጊዜ ትመራለህ መንፈስህ እነዚህን ስሜቶችህን በተቃወመች ጊዜ እጅግ ትቃወማለህ ከዚህ አይነቱ ተጽእኖ መቸ ትላቀቅ ይሆን? በዓይንህ ያየኸውን በጆሮህ የሰማኸውንና በእጅህ የዳሰስከውን ብቻ ታምናለህ በዓይን ካላየህ በጆሮ ካልሰማህ ሁሉንም ነገር ትጠራጠራለህ ለጥርጣሬህ ምክንያት ምን ይሆን? ለዚህ መንሥኤው በሥጋዊ ፍላጐት መኖርና በስሜትህ መመራትህ ነው ማንም እንዳያይህና እንዳይናገርብህ ስምህ እንዳይነሣ አጸያፊ ነገሮችን በድብቅ ትፈጽማለህ፡፡ ነገር ግን ሰው ሆይ ማንም እንዳላየህ ታስብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሐናንያንና የሰጲራን ሸፍጥና ክህደት ማየት በቂ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መዋሸት አይገባምና፡፡ የሐ. ሥራ 5÷1፡፡

አበው  እንደ መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ አባ (አባነጮ) የመሰሉ እግዚአብሔርን የሚያፈቅሩ ሁሉንም የመነኑ ሕጉንና ትእዛዙን አክብረው በንጽሕና ተጠብቀው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር የማትታይ፤ የማትለወጥ፤ የማትሞት፤ የማትሻር፤የማታልፍ ዘለዓለማዊ ኃይል አምላክ እያሉ ያለማቋረጥ እድሜ ዘመናቸውን በሙሉ ሲያመሰግኑት ኑረዋል፡፡ ለወደፊቱም እንዲሁ እያመሰገኑትና እያመለኩት ይኖራሉ፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምሥጢርን የሚያውቁ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙ ባሕታዊ ፈቃደ ሥጋን በፍጹም ልቡና በቁርጥ ሕሊና ቆርጦ በመጣል የታወቁ አበው ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ጻድቃንሰ ዔሉ ገዳማተ ወበዘብድወ ጠሊ ወበሐሜለት ጻድቃን ሁሉን እያጡ የበግና የፍየል ለምድ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በከርሰ ምድር ተቅበዘበዙ ዕብ. 11÷31-38

እኒህ ባሕታዊና ገዳማዊ አባት ሕይወታቸውን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጡ የሕይወት ዘመናቸውን ሁሉ ከእግዚአብሔርን በማገልገል አሳልፈዋል፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባነጮ) አገልግሎት ከሁሉም በላይ የሚወዱ የሚመክሩ ትዕግስትን ገንዘብ ያደረጉ አባት ነበሩ፡፡ አንድ መነኩሴ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዳሴ ጊዜ በጸአድወ አልባስ ከወትሮ ለየት ያለ መልክ ያላቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያስተናብሩ በተመስጦ አያቸው፡፡እጅግ በመገረምና በዝምታ በመመልከት ከቅዳሴ በኋላ ዛሬ ምንድነው ምክንያቱ ሕገ አበው ፈረሰ እንዴ! እንዴት ነጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ ብለው ጠየቁ፡፡ በገዳሙ ሕግ (ብጫ) ወይም ወይባ ብቻ ነው መልበስ የሚፈቀደው መ/ር አባ ገ/ሥላሴ ለመነኩሴው ሲሏቸው አባ ዝም ይበሉ ብለው ለብቻ ወስደው እርስዎ እግዚአብሔር ያደለዎት ምሥጢሩን የገለጸልዎት ትልቅ አባት ነዎት፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ያዩአቸው ሰዎች አይደሉም መላእክት ናቸው፡፡ ስለዚህ ለማንም እንዳይናገሩ ብለው መክረዋቸዋል፡፡ አባቶች በሰው ልቡና ገብተው ምን እንዳሰብክ ምን እንደሠራህና እንዳጋጠመህ ያውቃሉ፡፡ ልክ ዳዊት በኢዮብ፣ ኢዮብ በዳዊት ልብ፣ ሳኦል በአበኔር፣ አበኔር በሳኦል ልቡና ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያና ሲጲራ ምን እንዳደረጉ እንዳወቁ አበውም በሰው ልቡና ያለውን ሁሉ ያውቃሉ፡፡

ከዚህ በኋላ እኚህ አባት በጸሎት በአታቸው ሆነው አምላካቸውን በማመስገን እንዲወሰኑና ለዚህ እጅግ ጥልቅ ስለሆነው ስለ መንፈሳዊ ማዕረግ ልገልጽልዎት እፈልጋለሁ አሏቸው እና አባም እሺ አሏቸው፡፡ እየውልዎት የባሕታውየን የመጀመሪያው ማዕረግ በአራቱም አቅጣጫ መርሳት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአካባቢህ ስላሉ ሁሉም ነገሮች ምንም ሳትጨነቅ በበአትህ በጸሎትም ሆነኸ በተመስጦ መሆን አለብህ፡፡ ከዚያ ከተፈጥሮ ሕግ በላይ በሚሆን በሌላ ዓለም ትኖራለህ ከዚያ የት እንዳለህ እንኳን በቤት ውስጥ ይሁን በውጭ መሆንህ የምታውቀው ነገር አይኖርም፡፡ ያየኸውንም ተአምር ሁሉ ከእግዚአብሔር የሆነውን ለማንም አትናገር፡፡ ወደ ሀገረ ብፁዓን ብትነጠቅ ወይም ወደ ሰማይ ብትወሰድ እንኳ ምንም የምትለው ነገር የለም፡፡ “እንዲህ አይነቱን ጸጋ ለማግኘት ማንም ራሱን አያታልል፡፡ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን”፡፡ 1ኛ ቆሮ. 3÷18

ሦስቱ አሥራው ካሥሩ አሥራው ጋር የሚሠወሩበት የተክል ቦታ አለ፡፡ ልክ እንደኗ ዋልድባ ገዳም (ሐተታ) በምሥራቅ በኩል ያለ የተክል ቦታ ሌሊት ካደረበት ውርጭ የጧት ሙቀት ያገኛል ቀን ከዋለበት ሐሩር የማታ ጠል ያበርደዋል እንዲህ ሁኖ ሰባት ነገር ያስገኛል፡፡ ቅጠል፣ ልምላሜ፣ ጽጌ፣ ፍሬ፣ ጣዕም፣ መዓዛ፣ ነፍስ ያስገኛል፡፡ እንደ ሙቀት፣ እንደጠል ረድኤት እንደ ውርጭ፣ እንደ ሐሩር መከራ እንደ ተክል የባሕታዊ ሰውነት፣ እንደ ምድሩ ልቡና ነው፡፡ እንደዚህም ሁሉ ባሕታዊ በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቆ የኖረ እንደሆነ ሰባት ሀብታትን ከእግዚአብሔር ያገኛል፡፡ እንደ ቅጠል ሃይማኖት እንደ ልምላሜ አእምሮ እንደጽጌ ትሩፋት፣ እንደ ፍሬ ፍሬ ክብር እንደ ጣዕም ጣዕመ ጸጋ፣ እንደ መዓዛ መዓዛ ጸጋ እንደ ሥጋ ብርሃን ያስገኛልና “ወይስቅዮም”፣ ዐራቱን ባሕርያተ ሥጋ ካምስቱ ሕዋሳተ ነፍስ ጋራ ያከብራቸዋል፡፡ ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ካሥሩ ማዕርጋት ጋራ ይሰጣታሉ፡፡ በፍቅረ ቢጽ በፍቅረ መላእክት በፍቅረ እግዚአብሔር ልብ ከክብር ወደ ሚበልጥ ክብር ይመራል፡፡ ፍቅረ ቢጽ መከራ ይቀበላል፡፡ በፍቅረ መላእክት ወደ ጸጋ ይመራል፡፡ በፍቅረ እግዚአብሔር ለሚያድርበት የአምላክ የክብሩ መገለጫ ለመሆን በፍጹም ክብር ይከብራል፡፡ አንድም ግዙፋንን ረቂቃንን በማየት ልቡና ከክብር ወደሚበልጥ ክብር ይመራል፡፡ ግዙፋኑን በሚያይበት ጊዜ መከራ ይቀበላል ረቂቃኑን የእግዚአብሔር ክብር በሚያይበት ጊዜ ወደ ክብር ይመራል በፍጹም ክብር ይከብራል መ/ም አባ ገ/ሥላሴ ለወጣንያን መነኮሳትና አርድእት ሲመክሩ ፍጹም መሆን ትፈልጋለህ ነፍስህ ከእስር ተፈትታ ነጻነት ወዳለበት ቦታ እንድትሄድ ትፈልጋለህ? ከሁሉ በፊት ከዓለማዊ ምኞት፣ ከዓለማዊ ፍትወት ራቅ፣ ከፍቅረ ንዋይ ራቅ፣ ከስሜትህ ተጽእኖና ዓለም በውስጧ ከሳለችብህ ነገር ሁሉ ራቅ፡፡ በመጀመሪያ  በእግዚአብሔር ፊት ራስህን እንደ ትንሽ ሰው አድርገህ አቅርብ ብለው ይመክራሉ፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ በዋልድባ ገዳም ማንኛውም በገዳሙ የአርድዕትነት ሥራ ያልሠሩት ነገር የለም፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ በትህትና፤ በመቲረ ፈቃድ፤ በፍቅር፤ በመታዘዝ በተመደቡበት ኃላፊነት ሁሉ አሉ የሚባሉ ሥራዎችን በሙሉ ሠርተዋል፡፡ ማኅበሩ ለታላቅ መዓርግ ሲመርጣቸው እኔ ለዚሁ ታላቅ ገዳም ማኅበር በአበ ምኔትነት መምራት አይገባኝም፡፡ በሁሉም ነገር ከኔ የተሻሉ እነ እገሌ እያሉ አይሆንም ብለው በሌሊት ተነሥተው ወደ በረሃማው የገዳሙ ሌላው ገጽታ ገብተው በዋሻ ውስጥ ለመፍለስ ወሰኑ፡፡ ከወሰኑም በኋላ ወደ ዋሻው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን ጥሪው የእግዚአብሔር ስለሆነ የተወሰነ ደቂቃ ከተጓዙ በኋላ ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ በጣም የሚያስፈራ ከውፍረቱም ከርዝመቱም በጣም ትልቅ ዘንዶ መንገዱን ዘግቶ አላሳልፍ አላቸው፡፡ በወዲህ ቢሉ በወድያ እያሉ ለማለፍ ቢጥሩም እያለፈ መንገዱን በመዝጋት ከለከላቸው፡፡ አይ ይህ ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ስላልሆነ ነው ብለው ወደ ማኅበር ተመለሱ፡፡  ዘንዶም ሸኝቷቸው ተሰወረ፡፡ አበው በሁሉም ነገር በትሕትና እኔ አንሳለሁ፤ ከኔ እነ እገሌ ይሻላሉ፤  ለሥራው የበለጠ ውጤት ያስገኛሉ፤እነሱን ለምናችሁ ሹሙ በማለት  ከልብ በመነጨ ቀና አስተሳሰብ ምነናዊ ሕይወት ልሾም፣ ልታይ ልታይ የሚያሰኝ ፆር ጠፍቶላቸው የእግዚአብሔርን ሕግ በመጠበቅ ወደ ፍጹምነት መዓርጋት ይደርሳሉ፡፡ መንፈሳዊውና ባሕታዊ አርበኛ አባ ገብረ ሥላሴ(አባ ነጮ) ምርጫው የገዳሙ ማኅበርም የእግዚአብሔርም ስለሆነ በጸጋ የተቀበሉት በ1970 ዓ.ም ነበር፡፡

ለ. የስም ባሕታዊነት አያጸድቅም!!

በዋልድባ ገዳም በአንድ ወቅት አንድ የስም ባሕታዊ ፀጉሩን አስረዝሞ (ቀራንዮ) የብረት መስቀል ተሸክሞ ከከተማ ወደ ዋልድባ ገዳም የመጋቢት መድኃኔዓለም የዓመቱን ክብረ በዓል ለማክበር ይመጣል፡፡ ዋናው ቦታ ላይ አብረንታንት ከመድረሱ በፊት አውቆ ሠራ የምትባል የአትክልት ቦታ ደረሰ እና በገዳሙ ሕግ እግሩን አጥበው ቋርፍ ሰጥተው በእንግዳ ማረፍያ ቤት እደር አሉት፡፡ እንግዳው የተኛበት ቤት ከታች የአንድ ባሕታዊ መኝታ ቤት ሆኖ ከላይ ፎቅ ነገር ነው፡፡ እንግዳው ከተኛበት በእንቅልፍ ሰዓት ማለትም ሌሊት ሰውየው ይሰግዳል እንዲባል ተንጋልሎ ተኝቶ በእግሩ ቤቱን ይመታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግራ የገባቸው ከታች ያሉት ባሕታዊ ተነሥተው ቀስ ብለው ሲያዩት ሰውየው ተኝቶ እግሩን ብቻ እያወራጨ የተኛበትን መሬት ሲደበድብ ባሕታዊ አዩት፡፡ እኒህ አባት አባ ገ/ማርያም አውቆ ሠራ ይባላሉ፡፡ የአትክልት ቦታ ኃላፊው ናቸው፡፡ ዱላቸውን ይዘው ተነሱ፡፡ የሰውየውን ትክክለኛ ማንነቱን ስለ ደረሱበት አንተ አስመሳይ ሂድ ውጣ እንደ አንተ አይነቱ በአባ እንጦንስና መቃርስ ቆብ የሚቀልድ ወስላታና ውሸታም እዚህ አያድርም ብለው በሌሊት አስወጥተው አባረሩት፡፡

ለምን ቢባል በሰዎች ዘንድ ትልቅ መስሎ መታየት እውነተኛ ሳይሆኑ በሰው ዘንድ እውነተኛ ባሕታዊ መስሎ መታየት በእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ነው (ደካማና ኃጢአተኛ ከሰው ሁሉ የበታች እንደሆንክ ብታስብ ለአንተ መልካም ነው) ዋጋህን ታገኛለህና ዋጋህን የሚከፍልህ ሰው ሳይሆን ራሱ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማንኛውም መልካም ስጦታ ማንኛውም ፍጹም በረከት ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ያዕ. 1÷17፡፡

ከዕለታት አንድ ቀንም አንድ ባሕታዊ የጠለቀ ትምህርት የሌለው ሂዶ ብቻውን ከበረሃ በገዳሙ በአንዱ ክፍል በዋሻ ዘግቶ እየጸለየ እየሰገደ ተቀመጠ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ሰይጣን መጥቶ ምነው ከዚህ እልም ካለ በረሃ ብቻህን አለው? ባሕታዊው ሲመልስም እጸድቅ ብዬ ነው አለው፡፡ ሰይጣኑ ዝም ብሎት ሄደ እንደገና በሌላ ጊዜ መጥቶ ምነው አባ ብቻህን ከዚህ በረሃ አለው? ባሕታዊው ክርስቶስን ባገኘው ብዬ ነው አለው ያው ሰይጣኑ ያሁኑ ይባስ ብሎት ትቶት ሄደ፡፡ በሌላ ጊዜ አባ መቃርስ የሚባል አባት ወደባሕታዊው ሄደና የተደረገው ሁሉ ስለተገለጸለት ካንተ ዘንድ ሰው አልመጣም ብሎ ጠየቀው፡፡ አልመጣም አለው፡፡ አባ መቃርስም የእውነቱን ንገረኝ አለው፡፡ አወ መጥቶ ነበር አለው፡፡ ምን አለህ? አለው፡፡ ብቻህን ከዚህ በረሃ ለምን ተቀምጠሃል አለኝ፡፡ እጸድቅ ብዬ አልኩት፡፡ ዝም ብሎኝ ሄደ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ መጣ፡፡ ምነው ብቻህን አለኝ፡፡ ክርስቶስን ባገኝ ብዬ አልኩት፡፡ ያሁኑ ይባስ ብሎኝ ትቶኝ ሄደ አለው፡፡ አዬ ምነው እንዲህ ማለትህ የምትጸድቅና ክርስቶስን የምታገኝ አንተ ብቻ ነህ በዓለም ያሉ ሁሉ ክርስቶስን የሚያገኙት መሰለህ ተሳስተሃል ለሦሰተኛ ጊዜ የመጣ እንደሆነ የእኔስ ግብሬ የከፋ ስለሆነ ውሻን አሥረው ለብቻው እንደሚያኖሩት እኔም ባሕርዬ ቢከፋ ግብሬ ከሰው ባይስማማ ከዚህ መጥቼ ከሰው ተለይቼ፣ ከበዓት፣ ተከትቸ፣ ውኃ ተጎንጭቸ፣ ድንጋይ ተተርሼ፣ ተቀምጨአለሁ ብለህ በለው እንጂ እንደዛ እንዳትለው አለው፡፡ ሰይጣኑም በሌላ ጊዜ እንደ ልማዱ መጣ ጠየቀውም መነኩሴውም አባ መቃሪ እንደነገረው አድርጎ ነገረው (አኮ አንተ ዘገበርከ ዘንተ አባ መቃሪ ውእቱ) ይህን ያደረገ መቃሪ ነው አንተ አይደለህም ብሎት ትቶት ሄደ፡፡

በጓደኞችህ መካከል በተቀመጥህ ጊዜ እንዳታፍር ጥረው ግረው በላባቸው ያገኙትን ሀብት ተሰብስበው የሚበሉትን፤ የሚጠጡትን አዘጋጅተው ሲበሉ ሲጠጡ እገሌ ተስፋ የለውም ብለው ይጠሩታል፡፡ ያን ጊዜ እኔ ይህን ያህል አገባሁ አገኘሁ እያሉ ሲጫወቱ ያልሠራ ያፍራልና እንደዚህም ሁሉ በመንፈሣዊ ሥራ (አለል ዘለል) ቀልድ፤ አሉባልታ፤ ሐኬት የተቋራኙት ሰው አትሁን፡፡ በጻድቃን መካከል በተቀመጥህ ጊዜ እንዳታፍር በአባ ብሾይ ገዳም የቆስጠንጢኖስን ስም በጸሎተ ቅዳሴ በጸሎተ ማኅበር ይጠሩታል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቆስጠንጢኖስ መነኮሳት በክንፈ እሳት እየበረሩ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሲገቡ አይቶ በአካለ ነፍስ መጥቶ አባ ብሾይን “ሰላም ለክሙ ብፁዓን መነኮሳት” አላቸው አንተም ብፁዕ ነህ በዘመንህ ቀርነ ሃይማኖት ቁሞልሀልና አለው፡፡ ይህንስ አውቄ ቢሆን መንግሥቴን ለቅቄ ከበረሃ ወድቄ ጤዛ ልሼ ደንጊያ ተንተርሼ በኖርሁ ነበር አለ፡፡

የሁሉም አብነቱ አባቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ የትሩፋት አበጋዞች በሰውነት ያለ አእምሮ ጠባይዕ ሥራ ሠርቶ ሊገለጽ ነው እንጂ ተሰውሮ ሊቀር አይደለም፡፡ ሰውነታቸው በወዲህም በወድያም ከበረች (ወጻድቃንሰ ውስተ ሕይወት ዘለዓለም) ሥራውን ሠርተው ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ጻድቃንስ ሁልጊዜ በዘለዓለም ሕይወት ውስጥ ናቸው፡፡ በመሠረቱ ባሕታዊ ማለት ተባሕተወ ብቸኛ ሆነ፤ ከሰው ተለይቶ ሰው ወደማይደርስበት ቦታ ሔዶ ሥጋውን ክዶ ለነፍሱ ብቻ ያደረ ማለት ነው እንጂ በየከተማው እየዞረ የተባሕትዎ ልብስ ለብሶ የማስመሰያ ልብስ ለብሶ በቅዱሳን ባሕታውያን ስምና ልብስ ከተለያዩ ሥጋዊ ችግሮች ለመውጣት የሚደረግ ውዥንብር ፍጹም ሰይጣናዊ ሥራ ነው፡፡ ማታለልን ማስመሰልን እንዲያውም በአባቶች ስምና ልብስ ሳይበቁ በቅቻለሁ፤ ሳያውቁ አውቄአለሁ የሚሉ ምእመናንን ግራ የሚያጋቡ ከቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት ውጭ በፍጹም ከአንድ መንፈሳዊ ነኝ ከሚል እንዲያውም ባሕታዊ ገዳማዊ የማይጠበቅ ተግባራት ሲፈጽሙ ማየት በጣም ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዲህ አይነቱን ተግባር የሚፈጽሙ ግማሾቹ በጭራሽ ምንም አይነት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንኳ የላቸውም፡፡ የተወሰኑት ደግሞ “ዘጎየ እም ዐጸባ” ናቸው እግዚአብሔር ይቅር በላቸው፡፡

በነገራችን ላይ እነዚህን አበው ገዳማውያን መነኮሳትና መናንያን (ግሑሳን) ብለን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ባሕታዊ የሚለው እንዳለ ሆኖ ግሑስ ማለት ትርጉሙ ከዚህ ያልተለየ ሆኖ ፍሉስ፣ ፈላሲ፣ ምንም ምን የሌለው፣ ምንም ምን የማይፈልግ፣ ከምንም ከምን ጋር ግንኙነትና ፍላጐት ሁሉ የተለየ፤ ምሳውንም፣ ራቱንም ጸሎት ስግደት የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ያደረገ ማለት ነው፡፡ ልብሱንም ሳይለውጥ እላዩ ላይ የሚያልቅ የልብስ ዓይነቱም በጣም የተለየ ነው፡፡ ይህውም ሰሌን ወይም አጽፍ ነው፡፡ አጽፍ ማለት ከቆዳ የተሠራ ማለት ነው፡፡ የጽሞና ጊዜያቸው እግር በማታዘረጋ ዋሻ ወይም ጐጆ ሆነው ጌታዬ አምላኬ ሆይ ከራሴ ጋር ብቻዬን በምሆንበት ጊዜ አንተ ከእኔ ጋር ስለሆንክ እኔም ከአንተ ጋር ነኝ እባክህ አምላኬ ሆይ ሰዎችን እንድተውና እራሴን ከአንተ ጋር እንዳደርግ፡፡ እራሴን እንድረሳና ሐሳቤን በአንተ ላይ እንዳደርግ እርዳኝ፡፡ ይህ ለእኔ መልካም ነውና በማለት አምላካቸውን ይማጸኑታል፡፡

  • ራሳቸውን የማይላጩ፣ የሚያሰክር መጠጥ የማይጠጡ፣ ከሁሉም የማይገባ መጥፎ ነገር የተከለከሉ፣ ናዝራውያን ናቸው፡፡ ናዝራዊ ማለት ከክፉ ነገር ሁሉ የተከለከለ ማለት ነው፡፡ ቋንቋው የዕብራይስጥ ነው፣ ናዚር ወይም ናዛር ማለት ከክፉ ነገር ሁሉ የተከለከለ፣ ስእለት ወይም ብፅዓት ያደረገ፣ ሕይወቱን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠ፣ በሰውነቱም የተቀደሰና የተለየ ሰው ማለት ነው፡፡
  • እንደነ ሶምሶን፣ እንደነ ሳሙኤል መሳ. 13 ሳሙ. 11 ዮሐንስ መጥምቅ ሉቃ. 1-15 ናዝራውያን ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በተወለደበትና ባደገበት ናዝሬት ኢየሱስ ናዝራዊ ተብሏል ወይም ተብሎ ይጠራል፡፡
  • አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ከኩነኔና ከዘለዓለማዊ ሞት እንዲያድነው ጽኑ ተስፋና ብፅዐት ሰጥቶ የነበረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ናዝራዊ ተባለ፡፡ “ወቦአ ናዝሬተ ኀበ ተሐፅነ ከመ ይሰመይ ናዝራዊ፡፡” ናዝራዊ ይባል ዘንድ ናዝሬት ገብቶ አደረ፡፡ ማቴ. 2÷23 ለእኛም ተባሕትዎውንም ሆነ በገዳም መወሰንን፣ መጾም መጸለይን፣ መስገድን፣ በገዳም መኖርን የአስተማረን እርሱ ራሱ ሊቀ ካህናት መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስትናንም የመሠረተ እርሱ ነውና “ወእምዝ ወሰዶ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚእ ኢየሱስ ገዳመ ከመ ይትመከር እምኀበ ዲያብሎስ” ማቴ. 4÷1
  • “ወጾመ አርብዐ መዓልተ ወአርብዐ ሌሊተ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ፡፡” ሠራዔ ሕግ ነውና:: ሥራውን በገዳም መሠረተ፡፡ በገዳም ምን መደረግ እንዳለበት አስተምሮና ሠርቶ ካሳየ በኋላ ዓለሙን ለማስተማር “በዓለም በሚገኙት ሁሉ አስተማሪ እንዲሆኑ ሐዋርያትን መረጠ፡፡” መጀመሪያ ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ እንድርያስን ቀጥሎም ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሐንስን ጠራቸው፡፡ “ዓለሙን ተውት እኔን ተከተሉኝ” ማቴ. 4÷1-2፣ ማቴ. 4÷18-22፡፡
  • አባቱንና እናቱን፣ እኅትና ወንድሙን፣ ዘመድ አዝማዱን ትቶ ያልተከተለኝ የእኔ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም አላቸው፡፡ እነሱም ሁሉንም ትተው ተከተሉት፡፡ ማቴ. 4÷22፣ ማቴ. 19÷27፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም የጠየቀው ስለዚህ ነበር፤ እንዲህ ሲል እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፡፡ “ናሁኬ ንሕነ ኀደግነ ኩሎ ወተሎናከ ምንተ እንከ ንረክብ” ሁሉን ትተን ተከተልንህ የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው? አለው ጌታም እንዲህ ሲል መለሰለት፡፡ “አማን እብለክሙ አንትሙ ተለውክሙኒ አመ ዳግም ልደት አመ ይነብር ወልደ እጓለ እመሕያው ዲበ መንብረ ስብሐቲሁ አንትሙኒ ትነብሩ ዲበ ዐሠርቱ ወክልኤቱ መናብርት ወት£ንኑ ዐሠርተ ወክልኤተ ሕዝበ እስራኤል” እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ልትፈርዱ በዐሥራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፡፡ ማቴ. 19÷28

በዘመነ ነቢያት የተገኘ ሥርዓተ ተባሕትዎ በዘመነ አበው በነሄኖክና በእነመልከ ጼዴቅ ተያይዞ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተግባራዊ ሆኖ ከሐዋርያትና ከሰብዓ አርድዕት ደረሰ፡፡ ከዚያም እንደ አባ እንጦዮስ፣ የዋህ ጳውሊ፣ በዘመናችን ደግሞ እንደ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ አባ (ነጮ) ቅዱሳን ተገኝተውበታል፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ አባ (ነጮ) የተባሉበት ምክንያት ከቅላታቸው የተነሳ ነው እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ በጣም ቀይና ርቅቅ ያሉ ከአንደበታቸው ቃለ እግዚአብሔር ብቻ የሚወጣ አባት ናቸው፡፡ ከሠላሳ ሰባት ዓመታት በላይ እህል ሳይበሉ በገደሙ ሕግና ደንብ መሠረት (ቋርፍ) ማለትም ሥራ ሥርና ቅጠላ ቅጠል በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በመመገብ ለቁመተ ሥጋ ያኸል ነበር የሚኖሩት፡፡ ለዚህም ነው ሰውነታቸው (በቋርፍ) ተጐሳቁሎ ይታያል፡፡

9-2

ከአብረንታንት ገዳም ውጭ ወጥተው ሌላ ቦታ አይንቀሳቀሱም፡፡ ከቅጠላ ቅጠል በቀር ሌላ ቀምሰው አያውቁም ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖራለን እንጂ ከማንም እንጀራን አልበላንም እንዲያውም አልበላንም፡፡ ይህም እኛን ልትመልሱ በሥራ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁአለን፡፡ 2 ተሰ. 3÷8

“ብፁዓን እለ ይርኅቡ ወይጸምዑ በእንተ ጽድቅ” አባቶች አብዝተንማ ከተመገብን ሰውነታችን ገቶ ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለው ከሚበሉት ከሚጠጡት ከፍለው የሚራቡ ንዑዳን ክቡራን ናቸው ፡፡ ማቴ. 5÷6

መ/ም አባ ገብረ ሥላሴ /አባ ነጮ/ ገዳሙን በአበ ምኔትነት በሚያስተዳድሩበት ወቅት የማኅበረ መነኮሳቱ ብዛትና የገዳሙ ዕድገት ልዩ ነበር፡፡ በሌላ መልኩ ፈተናዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ ምንም እንኳን መነኮሳቱ ለፈተና ዝግጁ ቢሆኑም የራሱ የሆነ ታሪክ ትቶ አልፏል፡፡ ለምሳሌ የገዳሙን በርሃ (የኢህአፓ) እንቅስቃሴ ለመደበቅም ሆነ ለመተላለፍ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በከተማው (ደርግ) የሚያስተዳድርበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ማኅበረ መነኮሳቱ የሚለብሱት (አቡጀዴ) መግዛት የተከለከሉበት ቅጠል ለብሰው ጊዜውን በጸሎትና በእንባ ያሳለፉበት ክፉ ወቅት ነበር፡፡ ገዳማውያን መነኮሳት ወደ ከተማ ለማኅበሩ የሚያስፈልግ ፍጆታ ሁሉ ለመግዛት በሚሄዱበት ጊዜ ለሽፍታ ለወንበዴ ነው የምትወስዱት፤ ወንበዴ ነው የላካችሁ፤ በማለት መብታቸውን ያጡበት እንደሰው ያልታዩበት ወቅት ነበር፡፡ በገዳሙ ከ1000 (ከአንድ ሺህ) በላይ መነኮሳት ይኖራሉ፡፡ ለእነዚህ ማኅበረ መነኮሳት ሊቃነ አርድዕት ናቸው የራቀውን የሚያቀርቡ፡፡ ከነዚህ ውጭ የገዳሙ መነኮሳት ያለ ሥራ ወደ ከተማም ሆነ ወደ ገጠር መውጣት አይፈቀድላቸውም፡፡ ገዳሙ በወባ በሽታ የታወቀ ነው፡፡ ምንም እንኳን መነኮሳቱ የወባ (ክኒን) ባይጠቀሙም ነገር ግን በሽታው አቅም ስለሚያሳጣ ስኳር ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው ወታደራዊ ሥርዓት ለመነኮሳቱ ወታደሩ በየኬላው መነኮሳቱን ይፈትሽና ይዘውት የተገኘ ስኳርና ባትሪ ድንጋይ ምንድነው የያዝከው ስኳር ከሆነ ከአንድ ኪሎ በላይ አይፈቀድም ባትሪም እንደዚሁ ነው የተፈቀደው ሌላው ለወንበዴ ነው የምትወስደው መልስ በማለት የተገዛው የመነኮሳት ስኳርና ባትሪ ተወርሶ መነኮሳቱ ስኳር በመግዛታቸው ብቻ ከወር በላይ የታሰሩበት የተገረፉበት ጊዜ ነበር፡፡ በአንጻሩ የገዳሙን በረሃ የተቆጣጠረው (ኢሀአፓ) ደግሞ ለአረጋውያንና ለበሽተኞች የተቀመጠ (አቅምሐት) ማለትም ማር አምጡ በማለት በጉልበት ሲዘርፍ በተለይ በየአትክልት ቦታዎች የተመደቡ አርድዕት የመታሰር የመደብደብ ግፍና በደል ደርሶባቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት ከህወሓት በመዘጋ ወልቃይት አካባቢ ያደረጉት ጦርነት (የኢሀአፓ) ሠሪዊት አፈግፍጎና ተሸንፎ ወደ ዋልድባ ገዳም ሸሽቶ ገባ በዚሁ ምክንያት መነኮሳቱን በማስገደድ ያላቸውን ቋርፍና ቅጠላ ቅጠል በመቀማት የአረጋውያንና የገዳሙን ምግብ አራቆቱት፡፡ በዚህም አልበቃ ብሎ በውጊያ የቆሰሉትን በግዴታ በማሸከም መነኮሳቱን ያሰቃያሉ፡፡ ወደላይ ብንሄድ ወንበዴ በገዳም ቢኖሩ ቀማኛ  ገዳሙ በእንዲሁ የሥቃይ ዘመናትን አሳለፈ፡፡ ገዳሙ በበረሀ እንስሳ የታደለ ነው፡፡ የሌለ እንስሳ አይነት የለም፡፡ ከቀጭኔና ዝሆን በቀር ስለዚህ ከአካባቢ የገጠር ነዋሪዎች ለአደን ወደ ገዳሙ ይመጣሉ፡፡ በአንድ ወቅት በዋሻ የሚኖር ባሕታዊ አዳኙን አየውና ምን አለ መሰላችሁ “አዳኝም ለከርሱ መናኝም ለነፍሱ ማልደው ተነሥተው ሁሉም ገሰገሱ አሉ በዋሻ ያሉ ባሕታዊ ሲናገሩ፡፡ አዳኙ ሰማቸውና ወድያውኑ መሳሪያውን ጥሎ እኔም ለከርሴ ሳይሆን ለነፍሴ ብሎ መነነ”፡፡

 

9-4እንዲሁም አንድ የንጉሥ ልጅ ነበረ ከአባቱ ቤት መነኮሳት መጥተው አደሩ፡፡ ሌሊት መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ ለልጁ እነዚህን መነኮሳት ተከትለህ ሂድ አለው፡፡ ተከትሎም ሄደ፡፡ ከገዳሙ ሲደርስ ወድያውኑ በሽታ አደረበት፡፡ ታመመ (ከሃያ አምስት) ዓመታት በላይ በጽኑ ደዌ ወደቀ መነኮሳቱ ዐሥሩን ዓመታት ረድተውታል፣ ጠይቀውታል፣ አስታመውታል ዐሥራ አምስቱን ዓመታት ግን ሳይጠይቁት ወድቆ በስቃይ ኑሯል፡፡ ከዚህ በኋላ አባ ኪሮስ ጌታችን አምላካችንን  በጸሎት በመጠየቅ የአበው ባሕታውያን እረፍተ ሥጋ ወነፍስ እየዞሩ ለማየት ሲሄዱ ከዚያ ገዳም ደረሱ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ቢገቡ የእመቤታችንን ሥዕል አገኙ (ሰላም ለኪ) ቢሏት ሥዕሏ “ለከኒ” ለአንተም ሰላም ብላቸዋለች፡፡ ማኅበረ መነኮሳቱ የአባ ኪሮስ ፊታቸው እንደ ፀሐይ ሲያበራ መልካቸው ሲያጽደለድል አይተው እዚያው ይደር መነኮሳቱ ይህስ ዓለማዊ ነው ከዚያ ከእንግዳ ቤት በሽተኛው ድውዩ ካለበት ይግባ ብለው ወስዱዋቸው ሲገቡ ከድውዩ ጋር ቅዱስ ሚካኤል በራስጌ ቅዱስ ገብርኤል በግርጌ ሁነው ታማሚው ከመሐከል ወድቆ (ተኝቶ) አገኙት፡፡ አባ ኪሮስ ለመላእክቶች ከዚህ የተቀመጣችሁ ምን ሁናችሁ ነው? አሏቸው የመላእክት መልስ የዚህን ሰው ነፍሱን ከሥጋው ለይታችሁ አምጡ ተብለን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዘን ነበር ነገር ግን ነፍሱን ከሥጋው የማትለይልን ሁና እንጠብቃለን አሉ፡፡ አባ ኪሮስ ታማሚውን ደግሞ መልሰው አንተስ የወዴት አገር ሰው ነህ ብለው ጠየቁት፡፡ ታማሚውም የንጉሥ ልጅ ነበርኩ ከአባቴ ቤት መነኮሳት መጥተው አደሩ፡፡ ሌሊት መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ ተከትለሃቸው ሒድ አለኝ፡፡ እኔም በታዘዝኩት መሠረት ተከትያቸው መጣሁ፡፡ ከገዳሙ እንደ ደረስኩኝ በደዌ ተያዝኩኝ ይኸውና ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ሆነኝ ዐሥሩን ዓመት መነኮሳቱ ጠይቀውኝ ነበር ከዚያ ወድያ ግን አልጠየቁኝም እንዲህ ወድቄ እኖራለሁ አላቸው፡፡ አባ ኪሮስም አዝነው አልቅሰው ሲያበቁ አይዞህ እንዲህ እንደ አንተ ሁሉ የሮም ንጉሥ ልጅ ነበረ መንኖ ወጥቶ ዛሬ ይሙት ይዳን የሆነውን የሚያውቅ ማንም የለም አሉት ራሳቸውን ነው፡፡ አባ ኪሮስ ከዚህ በኋላ ወደ ጌታችን አመለከቱ፡፡ እረፍተ ነፍስ እንዲያገኝ፡፡ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡ ከዚያ ማኅበረ መነኮሳቱ አርፏል እንሂድ ጸሎተ ፍትሐት እናድርስ ብለው መጡ፡፡ አባ ኪሮስ ለመነኮሳቱ “አሰስሉ ማዕጠንተክሙ ሀለው መላእክት የዐጥንዎ” ብለው ገሠጿቸው ምክንያቱ ስልቹዎች በመሆናቸውና የገቡበትን ዓላማ በትዕግስት ያለመወጣት መንፈሣዊ ሕይወታቸውን ስለረሱ ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ በገዳሙ ወድቆ በበሽታ ሲሰቃይ ረሱት ዘነጉት ዓለማዊነት አጠቃቸው፡፡ (ፊልክስዩስ) 162 – ገጽ 203

እግዚአብሔር የሚመርጠው እንደ ሰው አይደለም፡፡ ሰው መልክና ቁመት አይቶ ሀብትና እውቀትን ጉልበትን ጤንነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ ለወገን ለዘመድ አድልቶ ይመርጣል፡፡ እግዚአብሔር ግን ፊትን ሳይሆን ልብን አይቶ ይመርጣል ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ለልዩ ልዩ አገልግሎት የመረጣቸው ቅዱሳን በሰው ዘንድ የተናቁትንና ከምንም የማይቆጠሩትን ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከፀሐይ የበሩ ከወርቅና ከእንÌ የከበሩ ናቸው፡፡ በዋልድባ ገዳም አንድ መናኝ ከገዳሙ ከገባበት ዕለት ጀምሮ በጤንነት ይሁን በበሽታ እስከ ዕለተ ሞት ድረስ በሊቀ አበው ይረዳል፡፡ በሥራም ከሆነ እስከተፈቀደለት ያገለግላል፤ ይረዳል ለተባሕትዎ ከተፈቀደለትም በኋላ ብዙ ምግባረ ትሩፋትን ያለሐኬት ሐሳብን ያለመከፋፈል ልቡናን ለዓለማዊ ምኞት ከሚጋብዙ ንግግርና ከሌሎችም ለተባሕትዎ የማይመቹ ጋር ጊዜን በከንቱ ያለማባከን ክፉ ሕዋሳት ከራሳቸው አርቀው እንደ ወጣኒ ሳይሆን በፍፁማን አምሳል ረሀቡን ጥሙን ዋዕየ ፀሐዩንና በሽታውን እየታገሱ በጾም በጸሎት በስግደት ጸንተው ከእግዚአብሔር አምላክ ኀላፍያትና መጻእያት የተገለጸላቸው አባቶች ያለፉም በሕይወተ ሥጋ ያሉም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ የምናኔ ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ ማዐርግ የበቁ አባቶች እግዚአብሔርን በመዘከር የጸኑ ናቸውና (ወይነጽሕ ልቦሙ) ልቡናቸውም ንጹሕ ይሆናልና (እስመ እለኒ ደለዎሙ በዝየ ነጽሮተ ዝንቱ እሙንቱሰ እለተናዘዙ በአንብቦተ እግዚአብሔር) በዚህ ማዕረግ ጊዜ ለነጽሮተ እግዚአብሔር የበቁ ሰዎች እግዚአብሔርን በመዘከር የጸኑ ናቸው፡፡ (ወቦቱ ይቀትልዎ ለሕማመ ሁከቶሙ) የኀልዮ ኃጢአትን ድል ነስተውታል፡፡ ልቡናቸውም ንጹሕ ይሆናል፡፡ ለነጽሮት የበቁ ሰዎች እግዚአብሔርን በመዘከር የጸኑ ናቸው ብቃታቸውም በታናሹ ብርሃን መሸፈን ሳይቀር በታላቁ ብርሃን መሸፈን ሳይኖር እግዚአብሔርን ማየት ይቻላቸዋልና፡፡

ታሪክ እንደ አባ ጳጉሚስ ባንዲት ሴት አጋንንት ሠፍረውባት አየ ጥንቱንም ሰው ደካማ ነው በዝያውም ላይ በሴት ባሕርይ ይህ ተጨምሮ እንደምን ይቻላል ጌታዬ ወደኔ መልሰው ብሎ ጸለየ፡፡ በሴትየዋ የነበሩ ርኩሳን መናፍስት ወድያውኑ ያንድ ቀፎ ንብ ወዳንዱ ቀፎ ያንድ ማድጋ ውኃ ወደ አንዱ ማድጋ እንደሚገለበጥ በሷ ላይ ሠፍረው የነበሩ ርኩሳን መናፍስት ወደሱ መጡ፡፡ አባ ጳኩሚስም ማቅ ምንጣፍ ለብሶ ከመሬትም ካመድም ላይ ተኝቶ ርኩሳን መናፍስቱን ያማስናቸው ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ ከዚህ ሰው እንሒድ እንሒድ ሲሉ ሰማቸው፡፡ ሰው ከወዳጁ ቤት ውሎ አድሮ አይሔድምን? እናንተስ ለምን አትቆዩም አላቸው፡፡ ርኩሳን መናፍስቱ ግን ከገነት ካስወጣነው ከአዳም ልጆች እንዲህ ያለ ጸሎተኛና አርበኛ አይተን አናውቅም ብለው ብን ብለው ሔዱ፡፡ አበው  እንደ አልባሌ ሰው በገዳም ልብሳቸውን ሳይለውጡ የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ጣጣው ሁሉ ጠፍቶላቸው እንደነ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባ ነጮ) ለወጣንያን ሲመክሩ እንዲህ ይላሉ፡፡ በልቡናህ የእግዚአብሔር ፍቅር በተሳለ ጊዜ ጣዕሙን አግኝተህ ደስ ይልህ ዘንድ ሕይወትህን በሙሉ ባለመሰልቸት እግዚአብሔርን በጸሎት በአምልኮት ጠይቀው፡፡ ይህን ምሥጢር በዓይነ ነፍስ ታየው ዘንድ እግዚአብሔር የሚሰጥህ ጸጋና ክብር ይህ ነው ማለት አይቻልም በሰው ልቡና ያልታሰበ ነው፡፡ በርታ የገዳሙን ሕግና ሥርዓት ጠብቀህ አባቶች ከደረሱባት ክብር መድረስ ትችላለህ ብለው ይመክራሉ፡፡

አበው ግሑሣን መነኮሳት

ከብዙ መናንያን (ግሑሣን) መካከል የአባ አስከናፍር ታሪክን መናገር እንችላለን፡፡ አባ አስከናፍር መልካም ሥነ ምግባር ካላቸው ቤተሰብ የተወለደ ነበር፡፡ ስለነፍሱ ብዙ ያስባል፡፡ ብዙም ይጨነቃል ቅዱሳት መጻሕፍትንም በእጅጉ ይከታተላል ያነባል፡፡

ከዕለታት ባንዱ ቀን በተወለደበት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ተሰብስበው ስለመነኮሳት ማኅበራዊ ኑሮ እያነሱ ሲወያዩ ይሰማል፡፡ በሰማውም ታሪክም ልቡ በጣም ይመሰጣል፤ ከዚህ በኋላም ፈጽሞ ሕሊናው ዕረፍት ያጣል፡፡

በአንዱ ገዳም መግባት አለብኝ ብሎ ያስባል፣ አስቦም አልቀረም ተነሥቶ በምናኔ ወደአንድ ገዳም ይገባል በገዳሙም ሆኖ የብዙ አባቶችን ፈቃድ እየፈጸመ እየተጋደለ፣ ሥርዓተ ገዳማትንና ሥርዓተ ምንኩስናን እያጠና አያሌ ዘመናት በዚሁ ገዳም ተቀምጧል፡፡

አንድ ቀን መነኮሳቱ ስለግሑሳን አባቶች ታሪክ ስለ ብቃታቸውና ጸሎታቸው ሲነጋገሩ ይሰማል፡፡ በነገራችን ላይ አባ አስከናፍር የዓለማዊ ወሬ ዋዛ ፈዛዛ ቀልድ ሓሜት ሲናገሩ ሲሰማ ጆሮውን ደፍኖ ይሸሻል ይሮጣል፡፡ ስለእግዚአብሔር መንግሥትና መንፈሳዊ ሕይወት ሲነገር ከሰማ ግን ሁሉንም ትቶ ሥራውንም ጥሎ ጆሮውን ከፍቶ ዐይነ ልቡናውን አቅንቶ በተመስጦ ይሰማል እንጂ አይነቃነቅም፣ ጥሎም አይሸሽም፡፡

አባ አስከናፍር ከፍ ብለን እንደጠቀስነው መነኮሳቱ ስለግሑሳን ኑሮ ሲናገሩ የሰማውን ወድያውኑ በጥያቄ አባቶች ከናንተ የበለጡ ግሑሳን፣ መናነያን አባቶች አሉን? ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ እነርሱም እንዴታ! እኛማ ከዓለም ትንሽ ነው የራቅነውና የተለየነው፡፡ አዎ ስንታመም አስታማሚ፤ ሐዘን፣ ችግር፣ ፈተና ሲደርስብን ምእመናን እየመጡ ያጽናኑናል፡፡ እነርሱ ግን ከአራዊትና ከጸብአ አጋንንት ጋር ዘወትር እየታገሉና እየተጋደሉ ነው የሚኖሩት፣ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ መላእክቱን ይልክላቸዋል ይሉታል፡፡

አባ አስከናፍር ግሑስ ለመሆን ተመኘ፣ አንድ ቀን ትንሽ ኅብስት ይዞ ከገዳሙ ይወጣል፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ ተጓዘ ያችን ቁራሽ ኅብስት እንኳ ሳይቀምሳት እልም ካለ በረሀና የአሸዋ ሙቀት ከበዛበት ቦታ ይደርሳል፡፡ ደክሞታልና በዚያው በሞቀ መሬት ይተኛል፡፡

ጠዋት ሲነሣ በራስጌው አንድ ቴምር በቅሎ ዐሥራ ሁለት ዘለላ አፍርቶ፣ ከአጠገቡም የውኃ ምንጭ ፈልቆ ሲፈለፍል እና ሲፈስ አይቶ ይደሰታል፡፡ ይህ ቴምር ትናንትና አልነበረም የውኃ ምንጩም እንደዚሁ ፈጽሞ አልነበረም አልታየኝም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እዚህ እንድኖር ፈቃዱ ቢሆን ነው ብሎ ወሰነ፡፡ አንድ የቴምር ዘለላ ለአንድ ወር እየተመገበ፣ ከምንጩም ውኃ እየጠጣ፣ ከእኩያን አጋንንት ከርኩሳን መናፍስት ከኃያላን አናብስትና አናብርት ጋር እየታገለ 67 ዓመት ሙሉ በዚሁ በረሃና ዋዕየ ፀሐይ በሚቃጠልበት ቦታ ኖረ፡፡

(አባ ነጮም) እና አባ አስከናፍር የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር የዓለማዊ ሥራ ሐሜትም ይሁን አሉቧልታ አይወዱም፡፡ እየተቆጡ ርቀው ይሄዱ ነበር፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴም በዋልድባ ገዳም 70 ዓመታት በተባሕትዎ ቋርፍ እየበሉ ማዬ ዮርዳኖስ እየጠጡ ኑረዋል፡፡

አባ አስከናፍር መላ ሰውነቱ የተሸፈነው በጠጉር ነበር፤ ከራሱ  እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ የተሸፈነው በመላ ሰውነቱ በበቀለው ጠጉሩ ብቻ ነበር፡፡ አባ አስከናፍር አናብስት፣ አናብርት፣ ሌሎችም አራዊት ዘገዳም የተገዙለት፣ የሚያገለግሉት፣ የሚያረጋጉትና የሚያጽናኑት መላእክት ታዘውለት ከሰማይ እየወረዱ ነበር የሚላላኩት ከብቃቱ የተነሣ፡፡ “መላእክቱን ስለ አንተ ይልካቸዋል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡልሃል” ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡፡ መዝ. 90/91 ቁ. 12

ከላይ በጠቀስነው ቦታ አባ አስከናፍር 67 ዓመት በሕርትምና እና በትሕርምትና በምነና ከቆየ በኋላ አባ ስንትዮስ የሚባል መነኩሴ ከነበረበት ገዳም በበረሀ በተባሕትዎ ያሉትን አባቶች መጎብኘት አለብኝ ብሎ ታጥቆ ተነሣ፡፡ ሐሳቡንም ለመፈጸም ጉዞውን ወደበረሀ ቀጠለ፡፡ በረሀውን ሲያስስም አባ አስከናፍርን አገኘው፤ አባ አስከናፍር መላ ሰውነቱ በጸጉር የተሸፈነ ስለነበረ አባ ስንትዮስ ባየው ጊዜ በጣም ደነገጠ፡፡ ምትሃት ነው ወይስ ሰው አለና ራሱን ስቶ በድንጋጤ ዝልፍልፍ ብሎ ወደቀ፡፡

አባ አስከናፍርም የአባ ስንትዮስን መፍራትና መርበትበት አይቶ አይዞህ ብሎ ቀኝ እጁን ያዘው እንዲህ አለው “ተንሥእ ኦ አባ ስንትዮስ ሠናይኑ ምጽዐትከ” አባ ስንትዮስ ወደዚህ በረሀ የመጣህበት ምክንያት በደህና ነውን? ብሎ አስነሣው፡፡ አባ ስንትዮስም አባ አስከናፍር በስሙ ስለጠራው ከድንጋጤው ተረጋጋ፣ ተጽናናም ተነሥቶም ቆመ ሁለቱም በሕብረት ጸሎተ ማርያም ጸልየው እንደጨረሱ ነገራተ እግዚአብሔርን እየተነጋገሩ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዓ በረከት ይዞ መጣ፡፡ ሁለቱንም አÌርቧቸው ሔደ፡፡

አባ አስከናፍር መልአኩ ከሔደ በኋላ ፊቱ የእሳት ፍም መሰለ ጥቂት ቆይቶም አረፈ፡፡ አባ ስንትዮስ በሁኔታው እጅግ አደነቀ፡፡ አባ አስከናፍርንም አጥቦ፣ ገንዞ ቀበረው፡፡ አባ ስንትዮስ አባ አስከናፍርን ከቀበረ በኋላ በዚያች ልዩ ቦታ ለመኖር ወሰነ፡፡

አባ ስንትዮስ በዚያች ሌሊት እዚያው ተኝቶ አደረ፤ ጠዋት ነቅቶ ወደቴምሩ ዛፍ ቢመለከት ደርቆ ከሥሩ ተመንግሎ አገኘው፤ ወደውኃው ቢመለከትም ከደረቅ አሸዋ በስተቀር የውኃ ምልክት እንኳ የነበረበት ቦታ አይመስልም ነበር፡፡

አባ ስንትዮስም እግዚአብሔር እዚህ እንድኖር አልፈቀደም ብሎ ወደገዳሙ ተመለሰ፤ የቅዱሳንን ገድል እየጻፈ ኖረ፡፡ የአባ አስከናፍርና የሌሎች ግሑሳን መናንያን አበውን ገድልና ተአምር እየዘገበ እስከ ዕለተ እረፍቱ ኖረ፡፡

ስለዚህ በከፋ ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፤ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌል በመዘጋጀት እግሮቻችሁን ተጫምታችሁ ቁሙ የክፉን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበት የእምነት ጋሻ አንሡ የመዳን ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ዘኢፆረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይጸመደኒ” መስቀሉንም የማይዝ በኋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ባለው ቃል መሠረት እነሆ እነዚህ አበው መነኰሳት ቃሉን ትእዛዙን እንደፈጸሙ ያሳስበናል፡፡ ማር. 8÷34፣ ሉቃ. 9÷23

ነገር ግን ውጫዊ ማንነታችን እንኳን ቢጠፋ ውስጣዊ ሕይወታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፡፡ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘለዓለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘለዓለም ነው፡፡ (2ኛ ቆሮ. 4÷16)

“ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ወይጽልኣ ነፍሶ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ” አበው መነኰሳት በገዳም ሲኖሩ ዋዕየ ፀሐይን ችለው፤ ብርዱንና ረሀቡን ታግሰው፤ ለዚች ለምታልፈው ጊዜያዊት ዓለም ምንም ሳያስቡና ከምንም ሳይቆጥሩ በሰው ዘንድ የተናቁ ከምንም የማይቆጠሩት ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከወርቅና ከዕንÌ ይልቅ የጠሩና የከበሩ ከብርሃናት ይልቅ ሰባት እጅ የሚያበሩ ናቸው፡፡

አበው መነኰሳት እንደ አባት ቅድስት ሥላሴ፤ እንደ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ወንድምና እንደ እኅት ቅዱሳን መላእክት እንደ ርስት እንደ ጉልት የማታልፍ ርስተ መንግሥተ ሰማያት አለቻቸውና ደስተኞች ናቸው፡፡ በገዳማዊ ሕይወት የሚገባ ሐዘን አለ፤ ይኸውም የራስን ኃጢአት አይቶ፤ ግፍዐ ሰማዕታትን ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን አስቦ፤ አምላክ ዓለሙን በሙሉ በምሕረት ዐይኑ እንዲጐበኘው መጸለይና በኃጢአት ምክንያት ለሚጠፋው ፍጥረት ማዘን የምንኩስና ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ በገዳም ውስጥ የሚኖሩ ገዳማውያን የተባሕትዎና የሱባኤያቸው ትርጉም ይህ ነው፡፡

ከኀልዮ ኃጢአት የሚያነጻ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የባሕታዊ ንጽሐ ጠባይዑ ተጠብቆበት የሚኖር በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ባሕታዊን በልሳነ ነፍስ እንዲናገር የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ  ነው፡፡  ረቂቅ ምስጋናን ከመላእክት ጋራ እንደ መላእክት ያመሰግናል፡፡  ምሥጢር የሚገልጥ እግዚአብሔር ያደረበት ባሕታዊ ንዑዱ ክቡር ነው፡፡ አምላክ ልቡናውን   እንዲህ አድርጐ ውስጥ ለውስጥ መንፈሳዊ ምግብን ይመግበዋል፡፡ ሕዋሳተ ሥጋ ሥጋዊውን ምግብ ከሆድ አግኝተው እንዲመገቡ አበው በዚያ ከቅጠልና ስራስር በቀር እህል የማይቀመስበት ገዳም በምስጋና ብቻ ሆዳቸው ሞልቶ ያገኙታል፡፡ እንግዲህ ማነው ከእኛ መካከል ከእህል ተለይቶ ለ40 ወይም 70 ዘመናት መቆየት ይቅርና ለሳምንት የሚሰነብት ማንም የለም፡፡ አባቶች ግን የእግዚአብሔር ጸጋ በዝቶላቸው እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እህል ሳይቀምሱ (በሕርመት) ከእህልም ከሰውም በመለየት ይኖራሉ፡፡ ልቡናን ውስጥ ለውስጥ የሚመግበው መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡

ለዚህ ቅድስና ብፅዕና የሚያበቃ ገድልና ትሩፋት የሠሩ በዚህ መሠረት በጾም በጸሎት ተወስነው ርእሰ ባሕታውያን ለመባል የበቁ ለቁመተ ሥጋ ያህል (ቋርፍ) ተመግበው (ማየ ዮርዳኖስን) ጠጥተው ቅዱስ ውዱስ ስቡሕ እኩት ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ እያሉ በየ ሰዓታቱና በየደቂቃው አባቶች ያመሰግኑታል፡፡ ምስጋናውም ምግብና ፈውስ የሕይወት መድኃኒት ሆኗቸው ይኖራል፡፡

የገዳሙን ዓፀባ ችለውና ታግሰው ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙ ታላላቅ ባሕታውያን ናቸው፡፡ አባቶች የዚህን ዓለም ትዝታ የሚያደርስባቸው ከዚያው ከገዳሙ የሚቀበሉት ፈተና በትዕግሥት ችለው ስለሚኖሩ፣ እርሱም ስለሚበዛባቸው ነው፡፡ ከረቂቃን አጋንንትም ጋር ጭምር ከመዋጋት አቋርጠው አያውቁም፡፡ በተጋድሎ ድል ነሥተው በመጨረሻ ጊዜ የማያልፈውን ዓለም መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ የድል አክሊል ይቀዳጃሉ፡፡

በጸሎትና በትምህርት እንዲሁም በትሩፋት ለሀገርና ለወገን ብሎም ለመላው ዓለም ሰላምና ደኅንነት ደብሩን ገዳሙን፣ አገራችን ኢትዮጵያን ሕዝቧን መንበረ ማርቆስን ቅ/ቤተ ክርስቲያናችንን አጽናልን ጠብቅልን እያሉ ዘወትር እግራቸው ሳይታጠፍ ዓይናቸው እንቅልፍና ሳይሻ የላመ የጣመ ሳይቀምሱ፣ የሞቀ የደመቀ ሳይለብሱ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ወደፍጹምነት ምልአት ደረጃ ላይ ደርሰው እግዚአብሔርን ከማሰብ ለአፍታ ያህል እንኳ ሳያቋርጡ ይጸልያሉ፡፡

አባቶች በፍጹም ተጋድሎ ለወጣት መነኮሳት አርአያ በመሆን ትዕግሥትን ገንዘብ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ አንድ መነኩሴ ራእይ በማየቱ የበቃሁ ሆኛለሁ ብሎ ያስብ ነበር ከገዳሙ አበምኔት ጋርም ስለመንፈሳዊ ሕይወታቸው እያነሱ ሲወያዩ አባቴ እኔ ዛሬ በራእይ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ግፍና በደል አየሁ፡፡ ስለዚህ የበቃሁ ሆኛለሁ ብሎ አጫወታቸው፡፡ አበምኔቱም አባ እስቲ በርትተህ ጸልይ ገና ነህ ብለው መለሱለት፡፡

እንደሁም በሌላ ጊዜ ወደ አበምኔቱ ቀርቦ አባቴ አሁንስ በቅቻለሁ ቅዱሳን መላእክት ከሰማይ ሲወጡና ሲወርዱ፣ የሕዝቡንም ኃጢአት ሲያስተሰርዩ አይቻለሁ አላቸው፡፡ እሳቸውም አባ ገና ነህ አሁንም በርታና ጸልይ ብለው ሸኙት፡፡ ይህም መነኩሴ ወደ ዋሻው ገብቶ አብዝቶ ይጾምና ይጸልይ ጀመር፡፡ ለሦስት ጊዜ ስላየው ራእይ ለአበምኔቱ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው፡፡ አባቴ ሆይ ዛሬስ በዓለም ሳለሁ የሠራሁትን ኃጢአት ሁሉ አንድ በአንድ አሳየኝ፤ የኃጢአቴ ብዛትም ስፍር ቁጥር የለውም ሳለቅስም አደርኩ ኃጢአቴም እጅግ ብዙ ነውና ይቅር ይለኝ ዘንድ ይጸልዩልኝ አላቸው፡፡ እርሳቸውም ልጄ ሆይ የበቃኸው አሁን ነው ብለው አሰናበቱት፡፡

እግዚአብሔር የሚመርጠው እንደ ሰው አይደለም ሰው መልክና ቁመት አይቶ ሀብትና እውቀትን ጉልበትን ከግምት አስገብቶ ለወገን ለዘመድ አድልቶ ይመርጣል፡፡

እግዚአብሔር ግን ፊትን ሳይሆን ልብን አይቶ የመርጣል፤ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ለልዩ ልዩ አገልግሎት የመረጣቸው ቅዱሳን አበው በሰው ዘንድ የተናቁና ከምንም የማይቆጠሩ ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከፀሐይ የበሩ ከወርቅና ከእንÌ የከበሩ ናቸው፡፡

አባቶች የነፍሳቸውን ቅድስና ለሥጋቸው የሥጋቸውን ቅድስና ለአለባበሳቸውና ለአረማመዳቸው የተረፈ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የቅዱሳን ትምህርታቸውና ሕይወታቸው ብቻ ሳይሆን ልብሳቸውም ጭምር የሰውን ሕይወት ይለውጣል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኤልሳዕ ሕይወቱ የተለወጠው ሁሉን ትቶ ለመከተል የቆረጠው የነቢዩ የኤልያስ መጐናፀፊያ ከትከሻው በወደቀበት ጊዜ ነው፡፡ 1ኛ ነገ. 19፣19፡፡

በጸሎት በተዘክሮ ጊዜ ክርስቶስን በልቡ አድሮ የሚያየው ብርሃኑንም አይቶ ደስ የሚለው መነኩሴ ድንቅ ነው፡፡ በልብሰ ብርሃን ተሸፍኖ የሚያየው ብፁዕ ነው ደስ የሚያሰኝ የመላእክትን ምስጋና በልቡ ተሥሎ ሲያመሰግኑ የሚሰማቸው በልሳነ ነፍስ ከመላእክት ጋር የሚያመሰግን ባሕታዊ ንዑድ ክቡር ነው፡፡ ሥጋዊ አንደበት ሊናገራቸው የማይችል ነገራትን ይናገራል፡፡ ማለት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ቸር አምላክ የፍጥረቱ ሁሉ ጠባቂና መጋቢ ምስጋና ክብር ይገባሃል እያለ ከመላእክት ጋር ያመሰግናል፡፡ ለእኔ ንጽሕና ያለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰባት የንጽሐ ልቡና ማዕረግ ይህችን ትመስላለች (ብፁዕ መነኮስ ዘተጠብለለ ልቡ በርእየተ ሥሉስ ቅዱስ) “ዘተጠብለለ፣ ዘጠለለ፣ ዘጠለ” ይላል አብነት ምሥጢራትን በማየት የከበረ መነኩሴ ጌታችን ለማገልገል ከሕፃንነት እስከ እርጅና ከወጣኒነት እስከ ፍጹምነት በትሩፋት የደከመ መነኩሴ ንዑድ ክቡር ነው ከጽማዌ እስከ ከዊነ እሳት ያሉ ማዕርጋትን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ገንዘብ ያደረጋቸው ባሕታዊ ንዑድ ክቡር ነው፡፡ መ/ም አባ ገ/ሥላሴ (አባ ነጮ) ከሕፃንነት ጀምረው እስከተባሕትዎ ደረጃ የደረሱ ገዳሙን በተለያየ መልኩ በመቲረ ፈቃድ በማገልገል ነው፡፡ እኒህ አባት የዘመናችን ጻድቅ ባሕታዊ ናቸው፡፡ በታላቁ ዋልድባ አብረንታንት ገዳም በተባሕትዎ ከኖሩ በኋላ መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም የደብረ ዘይት ቀን በዕለተ ሰንበት በእረፍተ ሥጋ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም ዘለዓለማዊ መንግሥት ፈልሰዋል፡፡ ነፍሳቸውን በአብርሃምና በይስሐቅ አጠገብ ያኑርልን፡፡ በሕይወት ያሉትን አባቶቻችንም ጸጋውን አብዝቶላቸው ለገዳማችን ብሎም ለሀገራችን ለሃይማኖታችን መመኪያ አለኝታ ናቸውና እድሜና ጤና ሰጥቶ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቅልን፡፡

በአጠቃላይ እንደ አላዋቂና ማንኛውም ዕውቀት እንደ ጎደለው ሰው ለማወቅ በእግዚአብሔር ፊት ቅረብ፡፡ ከዚያም ፍጹም ከሰው ልጅ ዕውቀት በሚለይና መንፈሳዊ በሆነው ዕውቀት ትሞላለህ፡፡ ይህም ዕውቀት ያልያዘው የለም፤ መንፈስም ጥልቅ ነገር እንኳን ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና (1ኛ ቆሮ. 2÷10) ድንኳን የሚሆነው ጊዜያዊ መኖርያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን፡፡ (2ኛ ቆሮ. 5÷1) መ/ር አባ ገብረ ሥላሴ በዋልድባ ገዳም 70 ዓመታት ከኖሩ በኋላ በጠቅላላ ከአባትና እናታቸው ቤት ተለይተው በምናኔ እንደወጡ ሳይመለሱ ለፍጹምነት መዓርግ ደርሰው በተወለዱ በ94 ዓመታቸው አረፉ፡፡ ነፍሳቸውን ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር ይደምርልን፡፡ አሜን

 

የጽሑፉ ምንጭ

ባሕታውያን በዋልድባ ገዳም ቁጥር ፩ እና ቁጥር ፪ መጻሕፍት ከአባ ተከስተ ብርሃን ወ/ሳሙኤል በ1995 እና በ1997 ዓ.ም ከታተመው  

 

በአሁኑ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን

ሊቀ ጳጳስ

መጋቢት 2009 ዓ.ም

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

«መነሻዬ ከገዳም ነውና በገዳም ጸንተው ለሚኖሩ አባቶች ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡»

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ ወደ መናገሻ አምባ ማርያምና የጋራው መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም በመመላለስ፤ በግላቸውና በልማት ኮሚሽኑ ለገዳሙ እጅግ ብዙ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በመሆናቸው፤ የጋራው መድኃኔዓለም ሕንፃ ቤተክርስቲያን አሠሪ ኮሚቴ በዚህ መጽሔት ብፁዕነታቸው ወደዚህ ገዳም ለመምጣት ምክንያት የሆናቸውን ምን እንደሆነ? በመጡበት ወቅት ገዳሙን እንዴት? እንዳገኙት፤ የነበራቸውን ትዝታዎቻቸውን፣ ወደ ገዳሙ ተመላልሰው ብዙ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የጋበዛቸውን ምክንያት እና አሁን ገዳሙ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ፤ እንዲሁም የልማት እንቅስቃሴውን እንዲያስተላልፉልን ስለፈለግን፤ አባታዊ ምክር እንዲሰጡን፤ጥያቄ አቅርበንላቸው እንደ ሚከተለው ነግረውናል፡፡

13

የመናገሻ መድንኔ ዓለም ገዳም ቤተ ክርስቲያን ሥራ ተጠናቆ ተመረቀ ቤተ ክርስቲያኑ በልዩ ሆኔታ የተሠራ ነው᎓᎓

መልካም ንባብ!!

በመጀመሪያ ብዙ የደከማችሁበት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሥራው ተፈጽሞ ለምርቃት በመድረሱ እንኳን ደስ አላችሁ! ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሰው የሠራው ሥራ ከፍጻሜ ሲደርስለት ይደሰታል፡፡ እናንተ ደግሞ እግዚአብሔር የሚመሰገንበትንና ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚገለገሉበትን፤ በዚያውም ላይ በታላቁ መናገሻ አምባ ማርያምና የጋራው መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም በመሆኑ ደስታችሁን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ በሥራችሁ መካከል የገጠማችሁን ችግር ሁሉ ተቋቁማችሁ በመጪው ትውልድ ስትታወሱ፤ የምትኖሩበትን ትልቅ ሥራ ሠርታችኋልና ልትመሰገኑ ይገባችኋል፡፡ ወደ ጥያቄው ስመለስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ ገዳም የመጣሁት፤ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት ለማክበር ፣ ከአባቶች መነኮሳት ጋር ለመስገድና ለመጸለይ ነበር፡፡ ገዳሙ በደን የተሸፈነ ተራራ ላይ ያለ በመሆኑ መንፈስን  ደስ የሚያሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን  ቤተክርስቲያኑ ጠባብ መሆኑ ፣ የአባቶች መነኮሳት በዓት ለቤተክርስቲያኑ የቀረበና ለአባቶች መኖሪያነት የማይመጥን መሆኑን፣ ቤተምርፋቅ አለመኖሩን፣ የገዳሙን ጥንታዊነት የሚገለጹ ነገሮች በተደረጀ መልኩ አለመቀመጣቸውና ቤተ መዘክር ( ሙዚየም) አለመኖሩን በማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ በተለይም ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በመገኘቱ ጎብኝዎችን በሚስብ መልኩ አለመደራጀቱ ቁጭት ፈጥሮኛል፡፡ እናንተ እንደምትሉት በግሌ ብዙ አስተዋፅዖ አድርጌአለሁ ለማለት አልችልም ፡፡ ቢሆንም እንኳን መነሻዬ ከገዳም ነውና በገዳም ጸንተው ለሚኖሩ አባቶች ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ስለሆነም “በርቱ ጽኑ” ለማለት ከጎናቸው እንዳለን ለመግለጽ በልማት ኮሚሽኑ በኩል ትላልቅ ብረት ድስቶች፣ የሹራብ መሥሪያ ማሽኖች ሲንጀሮች ፣ ለቢሮ መገልገያ ኮምፒውተሮች  ከነፕሪንተራቸው ፣ ቶዮታ ፒካፕ መኪና ሠጥተናቸዋል፡፡ የቦታው ትልቁ ችግር ውሃ ስለሆነ ጋራው ላይ ከቤተክርስቲያኑ በስተምሥራቅ  ረግረግ ስላለ የከርሠ ምድር ውኃ ልናገኝ እንችላለን ብለን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራንን ጋብዘን በባለሙያ ሲጠና ውሃ ቢኖርም ከተራራው እግር ሥር ይወጣል እንጂ እዚህ ሊቆም አይችልም ስላሉን ያ ጥረት ተቋርጧል፡፡ ነገር ግን የታችኛው ገዳምና የአካባቢው ሕዝብም የውሃ ችግር ስላለበት ከተራራው ግርጌ በመነኮሳቱ እርሻ መሬት ላይ የከርሠ ምድር ውሃ እንዳለ ስለተጠቆምን በባለሙያ አስጠንተን ከማስቆፈሩ ጀምሮ ከ 500,000.00 ( አምስት መቶ ሺህ ብር) በላይ ወጪ በማድረግ ውሃውን አውጥተን  ለአገልግሎት እንዲውል በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡  መነኮሳቱ እኛም ረድተናቸው ውሃውን ጥራት እና የማዕድን ይዘቱን አስጠንተው የታሸገ ውሃ ለገበያ ቢያቅርቡ የገቢ ምንጭ ይፈጥራል፡፡ ከገዳሙ የተገኘ በመሆኑም ከመጠጥነት ባሻገር እንደጠበል ስለሆነ ተፈላጊነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን የነበረበት ስውር ተብሎ የሚጠራው ላይ የተሠራ የተለየ ቤተ መቅደስ ነው᎓᎓ Continue Reading

12ቅድመ ዓለም የነበረ፣ አሁንም ያለና ለወደፊቱም የሚኖር ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አምላካች እግዚአብሔር ሰውን ከመሬት አፈር በእጁ የሠራው፣ በአርኣያውና በምሳሌው የፈጠረውም እርሱ ነው፡፡ (ዘፍ 1፡26)፡፡ እግዚአብሔር በአርዓያውና በአምሳያው የፈጠረውን ሰውም ከሌሎቹ ፍጥረታት በጸጋ አክብሮ በአእምሮ አልቆ በገነት እንደኖር አደረገው፡፡ Continue Reading

ባሕታዊ  ዘበህድአት! ገዳማዊ ሕይወት በመነሳት

9-1አንድ ሰው ኅሊናውን ለምናኔ አነሣሥቶ ወደ ገዳም በሚገባበት ወቅት የሚያጋጥሙት ፈተናወች እጅግ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓለማችን እንደ ገዳም ያለ ፈተና የሚበዛባት ቦታ የትም የለም፡፡ ሰብአዊ ፈተናዎች በሙሉ ተሰባስበው የሚገኙት በገዳም ነው። ምክንያቱም ብዙኅ ሕማሞሙ ለጻድቃን ማለት የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው በተባለው መሠረት፣ በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በምናኔ ወደ ገዳም በገቡ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፈተና የበለጠ ክብደት አለውና።

ገዳማውያን አበው መነኰሳትና እማት መነኰሳይያት  በገዳማዊ ሕይወታቸው የሚዋጉት ከዚህ ዓለም ካለው ከሚታየው፤ ከሚጨበጠው፤ ከሚዳሰሰውና ከሚሰማው ፈተና ብቻ ሳይሆን ከማይታዩ፤ ከማይዳሰሱ፤ ከማይጨበጡ ረቂቃን አጋንንት ጋርም  ከመዋጋት አቋርጠው አያውቁም። ውጊያውም እስከ ዕለተ እረፍተ ሥጋ ድረስ የሚያቆም ውጊያ አይደለም፡፡ ስለዚህ በገዳም በመናንያንና በመናንያት ላይ የሚደርሰው ፈተና ስፍር ቁጥር የለውም።

በመጀመሪያ ደረጃ በገዳማዊ ሕይወት የሥራን ክቡርነት መረዳት፤ የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙ መታገስን፣ ሲታዘዙ ያለማጕረምረምና ያለመታከት የታዘዙትን መፈጸም፣ ጾምን፣ ጸሎትን፤ ስግደትን፤ ሕርመትን መለማመድና ገንዘብ ማድረግ የግድ ነው። ምክንያቱም ገዳም የትጉሃን መናኸሪያ እንጂ የሰነፎች መኖሪያ፤ መጦሪያ ወይም መደበቂያ አይደለምና፡፡

ገዳማዊ መነኩሴ ወይም ገዳማዊት መነኩሲት በገዳማቸው ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሲመደቡ ማለትም አትክልትን መትከል፣ መኮትኮትና ውኃ ማጠጣትን፤ እርሻ ማረስን ሌሎችንም አስፈላጊና ተገቢ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን፤ በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መሰሎቻቸው ጋር በመስማማትና ማንኛውንም ዓለማዊና ሥጋዊ  ፈቃድን በማስወገድ  ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጸንቶ ማገልገል መንፈሳዊ ግዴታቸው ነው። ይህም ተግባርና አገልግሎት ደግሞ የአንድ ገዳማዊ ወይም ገዳማዊት ጠባይ፤ ችሎታ፤ ፍቅረ ቢጽነት የሚመዘንበት የምናኔ መስፈርት ነው። ልክ እንደ አባ ዮሐንስ ሐፂር ትዕግስትን መላበስ ይጠበቅባቸዋል።

       አባ አሞይ የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማ እስክታፈራ ድረስ ውኃ እንዲያጠጣት ለአባ ዮሐንስ አዘዘው አባ ዮሐንስም ያለማጕረምረም በትሕትና በመቲረ ፈቃድ ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ እያመላለሰ ያጠጣ ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመት ያች እንጨት ለምልማ አብባ ያማረ ፍሬ አፈራች። Continue Reading

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን ገዳማት

ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት፣ መነኵሳት ጻድቃን ሰማዕታት በሙሉ በዱር በገደል፣ በእሳት፣ በስለት፣ በረሀብ፣ በእርዛት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምናኔ እየተንገላቱ መከራ ተቀበሉት ለሃይማኖታቸው ለምግባራቸው፣ ለሥርዓታቸው፣ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ነው ለእምነታቸው፣ የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በማስተማርና በማስከበር ሁሉን የእግዚአብሔርን ስም ይጥራ፣ ሁሉም ከእግዚአብሔር የተገኘነውና በእግዚአብሔርም የሚረዳ ነው፣ በማለት ነው።

እነ ኤልያስ፣ እነ ኤርምያስ፣ እነ ኢሳይያስ በድንግልና በብሕትውና በማስተማር፣ ነገሥታት ነን ባዮችን፣ ድሀ አትበድሉ፣ ፍርድ አታጓድሉ፣ ጣዖት አታምልኩ፣ በእግዚአብሔር እመኑ በማለት የሰውን ነጻነት የእግዚአብሔርን ቸርነት ለመመስከር የአመቻቸው ብቸኝነታቸው ነው። ያስተማሯቸውም ለሰው ሕይወት ለሀገር ደኀንነትና ነጻነት ነው። Continue Reading

ሙሴ ጸሊም

Moses the Ethiopian

Moses the Ethiopian

አባ ሙሴ ጸሊም ይባላሉ፣ ሙሴ ኩሻዊ፣ ሙሴ ኢትዮጵያዊ ለማለት ነው፡፡ በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያዊ ማለት ጠይም ገጽ ማለት ነው፡፡ ሙሴ ጸሊም ማለት ሙሴ ኢትዮጵያዊ ማለት ነው፡፡ ሰኔ 24 ቀን የሚነበበው የግእዝ ስንክሳር እና በርካታ ዓለም አቀፍ ታሪክና የሥርዓተ ምንኵስና መጻሕፍት ስለ አባ ሙሴ ጸሊም ብዙ መረጃዎችን ጽፈዋል፡፡

ስንክሳር ዘሰኔ 24 በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ ሙሴ ጸሊም አረፈ፡፡ አስቀድሞ ሽፍታ፣ ወንበዴ፣ ዘማዊ ፣ጣኦት አምላኪ ነበር፤ በኃላ እንደ አብርሃም አምላኬ ማን ነው? ብሎ ተመራመረ፤ ወደ አስቄጥስ ገዳም ብትሄድ አምላክህ ማን እንደሆነ የበረሐ መነኰሳት ይነግሩሃል የሚል ራዕይ አየ፣ ተመለከተ፤ ተነስቶም ሄደ፡፡

አባ ኤስድሮስን አገኛቸው፤አጽናንተው አረጋግተው ወደ አባ መቃርስ ወሰዱት አባ መቃርስም ንሥሓውን ተቀብለው ቀኖና ሰጡት ኋላም አመነኰሱት ፤ የሽፍቶች አለቃ የነበረው የመነኮሳት አለቃ እስከመሆን ደረሰ፡፡ ሰይፉን ወርውሮ ከፍቅር ጋር ተወዳጀ፤ሌሊት እየተነሣ ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዳላቸው ነበር፤ ለሁሉም ይታዘዛቸው ነበር ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይህን አድርግልኝ ይሉታል አርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፤ ራሱን ዝቅ አደረገ ትሁትም ሆነ፤ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንም ነበር፡፡ Continue Reading